PLANET ETHIOPIA
Advertisment

Latest Articles


 • NEWS: ዚምባቡዌ የፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ ልደት ብሄራዊ በዓል እንዲሆን አወጀች

                                                   

  የዚምባቡዌ መንግስት የፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ ልደት ብሄራዊ በዓል ሆኖ እንዲከበር አወጀ።

  የካቲት 14 ቀን የሚከበረው የፕሬዚዳንቱ ልደት ብሄራዊ በዓል ሆኖ እንዲከበር የታወጀውም እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጣር ከ1980 ጀምሮ ሀገሪቱን በመምራት ላይ የሚገኙትን ሮበርት ሙጋቤን ለማክበር መሆኑም ተነግሯል።

  የሮበርት ሙጋቤ ብሄራዊ ቀን ሊታወጅ የቻለው የፓርቲያቸው ዛኑ ፒ ኤፍ ወጣቶች ሊግ ባቀረበው ተደጋጋሚ ጥያቄ ጫና ማሳደሩን ተከትሎ ነው ተብሏል።

  የዚምባቡዌ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ኢግናቲዩስ ቾምቦ ለሀገሪቱ ሄራልድ ጋዜጣ እንደተናገሩት፥ ብሄራዊ በዓሉን ማወጅ ያስፈለገው የዚምባቡዌ ወጣቶች ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤን በምሳሌነት በመውሰድ ከሳቸው እንዲማሩ በማሰብ ነው።

  ዛኑ ፒ.ኤፍ ፓርቲ የፕሬዚዳንቱ ልደት ብሄራዊ በዓል እንዲሆን ለዓመታት ጫና ሲፈጥር እና ሲጠይቅ መቆየቱን ተከትሎ የሀገሪቱ መንግስት ካቢኔ ውሳኔውን ማሳለፉንም ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

  ዛኒ.ፒ.ኤፍ ፓርቲ የዚንባቡዌ ዋናው አየር ማረፊያም በፕሬዚዳንቱ ሮበርት ሙጋቤ እንዲሰየም ጠይቋል ነው የተባለው።

  የ93 ዓመቱ ሮበርት ሙጋቤ ዚምባቡዌ ከእንግሊዝ ቀኝ ግዛት ነጻ በወጣችበት እንደ አውሮፓውኑ አቆጣጣር በ1980 ወደ ስልጣን የመጡት።

  ከዚያን ጊዜ አንስቶም ለ37 ዓመታት ሀገሪቱን በመምራት ላይ ይገኛሉ።

  በቀጣዩ ዓመት በዚንባቡዌ በሚደረገው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ላይም ፓርቲያቸው ዛኑ.ፒ.ኤፍን በመወከል ለፕሬዚዳንትነት እንደሚወዳደሩ ማስታወቃቸው ይታወሳል።

  ዛኑ ፒ.ኤፍ ፓርቲም የ93 ዓመቱ ሮበርት ሙጋቤ በቀጣዩ ዓመት ምርጫ ለፕሬዚዳንትነት እንዲወዳደሩ ሙሉ ድጋፉን ሰጥቷቸዋል።

  ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

  Read more »

 • NEWS: ጆሮ በጫጫታ ውስጥ መልዕክቶችን በግልፅ ካደመጠ የአዕምሯዊ ጤንነት ምልክት ነው ተባለ

                                                                         

  የሰው ልጅ በጆሮው አማካይነት የድምፅ መልዕክቶችን ሲያስተናግድ የሚውል ቢሆንም መልዕክቶችን በግልፅ ለማዳመጥ ሁከት ባይኖር የአብዛኛው ህዝብ ምርጫ መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ።

  የኦክስፎርድ፣ የፖርቶ፣ የዌስት ሚኒስትር፣ የዱርሃምና የለንደን ዩኒቨርሲቲዎች በጋራ ይፋ ባደረጉት ጥናት ጆሮ በድምጽ ሁከት ውስጥ መልዕክቶችን ለይቶ ካዳመጠ የሰዎች አዕምሯዊ ጤንነት መልካም መሆኑን እንደሚያሳይ አመላክቷል።

  ከየዩኒቨርሲቲዎቹ የተውጣጡ ተመራማሪዎች በተዘበራረቀ የድምፅ ፍሰት ውስጥ ቃላትና ሀረጋትን አገጣጥመው ሙሉ መልዕክትን ማዳመጥ መቻል የአዕምሯዊ ጤንነት ደረጃን ለመለካት ያለውን ሚና ተንትነዋል።

  ድምፆችን በአግባቡ የሚሰሙ ሰዎች አንጎል የፈጠነ ምላሽ የሚሰጥና ትኩረት የማድረግ አቅሙ ከፍተኛ መሆኑ በጥናቱ ሂደት በኤም አር አይ ምርመራ ተረጋግጧል።

  ከዓለም ህዝብ 15 በመቶ ያህሉ ድምፅን ለይቶ ትርጉም በሚሰጥ መልኩ የሚሰማው ሁከት በማይኖርበትና በቅርበት በሚሆንበት ጊዜ ነው።

  የድምፆች መደራረብና መዘበራረቅ በሚከሰትባቸው ቦታዎች መልዕክቶችን አጣርቶ ማዳመጥ የሚሳናቸውና ግራ የሚጋቡ ሰዎች ለአዕምሮ ጤና መዛባት ችግር የመጋለጣቸው ፍንጭ መሆኑን ተመራማሪዎች ጠቅሰዋል።

  በተለይም የጆሮ ድምፆችን አጣርቶ ትክክለኛውን ትርጉም በሚሰጥ መልኩ ወደ አዕምሯቸው የማድረስ ችሎታ ወደፊት በጤናው ዘርፍ ለሚደረግ የአዕምሮ ህክምና የመነሻ ግኝት እንደሚሆን ነው የተጠቆመው።

  በጥናቱ የተሳተፉ ሰዎች ከጫጫታ ውስጥ ቃላትን መርጠው የማዳመጥ ችሎታቸው እንዲለካ ተደርጓል።

  በዚህም መሰረት 75 በመቶ የሚሆኑ ተሳታፊዎች በድምፅ ሁከቱ ውስጥ የተነገሩ ዓረፍተ ነገሮችን በጉልህ መስማታቸው ተረጋግጧል።

  ፕሮፌሰር ሶፊ ስኮት በለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የንግግር ተግባቦት ቤተ ሙከራ ተመራማሪ ሲሆኑ፥ በተዘበራረቀ የድምፅ ፍሰት ውስጥ መልዕክትን ለይቶ የመስማትና የማውጣት ግኝቱ የሰዎቹን አዕምሯዊ ጤንነት ይመሰክራል ብለዋል።

  ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

   

  Read more »

 • ለጭንቀት የተጋለጡ ሴቶች ፅንሳቸው የመጨናገፍ እድሉ 42 በመቶ ይደርሳል::

                                                   

  ለረጅም አመታት ለጭንቀት የተጋለጡ ሴቶች በእርግዝና ወቅት ፅንሳቸው የመቋረጥ እድሉ 42 በመቶ እንደሚደርስ አንድ ጥናት አመለከተ።

  በለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ እና በቻይና በሚገኘው ዠጃንግ ዩኒቨርሲቲ አማካኝነት የተደረገው ጥናት በወጣትነታቸው ጭንቀት የሚያበዙ ሴቶች በኋለኛው እደሜያቸው በርካታ ችግሮች እንደሚገጥሟቸው አረጋግጧል።

  በጥናቱ ጭንቀት እና ሴቶች በእርግዝና ወቅት የሚያጋጥማቸው የፅንስ መጨናገፍ ያላቸው ግንኙነት ተዳሷል።

  ሴቶች ከፀነሱ ከ24 ሳምንታት በፊት የሚከሰተው የፅንስ መጨናገፍ፥ በእያንዳንዱ ነፍሰ ጡር ሴት የመድረስ እድሉ 20 በመቶ ነው።

  ሴቶች በእርግዝና ወቅት ስለ ትዳር አጋራቸው፣ ልጆቻቸው እና ቤተሰቦቻቸው ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ሲገቡ የፅንስ መጨናገፍ እንደሚከሰት ነው ጥናቶች የሚያሳዩት።

  የማህበራዊ ግንኙነት ችግር፣ የገቢ ማነስ፣ በትዳር አለመደሰት፣ በስራ ገበታ የሚያጋጥም ጫና እንዲሁም ከዚህ ቀደም ያጋጠመ የፅንስ መጨናገፍም ሌሎች አበይት ምክንያት ናቸው ተብሏል።

  በለንደን ዩኒቨርሲቲ እና ዠጃንግ ዩኒቨርሲቲ የተደረገው ጥናት የጭንቀት እና ፅንስ መጨናገፍ ዝምድና የጭንቀት ሆርሞኖች ከመመንጨታቸው እና መለቀቃቸው ጋር ይያያዛል ይላል።

  እነዚህ የጭንቀት ሆርሞኖች ለፅንሱ እድገት ወሳኝ የሆኑ ኬሚካሎች እንቅስቃሴን ያውካሉም ነው ያለው ጥናቱ።

  የጥናቱ ዋና አዘጋጅ እና በለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የስነ ልቦና አስተማሪ የሆኑት ዶክተር ብሬንዳ ቶድ፥ ከእርግዝና በፊት አልያም በኋላ የሚከሰት ከፍተኛ ስነ ልቦናዊ ጭንቀት ከፅንስ መጨናገፍ ጋር ሰፊ ግንኙነት እንዳለው አረጋግጠናል ብለዋል።

  ጥናቱ በተለይም በወጣትነት እድሜያቸው ለጭንቀት የተዳረጉ ሴቶች በእርግዝና ወቅት የሚገጥማቸው የፅንስ መጨናገፍ ችግር ወደ 42 በመቶ ከፍ ሊል እንደሚችልም ተናግረዋል።

  በመሆኑም ሴቶች ከማርገዛቸው በፊት ስነ ልቦናዊ የጤና ሁኔታቸውን ቢያውቁት መልካም ነው ብለዋል።

  ጥናቱ የጭንቀት እና ፅንስ መጨናገፍ ዝምድናን ያመላከተ ቢሆንም በቀጣይም ሌሎች ጥናቶች ሉደረጉ እንደሚገባም ነው ዶክተር ቶድ ያብራሩት።

  ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

   

  Read more »

 • NEWS: ኪም ጆንግ ኡን ብዛት ያለው ተተኳሽ ሮኬት እንዲመረት አዘዙ:;

                                       

  የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ብዛት ያለው ተተኳሽ ሮኬት እንዲመረት ትዕዛዝ አስተላለፉ።

  ኪም ትዕዛዙን ያስተላለፉት በሃገሪቱ ሚሳኤል አምራች ኬሚካል ተቋም ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ነው።

  በጉብኝታቸውም የተቋሙ ሰራተኞች ብዛት ያላቸውን ተወንጫፊ ሮኬቶች እንዲያመርቱ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን የሃገሪቱ ሚዲያ ተቋማት አስታውቀዋል።

  ኪም በካርበን ውህድ የሚሰሩ ተጨማሪ ተተኳሽ ሮኬቶችንና ሚሳኤሎችን እንደሚፈልጉ መናገራቸውንም የሃገሪቱ ቴሌቪዥ ጣቢያ ዘግቧል።

  በቴሌቪዥን ጣቢያው በተላለፈው ዘገባ ፒዮንግያንግ ከዚህ በፊት ያልነበራት አይነት የሚሳኤል ዲዛይን የሚያሳይ ፎቶም ታይቷል ነው የተባለው።

  “ፑክ ጉክሶንግ 3” የተሰኘው ሚሳኤል ፒዮንግያንግ አለኝ ከምትለው ሚሳኤል አይነቶች የተለየ ነውም እየተባለ ነው።

  ከዚህ ባለፈም “ሃውሶንግ 13” አልያም “ሃውሶንግ 11” ሊሆን ይችላል የተባለ ሚሳኤልም፥ በዜናው ላይ መታየቱንም ነው የዘርፉ ተንታኞች የተናገሩት።

  እነዚህ ሚሳኤሎች አህጉር አቋራጭ ሲሆኑ፥ በቀላሉ ኢላማቸውን መምታትና ማውደም የሚችሉ ናቸውም ተብሏል።

  የአሁኑ የኪም ትዕዛዝ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን፥ ፒዮንግያንግ ወደ ሰላማዊ ድርድር ትመጣለች የሚል እምነታቸውን ከገለጹ በኋላ የተሰጠ ነው።

  በአንጻሩ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተቃውሞ ባስተናገዱበት የፎኔክስ አሪዞና ሰልፍ ላይ፥ ኪም ጆንግ ኡን አሜሪካን ማክበር ጀምሯል ሲሉ ተደምጠዋል። 

  ፒዮንግያንግ ካለፈው አመት ጀምሮ በርካታ ሚሳኤሎችን ስታስወነጭፍ ሁለት የኒውክሌር ሙከራዎችን ደግሞ አድርጋለች።

  ይህ ሁኔታ ደግሞ ከበርካቶች ዘንድ በተለይም ከአሜሪካና አጋሮቿ ውግዘትን አስከትሎባታል።

  ከሶስት ሳምንታት ጀምሮም ከዋሽንግተን ጋር እሰጥ አገባው ውስጥ ገብተዋል።

  ለዚህም በፓሲፊክ ውቅያኖስ ላይ በሚገኘው የአሜሪካ ወታደራዊ ግዛት በሆነው ጉዋም ላይ ጥቃት እፈጽማለሁ ስትልም ዛቻና ማስፈራሪያ ስትሰነዝር ቆይታለች።

  አሜሪካ በበኩሏ ፒዮንግያንግ ለምትወስደው እርምጃ ጠንካራ አጸፋዊ ምላሽ እንደሚጠብቃት ስታስጠነቅቅ ቆይታለች።

  ባለፈው ሳምንት ደግሞ ከዚህ ሃሳቧ በተለየ፥ እርምጃ ለመውሰድ የአሜሪካን ድርጊት መነሻ አደርጋለሁ ብላ ነበር።

  ግን ዋሽንግተን ፒዮንግያንግን ይረዳሉ ባለቻቸው የቻይና እና ሩሲያ ግዙፍ ተቋማትና ግለሰቦች ላይ ማዕቀብ በመጣሏ፥ ለዘብ ያለ የመሰለው የሃገራቱ ፍጥጫ መልኩን እንዳይቀይር ተሰግቷል።

  በርካቶችም የአሁኑ የኪም ጆንግ ኡን ትዕዛዝ ፍጥጫውን እንዳያከረው በሚል ስጋታቸውን እየገለጹ ነው፤ አካሄዱ ጦር ለመስበቅ ዝግጅት ይመስላል በሚል።

  ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

   

  Read more »

 • NEWS: አሜሪካ ከሰሜን ኮሪያ ጋር በተገናኘ በቻይና እና ሩስያ ኩባንያዎች ላይ አዲስ ማዕቀብ ጣለች::

                                    

  አሜሪካ ከሰሜን ኮሪያ የኒዩክሌር ፕሮግራም ጋር ግንኙነት አላቸው ባለቻቸው የቻይና እና ሩስያ ኩባንያዎች ላይ አዲስ ማዕቀብ መጣሏን ይፋ አደረገች።

  የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው፥ በማዕቀቡ ኢላማ የተደረጉት 10 ኩባንያዎች እና ስድስት ግለሰቦች ፒዮንግያንግ የኒዩክሌር እና ሚሳኤል ፕሮግራሟን እንድታዘምን ተሳትፎ አድርገዋል።

  አዲሱ ማዕቀብም ኩባንያዎቹ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ያላቸውን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት እንዲያቋርጡ ያደርጋል የተባለ ሲሆን፥ አብዛኞቹ ማዕቀቦችም በቻይና በሚገኙ ኩባንያዎች ላይ እንደሚጣሉ ተገልጿል።

  ማዕቀቡ የሚጣልባቸው ኩባንያዎች እና ግለሰቦች ዝርዝር ግን ይፋ አልተደረገም።

  ማንኛውም ሰሜን ኮሪያን የሚደግፍ አካል በአሜሪካ ምንም አይነት የንግድ እንቅስቃሴ እንዳያደርግ ይታገዳል ብለዋል ሚኒስትሩ ስቲቭ ኑቺን።

  የሀገሪቱን የኒዩክሌር እና ሚሳኤል ፕሮግራም የሚደግፉ አካላትን ከአሜሪካ የፋይናንስ ስርአት ውጭ በማድረግም በሰሜን ኮሪያ ላይ ጫና መፍጠሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል። 

  በቻይና እና ሩስያም ሆነ ሌሎች ሀገራት የሚገኙ ግለሰቦች እና ኩባንያዎች፥ የኪም ጆንግ ኡን አስተዳደር ጠቅላላ ውድመት የሚያደርሱ እና ቀጠናውን የሚያተራምሱ የጦር መሳሪያዎችን እንዲያመርት መደገፋቸው ተቀባይነት የለውም ነው ያሉት ሚኒስትሩ።

  ቤጂንግ በአለም አቀፉ ማህበረሰብ እና በአሜሪካ ጫና ከፒዮንግያግ ጋር ያላትን የንግድ ግንኙነት በተወሰነ መንገድ መቀነሷን ትናገራለች።

   ይሁን እንጂ የቻይና ኩባንያዎች አሁንም ለተገለለችው ሰሜን ኮሪያ ዋነኛ የንግድ አጋር ናቸው።

  ሰሜን ኮሪያ ሁለት አህጉር አቋራጭ ሚሳኤሎችን መሞከሯን ተከትሎ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለፈው ወር ላይ በሀገሪቱ አዲስ ማዕቀብ እንዲጣል መወሰኑን ተከትሎ የኮሪያ ልሳነ ምድር ውጥረት አይሏል።

  ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

  Read more »

 • NEWS: የኢትዮጵያና እስራኤል ግንኙነት እያደገ መጥቷል - አምባሳደር በላይነሽ

                                   

  ኢትዮጵያና እስራኤል ግንኙነት እያደገ መምጣቱን ተሰናባቿ የእስራኤል አምባሳደር በላይነሽ ዛቫዲያ ተናገሩ።

  ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ የሥራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር በላይነሽ ዛቫዲያን ዛሬ አሰናብተዋል።

  ተሰናባቿ አምባሳደር በላይነሽ ከውይይቱ በኋላ እንደገለጹት ሁለቱ አገሮች በተለያዩ መስኮች ያላቸው ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መጥቷል።

  በእርሳቸው የሥራ ጊዜም በአገራቱ መካከል ያለውን ሁለንተናዊ ትብብር ለማጠናከር የሚያስችሉ በርካታ የሁለትዮሽ ሥምምነት መፈረማቸውን ጠቅሰዋል።

  የተደረሱት ሥምምነቶች በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በቱሪዝም፣ በግብርና እና በሌሎች ዘርፎች ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን አምባሳደሯ ገልጸዋል።

  የአገራቱን የትብብር አድማስ ለማስፋት የተደረሱትን ሥምምነቶች ወደ ተግባር የሚቀይር ኮሚቴ ተቋቁሞ ሥራዎች መጀመራቸውንም ነው ያነሱት።

  በቆይታቸው ወቅት 150 ሺህ ቤተ - እስራኤላዊያን ኢትዮጵያን እንዲጎበኙና ኢንቨስት እንዲያደርጉ መፈቀዱ ከተመዘገቡት ስኬቶች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን አስታውሰዋል።

  "ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም እስራኤልን መጎብኘታቸውና በተመሳሳይም የእስራኤሉ አቻቸው ቤንያሚን ኔታናየሁ ኢትዮጵያን መጎብኘታቸው ከተሰሩት ሥራዎች መካከል ይጠቀሳሉ" ብለዋል።

  እነዚህም ሥራዎች ባለፉት ዓመታት የሁለቱ አገሮች የሁለትዮሽ ግንኙነት እያደገ መምጣቱን እንደሚያመላክቱ ገልጸው በቀጣይም "ግንኙነቱ ይበልጥ እንዲጠናከር እሰራለሁ" ብለዋል። 

  ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ በበኩላቸው አምባሳደሯ በቆይታቸው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ እንዲሸጋገር ላበረከቱት አስተዋፅኦ ምስጋና አቅርበዋል።

  ርካታ የእስራኤል ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እያደረጉ መሆኑን ገልጸው፥ ይኸው ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል አምባሳደሯ የጀመሩትን ሥራ ሊገፉበት እንደሚገባ ተናግረዋል። 

  እስራኤል በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የካበተ ልምድ ያላት አገር መሆኗን ያነሱት ፕሬዚዳንት ሙላቱ፥ ከዚህም ኢትዮጵያ ልምድ መቀመር እንደምትሻ ነው ለአምባሳደሯ የገለጹት።

  በዚህም ብዙ መሥራት እንደሚጠይቅ ፕሬዚዳንቱ መናገራቸውን ውይይቱን የተከታተሉት በፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት የፕሮቶኮልና ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አሸብር ጌትነት ገልጸዋል። 

  ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

  Read more »

 • የዛሬ የዕለተ ማክሰኞ ነሐሴ 16 ቀን 2009 የሸገር ወሬዎች::

                                    

  በኦሮሚያ ክልል በሐሰተኛ የመንጃ ፈቃድ የሚያሽከረክሩ ሰዎች አደጋ ካደረሱ በኋላ እንደሚጠፉ ተነገረ፡፡ (ንጋቱ ሙሉ)

  በከፍተኛ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ውስጥ 26ቱ ትላንት ፖሊስ የጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተፈቀዶለታል፡፡ (እሸቴ አሰፋ)

  መረጃ ባለመሟላቱ ምክንያት በአዲስ አበባ ከ14 ሺ በላይ ይዞታዎች ለምዝገባ ብቁ ሣይሆኑ ቀርተዋል ተባለ፡፡ (ምህረት ስዩም)

  የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ያሰብኩትን ገቢ ሙሉ በሙሉ መሰብሰብ አልቻልኩም አለ፡፡ (ትዕግሥት ዘሪሁን)

  የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ለፆም ፍቺ በዛ ያሉ በሬዎችን አረድኩ አለ፡፡ (ወንድሙ ኃይሉ)

  የኮድ 3 ሚኒባስ ተሽከርካሪዎች በተመደቡበት መስመር ሳያቆራርጡ አገልግሎት እንዲሰጡ ያስችላል የተባለው የብረት ታፔላ ተቀየረ፡፡ (በየነ ወልዴ)

  ምንጭ:- የሸገር FM 102.1 ሬዲዮ

  Read more »

 • NEWS: አሜሪካ ከ241 ዓመት በኋላ የመጀመሪያዋ የሆነውን ሙሉ የፀሃይ ግርዶሽን ዛሬ ታያለች

                                             

  ዛሬ በዩናይትድ ስቴትስ ከምዕራብ ወደ ምሥራቅ የሚያቋርጥ የፀሐይ ግርዶሽ ይኖራል።

  ታሪካዊ ክስተቱ "ታላቁ የአሜሪካ የፀሃይ ግርዶሸ" ለመባል በቅቷል።

  በአጠቃላይ በ14 የዩናይትድ ስቴትስ ግዛቶች ጨረቃ ፀሃይን ሙሉ በሙሉ ስትጋርድ የማየት እድሉ አላቸው።

  የግርዶሽ ሙሉው መንገድ ኦሬጎን፣ አይዳሆ፣ ዋዮሚንግ፣ ነብራስካ፣ ሚስዩሪ፣ ኬንታኪ፣ ቴነሲ፣ ጆርጂያ፣ ሰሜን ካሮላይና እና ደቡብ ካሮሊና ግዛቶች ስለሚያዳርስ በነዛ ግዛቶች የሚኖሩ ዝጎች ይህንን ሁኔታ የማየት ዕድል ያገኛሉ፡፡.

  በዚህም መሰረት ግርዶሹ በተወሰኑ አካባቢዎች ሙሉ ግርዶሽ ሲሆን፥ ከፊል ግርዶሽ ሥር የሚያርፉ ስፋት ያላቸው የዩናይትድ ስቴትስና የካናዳ አካባቢዎች አሉ።

  ዋሺንግተን ዲሲና አካባቢዋ ከፊል ግርዶሽ ሥር ከሚያርፉት ናቸው።

  ምንም እንኳን በብዙ ቦታዎች ግርዶሹ ሙሉነት ቢኖረውም በየአከባቢው ያሉ ሰዎች ግርዶሹን ለማየት የሚኖራቸው ዕድል ከሁለት ደቂቃ እስከ 40 ሴኮንድ በመሆኑ ቆይታው አጭር ይሆናል።

  ያለፈው የፀሐይ ግርዶሽ ዩናይትድ ስቴትስ ምድር ላይ የታየው ከዛሬ 38 ዓመት በፊት ሲሆን፥ እንዳሁኑ ፀሃይ በጨረቃ ሙሉ በሙሉ የተጋረደችበትን አጋጣሚ ያየችው ግን ከ241 በፊት ነው። 

  እንዲህ ዓይነት ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ ያቋረጣት ግርዶሽ የነበረው ግን የዛሬ መቶ ዓመት ነበር።

  ጨረቃ ወደ ፀሐይ አንፃር ገብታ ሙሉ በሙሉ እስክትወጣ ሙሉው የግርዶሽ ጊዜ 2 ሰዓት ከ44 ደቂቃ ነው የሚሆነው።

  በተለይ ለዋሺንግተን ዲሲና አካባቢዋ ነዋሪዎች እጅግ የተመቸ እንደሚሆን ተተንብይዋል።

  ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ (FBC)

  Read more »

 • NEWS: የሩሲያ አየር ሀይል ከ200 በላይ የአይ.ኤስ ታጣቂዎችን መግደሉ ተነገረ

                                               

   

  የሩሲያ አየር ሀይል ከ200 በላይ የኢስላሚስ ስቴት (ኤይ.ኤስ) አሸባሪ ቡድን ታጣቂዎችን መግደሉ ተነገረ።

  አየር ሀይሉ ወደ ሶሪያዋ ዴይር አል ዞር ከተማ በማቅናት ላይ የነበሩ የአይ.ኤስ ታጣቂዎችን መግደሉንም የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴርን በመጥቀስ ሀገሪቱ የዜና ተቋማት ዘግበዋል።

  ራሱን ኢስላሚክ ስቴት እያለ የሚጠራው የአሸባሪው ቡድን አይ ኤስ የጦር ሀይሎቹን ዴይር አል ዞር ከተማ አካባቢ ላይ እያሰባሰበ እንደሚገኝም ተነግሯል።

  ይህ የሆነውም ቡድኑ በሶሪያ የምድር ጦር እና በሩሲያ አየር ሀይል በሚሰነዘርበት ጥቃት ደቡባዊ የራቃ ግዛት እና የምእራባዊ ሆመስ ግዛትን ለቆ ለመውጣት መገደዱን ተከትሎ መሆኑንም የሩሲያ መከላለያ ሚኒስቴር አስታውቋል።

  ከ200 በላይ የሽበር ቡድኑ ታጣቂዎች ከመገደላቸው በተጨማሪም ታጣቂዎቹ ሲጠቀሙባቸው የነበሩ በርካታ የጦር መሳራያዎች ማውደሙንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

  ሆኖም ግን ጥቃቱ መቼ ተፈፀመ ለሚለው ሚኒስቴሩ ምንም ያለው ነገር የለብ ተብሏል።

  ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ (FBC)

  Read more »

 • NEWS: ቻይና የወንጀል ጉዳዮችን የሚመለከት የኢንተርኔት ፍርድ ቤት ይፋ አደረገች

                                        

  ምስጋና ለቴክኖሎጂ ይሁንና በስብሰባዎችና ክብረ በዓላት ላይ በቀጥታ ኢንተኔት አማካይነት በቪዲዮ ኮንፍረንስ መታደም እየተለመደ መጥቷል፡፡

  በወሳኝ ጉዳይ ምክንያት በአካል መገኘት ያልቻሉ ሰዎች ሀሳባቸውን፣ ስሜታቸውን እና ውሳኔያቸውን በቀጥታ ኢንተርኔት የቪዲዮ መልዕክት ለታዳሚያን ሲያደርሱ ይታያል።

  የሩቅ ምስራቋ ቻይናም የቀጥታ ኢንተርኔት ፍርድ ቤት አገልግሎት መጀመሯን ይፋ አድርጋለች፡፡

  አገልግሎቱ ፍርድ ቤቱ ከሳሽና ተከሳሽ ባሉበት ቦታ ሆነው በኢንተርኔት የቪዲዮ መልዕክት ክሳቸውን ለዳኛ ማሰማትም ሆነ መከላከያቸውን ማቅረብ የሚችሉበት ነው።

  በእርግጥ ቻይና በህግ ስርዓቷ ላይ ግልፅነትን ለማሳደግ በሚል ካለፈው ዓመት ጀምሮ ችሎቶችን በኢንተርኔት ለመመልከት ጥረት እያረገች እንደነበር የቢቢሲ ዘገባ ያስረዳል፡፡

  አሁን ይፋ የሆነውና የኢንተርኔት ፍርድ ቤት ታላላቅ ወንጀሎችን ሳይሆን ቀላል ጉዳዮችን ነው የሚመለከተው፡፡

  በተለይም የኢንተርኔት ውንጀሎችና ሌሎች ማህበራዊ የደንብ ጥሰቶች በዚህ ፍርድ ቤት ይታያሉ፡፡

  በችሎቱ የመጀመሪያ ውሎም በድረ ገፅ ፀሐፊዎችና በድረ ገፅ ኩባንያ የተፈጠረ የቅጅ መብት ውዝግብ ቀርቧል፡፡

  ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ለማስተናገድ 20 ደቂቃዎችን ቢጠብቅም በከሳሽና ተከሳሽ በኩል የቀረበ ወገን ባለመኖሩ ችሎቱ ወደ ሌላ ቀን ተዛውሯል፡፡

  ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

  Read more »

Advertisment