PLANET  ETHIOPIA.com

ጤናማ ፀጉር እንዲኖርዎ ሊያደርጉ የሚገባዎት ጥንቃቄ - ከጽጌረዳ ጫንያለው

 

 

ከጽጌረዳ ጫንያለው

 ወንዶች ይልቅ ለሴቶች የውበት መገለጫ የሚሆነው ፀጉር መሆኑን ማንም አይክደውም። ይሁን እንጂ ለወንዶችም ቢሆን የውበት መገለጫ አይሆንም ማለት አይቻልም። ምክንያቱም ፀጉሩ ሉጫና ድፍት ያለ፣ የበዛ ወይም ቶሎ ቶሎ የሚያድግ ወንድ ልጅ ካየን «ታድሎ» ማለታችንና የፀጉሩን ውበት ማድነቃችን አይቀርም። ከመደናነቃችን መረዳት የሚይቻለው ማንኛውም ሰው

 ለፀጉሩ ልዩ ትኩረት መስጠት እንዳለበት ነው። ፀጉር በእንክብካቤ ውስጥ ሆኖና ምንም ዓይነት የፀጉር ችግር ባይኖርበትም እንኳን በእያንዳንዱ ቀን ከ70 እስከ 100 የሚደርሱ ፀጉሮች ሊረግፉ ይችላሉ። ነገር ግን የፀጉር መነቃቀሉ ከዚህ በላይ ከሆነ ጥያቄ የሚያስነሳ መሆን ይኖርበታል።

ለፀጉር ከሚደረግ እንክብካቤ አንጻር ፀጉር ይነቃቀላልየሚደረግ እንክብካቤስ ቢሆን ምን መምሰል አለበትከእንክብካቤ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ፀጉርን ሊጎዱ የሚችሉ ነገሮች ምንድንናቸውፀጉራችን ተነቃቀለ የምንለው ምን ሲሆን ነውምክንያቱስ ምን ሊሆን ይችላልና መሰል ነገሮችን በማንሳት በጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ኮሌጅ የቆዳና የአባለዘር በሽታዎች ስፔሻሊስት ዶክተር ፋይሰል አሎ ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርገናል። የሰጡንንም ምላሽ እንሆ።

አዲስ ዘመን፡የፀጉር መነቃቀልን ሊያስከትሉ የሚችሉ ነገሮች ምን ምን ናቸው?

ዶክተር ፋይሰል፡የፀጉር መነቃቀል ሲነሳ በሁለት ዓይነት ከፍሎ ማየት ይቻላል። ይኸውም ጠባሳ ሳይኖረውና ጠባሳ ኖሮት የሚፈጠር መነቃቀል ነው። ከእነዚህ መካከልም ውስጥ የፀጉር አበቃቀል መዛባት፣ የተመጣጠነ ምግብ አለማግኘት፣ ረዥም ጊዜ የሚቆይ ትኩሳት ወይም በቆዳ በሽታ ሊመጣ ይችላል። ሰውነት በተለያዩ በሽታዎች የሚያዝ ከሆነ ለምሳሌ፡በልብ በሽታ፣ በደም ማነስ፣ በኤች.አይ.ቪና ሌሎች በሽታዎች ሲጠቃ፣ ሰዎች ከሥነ ልቦና ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ሲገቡ፣ የተለያዩ ሻምፖዎችና ኮንዲሽነሮች መጠቀም እንዲሁም የቀለሞች መጠንና ዓይነት ባለማወቅ ፀጉር ይነቃቀላል።

ሌላው ደግሞ ለፀጉር እድገት የሚያገለግሉት የእንቅርት (የታይሮይድሆሮሞኖች መብዛት ወይም ማነስም የፀጉር መነቃቀልን ሊያስከትል ይችላል። በእራስ ቅል ወይም በማንኛውም ፀጉር በሚበቅልበት ቦታ ላይ ያሉ ቆዳዎች ችግር ካለባቸው፣ ከውስጥ ሕመምጋር፣ ከቫይታሚን መብዛትና ማነስ ጋር እንዲሁም በኢንፌክሽንና ፈንገስ ምክንያት የሚመጡ በሽታዎችም ቢሆኑ ለፀጉር መነቃቀር መንስኤ ናቸው።

አዲስ ዘመን፡ለፀጉር የሚደረጉ ቅባቶችና መዋቢያዎች ያላቸው ጎንዮሽ ጉዳት ምንድንነውለምሳሌ ጄል፣ቀለም ወዘተ?

ዶክተር ፋይሰል:- የፀጉርን ጤንነት ለመጠበቅ ተብሎ የሚወሰዱ የተለያዩ የፀጉር ሕክምና (መንከባከቢያ ፣ማሳመሪያነገሮችን መጠቀም እንደ ጥቅሙ ሁሉ ጉዳትም አለው። ከጉዳቶቹም ውስጥ የፀጉር ቀለም መቀባትን ማንሳት ይቻላል። ቀለም መቀባት የፀጉሩን ወደ ተለየ ወይም ከበፊቱ የተሻለ ቀለም ያለው በማስመሰል የሥነ ልቦና ጥቅም እንዲኖረው ያደርጋል። ሆኖም ግን የተቀቡት ቀለም የቆዳ አለርጂና መሰል ጉዳቶችን ሊያስከትልበት ይችላል። ስለዚህም ይህ ጉዳት ከመፈጠሩ በፈት በቅድሚያ የቀለሙን ትክክለኛነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል። ለምሳሌ ቀለሙ አለርጂ የሚፈጥር እንደሆነ ለማወቅ በመጀመሪያ ቀለሙን ከጆሮው በስተጀርባ ይቀባና ከሁለት እስከ ሦስት ቀናት ይጠብቅ። ከዚያም በጆሮው አካባቢ የአለጂ ምልክቶች ይታያሉ። ማለትም እንደ ቆዳ ማሳከክ፣ ማበጥ፣ መቅላት እንዲሁም ማቃጠል የመሳሰሉት ስሜቶች ይሰማሉ። በዚህ ጊዜም ያ ሰው በምንም ምክንያት ቀለሙን መጠቀም እንደሌለበት እንዲገነዘብ ያደርገዋል።

ሌላው ደግሞ የፀጉር ቀለምን ለመጠቀም መጀመሪያ የፀጉሩ ቀለም መልቀቅ ይኖርበታል። ምክንያቱም ሕይወት ያለውን የፀጉር ክፍል ማለትም ሥሩን ወይም እንደ ፀጉር ፋብሪካ የሚያገለግለውን ክፍል ቀለሙን በምንቀባው ጊዜ ይነካዋል። በዚህ ጊዜ ቆዳው እንዲቆጣ ወይም እንዲቆስል ያደርግዋል። ይህ ደግሞ በቆዳው ላይ የተለያዩ በሽታዎች እንዲከሰቱና ጸጉር እንዲነቃቀል ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። በሌላ በኩል ደግሞ በፀጉር ሥር ውስጥ ያሉት ሴሎች በብዛት እንዳይራቡና ፀጉር እንዳይፈጠርም ሊያደርግ ይችላል። የፀጉር ቀለም በአብዛኛው የሚወሰነው «ሜላኒን» በተባለው ጥቁር ቡናማ ቀለም ባለው ሥርጭትና መጠን ነው።

ሜላኒን በፀጉር፣ በቆዳና በዐይን ውስጥ የሚገኝ የተፈጥሮ ቀለም ነው። የቀለሙ መጠን በጨመረ መጠን ፀጉርም ጠቆር እያለ ይሄዳል። የሜላኒን መጠን እያነሰ ሲሄድ ደግሞ የፀጉር ቀለም ከጥቁር ወደ ቡናማነት ወይም ወደ ቢጫነት ያደላ ይሆናል። ፀጉሩ ምንም ሜላኒን ከሌለው ግን ሙሉ በሙሉ ነጭ ይሆናል። በዚህ ጊዜ ለፀጉራችን የሚሰማማና ጉዳት የማያመጣ ቀለም መቀባት ይቻላል። በቀለም ሴሎች የሚሠሩትን ሜላኒን መሥራት እንዲያቆሙና ፀጉር ቀለሙን እንዲቀይርም ያደርገዋል። በተለይ የፀጉር ቀለምን ለረጅም ጊዜ የሚጠቀሙ ሰዎች ፀጉራቸው እንዲሳሳ፣ ቆዳቸው እንዲጎዳና ለካንሰር በሽታ ተጋለጭ እንዲሆኑም ያደርጋል።

ቀለሙን ተቀብቶ ቆዳው ላይ ማቆየት አይገባም። ይልቁንም በውሃ በማራስ ፀጉር እንዲለሰልስ ማድረግ ተገቢ ነው። ይህ ካልሆነ ግን የቆዳን ቀዳዳዎች በመድፈን ፀጉር ኦክስጂን እንዳያገኝ በማድረግ የፀጉር ሴሎችን በመግደል ፀጉር እንዳያድግና እንዲነቃቀልም ያደርጋሉ።

አዲስ ዘመን፡አመጋገብ ለፀጉር መነቃቀል መንስኤ የሚሆን ከሆነ ምን ዓይነት ምግቦችን መመገብ አለብን?

ዶክተር ፋይሰል፡-ፀጉር እንደማንኛውም የሰውነት ክፍል የተመጣጠነ ምግብ ያስፈልገዋል። በቂ ውሃም ማግኘት አለበት። ይህ ከሆነ ደግሞ ፀጉር እድገቱ፣ ጥንካሬውና ዕድሜው በአስተማማኝ ደረጃ ላይ እንዲሆን ያደርገዋል። ካርቦ ሃይድሬት፣ ፕሮቲንና ማዕድናት እንዲሁም ቫይታሚኖችን በተለይ «ኤ፣ሲ እና ኢ» የመሳሰሉትን መመገብ ለፀጉር ህልውና ወሳኝ ናቸው። ፀጉር የተመጣጠነ ንጥረ ነገሮችን ሳያገኝ ከቀረ ግን ከመነቃቀሉ ባለፈ ሌሎች ተመሳሳይ ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል።

ፀጉር የተመጣጠነ ምግብ ማግኘት አለበት ሲባል ደግሞ በሁለት መልኩ ከፍሎ ማየት ይቻላል። የመጀመሪያው በምግብነት የምንጠቀመው ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ በእራስ ቅል ላይ በቅባት መልክ የምንቀባው ነው። በእራስ ላይ ከምንቀባው ይልቅ በምግብነት የሚወሰደው የተሻለ ጠቀሜታ አለው። ምክንያቱም አንድ የሰውነት ክፍል ከታመመ ለሁሉም የሰውነት ክፍሎች በሽታው እንደሚዳረስ ሁሉ በምግብነት የምንጠቀማቸው ንጥረ ነገሮችም ለሁሉም የሰውነት ክፍሎች በመዳረስ ማንኛውንም በሽታ የመከላከል አቅም እንዲኖራቸው ያግዛሉ።

አዲስ ዘመን፡ለፀጉር ተብለው የሚዘጋጁ ቅባቶች በራስ ቅል ቆዳ ላይ የሚያስከትሉት ጉዳት ይኖረው ይሆን?

ዶክተር ፋይሰል፡እንደ ቅባቶች ዓይነት ጉዳቱም ይለያያል። ለምሳሌ ለፀጉር የምንጠቀመው ቅባት ፓራፊን፣ ኦሊቫኦይልና የመሳሰሉት ነገሮች ለጤናማ ፀጉር ምቹ ሲሆኑ ለታመመ የራስ ቅል ቆዳ ምቹ ላይሆኑ ይችላሉ። ይልቁንም ችግሩ እንዲባባስ የሚያደርጉበት ሁኔታ ይኖራል። ኢንፌክሽን ያለበት ሰው የጭቃ ቅባት ቢጠቀም ጭቃነቱ እዚያ አካባቢ ለሚኖሩት ባክቴሪያዎች ምቹ መራቢያ ስለሚሆን ፀጉርን እንዲበጣጠስ ያደርገዋል። ስለዚህ ቅባቶችን ለፀጉሩ በሚመች መልኩ መርጦ መጠቀም ይገባል።

አዲስ ዘመን፡ፎረፎር ለፀጉር መነቃቀል ይዳርጋል ይባላል ትክክል ከሆነ ምክንያቱ ምን ይሆንበሕክምናስ መፍትሔ ይኖረው ይሆን?

ዶክተር ፋይሰል፡ፎረፎር «ማላሼዢያ ፎረፎር» በሚባል ፈንገስ የሚመጣ ሲሆን፤ በሁሉም ሰው ላይ የሚታይ ነው። በተለያዩ ውስጣዊና ውጫዊ ምክንያቶችም ሊመጣ ይችላል። በተለይም በፀጉር ቆዳችን ላይ የሚገኙ ነጭ የደም ህዋሳቶች ሲሞቱ ነው ፎረፎር የሚከሰተው። ፎረፎር ፀጉር እንዲያልቅና እንዲበጣጠስ ከማድረጉም በላይ የፀጉር ውበትንና ቆዳን ይጎዳል። በተለይ ቅባት በሚበዛባቸው ቦታዎች እንደ ጭንቅላት፣ ፊት፣ ግንባር ፣ የላይኛው የጀርባ ክፍልና ደረት አካባቢ ጎልተው ይታያሉ።

ፎረፎርን ሙሉ ለሙሉ ማጥፋት አይቻልም። ምክንያቱም በማንኛውም ጤነኛ ሰው ላይ የሚታይ ፈንገስ ነውና። ብዙን ጊዜ በማበጠሪያ፣ በልብስና በመሳሰሉት ነገሮች ተጋባብኝ ወይም ፎረፎር ያዘኝ ሲባል ይሰማል። ፎረፎር ግን ተላላፊ በሽታ አይደለም። ምክንያቱም በተፈጥሮ አንድ ሰው የሚፈጠርበት ክስተት እንጂ። ስለዚህ ፎረፎር እንዳይፈጠር ማድረግ በምንም መልኩ አይቻልም። ሆኖም ግን ፎረፎርን መቀነስና ከፎረፎር ጋር ተያይዘው የሚመጡ በሽታዎችን መከላከል ይቻላል። ይኸውም ህክምናው በሦስት ዓይነት መልኩ ሊሰጥ ይችላል።

የመጀመሪያው ህክምና የፈንገስ መጠኑን ሊቀንሱ የሚችሉ ጸረ ፈንገስ ሻምፖዎች፣ ክሬሞችና ቅባቶችን በመጠቀም የሚሰጥ ህክምና ነው። ሁለተኛው ደግሞ ቆዳ በተለያዩ ምክንያቶች ሲቆጣ ቁጣውን ለመቀነስ የሚያስችሉ ቅባቶችን በመጠቀም የሚሰጠው ሲሆን፤ ሦስተኛውና የመጨረሻው ሕክምና ደግሞ የፎረፎር ምልክቶችን ተከትለው የሚመጡ ህመሞች የሚታከሙበት ነው። ለምሳሌ፡የቆዳ መቅላት፣ ነጭ መሆን፣ ማበጥ፣ መቁሰልና መግል መያዝን ለማከም የተለያዩ መድኃኒቶችን በመጠቀም የሚሰጠው ህክምና ነው።

በእርግጥ መቁሰል ማበጥና መግል መያዝ የሚመጣው ፈንገሶቹ ከመጨመራቸው አንጻር ቢሆንም ብዙ ጊዜ ግን በኢንፌክሽን ምክንያት ቆዳ እየሳሳና በሽታን የመቋቋም ኃይሉ እየተዳከመ በመምጣቱ ሊከሰት ይችላል። ፎረፎር ብዙን ጊዜ የሚታየው ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በላይ ባሉ ሰዎች ላይ ሲሆን ከዘህ በታች ባሉት ላይ አይታይም። በእነርሱ ላይ የሚከሰተው ቆረቆር በመባል የሚጠራው ነው። ይሁን እንጂ ሁለቱም ቢሆኑ ለፀጉር መነቃቀል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። ስለዚህም ተገቢውን ህክምና በማድረግ ፀጉር እንዳይነቃቀል ማድረግ ይገባል።

አዲስ ዘመን፡በዘልማድ ላሽ እየተባለ የሚጠራው ድንገተኛ የፀጉር መነቀል እንዴት ይመጣልህክምናውስ ምን ይመስላል?

ዶክተር ፋይሰል፡የተወሰነ ቦታ የሚከሰት የፀጉር መመለጥ «አሎፔሺያ አሬታ» የሚባለው ሲሆን ጠባሳ በማይፈጥር መልኩ የሚከሰት ነው። በተለያየ የሰውነት ክፍሎች ላይም ሊታይ ይችላል። ላሽ የሚመጣው በሰውነት የበሽታ ተከላካይ ሕዋሳት ላይ በሚደርስ ቀውስ ምክንያት የራሳችን የበሽታ መከላከያ ዘዴዎች የፀጉር ስሮች በሚያጠቁበት ወቅት ነው። ላሽን በሦስት መልኩ ከፍሎ ማየት የሚቻል ሲሆን እነሱም፡ፀጉር አንድ ቦታ ላይ ብቻ ክብ ሆኖ ሲነሳ፣ እንዳለ የፀጉር ክፍል ሲነሳና ሰውነት ላይ ያለው ፀጉር በሙሉ ሲነሳ ናቸው። ይህንን ከፋፍሎ ማየቱ ያስፈለገበት ምክንያት ደግሞ በሽታውን ለይቶ በማውጣት ህክምና ለመስጠት እንዲቻል ነው። ይኸውም በአጭር ጊዜ የሚድነውንና ረጅም ጊዜ የሚወስደውን እንዲሁም ተያያዥ ችግሮች ያሉበትን የላሽ ዓይነት ለመለየት ያስችላልም። የላሽ ህክምና በመርፌ ብቻ፣ በመርፌና መድኃኒት፣ በመርፌ፣ በመድኃኒትና በቅባት መልኩ ሊሰጥ ይችላል።

አዲስ ዘመን፡በአጠቃላይ የፀጉር መነቃቀል እንዳይከሰት ምን ዓይነት ጥንቃቄ እንዲደርጉ ይመክራሉ?

ዶክተር ፋይሰል፡ፀጉር ፈጣን እድገት ካላቸው የሰውነት ክፍሎች አንዱ ነው። ሆኖም ግን በተለያዩ ምክንያቶች ሊነቃቀል ይችላል። ስለዚህ የፀጉር መነቃቀልን ለመከላከል የተለያዩ ነገሮችን ማድረግ ይቻላል። ከእነዚህም ውስጥ በቂና የተመጣጠነ ምግብ መመገብ፣ ፀጉር በቂ ውሃ እንዲያገኝ ማድረግ፣ አዘውትረን ፀጉራችንን አለመታጠብ ምክንያቱም የራስቅል ቆዳ የሚያመርተውን የቅባት መጠን ስለሚቀንስ የምንታጠብበትን ጊዜ መወሰን ይገባል። በሳሙና፣ ሻምፖና ኮንዲሽነር ስንጠቀም ደግሞ የተመረጡና ለፀጉሩ የሚስማሙ መሆን ይኖርባቸዋል። በተለይ በልብስ ሳሙና ፀጉርን መታጠብ ለፀጉር መነቃቀል ያጋልጣል። ስለዚህ የፀጉር መነቃቀልን ለመከላከል ከላይ የተጠቀሱትንና መሰል ተግባራት ማከናወን ተገቢ ነው። በተጨማሪም ወደ ህክምና ተቋም በመሄድ የህክምና ባለሙያዎችን በማማከርም መፍትሔ መሻት ያስፈልጋል።

ጸሐፊ ጽጌረዳ ጫንያለው 

Related Articles

Post your comment