PLANET ETHIOPIA
Advertisment

News


 • NEWS: በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆኑና ለልማት የሚነሱ ኤርትራውያን እንዴት ምትክ ቦታና ካሣ ይሰጣቸው የሚለው እስካሁን ውሣኔ አላገኘም ተባለ፡፡

                                           

  (ትዕግስት ዘሪሁን)

  ስለ ጉዳዩ ጥናት ተደርጎ ለመሬት ማኔጅመንት መቅረቡንም የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ኤጀንሲ ለሸገር ተናግሯል፡፡

  ለሀገር ደህንነት ሥጋት አይደሉም የተባሉና ከኢትዮ-ኤርትራ ግጭት በፊት ሀብት ንብረት አፍርተው በአዲስ አበባ ይኖሩ የነበሩ ኤርትራውያን በከተማዋ ይኖራሉ፡፡

  በመልሶ ማልማት ክልል ውስጥ ቤት ያላቸው ኤርትራውያን እንዴት ካሣና ምትክ ቦታ ማግኘት እንዳለባቸው ራሱን የቻለ ሕግ ስለሌለ የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ኤጀንሲ ሲቸገር መቆየቱን ሰምተናል፡፡

  ለጉዳዩ እልባት ለመስጠትም ከፍትህ ቢሮ ጋር ጥናት አካሂዶ ለመሬት ማኔጅመንት ማቅረቡን የኤጀንሲው ምክትል ኃላፊ የሆኑት አቶ ግርማ ብርሃኑ ለሸገር ተናግረዋል፡፡

  እስካሁን ግን ውሣኔ ያላገኘ ጉዳይ እንደሆነም ነግረውናል፡፡

  ለመልሶ ማልማት ቤቶች ሲፈርሱ በየክፍለ ከተማው አንድም፣ ሁለትም የኤርትራውያን ጉዳይ ያጋጥመናል ያሉት አቶ ግርማ ከዚህ ቀደም ቤታቸው የፈረሰባቸው ምትክ ቦታና ካሣ አልተሰጣቸውም ብለዋል፡፡

  ይሁንና የቤታቸውን ሁኔታና የቦታ ልኬታቸውን ሙሉ መረጃ ይዘናል በጥናቱ መሠረትም የከተማዋ ካቢኔ በሚያሣልፈው የውሣኔ ኃሣብ መሠረት ይስተናገዳሉ ብለዋል፡፡

  አሁን ግን ለጊዜው ቤታቸው ያልፈረሰባቸው ኤርትራውያን አካባቢው ለመልሶ ማልማት ቢፈለግም ጉዳዩ ውሣኔ እስኪያገኝ ድረስ እንዳይፈርስባቸው ስምምነት ላይ ተደርሷል ብለዋል፡፡

  ምንጭ:- የሸገር FM 102.1 ሬዲዮ

   

  Read more »

 • NEWS: ኢስት አፍሪካን ቦትሊንግ አክሲዮን ማህበርና አንቦ ማዕድን ውሃ አክሲዮን ማህበር ህገ-ወጥ የውህደት ድርጊትና የውህደት ቅንብር ፈፅመዋል በሚል ለቀረበባቸው ክስ ዛሬ መልስ ሰተዋል፡፡

                                                                                        

  (ንጋቱ ረጋሳ)

  ኢስት አፍሪካን ቦትሊንግ አክሲዮን ማህበርና አንቦ ማዕድን ውሃ አክሲዮን ማህበር ህገ-ወጥ የውህደት ድርጊትና የውህደት ቅንብር ፈፅመዋል በሚል ለቀረበባቸው ክስ ዛሬ መልስ ሰተዋል፡፡

  ሁለቱ አክሲዮን ማህበራት ህገ-ወጥ ውህደት በመፈፀም ተገቢ ያልሆነ ውድድር ፈጥረዋል በማለት የከሰሳቸው የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን ነው፡፡

  ባለሥልጣኑ እንዳለው የአክሲዮን ማህበራቱ ኃላፊዎች ካለፈው ጥር ወር አንስቶ ውህደት መፈፀማቸውን በቃል ተናግረዋል፡፡

  በአከፋፋዮች ላይም የሁለታችንንም ምርቶች ነው መያዝ ያለባችሁ የሚል ግዴታ አስቀምጠዋል፡፡

  አንዱ የሌላውን አርማና የንግድ ምልክት መጠቀሙንም ባለሥልጣኑ በክሱ ላይ አስፍሯል፡፡
  ሁለቱ አክሲዮን ማህበራት በጋራ የሥራ አመራር አቅጣጫ ነድፈዋልም ብሏል፡፡

  የአንዱን አክሲዮን ማህበር ሠራተኛ ወደ ሌላው የማዘዋወር ተግባር ፈፅመዋል ሲልም ባለሥልጣኑ በክሱ ላይ አስፍሯል፡፡

  እነዚህ ተግባሮች በሁለቱ አክሲዮን ማህበራት መካከል ውህደት ወይም መቀላቀል መፈጠሩን የሚያረጋግጡ ናቸው ብሏል፡፡

  ኢስት አፍሪካን ቦትሊንግና አንቦ ማዕድን ውሃ አክሲዮን ማህበራት በቃል ተዋህደናል ብላችኋል ተብሎ የተነገረው ስህተት ነው፣ ብንል እንኳ ውህደት የሚፈፀመው ብዙ ሂደት አልፎ በሰነድ ነው እንጂ በቃል አይደለም ሲሉ ተከራክረዋል፡፡

  አከፋፋዮች የሁለታችንንም ምርቶች እንዲይዙ ግዴታ አስቀምጣችኋል መባላችንም ስህተት ነው ሲሉም መልሰዋል፡፡

  አንዱ የሌላውን አርማ ተጠቅሟል በሚል የቀረበው ክስም ትክክል እንዳልሆነ በመቃወሚያቸው ላይ አስፍረዋል፡፡

  በድርጅቶች መካከል ሰራተኛ መዋዋስ በኢትዮጵያ የተለመደ አሰራር መሆኑን በመጥቀስ ይህንን የሚከለክል ህግ የለም ሲሉም ተከራክረዋል፡፡

  በአጠቃላይ በሁለቱ አክሲዮን ማህበራት መካከል የተፈጠረ ውህደት የለም፤ ይህንን የሚያሣይ ማስረጃም በከሣሾቹ በኩል አልቀረበም ብለዋል፡፡

  ጉዳዩን እያየ ያለው የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን የዳኝነት ችሎትን ብይን ለመስጠት ለነሐሴ 17 2009 ዓ.ም ቀጠሮ ይዟል፡፡

   

  Read more »

 • NEWS: የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በግንባታ ላይ ያሉ የ40/60 ቤቶች በ18 ወራት ተጠናቀው ለቆጣቢዎች ይሰጣሉ መባሉ በስህተት የተናገርነው ነው አለ፡፡

                                                       

  (ዮሐንስ የኋላወርቅ)

  “በግንባታ ላይ ያሉት ቤቶች በሙሉ በ18 ወራት ተጠናቀው ለቆጠባችሁት እንሰጣችኋለን ያልናችሁ በስህተት ነው ፤ በዚህ ፍጥነት በኢትዮጵያ ውስጥ አንድን ህንፃ ገንብቶ ሲጠናቀቅ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም ፤ እኛም ተሳስተን ግን እንጨርሳለን ብለናችሁ ነበር…”

  የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባግንባታ ላይ ያሉ የ40/60 ቤቶች በ18 ወራት ተጠናቀው ለቆጣቢዎች ይሰጣሉ መባሉ በስህተት የተናገርነው ነው አለ…

  እየተገነቡ ነው የተባሉት ከ38 ሺ በላይ የ40/60 ቤቶች መቼ እንደሚጠናቀቁ አይታወቅም፡፡

  መስተዳደሩ ይህን ያለው ዛሬ በ40/60 ቤቶች የ2009 ዓ.ም አፈፃፀምና የ2010 ዓ.ም የሥራ ዕድቅ ላይ ከኮንትራክተሮች፣ ከአማካሪዎችና ከሚመለከታቸው ጋር ውይይት ባደረገ ጊዜ ነው፡፡

  የአዲስ አበባ ቁጠባ ቤቶች ኢንተርፕራይዝ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሣቢና የከተማዋ ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው ከጋዜጠኞች ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ሲመልሱ በቅርቡ እጣ የወጣባቸው የ40/60 መኖሪያ ቤቶች ከውል ውጭ ሰፋፊ ሆነው በስህተት ተሰርተዋል ብለዋል፡፡

  በዚህም ሳቢያ ባለ1 መኝታ ቤት የሚባለው ቀርቶ ያልታሰበው ባለ 4 መኝታ ቤት ተገንብቶ እጣ ወጥቶበታል ነው ያሉት፡፡

  ይሁን እንጂ ቤቶቹ አንዳንድ ክፍል የተጨመረባቸው ለሠራተኛ ተብሎ የተገነቡት ክፍሎች ተጨምረው ነውና ይህ አግባብ ነው ወይ ? ተብለው የተጠየቁት ምክትል ከንቲባው የቤቶቹ ስፋት ጋር አያይዘው ብቻ መልስ ሰጥተዋል፡፡

  ይህ በአሰራር ሂደት የሚያጋጥምና ወደፊትም በዲዛይን ለውጥ ሳቢያ ሊያጋጥም የሚችል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

  ምንም እንኳ ቤቶቹ በህዝብ ገንዘብ ጭምር ቢገነቡም ለተፈጠረው ስህተት ህዝቡን ይቅርታ አንጠይቅም ብለዋል፡፡

  ከውል ውጭ ባለ 4 መኝታ ቤት እጣ የወጣላቸው ሰዎች አንወስድም ቤቱን ካሉ መስተዳድሩ መልሶ ይረከባቸዋል ያሉ ሲሆን ባለ 1 መኝታ ቤት ፈላጊዎች ሆነው የተዘለሉት በቀጣዩ አመት በስፋት ተገንብቶላቸው ቤታቸውን ይወስዳሉ ብለዋል፡፡

  በሌላም በኩል በግንባታ ላይ ያሉት ቤቶች በሙሉ በ18 ወራት ተጠናቀው ለቆጠባችሁት እንሰጣችኋለን ያልናችሁ በስህተት ነው ፤ በዚህ ፍጥነት በኢትዮጵያ ውስጥ አንድን ህንፃ ገንብቶ ሲጠናቀቅ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም ፤ እኛም ተሳስተን ግን እንጨርሳለን ብለናችሁ ነበር ብለዋል፡፡

  ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ከ39 ሺ በላይ የ40/60 ቤት ፈላጊዎች ተመዝግበው ቤት እየጠበቁ ቢሆንም እስካሁን እጣ የወጣላቸው 972 መኖሪያ ቤቶች ብቻ መሆኑ ይታወቃል፡፡

  ቀሪዎቹስ ከ38 ሺ በላይ የሚሆኑት የ40/60 ቤቶች ተጠናቀው ቤቶቹን ለሚናፍቁና ጥሪታቸውን እየቆጠቡ የሚጠብቁ ሰዎች መቼ ተጠናቀው መቼ ይሰጣቸው ይሆን? ተብለው የተጠየቁት ምክትል ከንቲባው ቤቶቹ ሲጠናቀቁ ይተላለፋሉ ብለዋል፡፡ መቼ እንደሚጠናቀቁ ግን ሊነግሩን ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡

  ምንጭ:- የሸገር FM 102.1 ሬዲዮ

  Read more »

 • የዛሬ የዕለተ ማክሰኞ ሐምሌ 18 ቀን 2009 ዓ.ም የሸገር ወሬዎች::

                                         

  የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በግንባታ ላይ ያሉ የ40/60 ቤቶች በ18 ወራት ተጠናቀው ለቆጣቢዎች ይሰጣሉ መባሉ በስህተት የተናገርነው ነው አለ፡፡ ከውል ውጭ ባለ አራት መኝታ ቤት የደረሳቸውም ካልፈለጉ አስተዳደሩ ቤቱን ይረከባቸዋል ተብሏል፡፡ (ዮሐንስ የኋላወርቅ)

  ኢትዮጵያ በዚህ ክረምት 3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ተዘጋጅታለች ተባለ፡፡ (ንጋቱ ሙሉ)

  የሳውዲ አረቢያ መንግሥት የይውጡልኝ ተጨማሪ እፎይታ ጊዜ አብቅቷል፡፡ አሁንም ግን የሚጠበቀውን ያህል ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው አልተመለሱም፡፡ (የኔነህ ሲሣይ)

  ኢትዮጵያና ቼክ ሪፐብሊክ ባለፉት 5 አመታት ያካሄዱት የንግድ ልውውጥ 150 ሚሊዮን ዶላር እንኳ መድረስ አልቻለም ተባለ፡፡ (ንጋቱ ሙሉ)

  ፍትሃዊ የንግድ ውድድርን የሚጐዳ ውህደትና ቅንብር ፈፅመዋል በሚል ክስ የተመሠረተባቸው ሁለት ኩባንያዎች ዛሬ ለፍርድ ቤት መልስ ሰጥተዋል፡፡ (ንጋቱ ረጋሣ)

  በአዲስ አበባ ለልማት የሚነሱ ኤርትራውያን ባለ ይዞታዎች ምትክ ቦታና ካሣ የሚያገኙበት ጥናት ለመሬት ማኔጅመንት መቅረቡ ተሠማ፡፡ (ትዕግሥት ዘሪሁን)

  በአዲስ አበባ በክርክር ላይ ያሉ ይዞታዎችን ጉዳይ ዳር ለማድረስ በቅደም ተከተል በዝርዝር ሊታይ ነው፡፡ (ምህረት ስዩም)

  ምንጭ:- የሸገር FM 102.1 ሬዲዮ

  Read more »

 • NEWS: የአካባቢ ብክለትን ለማሳየት ከተጣሉ የፕላስቲክ ጠርሙሶች የተሰራው ጀልባ

                                               

  በእንግሊዝ በአካባቢ ጉዳዮች ላይ የሚሰራው የበጎ አድራጎት ቡድን በየቦታው የሚጣሉ የፕላስቲክ ጠርሙሶች በአካባቢ ላይ የሚያመጡት ጉዳት ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር አዲስ ነገር ይዘዋል።

  የበጎ አድራጎት ቡድኑ ግንዛቤውን ለመፍጠርም በእንግሊዝ ውስጥ ከሚገኙ የባህር ዳርቻዎች በተሰበሰቡ የፕላስቲክ ጠርሙሶች ጀልባ ሰርተዋል።

  እንደ ቡድኑ ገለጻ፥ ጀልባው የተሰራው ሙሉ በሙሉ ውቅያኖስ ላይ ከተጣለ ፕላስቲክ ነው የሰሩት።

  ይህ ደግሞ የፕላስቲክ ጠርሙሶች በአካባቢ ላይ ምን ያክል ብክለት እያመጣ እንደሆነ ያሳያል ሲሉም ያብራራሉ። 

  ይህን ጀልባ ለመስራት ያነሳሳቸውም የፕላስቲክ ጠርሙሶች በውቅያኖሶች ላይ ምን ያልክ ጉዳት እያደረሱ እንደሆነ ግንዛቤ ለመፍጠር ነው ብለዋል።

  የበጎ አድራጎት ቡድኑ በቀጣይም ውቅያኖሶች እና የሰዎች የመኖሪያ አካባቢ ከፕላስቲክ ነፃ እንዲሆን የሚረዱ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ፈጠራዎቸን እንደሚሰራ አስታውቋል።

  ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

   

  Read more »

 • NEWS: የተምች ወረርሽኙ በዚሁ ከቀጠለ በምስራቅ አፍሪካ የምግብ እጥረት ሊፈጠር እንደሚችል ፋኦ ገለፀ

                                                

  የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት በአሜሪካ መጤ ተምች ላይ የተቀናጀ የተባይ ስራ አመራር እርምጃ ካልወሰዱ በቀጠናው የምግብ እጥረት ሊፈጠር እንደሚችል የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ)ገለጸ።

  በድርጅቱ የምስራቅ አፍሪካ ንዑስ ቀጠና ዳይሬክተር ዶክተር ፓትሪክ ኮርማዋ በያዝነው የፈረንጆች 2017 ዓመት መጀመሪያ ላይ፥ በቀጠናው የተከሰተው ሰብል አውዳሚ መጤ ተምች በሁሉም የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት መዛመቱን ገልጸዋል።

  ከ80 በላይ ሰብሎችን የሚያጠቃው ይህ ተምች በተለይ በቀጠናው ሀገራት ዋነኛ ምግብ የሆነው የበቆሎ ሰብልን በስፋት የሚያጠቃ በመሆኑ ጉዳቱ ዘርፈ ብዙ ሊሆን እንደሚችልም ጠቁመዋል።

  በተለይም ከኤል ኒኖ ድርቅ እያገገሙ ያሉ ሀገራት ለችግሩ ይበልጥ ተጋላጭ እንደሚሆኑ አንስተዋል።

  አፋጣኝና የተቀናጀ የተባይ ስራ አመራር እርምጃዎች ካልተወሰዱ በምግብ ሰብል ላይ የምርት መቀነስና የዋጋ ንረት ሊከሰት ስለሚችል የቀጠናው ዜጎች ለምግብ ዋስትና እጦት ችግሮች ሊዳረጉ እንደሚችሉም ጠቅሰዋል፡፡

  የሚያስከትለውን የምርት ጉዳት ለመቀነስና የዜጎች የምግብ ዋስትና እጦት እንዳይከሰት የቀጠናው ሀገራት የተቀናጀ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።

  አሁን ላይም ድርጅታቸው በቅድመ ተባይ መከላከል፣ በቁጥጥር ውጤት ግምገማ፣ በዘላቂ የተምች ስራ አመራርና በትብብር አራት ቁልፍ መንገዶች የተምች መከላከል ማዕቀፍ ቀርጾ ከየሀገራቱ ተጠሪ ተቋማት ጋር በመተባበር እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

  ተምቹን ለመከላከልም የተቀናጀ የመረጃ ልውውጥ ስርዓት ካልተዘረጋና ሃገር አቀፍ፣ ክፍለ አህጉርና አህጉር አቀፍ በሆነ መልኩ በቅንጅት ሊሰራ ይገባል ነው ያሉት፡፡

  በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) የምግብ ዋስትና ስነ ምግብ ባለሙያ አብዱል ሱልማን ኢልሆዎርልስ በበኩላቸው፥ ቀጠናው የምግብ ዋስትና ችግር እንዳለበት ገልጸዋል።

  በቀጠናው ለተጀመሩ የተምች መከላከልና መቆጣጠር ፕሮጀክቶች ተፈጻሚነትም ኢጋድ ድጋፍ እንደሚያደርግ አብራርተዋል።

  በኬንያ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት /ዩ ኤስ አይ ዲ/ ተወካይ ዶክተር ትሬሲ መክረኬን ድርጅቱ መጤ ተምቹን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የአዋጭ ቴክኖሎጂና የአቅም ግንባታ ድጋፉን ያደርጋል ብለዋል፡፡

  ተምቹ በኢትዮጵያ ከ500 ሺህ ሄክታር በላይ የበቆሎ ማሳ ላይ የተዛመተ ሲሆን ሩዋንዳና ኬንያ በስፋት ተምች የተስፋፋባቸው ሀገራት ናቸው።

  ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ ዓመት መባቻ በምዕራብ አፍሪካ የተከሰተው የአሜሪካ መጤ ተምች በ25 የአፍሪካ ሃገራት ሲዛመት ናይጀሪያ 700 ሺህ ሄክታር የበቆሎ ማሳ በተምች ወረርሽኙ የተጠቃች ቀዳሚዋ ሀገር ናት።

  ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

   

   

  Read more »

 • NEWS: ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ግብር ከፋዮች ያመኑበትን ይከፍላሉ በሚል የተናፈሰው መረጃ ሀሰት ነው - አቶ ከበደ ጫኔ

                                                     

  በበላይ ተስፋዬ

  በቀን ገቢ ግምቱ ላይ ቅሬታ ያለው ማንኛውም የደረጃ ሐ ግብር ከፋይ አሳማኝ መረጃ ይዞ እስከመጣ ድረስ ተገቢ ምላሽ ይሰጠዋል አለ የኢትዮጵያ ገቢዎች እና ጉምሩክ ባለስልጣን።

  የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ከበደ ጫኔ ማምሻውን በሰጡት መግለጫ፥ በህጋዊ መንገድ ቅሬታን ማቅረብ እየተቻለ ሌላ ህገወጥ ድርጊት መፈፀም በህግ ያስጠይቃል ብለዋል።

  በአዲስ አበባ 148 ሺህ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች የቀን ገቢ ግምት ተከናውኖላቸዋል።

  በእለት ገቢ ግምቱ በገማቾች እና ነጋዴዎች መካከል የመረጃ ልውውጥ ችግር ነበር ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፥ በአብዛኛው የቀን ገቢ ግመታው ትክክል መሆኑን ገልፀዋል።

  68 በመቶ የሚሆኑ የእለት ገቢያቸው የተገመተላቸው ሰዎች ትክክል መሆኑን አምነውበት ግብራቸውን መክፈል ጀምረዋል፤ 32 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ቅሬታ አቅርበዋል ብለዋል።

  በአጠቃላይ 23 ሺህ ቅሬታዎች ቀርበው የ20ሺዎቹ የመጀመሪያው ግምት ፀድቆ መክፈል እንዳለባቸው ተወስኗል ነው ያሉት አቶ ከበደ።

  በአጠቃላይ ከደረጃ “ሐ” የቀን ገቢ ግመታ ጋር ተያይዞ አሁንም የሚቀርቡ ቅሬታዎች ካሉ ባለስልጣኑ ለመፍታት ዝግጁ መሆኑንም አንስተዋል። 

  የደረጃ “ሀ” እና “ለ” ግብር ከፋዮች ግን የሂሳብ መዝገብ እና ካሽ ሪጂስተር ስላላቸው የእለት ገቢ ግምቱ አይመለከታቸውም ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ።

  ዛሬ ማለዳ በአዲስ አበባ መርካቶ ነጋዴዎች ሱቆቻቸውን እንዳይከፍቱ ቅስቀሳ ሲደረግ እንደነበርና የተወሰኑ ሱቆች እስከ እኩለ ቀን ድረስ ተዘግተው መቆየታቸውን ነው ያነሱት አቶ ከበደ።

  ከአክሲዮን ማህበራት ጋር በተደረገ ውይይትም ነጋዴዎቹ በራሳቸው ተነሳሽነት ሳይሆን የቅስቀሳ ወረቀት እና የተለያዩ የስለት መሳሪያዎችን ይዘው የሚንቀሳቀሱ አካላት ዛቻ ምክንያት ሱቆቻቸውን ሊዘጉ መቻላቸውን አረጋግጠናል ብለዋል።

  ከነጋዴዎቹ ማህበራት ጋር ከተደረገው ውይይት በኋላ መርካቶ በእኩለ ቀን ወደ መደበኛ እንቅስቃሴዋ መመለሷንም አንስተዋል። 

  በስፍራው ነጋዴዎችን ሱቆቻቸውን እንዲዘጉ በሃይል ሲያስፈራሩ ከነበሩ ሶስት ግለሰቦች ውስጥም ሁለቱ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

  በሌላ በኩል በዝቅተኛ የስራ ንግድ ላይ ግብር ከፋዮች ያመኑበትን ይክፈሉ ተብሏል በሚል ሲናፈስ የነበረው መረጃም ፍፁም ከእውነት የራቀ መሆኑንም ነው አቶ ከበደ ያነሱት።

  ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

   

  Read more »

 • NEWS: ሞሮኮ በአፍሪካ ቀዳሚውን ሰማይ ጠቀስ ህንጻ ልትገነባ ነው::

                                                    

  ሞሮኮ በአፍሪካ ረጅሙን ሰማይ ጠቀስ ህንጻ ልታስገነባ ነው ተብሏል።

  ሰሜን አፍሪካዊቷ ሃገር ረጅሙን ሰማይ ጠቀስ ህንጻ ለማስገንባት ከቻይና ሬልዌይ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ጋር ስምምነት ፈጽማለች።

  በዋና ከተማዋ ራባት የሚገነባው ህንጻ ባለ 55 ወለል ሲሆን፥ 250 ሜትር ከፍታም አለው ነው የተባለው።

  ህንጻው ከአካባቢ ስነ ምህዳር ጋር እንዲስማማ ሆኖ እንደሚገነባም መረጃዎች ይጠቁማሉ።

  ህንጻው ሆቴሎች፣ ቢሮዎች እና ዘመናዊ መኖሪያዎችን ያካተተ እንደሚሆንም ተገልጿል።

  ሰማይ ጠቀሱ ህንጻ መዲናዋ በምትገነባው ዘመናዊ መንደር የሚያርፍም ይሆናል።

  ህንጻው የከተማዋን ባህላዊ ገጽታዎች በሚያስተዋውቅ መልኩ የሚገነባ ሲሆን፥ የራባት ቲያትር አዳራሽን ጨምሮ በርካታ ባህላዊ እሴቶችን ባስጠበቀ መልኩ ይከወናል።

  ከዚህ ባለፈም አጠቃላይ የሞሮኮን የቆዩና ጥንታዊ መገለጫዎችን በሚያሳይ መልኩ ይገነባልም ነው የተባለው።

  የህንጻው አጠቃላይ ወጪና ዝርዝር ጉዳዮችን የተመለከቱ መረጃዎች ግን እስካሁን አልወጡም።

   

  ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

   

   

   

  Read more »

 • NEWS: የአሜሪካ እና ብሪታንያ ኢኮኖሚያዊ እድገት በሚያዚያ ከተተነበየው በታች ይሆናል - አይ ኤም ኤፍ

                                                   

  በ2017 የአሜሪካ እና ብሪታንያ ኢኮኖሚያዊ እድገት ከዚህ ቀደም ከተገመተው በታች እንደሚሆን የአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) ትንበያ አመላከተ።

  በ2017 የመጀመሪያ ሶስት ወራት ብሪታንያ የ1 ነጥብ 7 በመቶ እድገት ያስመዘገበች ሲሆን፥ ይህም ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ0 ነጥብ 3 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል።

  ተቋሙ አሜሪካ በዚህ አመት የ2 ነጥብ 3 በመቶ እድገት ታስመዘግባለች የሚል ትንበያውንም ወደ 2 ነጥብ 1 በመቶ ዝቅ አድርጎታል።

  ይሁን እንጂ በሚያዚያ ወር ይፋ እንደሆነው ሁሉ አጠቃላይ አለም አቀፋዊ የኢኮኖሚ እድገቱ በ2017 የ3 ነጥብ 5 በመቶ፣ በ2018 ደግሞ የ3 ነጥብ 6 በመቶ እንደሚሆን ተንብዩዋል።

  አይ ኤም ኤፍ ቀደም ሲል እንደተነበየው ብሪታንያ በ2018 የ1 ነጥብ 5 በመቶ እድገት ታስመዘግባለች ተብሎ ይጠበቃል።

  የአሜሪካ ግን ተቋሙ ቀደም ሲል ካስቀመጠው የ2 ነጥብ 5 በመቶ እድገት ዝቅ ያለ የ2 ነጥብ 1 በመቶ እድገት እንደምታስመዘግብ ነው አይ ኤም ኤፍ ያስታወቀው።

  ብሪታንያ በ2018 የ1 ነጥብ 5 በመቶ እድገት እንደምታስመዘግብው የተተነበየው አሁንም ፀንቷል።

  ነገር ግን አሜሪካ በ2018 ታስመዘግባለች ተብሎ ቀደም ሲል በአይ ኤም ኤፍ ከተተነበየው የ2 ነጥብ 5 በመቶ እድገት ዝቅ ያለ የ2 ነጥብ 1 በመቶ እድገት ታስመዘግባለች ነው የተባለው።

  አዲሱ የአይ ኤም ኤፍ የኢኮኖሚ እድገት ትንበያ አለም አቀፍ እድገቱ በሚያዚያ ወር ይፋ በተደረገው ትንበያ መሰረት እንደሚቀጥል ጠቁሟል።

  ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

   

  Read more »

 • የዛሬ የዕለተ ሰኞ ሐምሌ 17 ቀን 2009 የሸገር ወሬዎች::

                                                            

  በየእለቱ ለሚደርሱ የትራፊክ አደጋ አንዱ ምክንያት መሆኑ የተነገረለት የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ በአዲስ ሊተካ ስራዎች እንዳለቁ ተሠማ፡፡ በቅርቡ ሥራ ይጀምራል ተብሏል፡፡ (አስፋው ስለሺ)

  በመርካቶ የሚገኙ ሱቆች አብዛኛዎቹ ተዘግተዋል ምክንያቱ የቀን ገቢ ግምቱ ነው ተብሏል፡፡ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በበኩሉ የተወሰኑ ሱቆች በመክፈት ላይ ናቸው ብሏል፡፡ (ቴዎድሮስ ብርሃኑ)

  በትግራይና በአማራ መንግሥታት የወሰን ማካለል አስመልክቶ የሚነሱ ጥያቄዎችን በአጭር ጊዜ መልስ እንዲያገኙ እንሰራለን ሲሉ የአገር ሽማግሌዎች ተናገሩ፡፡ (አስፋው ስለሺ)

  በአቪየሽን ኢንዱስትሪው ዘርፍ ኢትዮጵያና ቻይና ሊተባበሩ ነው ተባለ፡፡ (ምሥክር አወል)

  የአዲስ አበባ ቀይ መስቀል ማህበር ከሳውዲ ተመላሾች ድጋፍ እያደረገ ነው፡፡ (ወንድሙ ኃይሉ)

  በአባይ ውሃ ጉዳይ በተለያዩ አመታት የተደረጉ ስምምነቶችን የኢትዮጵያ መንግሥታት በመቃወም ሲናገሩ የነበሩት ንግግር ለዛሬው ውጤት ዋናው መሠረት ነው ተባለ፡፡ (የኔነህ ሲሣይ)

  ከ5 ሺ ካሬ ሜትር ቦታ በላይ የያዘ የንብረት ክምችት አላቸው ከተባሉ 108 የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች መካከል በሽያጭ አስወግደው ለመንግሥት ገቢ ያደረጉ 48 ብቻ ናቸው ተባሉ፡፡ (ትዕግሥት ዘሪሁን)

  ባለፈው በጀት ዓመት መንግሥት ጠበቃ ካቆመላቸው ተከሣሾች ወደ 380 የሚጠጉት መዝገባቸው ተዘግቶ በነፃ ተሰናብተዋል ተባለ፡፡ (ንጋቱ ረጋሣ)

  የመከላከያ ሠራዊታቸውን ወደ ጁባ የላኩ የኢጋድ አባላት የመከላከያ ሚኒስትሮች ስብሰባ በአዲስ አበባ ተጀመረ፡፡ (የኔነህ ሲሣይ)

  ምንጭ:- የሸገር FM 102.1 ሬዲዮ

   

  Read more »

Advertisment