PLANET  ETHIOPIA.com

ሞሪንጋ (ሽፈራው ወይም ሽፈሬ) - የተፈጥሮው መድሐኒት

                                          

              ሞሪንጋ ለሰው ልጅ ጤንነት ከሚሰጠው ሰፊ ጠቀሜታ በመነሳት “ተአምረኛው ቅጠል” ተብሎ እስከመጠራት ደርሷል። ይህ ቅጠል በአብዛኛው በቀድሞ ጊዜያት በህንድ እና እስያ ሀገራት ነበር በስፋት ጥቅም ላይ ሲውል የነበረው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በሀገራችንም በከፍተኛ ደረጃ አገልግሎት ላይ እየዋለ ሲሆን፤ ለበርካታ በሽታዎችም መድሃኒት መሆኑ በተለያዩ ባለሞያዎች ተረጋግጦለታል። የሞሪንጋ ቅጠል በሳይንሳዊ መንገድ ከሚሰሩ መድሐኒቶች የሚወዳደር የጤና ጠቀሜታ እንዳለው ከመግለፅም ባለፈ በመድሐኒት ፋብሪካዎች ጭምር እንደ ግብዓት ከሚያገለግሉ ነገሮች ዋንኛው እየሆነ ነው።

የሞሪንጋ ይዘት

የሞሪንጋ የስነምግብ (nutration) ይዘቱ በአብዛኛው የሚገኘው በቅጠሉ ውስጥ ነው። ይህ የሞሪንጋ ቅጠል ታዲያ ከፍተኛ የሆነ ፕሮቲኖች፣ ቫይታሚኖች እና ማዕድናት አሉት። የአሜሪካ ብሔራዊ ጤና ተቋም እ.ኤ.አ. በ2012 ሞሪንጋን አስመልክቶ አስገራሚ መረጃ ይፋ አድርጓል። ይኸውም የሞሪንጋ ቅጠል ከሌሎች ምግቦች ጋር ሲነፃፀር በውስጡ የሚይዛቸው ንጥረ ነገሮች ከፍተኛ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው። ለአብነት ያህልም በሞሪንጋ ቅጠል ውስጥ የሚገኘው ቫይታሚን ሲ በብርቱካን ውስጥ የሚገኘውን ሰባት እጥፍ ሲሆን፣ የካልሲየም ይዘቱ ደግሞ በወተት ውስጥ የሚገኘውን አራት እጥፍ ነው። ሞሪንጋን በመጠቀማችን በካሮት ውስጥ የሚገኘውን ቫይታሚን ኤ አራት እጥፍ እንዲሁም በሙዝ ውስጥ የሚገኘውን ፖታሲየም ማዕድን ሶስት እጥፍ እና በእርጎ ውስጥ የሚገኘውን ፕሮቲን ሁለት እጥፍ እናገኛለን። በተጨማሪም ሞሪንጋ ለሰው ልጅ ሰውነት ከሚያስፈልጉ 20 ፕሮቲኖች መካከል 18ቱን የያዘ የተፈጥሮ ምግብ ነው። በስጋ ውስጥ የሚገኙ እና ለጤንነት እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ስምንት አሚኖ አሲዶችም በሞሪንጋ ቅጠል ውስጥ ይገኛል።

ሞሪንጋ ቅል በተፈጥሮ ለሰውነት አስፈላጊ በሆኑ አሚኖ አሲዶች፣ ቫይታሚን ኤ፣ ቫይታሚን ቢ1፣ ቫይታሚን ቢ2፣ ቫይታን ቢ3 እና ቫይታሚን ቢ6 እንዲሁም በቫይታሚን ሲ የበለፀገ ነው። የሞሪንጋ የማእድን ይዘትን በተመለከተም ከፍተኛ የሆነ የካሊሲየም፣ ፖታሲየም፣ ብረት፣ ማግኒዚየም፣ ፎስፈረስ እና ዚንክ ምንጭ ነው ሞሪንጋ።

የሞሪንጋ የጤና ጥቅሞች

ሞሪንጋን በተለያዩ መንገዶች መጠቀም ለጤና በርካታ ጠቀሜታዎች አሉት። ከእነዚህ ውስጥም ለሆድ ህመም እና አለመስተካከል፣ ለአለርጂ፣ ለጉበት፣ ለአጥንት፣ ለልብ እና ከልብ ጋር ለተያያዙ ችግሮች፣ ለስኳር ህመም ፣ ለአይን ጤንነት ለቁስል እና ለቆዳ እንዲሁም ለፀጉር የሚሰጣቸው ጠቀሜታቸው ዋና ዋናዎቹ ናቸው። የዚህ የሞሪንጋ ፀረ ፈንገስ እና ፀረ ባክቴሪያ ባህሪያትም የተለያዩ ኢንፌክሽኖች እና እብጠቶችን ለመከላከል እንዲጠቅም አድርጎታል። በተጨማሪም ካንሰርን፣ የምግብ ልመት ችግርን፣ የመተንፈሻ አካላት ህመምን እንዲሁም የኮሌስትሮል እና የደም ግፊትን በማስተካከል ረገድ ሞሪንጋ ጠቀሜታው ብዙ ነው። ሞሪንጋ የደም ማነስን የመከላከል፣ ሰውነታችን በሽታን በቀላሉ እንዲቋቋም የማድረግ ጠቀሜታም አለው። በሞሪንጋ ውስጥ የሚገኙት ስቦች እና አደገኛ ኮሌስትሮሎች መጠናቸው ዝቅተኛ በመሆኑ ከመጠን ያለፈ የሰውነት ክብደትን የመከላከል ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው።

ሞሪንጋ ለውስጥ ደዌዎች

ሞሪንጋ ከፍተኛ የሆነ ፀረ ባክቴሪያ ንጥረ ነገሮች ስላሉት የስኳር ህመምን ለመከላከል እና ለማስታገስ ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው። በሞሪንጋ ውስጥ በብዛት የሚገኘው ቫይታሚን ኤ በሰውነታችን ውስጥ የሚገኘውን ቤታ ኬሮቲን ወደ ጠቃሚ ንጥረ ነገሮች በመቀየር የስኳር ህመም ያለበትን ሰው ለአይነ ስውርነት የመጋለጥ እድል ይቀንሳል። በተጨማሪም በዚህ ቅል ውስጥ የሚገኘው ቫይታሚን ሲ በሰውነታችን ውስጥ የሚከናወነውን የኢንሱሊን ምርት በማመጣጠን ለስኳር ህመም ያለውን ተጋላጭነት የሚቀንስ ሲሆን፣ ቫይታሚን ዲ ደግሞ ህጻናት በመጀመሪያ ደረጃ ስኳር እንዳይጠቁ ያግዛል። ሞሪንጋ በደም ውስጥ የሚኖረውን ግሉኮስ፣ የሽንት ስኳርን እና በሽንት ውስጥ የሚኖረውን ፕሮቲን በማመጣጠን ወደር የሌለው ጠቀሜታ አለው።

ከስኳር ህመም በተጨማሪም ሞሪንጋ የደም ግፊት መጠንን የማስተካከል ጠቀሜታ አለው። በሞሪንጋ ውስጥ የሚገኙት ባዮአክቲቭ ንጥረ ነገሮች ደም ቅዳ እንዳይጠብ በማድረግ ከፍተኛ የደም ግፊትን ይከላከላሉ።

አይስቲዮሳይናይነስ የተባለው እና በብዛት በሞሪንጋ ቅጠል ውስጥ የሚገኘው ንጥረ ነገር በሆድ ውስጥ በሚከሰቱ እንደ ሆድ ድርቀት፣ የጨጓራ ህመም እና የሆድ ውስጥ ቁስለትን ለመከላከል ያግዛሉ። በሞሪንጋ ውስጥ የሚገኙት ፀረ ባክቴሪያ እና ፀረ ጥገኛ ተዋሲያን ንጥረ ነገሮችም በሆድ ውስት የሚከሰተውን የተዋሲያን እድገት በመግታት ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። ይህን በማድረግም ለተቅማጥ የሚዳርጉ ተዋስያንን ለማስወገድ ያገለግላል። ሞሪንጋ በጥቃቅን ተዋስያን እና በባክቴሪያ ሳቢያ የሚከሰቱ የሆድ ውስጥ ህመሞችን የመፈወስ ሃይሉም ከፍተኛ ነው። ጃማይካ ኦብዘርበር የተባለ ድረ-ገፅ ጥናቶች እንዳመለከቱትም ከሞሪንጋ የሚገኙ ፀረ ባክቴሪያ እና ፀረ ተዋሲያን ንጥረ ነገሮች ምግብ ወለድ የሆኑ በሽታዎችን የመከላከል አቅሙ ከፍተኛ ነው። የሞሪንጋ ቅጠል የአንጀት ትላትሎችንም የመግደል ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው።

አሁን ባለው ሁኔታ ካንሰርን ለመፈወስ በርካታ ሙከራዎች ተደርገዋል። ለዚህ ፈታኝ በሽታም በሞሪንጋ ውስጥ የሚገኙ ንጥረ ነገሮች ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተገልጿል። ሞሪንጋ ፀረ ካንሰር እንደሆነ የገለፀው በፓኪስታን በተካሄደ ጥናት ላይ ተመርኩዞ በጆናል ኦቭ ኸርቫል ሜዲሲን የወጣ መረጃ፤ በሞሪንጋ ውስጥ የሚገኘው ባዮአክቲቭ ንጥረ ነገር የካንሰር ሴሎች ማደግን የመግታት ጠቀሜታ አለው። ሞሪንጋ በሰውነት ውስጥ ያሉ ኬሚካሎችን የማመጣጠን አገልግሎት ስለሚሰጥ የማህጸን ካንሰርን እና ሌሎች የካንሰር አይነቶችን የመከላከል ጠንካራ አቅም አለው።

በሌላ በኩል በሞሪንጋ ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያላቸው ማዕድናት መገኘታቸው ሞሪንጋ ለአጥንት ጤንነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ያደርገዋል። ሞሪንጋ በመገጣጠሚያ እና በአጥንት ላይ የሚደርሱ የተለያዩ ኢንፌክሽኖችን እብጠቶችንና ህመሞችን ለመከላከል በሞሪንጋ ውስጥ የሚገኙት ካልሲየም እና ፎስፈረስ የተባሉት ማዕድናት ከፍተኛውን አስተዋፅኦ ያበረክታል።

ሞሪንጋ የመተንፈሻ አካላት ችግሮችን የመከላከል እና የመፈወስም ጠቀሜታው ቀላል የሚባል አይደለም። በተለይ እንደ አስም ያሉ የመተንፈሻ አካላት ህመሞችን ለማስታገስ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። የሞሪንጋ ቅጠልን መጠቀም በአስም እና በሌሎች የመተንፈሻ አካላት ህመሞች ምክንያት የሚከሰቱ እንደ ማፈን፣ ማሳል እና መጨነቅ ያሉ ስሜቶችን ለማስታገስ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። ይህ ቅጠል በመተንፈሻ አካላት እና በሳንባ አካባቢ የተስተካከለ የአየር ዝውውር እና አተነፋፈስ እንዲኖር ያደርጋል።

በሽንት መመረት እና በሽንት መወገድ ዙሪያ ያሉ የሰውነት ሂደቶች ላይም ሞሪንጋ ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ እንደሆነ ባለሞያዎች ይገልጻሉ። በሞሪንጋ ውስጥ የሚገኙ ማዕድናት በኩላሊት እና በፊኛ ውስጥ የሚፈጠረውን እና ለኩላሊት ጠጠር መንስኤ የሚሆነውን ጠጣር ነገር የመከላከል አቅማቸው ከፍተኛ ነው። በተለይ ከሞሪንጋ ስራስር የሚገኘው ክፍል ይህን አይነቱ ጠጣር ነገር በሰውነት ውስጥ እንዳይፈጠር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ስላለው የሽንት ምርትና አወጋገድ ሂደቱ የተሻለ እንዲሆን ያደርጋል።

ከመጠን ያለፈ ውፍረትን ለመከላከል እና አላስፈላጊ ኮሌስትሮልን በማስወገድ ረገድም ሞሪንጋ ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው። ሞሪንጋ በሰውነታችን ውስጥ የሚከማቹ አላስፈላጊ ስቦችን በማስወገድ ጉበት፣ ኩላሊት እና ልብ ተግባራቸውን በአግባቡ እንዲያከናውኑ ያግዛል። ሞሪንጋው በራሱ አነስተኛ ኮሌስትሮል እና ስብ ስላው ተጨማሪ ስብ ወደ ሰውነት አይገባም። በሞሪንጋ ውስጥ የሚገኘው ቫይታሚን ቢ የምግብ ልመት የተስተካከል እንዲሆን በማድረግ ምግብ ወደ ኃይል እንዲቀየር እና በሰውነት ውስጥ የሚከማች ስብ እንዳይኖርም ያግዛል።

ሞሪንጋ ለውጫዊው አካላት

ሞሪንጋ በቆዳ ላይ በተለያዩ ቫይረሶች ሳቢያ የሚከሰቱ ችግሮችን ለማከምም ይጠቅማል። በሞሪንጋ ውስጥ የሚገኙት ፀረ ቫይረስ ንጥረ ነገሮች በቆዳ ላይ የሚወጡ እብጠቶች እና ቁስሎች እንዳይስፋፉ በማድረግ ህመሙ በቀላሉ እንዲድን ያደርጋል። በተጨማሪም የውሃ ይዘቱ ከፍተኛ የሆነው የሞሪንጋ ቅጠል ቁስልን የመፈወስ ጠቀሜታው ከድሮ ጀምሮ የተመሰከረለት ነው። ዘመናዊ የጥናት ውጤቶች እንዳመለከቱትም ሞሪንጋ ቁስል በቀላሉ እና በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲድን፣ ከቁስል በኋላ ቆዳ ወደ ቀድሞ ጤንነቱ እንዲመለስ እንዲሁም ጠባሳው እንዳይሰፋ እና በቀላሉ የቆዳውን ቀለም እንዲይዝ የሚያደርግ የተፈጥሮ መድሃኒት ነው።  

የሞሪንጋ ቅጠል ውስጥ የሚገኙ ፀረ- ባክቴሪያ ንጥረ ነገሮች ቆዳችን በባክቴሪያ በቀላሉ እንዳይጠቃ ያግዛሉ። ከዚህ በተጨማሪም በቆዳችን ላይ የሚያርፉ የተለያዩ ብናኞች ቆዳችንን እንዳይጎዱ እንዲሁም ቆዳችን በእድሜ መግፋት ምክንያት ፈጥኖ እንዳይጎ ያደርገዋል። በሞሪንጋ ውስጥ የሚገኘው ከፍተኛ መጠን ያለው ፕሮቲን ደግሞ የቆዳችን የላይኛው ክፍል ከኢንዱስትሪ እና ከተለያዩ ነገሮች በሚለቀቁ አደገኛ ንጥረ ነገሮች እንዳይጎዱ ይከላከላል።

ምንጭ:- ሰንደቅ

Related Articles

Post your comment