PLANET ETHIOPIA.com

Documentary-ዘገባ


 • ስለኢትዮጵያ የቤተ ክርስቲያን ስዕሎች ምን ያህል ያውቃሉ?

   

  ኢትዮጵያ ከሶስት ሺ አመታት የሚሻገር የስነ ጥበብ ታሪክ እንዳላት አጥኝዎች ያወሳሉ።

  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስትና ከፍ ያለ ሚና እንደተጫወተ የሚመሰክሩ በየአብያተ ክርስትያናቱና በየገዳማቱ ግድግዳዎች ላይ ፤ በኃይማኖታዊ ድርሳናት ውስጥ እንዲሁም በእንጨት ላይ የተሰሩ በርካታ ስዕሎች ለዘመን መደራረብ እጅ ሳይሰጡ ይገኛሉ።

  በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አለ የስነጥበብና ዲዛይን ትምህርትቤት የስነ ጥበብ ታሪክ መምህርና ተመራማሪው አበባው አያሌው 'ኧ ግሊምስ ኦፍ ኧ ስሪ ሚሊኒያ ኦፍ ኢትዮፒያን አርት' በተሰኘ ፅሁፋቸው እንደሚያስረዱት በሶስተኛው እና በአራተኛው ክፍለ ዘመን መባቻ አካባቢ የቅድመ ክርስትና ስነ ጥበባዊ ስኬት ተመዝግቦ ነበር።

  በወቅቱ የአክሱም ስርወ መንግስት በአገር ውስጥና ከሌሎች የውጭ አገራትም ጋር የሚደረጉ የንግድ እንቅስቃሴዎች እጅጉን ስኬታማ መሆኑ በተለይም ለኪነ ሕንፃና ለቅርፃ ቅርፅ ባለሞያዎች ከፍተኛ ድጋፍ ችሮታል።

  በ4ኛው ምዕተዘመን ክርስትና የአክሱም መንግስታዊ ኃይማኖት ሊሆን ከበቃ በኋላ ግን ለሙታን መታሰቢያ የሚሆኑ ምስለ-ቅርፆችን እና ግዙፍ ሃውልቶችን ማቆም አንድም ከእምነቱ አስተምህሮ ጋር የሚፃረር ሆኖ በመታየቱ፤ በተጨማሪም የአረማዊ ዘመን ልማድ ተደርጎ በመቆጠሩ የቅርፃ ቅርፅ ጥበብ እየከሰመ ሲመጣ በፋንታው ክርስቲያናዊ ስነ-ስዕል አብቧል።

  ነገር ግን በአክሱም ዘመን ከተሰሩት ክርስትያናዊ ስዕሎች ብዙዎቹ በተደጋጋሚ የአብያተ ክርስትያናትና የገዳማት እድሳት ምክንያት ጠፍተዋል።

  ከቅድመ ክርስትያናዊ የጥበብ ስራዎች መካከል እስካሁን ያለው ትክክለኛነቱ የተረጋገጠው ብቸኛ ስዕል የአቡነ ገሪማ የወንጌሎች የድርሳን ውስጥ ምስል ነው።

  ምንጭ: ቢቢሲ

   

   

  Read more »

 • ለኢትዮጵያውያን ዲፕሎማቶች ቪዛ ስለማትጠይቀው ኳታር 5 ነገሮች - Five Things About Qatar Where Ethiopian Diplomats Do Not Need Visas

   

  ወደ ኳታር መጓዝ የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ዲፕሎማቶች ካሁን በኋላ ቪዛ አያስፈልጋቸውም፤  

  እስኪ ለወደፊቶቹ ጎብኚዎች 5 ጠቃሚ ነጥቦችን እናካፍላችሁ። 

  1. የዓለማችን ሃብታም ሀገር ናት 

  ምንም እንኳ የነዳጅ ዋጋ እየቀነሰ ቢመጣም ኳታር ግን በሚያስገርም ሁኔታ እያደገች ነው። 

  በሀገር ውስጥ ምርት በሚገኝ የነፍሰ ወከፍ ገቢ ዓለምን እየመራች ነው። ዓለማቀፉ የገንዘብ ተቋም ያወጣው አሃዝ እንደሚያሳየው እያንዳንዱ ዜጋ በነፍስ ወከፍ በዓመት 129,726 ዶላር ገቢ ያገኛል።

  ይህ ደግሞ በሁለተኝነት ከምትከተላት ሉክዘምበርግ እንኳን በ30, 000 ዶላር ይልቃል። ከአሜሪካ ደግሞ ከእጥፍ በላይ ይበልጣል።

   

  2. የበርካታ ስደተኞች መኖሪያ ናት 

  በኳታር 2.6 ሚሊዮን የሚሆን ህዝብ ይኖርባታል። ከእነዚህ መካከል 300,000 የሚሆኑት ብቻ ናቸው ዜጎቿ። ይሄ ማለት ከአጠቃላይ ነዋሪዎቿ የሀገሪቱ ዜጋ ከ7 ሰዎች አንዱ ብቻ ነው ማለት ነው። 

  ከእነዚህ ደግሞ ብዙዎቹ ከደቡብ እሲያ ፣ ከህንድ ፣ከኔፓልና ከባንግላዴሽ የመጡ ናቸው። 

  በዚህ የአውሮፓውያን ዓመት መጀመሪያ ለ80 ሃገራት ያለቪዛ የመግባት ፈቃድ በመስጠቷ ወደሃገሪቱ የመሄዱን ሂደት አቅለዋለች።

   

  3. የወንዶች ቁጥር ከሴቶች በእጅጉ ይበልጣል 

  በእርግጥ ኳታር ሚስት ለማግኘት ተመራጭ ሀገር አይደለችም ምክንያቱም ከህዝብ ብዛቷ ሴቶች 25 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው ። ከስደተኞቹ ብዙዎች ወንዶች መሆናቸው ለዚህ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው።

   

  4. ነጻ ሃሳብን ትደግፋለች(ገደብ ቢኖረውም) 

  በርካታ የአረብ ሀገራት በመንግሥታቸው ላይ ትችቶችን ስለሚዘግብ በአልጀዚራ ደስተኞች አይደሉም። ይህም በአንዳንድ የአረብ ሀገራትና በኳታር መካከል ዲፕሎማሲያዊ ውጥረትን ፈጥሯል። ሆኖም የኳታሩ ኤሚር ራሳቸውን በተመለከተ ምንም አይነት ትችት አይቀበሉም፤ ይህን ተላልፎ እርሳቸውንም ሆነ ቤተሰባቸውን የሚያሳጣ ነገር ያሳተመ ከፍተኛ ቅጣትና የእስር ጊዜ ይጠብቀዋል። 

  5. የዓለም ዋንጫን ልታስናግድ ነው 

  በአምስት ዓመታት ውስጥ የዓለማችን ታልቁ የስፖርት ክስተት በኳታር አስተናጋጅነት ይካሄዳል። በእርግጥ እስካሁን የዓለም ዋንጫን ለማዘገጃት የሚያስችላትን ውድድር ለማሸነፍ ጉቦ ሰጥታለች በሚል በመወንጀሏ መቶ በመቶ አልተረጋገጠም። 

  ይህ እውነት መሆኑ ከተረጋገጠ ዕድሉ ለሌላ ሀገር ሊሰጥ ይችላል።ካስተናገደች ደግሞ የኳታርን ከፍተኛ ሙቀት ለመከላከል በክረምት የሚካሄድ የሚጀመሪያው ዓለም ዋንጫ ይሆናል።

    

  ምንም እንኳ የዓለማችን ሃታም ሀገር ብትሆንም ጫወታው የሚካሄድባቸውን ስታዲየሞች በሚገነቡት ስደተኞች ላይ ያለፈቃዳቸው በጉልበት የማሰራትና የሰብአዓዊ መብት ጥሰት ትፈጽማለች በሚል በሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ተወንጅላለች።

  ምንጭ: ቢቢሲ

   

   

   

  Read more »

 • ሞትን አምልጦ የብዙዎችን ተስፋ ያንሰራራው ወጣት - The Young Man Who Escaped Death Gives Hope To Others

                                                        

  በብዙዎች ዘንድ አሰቃቂ ትውስታን ጥሎ ያለፈው የ 1977 ዓ.ም ረሃብ በተለይም በትግራይና በወሎ አካባቢ ከፍተኛ የሆነ ጠባሳን ጥሎ አልፏል። ሰው የሚላስ የሚቀመስ ባጣበት ወቅት ደርግ መፍትሄ ያለውን እርምጃ ወስዷል።

  ህዝቡ ቢቀበለውም ባይቀበለውም ከያሉበት በማሰባሰብ ውሃና ልምላሜ ይገኝባቸዋል ወደ ተባሉ የሃገሪቱ ክፍሎች ሄዳችሁ መስፈር ኣለባችሁ በማለት ኣወጀ። ይህ ውሳኔ በብዙዎች ዘንድ ሰፈራ በመባል የሚታወቀው ነው።

  በዚህም አጋጣሚ በኣላማጣ ዙርያ ሎላ በተባለች ቀበሌ ነዋሪ የነበሩት ባልና ሚስት ከበኩር ልጃችው ጋር ለገበያ ወደከተማ እንደወጡ ቤት የቀሩትን ልጆቻቸው ለጎረቤት አደራ ሳይሰጡ ነበር ታፍሰው በሄሊኮፕተር ወደ ወለጋ የተወሰዱት።

  እንደስሟ አልሆነላትም እንጂ ሎላ ማለትስ ኣረንጓዴ/ልምላሜ ማለት ነበር። መጥፎ አጋጣሚ ሆኖ ወላጆቹ የተወሰዱበት የ6 ዓመቱ ህፃን አበበ ፋንታሁን ከሴት አያቱ ጋር በሎላ መኖር ጀመረ። ወላጆቹን በቅጡ ሳያውቃቸው እነሱም አንደልጅ አይተው ሳይጠግቡት መለያየታቸው ግድ ሆነ።

  መለያት

  በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ህፃኑ በረሃብ ምክንያት መታመም በመጀመሩ ምን ማድረግ እንዳለባቸው የማያውቁት አያቱ እንደጨርቅ ጠቅልለው ኣላማጣ ወደ ሚገኝ የካቶሊክ ተራድኦ ወሰዱት። የድርጅቱ ሰራተኞችም ''ይህማ በቃ ሞቷል።

  ከሚቀበሩት ተርታ ይቆይ'' በማለት አስቀመጡት። ልጁን ያዩ የአካባቢው ሰዎችም በጨለማ ከተቀመጠበት ሰርቀው ወስደው ለአያቱ መልሰው ሰጧቸው።

  በሁኔታው ደስተኛ ያልነበሩት አያቱ ግን "ለምን ይዛችሁት መጣችሁ? ልጁ አይኔ እያየ መሞት የለበትም!" በማለት እንደገና መልሰው ወደ በጎ አድራጎት ድርጅቱ ወሰዱት።በዚህ ሁኔታ የተደናገጡት የድርጅቱ ሰራተኞችም "ይህን ህፃን ሞቶ ቀብረነው ነበር፤ እንዴት ተመልሶ መጣ?" በማለት ዳግም ተቀበሏቸው።

  ድርጅቱም ህፃኑን በማከምና በመንከባከብ ጤንነቱን ከመለሱ በኋላ ለሴት አያቱም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ኣስረከቧቸው።

  ጥያቄ

  እያደገና ነገሮችን መለየት ሲጀምር ህፃኑ "አባትና እናቴ የት ናቸው?" በማለት ጥያቄ ማንሳት ጀመረ። የአያቱም መልስም "ገበያ ወርደዋል፤ ይመለሳሉ።" የሚል ጊዚያዊ መልስ ነበር።

  በዚህ መልስ ተስፋ አድርጎ መቆት ያልቻለው አበበ ከአያቱ ጋር መቆየት አልፈለገም። በተቃራኒው እግሩ ወደሚመራው ለመጓዝ መንገድ ጀመረ።

  ኣላማጣ ከተማ ደርሶ በልመና የጎዳና ላይ እየኖረ ሳለ፤ ደርግ ወላጆቻቸውን ያጡና በየመንገዱ የሚኖሩትን ህፃናት እያሰባሰበ ወደ ሰፈራ መውሰድ ጀመረ። ከተወሰዱትም መካከል አበበ አንዱ ቢሆንም ወደ ታሰበው ቦታ አልደረሰም።

  ምክንያቱም ወደ ምዕራብ ኢትዮጵያ በሚወሰዱበት ጊዜ አዲስ አበባ መቅረትን መረጠ። እዚያም ቀድሞ የማያውቃቸውን ጫት መቃምና ሲጋራ ማጨስን ለመደ። ቀኑን ሙሉ ለልመና ሲዞር ይውልና ሲመሽ ካገኘበት ይተኛል።

  በዚህ ጊዜ ነበር ከየት እንደመጣና ማንነቱን ለማወቅ ጥረት የጀመረው። ትግርኛ መናገር መቻሉ ከትግራይ መምጣቱን እንዲያውቅ ረዳው።

  ፍለጋ

  ደርግ ከስልጣን ተወግዶ ኢህአዴግ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር በከተማዋ የነበሩ ህፃናት በመቐለ ከተማ በተዘጋጀ ማሳደጊያ እንዲገቡ ተደረገ። ኤልሻዳይ ወይም በቀድሞ ስሙ ለስ ፕራንስ (ተስፋ) የተባለ በጎ ኣድራጎትም እሱን ለማሳደግ ተረከበዉ።

  ማሳደጊያ ቢገባም አሁንም ከማሳደጊያው ተደብቆ በመውጣት ሲዞር ነበር የሚውለው። ትምህርት ቤት የገባው እድሜው ከገፋ በኋላ 13 ዓመት ሲሞላው ነበር። በውቕሮ ክልተ ኣውላዕሎ እስከ 3ኛ፣ በመቐለ ከተማ እስከ 9ኛ ክፍል፣ ከ10ኛ እስከ 12ኛ ደሞ አዲስ አበባ ተምሯል።

  በዛን ወቅት ስለቤተሰቦቹ ምንም አይነት መረጃ አልነበረውም። ወላጆቹም ስለእሱ በህይወት መኖር አያውቁም ነበር። በዩኒቨርስቲ ቆይታው ስለወላጆቹ መኖር አንድ ፍንጭ አገኘ።

  ይህም በመገናኛ ብዙሃን የአፋልጉኝ ማስታወቂያ ሲነገር በእሱ እድሜ ያለ አበበ የሚባል ሰው ከትግራይ አካባቢ መጥፋቱን ሰማ። ከዚህ ማስታወቂያ በኋላ ወላጆቹን መፈለግ ጀመሮ ከወንድሙ ጋር በደብዳቤ ለመገናኘት ቻለ።

  ለትራንስፖርት የሚሆን ገንዘብ ስላልነበረው ከሰዎች ወስዶ ወደ ወለጋ ነቀምት በማምራት ከወላጆቹና ከወንድሙ ጋር ለመጀመርያ ጊዜ በአካል ለመተያየት በቃ።

  ለዓመታት ተለያይው የቆዩት ቤተሰቦች ለመጀመሪያ ጊዜ በአካል ሲገናኙ መተዋወቅ እነዳልቻሉ የሚናገረው አበበ "ሁላችንም ፈዘን ቆመናል፤ ወላጅ እናቴ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ነገሮቸን በውስጧ ስታብላላ ከቆየች በኋላ መቆም ተስኗት ወደቀች። " በማለት ይናገራል።

                                                                       

  ሌሎችን መርዳት

  ለጥቂት ጊዜ ከቤተሰቦቹ ጋር ከቆየ በኋላ አዲስ አበባ ተመልሶ መጣ። በዩኒቨርሲቲ ቆይታውም ከትምህርቱ ጎን ሰዎችን መርዳት ያዘወትር የነበረው አበበ ከተመረቀ በሁዋላም በደማቸው ኤች አይ ቪ ቫይረስ ያለባቸውን ህፃናት በሚረዳ ድርጅት ውስጥ ተቀጠረ።

  በወቅቱ በደማቸው ቫይረሱ ያለባቸው ህፃናት እርዳታ ለማግኘት ከትግራይ ወደ አዲስ ኣበባ ሲመጡ በማየቱ በራሱ ተነሳሽነት ሎላ ብሎ የሰየመውን የህፃናት መንከባከቢያ በ2001 ዓ.ም ኣቋቋመ። ሥራውን የጀመረው ቫይረሱ በደሟ ያለባትን የስድስት ወር ህፃን በመቀበል ነበር።

  ድርጅቱን ለማቋቋም አሜሪካዊና አንግሊዛዊ ዜግነት ያላቸው ባልና ሚስትም የገንዘብ ድጋፍ አድርገውለታል። ከሞት አፋፍ የተረፈው የትናንትናው አበበ ዛሬ ከሞት ጋር ትግል ላይ ያሉትን ህፃናት እየተንከባከበ ይገኛል። ይህም ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ ህፃናትን በመንከባከብ በትግራይ ቀዳሚ የበጎ ኣድራጎት ድርጅት ሆኗል።

  ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የጤና ችግር ያጋጠማቸው ህፃናት በማህበራዊ ጉዳይ ፅህፈት ቤት እየተመረጡ ይሰጡታል። በዚህ መሰረትም ሎላ የህፃናት መንከባከቢያ ድርጅት 20 ወላጅ አልባ ህፃናትን እያሳደገ ይገኛል። ከዚህም በተጨማሪ በየቤታቸው ሆነው እርዳታ የሚያገኙትም ቀን በድርጅቱ ሲረዱ ይውሉና ማታ ወደየቤታችው ይላካሉ። በድምሩ 56 ህፃናት ከድርጅቱ እርዳታ ያገኛሉ።

  አበበ ህፃናቶቹን ለመርዳት በመቐለ ከተማ ቀበሌ 17 ለተከራየው ቤት በየወሩ 10 ሺ ብር ይከፍል ነበረ። አሁን ግን የመቐለ ከተማ አስተዳደር 5000 ካሬ ሜትር ቦታ ሰጥቶት በከተማዋ ደብረ ገነት ተብሎ በሚጠራ ኣካባቢ ማዕከሉን ገንብቷል።

  አበበ በማዕከሉ ያሉ ልጆቹ ከምንም ነገር በላይ ትምህርት ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ይጥራል። "የህዝብና የሃገር ሸክም ሳይሆኑ፤ ችግር ፈቺ ዜጎች ለማፍራት እጥራለሁ። በጥሩ ሥነ-ምግባር ታንፀው ሌሎችን እንዲያስተምሩም እፈልጋለሁ።" በማለት አበበ ይናገራል።

  ከሁሉም በላይ ደግሞ ያቋቋመው ድርጅት በእሱ ብቻ ተገድቦ እንዳይቀርና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት እንዲሁም ህዝቡ ተገቢውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪውን ያቀርባል። አበበ ፋንታሁን ባለ ትዳር ሲሆን ወላጆቹ ዛሬም ድረስ የሚኖሩተረ ምዕራብ ኢትዮጵያ ወለጋ ውስጥ ነው።

  ምንጭ: ቢቢሲ

  Read more »

 • ተዓምራዊቷ ቅድስት ማርያም ውቕሮ ገዳም - The Mysterious St. Mary Monastery in Ethiopia

  ትግራይ ምድር አቅፎ ከያዛችው ከ120 በላይ የሆኑት ከአለት ተፈልፍለው የታነፁት አብያተ ክርስትያን ለዛሬ አንዱን እናስተዋውቃችሁ።

  ቅድስት ማርያም ውቕሮ ትባላለች። ወደ አካባቢው ለመድረስ በጣም አስቸጋሪ የጠጠር መንገድና ወንዝ መሻገር የግድ ነው። መኪናችን ወንዙን መሻገር አቅቷት ስትንገዳገድ የተመለከቱት የአከባቢው አርሶ አደሮች ተጠራርተው መንገዱን አስተካክለው አሻግረውናል።

  ወደ ገዳሙ ቅጥር ግቢ ከተገባ በኋላ መጀመርያ ከአለት የተሰራው ሙዳዬ ምጽዋት ይገኛል። የገዳሙ አስተዳዳሪ ቄስ ዘሚካኤል ወልደጊዮርጊስ ሙዳዬ ምጽዋቱን ከማለፋችን በፊት ጫማችንን እንድናወልቅ ቀጭን ትዕዛዝ አስተላለፉ።

  በሰንሰለት ዙርያ ጥምጥም የተቆለፈው የገዳሙን በር ከፍተው አስገቡን። የበሩ መዝጊያ ከአንድ የዛፍ እንጨት ብቻ እንደተዘጋጀ ለመረዳት አይከብድም።

  ቄስ ዘሚካኤል፤ ገዳሟ መቼና እንዴት እንደተቆረቆረች ይናገራሉ።

  "ይህች ገዳም ንግሥት ማርያም በ333 ጐንደር ላይ ሆነው በህልም ተገልፆላቸው ነበር የታነፀው። ደግሞ የሰው ልጅ በዶማ ቆፍሮ ነው ያነፀው በሉና እመኑ" ሲሉ አፌዙብን። ብታምኑም ባታምኑም 'አብ ሃነጸ ወልድ መንፈስ ቅዱስ' ራሱ መንፈስ ቅዱስ ነው ያነፃት ብለን ነው የምናምነው" ይላሉ።

  ገዳሟ ውስጥ የአንድ ትልቅ የጥድ ዛፍ ቁመት ያላቸው 44 ዓምዶች ይገኛሉ። በሌሎች ገዳማትና አድባራት እንደሚደረገው ሁሉ በቅድስት ማርያምም ወንዶችና ሴቶች ተለያይተው ነው የሚቀመጡት።

  በጣሪያው ላይ ሦስት እምነ አድማስ ነበሩ። አንደኛው ወድቆ እንድያውም ጣልያን ለመውሰድ ሞክሮ አልተሳካለትም። ሁለቱ እስከ አሁን ድረስ አሉ። ድንጋዩ ላይ በእብራይስጥ ቋንቋ የተፃፈ ፅሑፍም ይታያል።

  እምነ አድማስ ድንጋይን ለመቁረጥና ለመጥረብ ኃይል የተሰጠው የድንጋይ ዘር ነው።

  ገዳሟ ውስጥ ከሚታወቅ ይልቅ የማይታወቀው ስለሚበዛ ቄስ ዘሚካኤል ያስታወሱትንና የነገሩንን ብቻ አሳጥሬ ልንገራችሁ።

  በአንድ የገዳሟ ጓዳ ውስጥ ልጅ መውለድ የዘገየባችው እንስቶች ተቀምጠው ፈጣርያቸውን የሚለምኑበት ከአለቱ ተፈልፍሎ የተዘጋጀ ወንበር ይታያል። ከፊት ለፊቱ ደግሞ መባ የሚያስቅምጡበት መደርደርያ አለ። 

  በአንደኛው የገዳሟ ክፍል የቅድስት ማርያም መንበረ ታቦት አለ። መንበረ ታቦቱ ራሱ ሙሉ ለሙሉ ከአለት ተፈልፍሎ ነው የተሰራው።

  ከመንበረ ታቦቱ አናት ላይ 4 ጉልላት ይታያል። ወደ መንበረ ታቦቱ ከካህንና ከዲያቆን ውጪ ምዕመን እንዲገባ አይፈቀድለትም።

  ገዳሟ ውስጥ የሚገኘው የጨለመው በር ፈለገ ኦር ይባላል። ሊቃውንቱ ጉድጓዱ ቀጥ አድርጐ እስራኤል ነው የሚያስገባው ብለው ያምናሉ። ድሮ ነው አሉ 5 ካህናት ማሾና ጧፍ ይዘው ገብተው በዛው አልተመለሱም ብለውናል።

  መሪጌታ ቁጭ ብሎ ወደ ታቦቱ እያየ የሚጸልይበት ዙፋንም ተቀርጾ ይታያል። ዙፋኑ ከላይ ዘውድ አለበት፤ ይህም ከአለት ተፈልፍሎ ነው የተዘጋጀው።

  ገዳሟ ውስጥ የተለያየ ትርጉም ሊሰጣቸው የሚገቡ 5 ጉልላት አሉ፤ የኮከቦች ተምሳሌት ብለው የሚጠሩዋቸው ቅርፆችም አሉ።

  የገዳሟ የበር መዝጊያዎች ከእየሩሳሌም በቀስተ ደመና ተጠፍረው እንደመጡ ይነገራል። ገዳሟ በር የሌላቸው 12 መስኮቶችም አሉት።

  ልክ እንደ መንበረ ታቦቱ ከካህንና ዲያቆን ውጪ ሌላው ምዕመን የማይገባበት ቤተልሔምም አለ።

  በአንድ ትልቅ አለት ላይ ሆኖ ከቅድስት ማርያም በተጨማሪ የቅዱስ ጊዮርጊስ ገዳም አለ። ገዳሟ መወጣጫ አልነበራትም። በቅርቡ አንድ ምግባረ ሰናይ ግለሰብ ከብረት የተዘጋጀ መሰላል አሰርቶላታል። 

   ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ገዳም የሚያስወጣ መሰላል

  የቅዱስ ጊዮርጊስ ገዳም መስኮተ አብርሃምን ጨምሮ 6 መስኮቶች አሉዋት። በመስኮተ አብርሃም በኩል አሻግሮ የቅድስት ማሪያም መንበረ ታቦትን ማየት ይቻላል።

  ሁለቱ ገዳማት ተአምራዊ የጥበብ ሥራ እንዳረፈባቸው ፍንትው ብሎ ይታያል።

  እነኝህን ታሪካዊ ገዳማት በእንግዶች እንዳይጐበኙ ወደ አከባቢው የሚወስደው የመኪና መንገድ አይመችም። ሌላው ቀርቶ ወንዙን በቀላሉ ለመሻገር እንኳን ድልድይ አልተሰራለትም። የወረዳው አስተዳደር ድልድዩን ለመስራት ሽርጉድ ሲል ተመልክተናል።

  ትግራይ ምድር ውስጥ የሚገኙት አብዛሃኛዎቹ ገዳማት በየተራራውና ሸንተረሩ ስለሚገኙ መሰረተ ልማት ካልተሟላላቸው በእንግዶች ሊጐበኙ አይችሉም።

  መንግሥት በዚህ ዙርያ ብዙ መስራት ይጠበቅበታል። ሌላው ቀርቶ ገዳማቱን ለማየት የሚሄዱት እንግዶች የሚያርፉበት መጠለያ እንኳን የላቸውም። ባለሃብቶችም መዋዕለ ንዋያቸውን በዚሁ ዙርያ እንድያውሉ ማበረታትና ሁኔታውን ማመቻቸት ይጠበቃል።

  ገደማቱም ጥገናና እንክብካቤ ይሻሉ። ከዚህ ውጭ የቅድስት ማሪያም ውቕሮ ተአምራዊ ናት ከማለት ባለፈ የተሰነደ ማስረጃ እንኳን የላትም።

  ምንጭ: ቢቢሲ

  Read more »