PLANET  ETHIOPIA.com

ምክር- የስኳር ህመም ላለባቸው ነፍሰጡሮች

 

                                                                                                                  

                  አንዲት ሴት በእርግዝናዋ ጊዜ የተለያዩ የጤና ችግሮች ይገጥሟታል ተብሎ ይታመናል። አንዳንዶቹ እርግዝናን ተከትለው መጥተው በዛው ሊቀሩ የሚችሉ ሊሆኑ ይችላሉ። ሌሎቹ ደግሞ የእድሜ ልክ የጤና ችግር ሆነው ይዘልቃሉ። ከእነዚህ ህመሞች መካከል የስኳር ህመም አንዱ ነው። በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት የስኳር ህመም ከእርግዝና በፊት ከነበረ የስኳር ህመም የሚለይ ሲሆን፤ እርግዝናውን ተከትሎ ይመጣል፡፡ የታወቀ የስኳር ህመም ያለባት እናት ግን ከማርገዟ በፊት የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶችን እና ጥንቃቄዎች ማድረግ እንዳለባት ሐኪሞች ይመክራሉ፡፡ ምክንያቱም የስኳር ህመም በእርግዝና ላይ የተለያዩ ተፅዕኖዎች አሉትና፡፡ እርግዝናም ቢሆን በህመሟ ላይ ጫና ያሳድራል ፡፡

ስለዚህ ጉዳይ መረጃ የሚሰጡን የስኳር ህመም ማህበር ፕሬዚዳንት የሆኑት ዶክተር አህመድ ረጃ ናቸው። ዶክተር አህመድ ከእርግዝና በፊት የሚመጣ የስኳር ህመም በየትኛውም ጊዜ የደም ውስጥ የስኳር መጠን ከ200 ./.ሊ በላይ እና የህመሙ ምልክቶች ሲኖሩ አሊያም ከስምንት ሰዓት በላይ ምግብ ሳይበሉ የደም ግሉኮስ መጠን ከ126 ./.ሊ በላይ ከሆነ ይከሰታል ይላሉ፡፡ ይህንና ይሄን የመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ መረጃ ሊሰጡን ፍቃደኛ ስለሆኑ እናመሰግናለን።

አዲስ ዘመን፡የስኳር ህመም በእርግዝና ላይ የሚያስከትላቸው ችግሮች ምንድን ናቸው?

ዶክተር አህመድ፡የደም የስኳር መጠን ከፍ ማለት እና በደንብ ያልተቆጣጠሩት የደም ስኳር መጠን መዋዠቅ በእናት እና በፅንሱ ላይ የተለያዩ ጉዳቶችን ያመጣል፡፡ ከፍተኛ የደም የስኳር መጠን ተደጋጋሚ ውርጃን ያስከትላል፡፡ ከውርጃ ያመለጠ እርግዝና ካለ ደግሞ ፅንሱ ላይ ችግር እንዲኖር ያደርጋል፡፡ ከብዙዎቹ መዘዞች መካከል በሰፊው የሚያጋጥመው የሚወለደው ህፃን ክብደቱ ከመደበኛው ከፍ ያለና ትልቅ ሕፃን መሆኑ ነው፡፡ በስኳር ህመም የተጠቃች እናት የምትወልደው ህፃን የክብደት መጠን ከ2ነጥብ5ኪሎ እስከ ኪሎ እንደሚሆን ሲጠበቅ ከዚህ ክብደት በላይ የሆነ ክብደት ያለው ልጅ ከተወለደ ትልቅ ህፃን ይባላል፡፡

በእናት ደም ውስጥ ያለው የስኳር መጠን ከፍ ሲል በእንግዴ ልጁ አድርጎ ወደልጁ የሚገባው የስኳር መጠንም በዚያው መጠን ይጨምራል፡፡ የስኳር መጠንን የሚቆጣጠርልን የኢንሱሊን ሆርሞን እንግዴ ልጁን ማለፍ ባይችልም ልጁ ግን ይህንን ሆርሞን ማምረት የሚጀምረው ቀደም ባሉት ሳምንታት ስለሆነ በራሱ ኢንሱሊን ከእናቱ ደም ጋር የሚመጣውን ስኳር ሊቆጣጠር ይሞክራል፡፡ ኢንሱሊን በማንኛውም ደም ውስጥ ያለው የስኳር መጠን ሲበዛ እንደሚያደርገው በዚህም ጊዜ ትርፉን ስኳር ወደስብ ይቀይረዋል፡፡

ትልቅ ህጻን የአወላለድ ሥርዓትን ሊቀይር ይችላል፡፡ ይህም ከማህፀን አቅም በላይ ከሆነ ቀዶ ጥገና ሊሰራ ይችላል፡፡ የሚወለደው ልጅ የተለያዩ የአካል ጉድለቶች ሊኖሩበት ይችላል፡፡ የልብ፣ የአእምሮ፣ የሆድ እቃ እና ኩላሊት በመሳሰሉት ዋና ዋና የሰውነት ክፍሎች ላይ የተለያዩ የአፈጣጠር ችግሮች (malformations) ሊመጡ ይችላል፡፡ የደም የስኳር መጠን በእርግዝና ወራት ሁሉ ከፍ ካለ በተለይ ደግሞ ከወሊድ በፊት ባለው 24 ሰዓት ውስጥ ከፍ ካለ ልጁ ሲወለድ የደም የስኳር መጠኑ በጣም ዝቅ ሊል ይችላል፡፡ ይህም የሚሆነው ልጁ በእናቱ ደም በኩል ሲያገኝ የነበረውን ከፍተኛ የስኳር መጠን ለመቆጣጠር ያመርት የነበረውን ከልክ ያለፈ ኢንሱሊን ከወለደችም በኋላ ሊያመርተውና ከፍ ብሎ ሊቆይ ይችላል፡፡ ነገር ግን ልጁ ሲወለድ ከናቱ ደም ጋር ያለው ግንኙነት ስለሚቋረጥ ሰውነቱ ውስጥ ያለውን ስኳር ይጨርሰዋል፡፡ በዚህም ጊዜ የደም የስኳር መጠኑ በከፍተኛ ደረጃ በትንሽ ጊዜ ውስጥ ይቀንሳል፡፡ ይህ ችግር ግን በቀላሉ ግሉኮስ በደም ቱቦዎች በመስጠት መቆጣጠር ይችላል፡፡

ከደም የስኳር ችግር በተጨማሪ የተለያዩ ጠቃሚ እንደ ካልሺየም እና ማግኔዥየም የመሳሰሉ ንጥረ ነገሮች መጠን መዛባትም በልጁ ላይ ሊያስከትል ይችላል፡፡ ከጊዜው በፊት የሚከሰት ምጥ፣ እርግዝናን ተከትሎ የሚመጣ የደም ግፊት፣ የእንሽርት ውሃ መብዛት የመሳሰሉ ችግሮችንም ከመዘዞቹ መሀከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡

አዲስ ዘመን፡-የስኳር ህመም ተጠቂ የሆነች ሴት ከማርገዟ በፊት ምን አይነት ቅድመ ዝግጅቶችን ማድረግ አለባት?

ዶክተር አህመድ፡እርግዝና ሲታሰብ በቅድሚያ የስኳር መጠን መቆጣጠር አስፈላጊ ነው፡፡ ይህንንም ከዶክተሮች ጋር በመተባበር ሊስተካከል ይችላል፡፡ አመጋገብን በማስተካክል፣ ቀላል አካላዊ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ፤ እንዲሁም የቤት ውስጥ የደም ግሉኮስ መለኪያ መሳሪያውን በቀን ከ4እስከጊዜ በመጠቀም የስኳር መጠንን ማስተካከል ይኖርባታል፡፡

ነፍሰጡሯ የምትመገበውን ምግብ ከ40እስከ 50በመቶ ካርቦሀይድት፣ 30እስከ 40በመቶ ጮማ እና 20በመቶ ፕሮቲን ቢይዝ ይመረጣል፡፡ ከምግብ በኋላ የስኳር መጠንን በመለካት ተስማሚ የሆነውን ምግብ መጠንና አዘገጃጀት ማስተካከል ይቻላል፡፡ ባለቤቷና ሌላ የቤተሰብ አባል ይህንን አመጋገብ ቢጋሯት ይመከራል፡፡ቀደም ብላ የኢንሱሊን ተጠቃሚ ከነበረች ጥንቃቄው ከፍ ይላል፡፡

የስኳር ህመም ለሚያመጣቸው እንደ ዓይን እና የልብ ችግር የሚደረግ ቅድሚያ ምርመራ ከማርገዟ በፊት ልታደርግ ይገባል፡፡ በትንሽ ጊዜ በከፍተኛ ፍጥነት የሚመጣ የስኳር መጠን ማስተካከል አንዳንድ ጉዳቶች ሊኖሩት ስለሚችል በተቻለ አቅም በቀስታ እና ረዘም ላለ ጊዜ በሚደረግ ክትትል የስኳር መጠንን ማስተካከል ይመረጣል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም እንደ ዶክተሯ ትእዛዝ ቫይታሚን እና አይረን ፎሌት ልትወስድ ትችላለች፡፡

ስለዚህ አንዲት ሴት ለማርገዝ ስታስብ መጀመሪያ ዶክተሯን ማማከር፤ በመቀጠልም የስኳር መጠንን በደንብ መቆጣጠር እና ትእግስተኛ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ በመጨረሻም የሚፈለገው የስኳር መጠን ላይ ስትደርስ ዶክተሯን በማማከር የወሊድ መቆጣጠሪያ መንገዷን ማቆም ትችላለች፡፡

አዲስ ዘመን፡-እርግዝና እና የደም የስኳር መጠን ያላቸው ግንኙነት ምን ይመስላል?

ዶክተር አህመድ፡-ከስኳር ህመም ጋር ተያይዘው የሚመጡ የፅንስ ችግሮች ባጠቃላይ ከደም የስኳር መጠን ከፍ ማለት እና መዋዠቅ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው፡፡ የአንድ ፅንስ ዋና ዋና አካላት የሚፈጠሩት በመጀመሪያዎቹ ስምንት ሳምንታት ስለሆነ በዚህ ጊዜ የሚከሰት ማንኛውም በፅንሱ ላይ ጉዳት ሊያመጣ የሚችል ነገር ሁሉ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል፡፡ ከማርገዝ በፊት የስኳር መጠንን መቆጣጠር ከውርጃ እና ህፃኑ ላይ ሊከሰቱ ከሚችሉ ከፍተኛ የአካል ጉዳቶች ይከላከላል፡፡

ጥሩ የደም የስኳር መጠን የሚባለው ከ70 እስከ 100 ..ሊ ከምግብ በፊት እና ከ120 ..ሊ በታች ከምግብ በኋላ ባሉት ሁለት ሰዓታት ውስጥ ከሆነ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ጥሩ እንቅስ ቃሴ፣ የተመጣጠነ ምግብ እና መድኃኒቶችን በስርአት መውሰድን ያጠቃልላል፡፡

አዲስ ዘመን፡በእርግዝና ወቅት የስኳር ህመም መድኃኒቶችን መጠቀም ጉዳት አያስከትል ይሆን ?

ዶክተር አህመድ፡-የሚዋጡ የስኳር ህመም መድኃኒቶችን ተጠቃሚ ከሆነች በእርግዝና ጊዜ ዶክተሩ ወደ ኢንሱሊን ይቀይራቸዋል፡፡ ይህም አንዳንዶቹ መድኃኒቶች እራሳቸው ፅንሱ ላይ ችግር ሊያመጡ የሚችሉ ስለሆነና የስኳር መጠንን በደንብ ለመቆጣጠር ስለሚረዳ ነው፡፡ በእርግዝና ጊዜ በተለይ በመጨረሻዎቹ ወራት የሰውነት የኢንሱሊን ፍላጎት ይጨምራል፡፡ ስለዚህ እንዳስፈላጊነቱ በሐኪም ትእዛዝ የኢንሱሊን መጠንን ሊጨምር እና ሊቀንስ ይችላል፡፡ የሐኪም ትእዛዘን መጠበቅ ግን የግድ አስፈላጊ ነው። ኢንሱሊን በልጁም ሆነ በእናቲቱ ጤና ላይ ምንም ችግር አያመጣም፡፡

አዲስ ዘመን፡-በእርግዝና ወራት የስኳር ታማሚ እናት አመጋገብ ምን መምሰል ይኖርበታል?

ዶክተር አህመድ፡-በእርግዝና ጊዜ ሰውነት የሚያስፈልገውን የምግብ መጠን ይጨምራል፡፡ ስለዚህ እናቲቱ ከሐኪሟ ጋር በመመካከር ከማርገዟ በፊት የነበራትን የአመጋገብ ሁኔታ ማስተካከል ይኖርባታል፡፡

የአልትራ ሳውንድ ምርመራም እንደማንኛውም እርጉዝ ሴት ሊደረግላት ይገባል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ሊያጋጥማት ስለሚችል ይሄንን በቀላል መድኃኒቶች ለመቆጣጠር የሚቻልበት ሁኔታ ከሐኪሟ ጋር መፍጠር ይኖርባታል፡፡ የልጅን እንቅስቃሴ ("kick counts") መቁጠርም አስፈላጊ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡ነፍሰጡሯ በምጥ እና በወሊድ ጊዜ ምን ማድረግ ይኖርባታል ?

ዶክተር አህመድ፡ከጊዜው የቀደመ ምጥ ሊከሰትባት ይችላል፡፡ የስኳር ህመም ያለባቸው እናቶች እርግዝናቸው በገፋ ቁጥር በተለይ ከ39 ሳምንት እያለፈ በሄደ ቁጥር ባልታወቀ ምክንያት ልጆቻቸው ላይ የተለያዩ ጉዳቶች ሊደርሱ ይችላሉ፡፡ የልጆቹ ክብደትም ከመጠን በላይ ይጨምራል፡፡ ስለዚህ ከዶክተራቸው ጋር በመመካከር የተለያዩ ምርመራዎች ከተደረጉላቸው በኋላ ምጥን በአርቴፊሻል መንገድ እንድትጀምሩ፤ ወይም በቀዶ ህክምና እንድትወልድ ሊያደርግ ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜም ቢሆን ግን የስኳር መጠንን እንደተለመደው መቆጣጠር የግድ ይላል።

ምንጭ:- አዲስ ዘመን

Related Articles

Post your comment