PLANET  ETHIOPIA.com

የእብድ ውሻ በሽታ (Rabies)

 

                                                                                                                         

ታማኝነታቸውና ጠባቂነታቸው ቀድሞ የሚታሰበን ውሾች፥ ይህም ህይወታቸውን ለአሳዳጊዎቻቸው አሳልፈው እስከመስጠት እንዳደረሳቸው የሚናገርን ታሪክ ማንበብ ወይም መስማት እንግዳ አይደለም፤ አንዳንዶቹ እንዲያውም በህይወት ከሌሉ አሳዳጊዎቻቸው መቃብር ስር አይታጡም ሲሉ ብዙዎች ሲናገሩ ተደምጠዋል።
ዛሬ ግን ማውሳት የምንሻው የውሻውን ህመም ነው፤ በአገራችን ባለቤት የሌላቸውንና ምግባቸውን ከመንደር መኖሪያቸውን ከጎዳና ያደረጉ ውሾችንም ሆነ በግቢ ውስጥ ጥበቃ ተደርጎለት የሚያድግ ውሻን ሊይዝ ስለሚችለው የእብድ ውሻ በሽታ ነው፤ በተለይም ከሰው ጋር ስላለው ንኪኪ ።
የእብድ ውሻ በሽታ አንድ ሰው በውሻው ከተነከሰ በዃላ ወዲያው ህክምናውን ካላገኘ በአጭር ጊዜ በውስጡ የሚዛመት እና ለሞት የሚዳርግ አደገኛ በሽታ ሲሆን፥ የተነከሰው ሰውም ምልክቶቹ ከታዩበት መዳን አይችልም።
ዶክተር ሮማን የእንስሳት ሀኪም ሲሆኑ፥ የእብድ ውሻ በሽታን ስር ሳይሰድ በክትባት ልንከላከለው እንደምንችል ይሁንና በአደጉ አገራት በተነከሰው ቦታ ላይ የሚጨመርና ቫይረሱን ለማክሸፍ የሚረዳው “ሀይፐር ኢሚውንሴር” የተሰኘው የህክምና ዘዴ ግን በአገር ውስጥ አለመጀመሩን ይጠቅሳሉ።
የደመ ሞቃት እንስሳት በሽታ የሆነውና በተለምዶ የእብድ ውሻ በሽታ የምንለው ፥ ውሾችን ብቻ የሚያጠቃ በሽታ ሳይሆን፥ ከቤት እንስሳት ድመቶችን እና የጋማ ከብቶችን፤ ከዱር እንስሳትም ቀጭኔ፣ አንበሳና አጋዘንን ሊያጠቃ ይችላል።
ታዲያ ያሳደጉትም ሆነ መንገደኛ ውሻ ከተቅበጠበጠ፣ ብቸኝነትን የሚመርጥ ከሆነ፣ ድምፁ ከተቀየረ፣ ከተንገዳገደ እንዲሁም ያልተለመደ ቁጣ ካስተዋሉበት ችግር አለ፤ ምክንያቱም እነዚህ የህመሙ ምልክቶች ስለሆኑ።
የአለም የጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያወሳው አንድም በህመሙ የተጠቃ ውሻም ሆነ በውሻው የተነከሰና ምልክቶቹ በግልፅ የታዩበት ሰው ሊድን አልቻለም።
ይሁንና በውሻው የተነከሰ ግለሰብ ለ15 ደቂቃ በውሃና በሳሙና በደንብ ቢታጠብ ወደ ሰውነት ዘልቆ የሚገባውን የቫይረስ መጠን መቀነስ እንደሚችል እንዲሁም የተነከስንበት ቦታ ከአንጎላችን ያለው ርቀትም በሽታው በሰውነታችን የሚሰራጭበትን ጊዜ እንደሚወስነው ነው ዶክተር ሮማን የገለፁት።
በመሆኑም ሰዎች የሚያሳድጉትን ውሻ በየጊዜው ማስከተብ እና ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ግን ወሳኝ ተግባር ሊሆን ይገባል።


ምንጭ፡ ፋና ራድዮ

Related Articles

Post your comment