PLANET  ETHIOPIA.com

ቸል ልንላቸው የማይገቡ የሳንባ ካንሰር ምልክቶች

                                                   

           አዲስ አበባ፣ ህዳር 13፣ 2008 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሳንባ ካንሰር የሳንባ ህዋሳት ከቁጥጥር ውጪ በሆነ መልኩ ቁጥራቸው ሲጨምር ይከሰታል። እነዚህ ህዋሳት በአጭሩ መፍትሄ ካልተበጀላቸው ወደ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች የመራባት ባህሪ አላቸው። ለሳንባ ካንሰር ህመም ሲጋራ ማጨስ በዋነኝነት በምክንያትነት ይጠቀሳል። ይሁን እንጂ በሽታው በማያጨሱ ሰዎች ላይም ይከሰታል። በሳንባ ካንሰር ተጠቂ የሆኑ ቤተሰብ ያላቸው ሰዎች ለበሽታው ተጋላጭነታቸው እንደሚጨምርም ይነገራል። ከአጫሽ ሰዎች ጋር ቅርብ ግንኙነት ያላቸው ሰዎችም እንዲሁ ለሳንባ ካንሰር የመጋለጥ እድላቸው ሰፊ ነው። የሳንባ ካንሰር በዋናነት በእድሜ ገፋ ባሉ ሰዎች ላይ የሚከሰት ሲሆን፥ 70 በመቶ የሚሆኑት የበሽታው ተጠቂዎች እድሜያቸው ከ65 አመት በላይ ነው፤ 3 በመቶው ደግሞ ከ45 አመት በታች ናቸው። የአሜሪካ የበሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ማዕከል (ሲዲሲ) መረጃ እንደሚያመለክተው፥ የሳንባ ካንሰር በተለያዩ የካንሰር ህመሞች ምክንያት ከሚከሰት ሞት 27 በመቶውን ይሸፍናል። ከአንጀት፣ የጡት እና ፕሮስቴት ካንሰር በበለጠ የሳንባ ካንሰር በየአመቱ በርካታ ሰዎችን ለህልፈት እንደሚዳርግም ነው መረጃው የሚጠቁመው። የህመሙ ምልክቶች እድሜ እየገፋ ሲመጣ መታየታቸው ህመምተኞቹን ለማከም የሚደረገውን ጥረት አስቸጋሪ አድርጎታል።

 በመሆኑም ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ነጥቦች የሳንባ ካንሰርን ከስሩ ለመቅጨት ያግዛልና ቢያጤኑት ይላል የቶፕ ሄልዝ ሪሜዲስ ድረ ገጽ ዘገባ።

 1.    ደረቅ ሳል

ለሶስት ሳምንት እና ከዚያ በላይ የዘለቀ እና ደረቅ ሳል የሳንባ ካንሰር ምልክት ሊሆን ይችላል። በሳል ወቅት ከደረት ጀምሮ እስከ ወገብ የሚዘልቅ የህመም ስሜት ሲሰማም ለዚሁ በሽታ  መጋለጥን ሊያመላክት እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ።

 2.    ደም የቀላቀለ ሳል

 በተለይም አጫሾች ደም የቀላቀለ ሳል ካላቸው ለበሽታው ተጋላጭ መሆናቸውን ሊያሳይ ስለሚችል  የህክምና ባለሙያዎችን ማነጋገር ተገቢ ነው። ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ከባድ ሳል፣ የመተንፈስ ችግር እና ትኩሳትም የህመሙ ምልክቶች ናቸው።

 3.    የድምጽ መቀየር

የአየር መተላለፊያ ቧንቧዎች መጥበብ ወይም መዘጋት የድምጽ መቆራረጥና መቀየር ያስከትላል። ለአስም እና ለተለያዩ አለርጂዎች መጋለጥ ብዙ ጊዜ ለድምጽ መቀያየር በምክንያትነት ይጠቀሳሉ፤ ይሁን እንጂ የሳንባ ካንሰር ምልክትም ሊሆኑ እንደሚችሉ ይነገራል። የድምጽ ለውጡ ለተከታታይ ቀናት ከቀጠለ እና ጉንፋንም ይሁን አስም ከሌለበዎት ሀኪም ማማከር ይገባል።

 4.    የትንፋሽ መቆራረጥ

 ከ10 የሳንባ ካንሰር ተጠቂዎች ዘጠኙ የትንፋሽ መቆራረጥ ችግር ይስተዋልባቸዋል። የደም ቧንቧዎች መዘጋት፣ የደም ማነስ፣ የመተንፈሻ አካላት ማመርቀዝ እና ከፍተኛ ቦታዎች ላይ መኖር የአተነፋፈስ ስርዓትን ሊያዛባ ይችላል። ነገር ግን ከመደበኛ ኑሯችን በተለየ አየር የመሳብ ችግር ካጋጠመን እና ከዚህ ቀደም በቀላሉ የምንከውናቸው ስራዎች እጅግ እየከበዱን ከመጡና መተንፈስ ካቃተን ለሳንባ ካንሰር መጋለጣችን ያሳያል።

 5.    የደረት እና አጥንት ህመም

 በሳል ወቅት የሚበረታ የደረት ህመም፣ ሳቅ እና ጥልቅ አተነፋፈስ በአብዛኛው የሳንባ ካንሰር የመጀመሪያ ምልክቶች ናቸው። እነዚህ ምልክቶች የሚስተዋሉት ካንሰር በሳንባ ውስጣዊ ግድግዳ ላይ ሲስፋፋ ነው። ካንሰሩ ሲጠናከርም ወደ ተለያዩ አጥንቶች የሚዘልቅ ሲሆን፥  በእጅ፣ አፍንጫ፣ ወገብ፣ ጀርባ እና የተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ላይ የህመም ስሜትን ይፈጥራል። ስለሆነም ለአራት ሳምንት እና ከዚያ በላይ የቆየ የደረት እና አጥንት ህመም የሳንባ ካንሰር ምልክት ሊሆን ስለሚችል ባለሙያ ማማከር ይበጃል።

 6.    የጉሮሮ ቁስል እና የሳንባ ምች 

 ፀረ ባክቴሪያ መድሃትን እየወሰድን እንደ ብሮንካይት ያሉ የደረት አካባቢ ኢንፌክሽኖን በተደጋጋሚ የሚከሰቱብን ከሆነ ሌላው የሳንባ ካንሰር ምልክት ሊሆን ስለሚችል  አስቸኳይ ምርመራ ማድረግ ተገቢ ነው ።

 7.    ምግብ የመዋጥ ችግር

 ለተከታታይ ሳምንታት የዘለቀ ምግብ የመዋጥ ችግር የጉሮሮ አልያም የሆድ ካንሰር ምልክት ሊሆን ይችላል። ምግብ በምንወሰድ ስዓት ለመተንፈስ የመቸገር እና የሚያስለን ከሆነም ለሳንባ ካንሰር መጋለጥን ያሳያሉ። በ2004 በግብጽ የተደረገ ጥናት ምግብ የመዋጥ ችግር ዋነኛ የሳንባ ካንሰር ምልክት መሆኑን ጠቁሟል። 

 8.    ከፍተኛ የክብደት መቀነስ

 ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከ10 የሳንባ ካንሰር ተጠቂዎች ስድስቱ ክብደታቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ  ቀንሷል። የካንሰር ህዋሳት በሰውነታችን ውስጥ የተጠራቀመውን ሀይል መጠቀም ሲጀምሩ ነው ክብደታችን የሚቀንሰው። ከክብደት መቀነሱ ተዳምሮ የድካም ስሜት፣ የምግብ ፍላጎት ማነስ እና አቅም ማጣት የህመሙ ምልክቶች ናቸው።

 9.    የጣት እና ጥፍሮች ቅርጽ መበላሸት

 ከልብ አልያም ከሳንባ ጋር በተያያዘ ችግር በደም ውስጥ የሚገኘው የኦክስጅን መጠን አነስተኛ መሆን ለጣት እና የጣት ጥፍሮች ቅርጽ መበላሸት ይዳርጋል። የሳንባ ካንሰር ተጋላጭነትን ለመቀነስ፡-

 -    አጭሰው የማያውቁ ከሆነ እንዳይጀምሩት፤ እያጨሱም ከሆነ የማቆሚያዎ ጊዜ አሁን ነው።

 -    ከሚያጨሱ ሰዎች ጎን አለመሆንዎን ያረጋግጡ

 -    በከፍተኛ ሁኔታ ወደ ተበከሉ እና የኢንዱስትሪ ስፍራዎች ከማምራት ይቆጠቡ ፤ ወደነዚህ ስፍራዎች መጓዝ ግድ ከሆነበዎትም አስፈላጊውን ጥንቃቄ ያድርጉ

 -    የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ ይሞክሩ

 -    ፍራፍሬ፣ አትክልት እና ጥራጥሬዎችን አመጣጥነው ይመገቡ

 -    ፍርሃት እና ጭንቀትን ያስወግዱ

-    በቀን 2 ወይም 3 ጊዜ የዝንጅብል ሻይ ይጠጡ

 -    ከሀኪም ትዕዛዝ ውጪ የትኛውንም አይነት መድሃኒት አይውሰዱ

-    ንጽህናዎን ይጠብቁ፤ በየጊዜው የሀኪም ክትትል ያድርጉ።

 የትርጉም ምንጭ:- FBC

 

 

 

 

 

Related Articles

Post your comment