PLANET  ETHIOPIA.com

እኔና ምኞቶቼ.........

እኔና ምኞቶቼ.........
እኔ 'working class of ethiopia' ነኝ፡፡ ስተረጉመው እኔ በወዙ የሚያድረው የኢትዮጲያ ህዝብ አባል ነኝ፡፡በጣም ወጣት ነኝ፡፡ እሳቱ ሰ ልትሉኝ ትችላላችሁ፡፡እሳቱ ሰ ሲተረጎም ደግሞ እሳቱ ሰው ማለት ነው፡፡
እናማ ይሄውላችሁ ሰሞኑን አገራችን ይገባሉ ተብለው ይጠበቁ በነበሩት መሪ ኦባማዬ ምክኒያት በተፈጠሩ ክስተቶች አንዳንድ ምኞቶቼ አናቴ ላይ ወተው ዳንኪራ ይረግጡ ጀመር፡፡ በነገራችን ላይ እነዚህ ምኞቶቼ የአፍሪካ ህብረት ስብሰባዎች እና የኢኮኖሚ ፎረም ስብሰባዎች ላይ ይከሰታሉ፡፡
ክስተት 1 - መንገድ ይዘጋል
ያው እንደ ላብ አደርነቴ አሞራ ዞሮ የማይጨርሰውን ያገር ሰልፍ ለ 30 ደቂቃ(በትንሹ) ቆሜ ከተሰለፍኩ በሁዋላ አንድ አንካሳ ታክሲ ውስጥ ወይም ቁመቱ የኮንዶሚኒየም ህንጻ ጋር እኩል የሆነ ብሬክ ዳንስ የሚደንስ ድጋፍ ሰጪ ካቻማሊ ውስጥ እገባለሁ፡፡የገባሁበት ታክሲ ወይም አውቶቡስ በእርጅና 3ቴ አስነጥሶ ከተነሳ በሁዋላ አንድ ኪ.ሜ እንኩዋን ሳይሄድ በጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን መንገድ ይዘጋል፡፡መንገዱ ከተዘጋ ከ 20 ደቂቃ በሁዋላ ቀይ እና ሰማያዊ መብራቶች እየተብለጨለጩ ሞተር ብስክሌቶች እና ሰንጋ መኪኖች እያናፉ ከመሀላቸው አፍንጫዋን በባንዲራ ያስጌጠችውን ውሃ ማርቼዲስ መኪና እንደገጠር መኪና ሸፋፍነው እብስ ይላሉ፡፡ ይሄን ይሄን ሳይ ኮሌጅ በጥሼ ጋራ ደርምሼ ባለስልጣን መሆን እመኛለሁ፡፡ ክፍት መንገድ ምን እንደሚመስል ለማየት..........
ክስተት 2 - ተፈተሽኩ
ይህቺኛዋ ክስተት ከጋሽ ኦባማ ጋር ተያይዛ የመጣች መላ ናት፡፡ እኔም ከጦር ሀይሎች ሜክሲኮ ስደርስ የተወሰኑ መለዮ ለባሽ የሀገሬ ቦሊሶች የተሳፈርኩባትን ታክሲ ይፈትሹ ጀመር፡፡ተሳፋሪዎች ደግሞ በየጾታ ወገናቸው ከታክሲ ወርደው ይፈተሹ ገቡ፡፡እኔንም ፖሊስ እህቴ በፈረጠመ እጁዋ ጨመቅ ጨመቅ ታደርገኝ ጀመር ፡፡ በፍተሻ ሰበብ መንግስታችን መለስተኛ ማሳጅ ሸለመኝ፡፡ ይሄኔ ይቺ ፍተሻ በወር ሁለቴ ብትኖር ብዬ ተመኘሁ..... አሀ! እኔ ማሳጅ ቤት ገብቼ አላውቅ ሚያሽ ከተገኘ መታሸት ነውይ!!
ክስተት 3 - ጉጉትና ቁጣ
ከፍተሻው በሁዋላ በቤተ መንግስታችን ሌቱ አልነጋ አለ፡፡ በዩኒፎርማቸው ቢጫነት የጁስ ብርጭቆ መስለው በከረሙት የጽዳት ሰራተኛ ጉዋደኞቼ ፏ! ያሉት የቦሌ መንገዶች ጽልመቱ ረዝሞባቸው የእሁድ ጀንበር መታየት ስትጀምር እግራቸውን ይዘረጋጉ ጀመር፡፡ ያገሬ መገናኛ አውታርም በእንግሊዘኛ ጥሩ አፍ አላቸው ብሎ ያሰባቸውን ጋዜጠኞች በአውሮፕላን ማረፊያው አሰለፈ፡፡ ገራገር ሚንስትሮቼም ሴት ልጃቸውን በሙሽራ ወግ እንደሚጠብቁ የከተማ እናቶች ተሰልፈው ጣሃዩን ያሜሪካ ፕሬዚዳንት ይጠብቁ ገቡ፡፡ ይህን ሁሉ ታዲያ ያየሁት እቤት ባለች 14 ኢንች ቴሌቪዥን ላይ አጨንቁሬ ነው፡፡ በርግጥ በደንብ ለማየት ያመቸኝ ዘንድ ቤት ውስጥ ባገኘሁት አጉሊ መነጽር 14ቱዋን ኢንች ወደ 42 ከፍ አደረግሁዋት፡፡ልክ 12፡10 ሰአት ገደማ በግዝፈቱ እና በቅንጡነቱ የተወራለትን የአሜሪካ አውሮፕላን ካገሬ ምድር ላይ አርፎ ምላሱን ሲዘረጋ አየሁት፡፡ ከዚያም በብዙ ሰዎች የታጀቡት ሰው(the ሰው)ታዩ፡፡ትንሽ ቀላ ከማለታቸው ውጪ እራሳቸው ናቸው፡፡ ከአውሮፕላኑ ወርደው ወደ ሚንስትሮቹ ሰልፍ ሲደርሱ ያ የሰርገኛ ሰልፍ የመሰለ አቁዋቁዋም ቡሄ ወደሚጨፍሩ ህጻናት ከበባ ተቀየረ፡፡ይሄን ሳይ አለቆቼ ለጣሀዩ መሪ እንዲህ ሚሉ መሰለኝ
‹‹ እዚ ማዶ ሆ! አንድ ሻሽ እዛ ማዶ ሆ! አንድ ሻሽ ሆ....
የኔ ኦባማ ሆ! ዶላር ለባሽ ሆ......
ሆያ ሆዬ ጉዴ
መሽቆጥቆጥ ነው ልማዴ...........››
በዚህ ጊዜ አንድ ምኞት ተመኘሁ.... እኚህ ሰውዬ እንደነብራድ ፒት በአዛውንት ጉዲፈቻ ልጅነት እንኩዋን ቢወስዱኝ እና ለአንዲት ቀን እንኩዋን መሪዎቼ ቢሽቆጠቆጡልኝ ብዬ ተመኘሁ፡፡‹ ነብይ ባገሩ አይከበርም› እንዲል መጽሃፉ ባገሬ ላይ ሆኜ የሌላ ወንዝ ወዝ ተመኘሁ፡፡ወዲያው ደግሞ ‹‹ምድረ ፍናፍንት እንዲጋባ የፈቀደ ሰውዬ ምን ብለው ነው የሚጠጉት!!! ›› የሚለውን የአንድ አዛውንት ተግሳጽ ስሰማ በምኞቴ ተሰቀቅሁ፡፡ከዚያ በሁዋላ ደግሞ ቁጣ ተተካ! ለምን ቁጣ ተተካ ቁጣ እኔ ላይ አይደለም የተተካው ፡፡ እኔና ህዝብ ስንሆን ግን ቁጣ ቁጣ ይለናል ! የሚሊዮኖች ሰአትና ፕሮግራም ለጥቂቶች ሲሰጥ እናቄማለን፡፡እንግዳ መቀበል አኩሪ ባህላችን ቢሆንም መስተንግዶዋችን ልጆቹን አፈር ላይ እያስተኛ እንግዶቹን ቅንጡ አልጋ ላይ እንደሚያጋድም አሳዳጊ አንሁን፡፡ የብዙሃኑን ጥቅም በማይጎዳ መልኩ እንግዶች የመንገድና የመስተንግዶ አገልግሎት ያግኙ፡፡ ደግሞ ጎበዝ ለማንኛውም አንባላም(እኛ ሀበሾች) ....
እኔም ከምኞቴ ልገላገል! አበቃሁ!


ከቤተልሄም ኒቆዲሞስ

Related Articles

Post your comment