PLANET  ETHIOPIA.com

ልማት አደናቃፊ ውሾች.......

ልማት አደናቃፊ ውሾች.......
ትናንት ምሽት የሰፈራችን አየር በሚሰቀጥጥ የውሾች ለቅሶ ተመታ፡፡ ውሾቹ ወልደውና ተዋልደው አርባ አምስት ደርሰዋል፡፡ቆይ ቆይ እኔ የት እንደምኖር ለካ አልነገርኳችሁም....መጀመሪያ አዲስ አበቤ ሁላ ቆጥ ላይ ከምሰቀል ጭቃ ቤቴ ይግደለኝ ብሎ ንቆት አሁን ግን ከግድቡ ቀጥሎ እየተረባረበበት ባለው የኮንዶሚኒየም ህንጻ ላይ ነው፡፡እና ምን አለፋችሁ አንዱ ህንጻ በነፍስ ወከፍ በአርባ አምስት ውሾች ተከቦ ነው ምሽቱ የሚደራው፡፡ ተባእት ውሾች የቴዲ አፍሮን ‹ሰባ ደረጃ› እየዘፈኑ‹ሲመሽ ወደማታ ማታ ማታ አቤት ያንቺ ፍቅር ሲበረታ...› እያሉ(በውሽኛ) የቡችሎቻቸውን እናቶች ያሽኮረምማሉ፡፡ከድሪያው አለፍ ያለ ንቃተ ህሊና ያላቸው የማህበሩ አባል ውሾች ከመንጋቸው ነጠል ብለው የእግረኛ ውሾች መንገድ እንዲሰራላቸው ለሰፈሩ የሰው ኮሚቴዎች ደብዳቤ በመጻፍ ተጠምደው ለሊቱን ያጋምሱታል፡፡ስጋ ቤቶችን ‹በመጃለስ› ለአራስ ሚስቶቻቸው ቀለብ ያመጣሉ፡፡ቡችሎች ላልተፈለገ እርግዝና እንዳይጋለጡ እንዲሁም ውሻዊ ስነምግባርን ያልተከተለ የጾታ ግንኙነት እንዳይኖራቸው ደጋግመው ይመክራሉ፡፡ቡችሎቹም ከፋርማሲ ገብተው ‹ፖስት ፒል› መግዛት ስለማይችሉ አይቀብጡም፡፡ገና ተባእቶቹ ሲጠጓቸው ‹ሶሪ ካረገዝኩ ሼፔ ይበላሻል ...› እያሉ ወደ ቡድናቸው ይቀላቀላሉ፡፡እውነት ነዋ ውሻ አረገዘ ማለት ዶላር ወደብር ተመነዘረ ማለት ነው ፡፡ነፍ ነዋ የሚቀፈቅፉት!!
የዛሬው ግን ለየት ያለ ነው፡፡መልአከ ሞትን ስኪኒ ሱሪ ለብሶ ሲመጣ ያዩታል የሚባሉት እኚህ ፍጡራን ማላዘን ጀመሩ፡፡እርግጥ ነው ጎረቤቴ ናቲ ሲመጣም አንዳንዴ በስህተት ያላዝናሉ፡፡ምክኒያቱን ከውሾቹ ጠይቄ እንደተረዳሁት ከሆነ የናቲ አቋምና ሱሪ ከፍንዳታው መልአከሞት ጋር በጣም ስለሚመሳሰልና የመንፈስ ራዳራቸው የቴክኒክ ብልሽት ስለገጠመው እንደሆነ ነበር፡፡ዛሬም ከሶስተኛው ቆጥ ላይ አንገቴን በመስኮቴ በኩል ብቅ አድርጌ የውሾችን ሰልፍ አይ ገባሁ፡፡ጆሮ ቆራጣው ‹አለም በቃኝ› የተለመደ ያስለቃሽነት ስራውን ጀምሮ በአንካሳ እግሩ እየተጎተተና በግራ አይኑ እያለቀሰ እዬዬውን ያስነካዋል፡፡ሌሎቹም አርባምናምን ውሾች ይቀበሉታል፡፡ድምጻቸው በጣም ስለመረረኝ ‹‹አንተ አለም በቃኝ ሰው ተኝቷልኮ! እንዴ ለደንቡስ ቢሆን ማለዳ ላይ ነውኮ መርዶ ሚነገረው!አሁን በጅቦች አየር ሰአት እየገባችሁ ሰፈሩን ለምን ትበጠብጣላችሁ?›› አልኩት አይኔን እያሻሸሁ፡፡‹‹አይይ ቢጩዬ ጉዳችሁን አላወቃችሁ ዛሬ አንድ ሰው እዚህ ሰፈር በህይወት አያድርም፡፡ሞት ከነሰራዊቱ ሲመጣ ይታየኛል ...ሳስበው ህንጻው ሊደረመስ ነው መሰለኝ..››አለና እዬዬውን ቀጠለ፡፡‹‹ስማ ...እና ህንጻው ይፈርሳል ነው የምትለኝ ... ምን ተሻለ?›› አልኩት ለክፉም ለደጉም የላጤ ቦርሳዬን በጀርባዬ አንግቤ ከቤቴ ለመውጣት እየተዘጋጀሁ፡፡እውነት ነዋ የአለም በቃኝ ውሻዊ ራዳር የመልአከሞትን ያገዳደል እቅድ አነፍንፎ ይሆናል፡፡ስለዚህ እውነትነቱን ካረጋገጥኩ መውጣቴ እዳው ገብስ ነው፡፡‹‹አይ እሱንኳ አልተረጋገጠም ግን ምን መሰለሽ አንዳንድ የግንባታ ግድፈቶች ስላሉበት ሰበብ እንዳይሆን ብዬ ነው፡፡አንቺ ግን አሪፍ ልጅ ነሽኮ ለምን ከኛ ጋር አትኖሪም?ከሰፊው ሟች ጋር ከመሞት ከኛ ጋር መቀየስ አያዋጣሽም? ››አለኝ ጭራውን እየወዘወዘ፡፡‹‹ኧረ ባክህ ብርዱንስ ማን ይችለዋል?››አልኩት በመስኮቴ በኩል የሚያጣፋኝን ውሽንፍር እየጠጣሁ፡፡‹‹እንዴ እኛ ምን ሆንን? ውሻ እንደሆነው ሆነሽ መዞር ነዋ! ›› አለኝ፡፡ ‹‹ኧ.....ረ! ውሻ እንደሆነው ሆኜ? አለም በቃኝ ትሰማለህ አሁን እኔ እንዳንተ ልሁን ብል ሰማይ ቤት ያሉት መላእክት ራሱ እንኳን ከሞት ሊያሰጥሉኝ ይቅርና ‹ደሞ እንደውሻ ከካፖርት የወፈረ ጸጉር የተገጫት መስሏት መላጣ እንብርቷን ይዛ ከቤት ወጣች› ብለው ሙድ ይይዙብኛል፡፡በዛ ላይ ከነሙቀቴና ወዜ ብሞት ይሻለኛል እንጂ ሸማቾች ሱቅ በር ላይ ለሊቱን በአስረሽ ምቺው ከንዳንተ አይነቶች ጋር መጨፈር አልፈልግም›› አልኩት፡፡እሱም በጣም ተስፋ በቆረጠ መንፈስ ‹‹አይይ ቢጩዬ ....ከሰው ሁሉ ያንቺ ሞት ቆጨኝ አውውውው.....›› ብሎ ማላዘን ሲጀምር ጀሌዎቹም ተከተሉት፡፡ድንገት ሁለተኛ ቆጥ ላይ የምትኖረው አልማዝ ነጭ ሽንኩርት ልትነለቅጥ ጠዋት ከኮብልስቶኑ መንገድ ላይ የነቀለቻቸውን ሁለት ድንጋዮች ይዛ በመስኮቱ በኩል ብቅ አለች፡፡ድንጋዮቹን በብርሀን ፍጥነት እነ‹አለም በቃኝ› ቡድን ላይ አዘነበቻቸው፡፡ውሾቹም‹‹አይ ...›› ብለው ተበተኑ፡፡‹‹ምናባታቸው ሟርተኛ ልማት አደናቃፊ ሁላ.....ከዚህ በኋላ ድርሽ ትሉና ደግሞ አመዳሞች!ልጄን እኮ አላስተኛ አሏት ...›› ብላ ተመልሳ መስኮቷን ዘጋች፡፡እኔም መጋረጃዬን ጋረድኩ፡፡ህይወት ይቀጥላል፡፡ እንደማልሞት ስለገባኝ ቦርሳዬን ከቤቴ ወለል አሳረፍኳት፡፡የአልማዝ‹ልማት አደናቃፊ› ውሾችም ሞትን ሊሰብኩ ወደሌላ ብሎክ ሄዱ፡፡እስኪነጋ ድረስ................

ከቤተልሄም ኒቆዲሞስ
(መታሰቢያነቱ ለእንትና እና አልቃሾ)

Related Articles

Post your comment