PLANET ETHIOPIA
Advertisment

Health ጤና


 • ለጭንቀት የተጋለጡ ሴቶች ፅንሳቸው የመጨናገፍ እድሉ 42 በመቶ ይደርሳል::

                                                   

  ለረጅም አመታት ለጭንቀት የተጋለጡ ሴቶች በእርግዝና ወቅት ፅንሳቸው የመቋረጥ እድሉ 42 በመቶ እንደሚደርስ አንድ ጥናት አመለከተ።

  በለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ እና በቻይና በሚገኘው ዠጃንግ ዩኒቨርሲቲ አማካኝነት የተደረገው ጥናት በወጣትነታቸው ጭንቀት የሚያበዙ ሴቶች በኋለኛው እደሜያቸው በርካታ ችግሮች እንደሚገጥሟቸው አረጋግጧል።

  በጥናቱ ጭንቀት እና ሴቶች በእርግዝና ወቅት የሚያጋጥማቸው የፅንስ መጨናገፍ ያላቸው ግንኙነት ተዳሷል።

  ሴቶች ከፀነሱ ከ24 ሳምንታት በፊት የሚከሰተው የፅንስ መጨናገፍ፥ በእያንዳንዱ ነፍሰ ጡር ሴት የመድረስ እድሉ 20 በመቶ ነው።

  ሴቶች በእርግዝና ወቅት ስለ ትዳር አጋራቸው፣ ልጆቻቸው እና ቤተሰቦቻቸው ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ሲገቡ የፅንስ መጨናገፍ እንደሚከሰት ነው ጥናቶች የሚያሳዩት።

  የማህበራዊ ግንኙነት ችግር፣ የገቢ ማነስ፣ በትዳር አለመደሰት፣ በስራ ገበታ የሚያጋጥም ጫና እንዲሁም ከዚህ ቀደም ያጋጠመ የፅንስ መጨናገፍም ሌሎች አበይት ምክንያት ናቸው ተብሏል።

  በለንደን ዩኒቨርሲቲ እና ዠጃንግ ዩኒቨርሲቲ የተደረገው ጥናት የጭንቀት እና ፅንስ መጨናገፍ ዝምድና የጭንቀት ሆርሞኖች ከመመንጨታቸው እና መለቀቃቸው ጋር ይያያዛል ይላል።

  እነዚህ የጭንቀት ሆርሞኖች ለፅንሱ እድገት ወሳኝ የሆኑ ኬሚካሎች እንቅስቃሴን ያውካሉም ነው ያለው ጥናቱ።

  የጥናቱ ዋና አዘጋጅ እና በለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የስነ ልቦና አስተማሪ የሆኑት ዶክተር ብሬንዳ ቶድ፥ ከእርግዝና በፊት አልያም በኋላ የሚከሰት ከፍተኛ ስነ ልቦናዊ ጭንቀት ከፅንስ መጨናገፍ ጋር ሰፊ ግንኙነት እንዳለው አረጋግጠናል ብለዋል።

  ጥናቱ በተለይም በወጣትነት እድሜያቸው ለጭንቀት የተዳረጉ ሴቶች በእርግዝና ወቅት የሚገጥማቸው የፅንስ መጨናገፍ ችግር ወደ 42 በመቶ ከፍ ሊል እንደሚችልም ተናግረዋል።

  በመሆኑም ሴቶች ከማርገዛቸው በፊት ስነ ልቦናዊ የጤና ሁኔታቸውን ቢያውቁት መልካም ነው ብለዋል።

  ጥናቱ የጭንቀት እና ፅንስ መጨናገፍ ዝምድናን ያመላከተ ቢሆንም በቀጣይም ሌሎች ጥናቶች ሉደረጉ እንደሚገባም ነው ዶክተር ቶድ ያብራሩት።

  ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

   

  Read more »

 • ቦርጭ ለማጥፋት የሚመከሩ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች

                                          

   

   

  ቦርጭ ለሰውነት ቅርፅ  

  መበላሸት ብቻ ሳይሆን ለጤና የማይበጅ መሆኑ ይነገራል።

  በስብ እና ቅባት ክምችት የሚከሰተው ቦርጭ፥ ለስኳር በሽታ፣ ለልብ እና ተያያዥ የጤና እክሎች፣ ለደም ግፊት እና ለበርካታ የካንሰር አይነቶችም ያጋልጣል።

  ቦርጭን በጊዜ ካላጠፉትና መፍትሄ ካልፈለጉት ደግሞ ለመቀነስ አሰቸጋሪና ለጤናም ጠንቅ መሆኑን ይቀጥላል።

  ይህን አላስፈላጊ ትርፍ ክፍል ለማስወገድ ታዲያ አመጋገብና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ዋነኛ መፍትሄ መሆናቸውን ባለሙያዎች ይመክራሉ።

  ከአመጋገብ ጋር ተያይዞ በፕሮቲን የበለጸጉና በካርቦሃድሬት ይዘታቸው ከፍ ያሉ ጥራጥሬዎችን መመገብ ይመከራል።

  ከዚህ ባለፈም አትክልትና ፍራፍሬ በመመገብ፥ ነጭ ዳቦ፣ ፓስታና ስኳር ያለባቸውን መጠጦች ደግሞ መቀነስ።

  የሚያደርጉት የአካል ብቃት እንቅስቃሴም የተከማቸውን የስብ መጠን ለማቃጠልና ለማስወገድ ይረዳዎታል።

  እነዚህ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች ሆድ አካባቢ በስብ ብዛት የሚፈጠረው ቦርጭ እንዳይከሰት ማድረግና ብሎም የማቃጠል አቅማቸው ከፍ ያለ ነው።

  የጤና እና የአካል ብቃት ባለሙያዎችም ቦርጭን ለማስወገድ የሚረዱ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን ይጠቁማሉ።

  ግማሽ ሲት አፕ፦ በጀርባ በመተኛት ሁለት እግር ትሪያንግል ቅርጽ እስከሚሰራ ወደ ላይ በጥቂቱ ማጠፍ፤ እግርዎ በትክክል መሬት መያዝ መቻል አለበት።

  ከዚያም እጅን ደረት ላይ አድርጎ ማጣመርና ከጭንቅላትዎ እስከ ደረትዎ ቀና እያሉ ግማሽ ሲት አፕ መስራት።

  ይህን እንቅስቃሴ ከ10 እስከ 12 ለሆነ ድግግሞሽ መስራትና በሳምንት ለአራት ቀናት መከወን።

  ተኝተው ብስክሌት የመጋለብ እንቅስቃሴ፦ ጭንቅላትዎን ሁለት እጅዎ ላይ በማሳረፍ በጀርባ መተኛት።

  ከዚያም ሁለት እግርዎን ጥቂት አጠፍ አድርገው ተመቻችተው መተኛት።

  እግርዎን በተቃራኒ የእጅዎ አቅጣጫ በማንሳት ወደ ደረትዎ እያስጠጉ እንቅስቃሴውን መስራት፤ ግራ እግርዎን ካነሱ ከጭንቅላትዎ ቀና በማለት የቀኝ እጅዎን ወደ ጉልበትዎ ማስጠጋት።

  ይህን ድግግሞሽ 10 በግራ 10 ደግሞ በተቃራኒው አቅጣጫ እያደረጉ ለሁለት ጊዜያት ያክል በሳምንት ለአራት ቀናት መከወን።

  እግርን ማዟዟር፦ እግርዎን ዘርግተው በጀርባዎ መተኛትና ሁለት እጅዎን ቀጥ አድርገው በእግርዎ ትይዩ መዘርጋት።

  ከዚያም አንደኛውን እግርዎን በማንሳት 90 ዲግሪ እስከሚሰራ ማዟዟር፥ ይህን ሲያደርጉ መሬት የያዘው እግርዎ ጣቶች ወደ ፊት መሆን መቻል አለባቸው።

  እንቅስቃሴውን በግራ እግር ለስድስት ጊዜ ያክል በተቃራኒውም እንደዛው በማድረግ በቀን ለ10 ጊዜ በድግግሞሽ መስራት።

  አንደኛው እግርዎ ሲንቀሳቀስ ሌላኛው እግር መሬት መያዝና እጅም ከቦታው መንቀሳቀስ የለበትም።

  ሌን ወደላይ እያነሱ መስራት፦ ተመቻችተው በጀርባዎ መተኛትና እጅና እግርዎ እንደተገጠሙ ወደ ፊት መዘርጋት።

  ከዚያም እጅዎ መሬቱን ሳይለቅ ሁለት እግር እንደተገጠመ ወደ ላይ በማንሳት 90 ዲግሪ እስከሚሰራ ድረስ ወደ ኋላ ከፍ ማድረግ።

  ይህን ሲያደርጉ የዳሌዎ ክፍል መሬቱን ለቆ ወደ ላይ ከፍ ይላል፤ እግር ምንም ቢሆን ሊታጠፍ አይገባም።

  ይህን በቀን ለ10 ጊዜ ያክል በድግግሞሽ በማድረግ በሳምንት ለአራት ቀናት ደጋግመው መስራት።

  እግርን እያነሱ ወደታች ማውረድ፦ ቀጥ ብለው በጀርባዎ ከተኙ በኋላ እግርዎ ሳይታጠፍ ወደ ላይ ማውጣትና ጥቂት ያዝ ማድረግ።

   

  Leg_Drops.jpg

  ከዚያም ባወጡበት ሃይል ቀስ ብለው ወደታች ማውረድ፤ እጅዎ መሬት መልቀቅ የለበትም እግርም ቀጥ እንዳለ መውጣትና መውረድ ይኖርበታል።

  በየቀኑ ለ10 ጊዜ ያክል በድግግሞሽ ቢሰሩ ውጤት ያዩበታል።

  የእጅ ክብደት በመያዝ ቁጭ ብድግ መስራት፦ ሁለት ተመሳሳይ መጠን ያላቸው የእጅ ክብደቶችን በግራና ቀኝ እጅዎ መያዝ።

  ከዚያም ተስተካክለው መቆምና ክብደቱን እንደያዙ እግርና እጅን ሰፋ አድርጎ ወደ ታች ቀስ ብሎ መውረድና መልሰው በመነሳት ቁጭ ብድግ መስራት።

  ከአምስት እስከ 10 ለሚደርስ ጊዜ በመደጋገም አረፍ እያሉ በሳምንት ለሶስት ቀናት መስራት።

   

  ምናልባት ጀማሪ ከሆኑ እስከ 1 ኪሎ ግራም ክብደት ያላቸውን ክብደቶች ብቻ ይጠቀሙ ከዚያ በላይ አይመከርም።

  ማሽ ቁጭ ብድግ፦ ይህ ደግሞ የወንበር ቅርፅ በመስራት የሚሰሩት ቁጭ ብድግ ሲሆን ሙሉ በሙሉ ሳይሆን በግማሽ እየተወረደ የሚከወን ነው።

   

  chairpose.jpg

  የሁለት እጅዎን መዳፍ በማጋጠም ወደ ላይ ቀጥ አድርጎ መዘርጋት፥ ከታች እግርዎም መገጠም ይኖርበታል።

  ከዚያም በግማሽ እስከ 45 ዲግሪ ወረድ እያሉ ዳሌዎን ጥቂት ያዝ እስከሚያደርግዎት ድረስ በጥቂቱ ወረድ ብለው መልሰው መነሳት።

  በዚህ መልኩ በግማሽ ቁጭ ብድግ እያሉ ከ10 እስከ 15 ለሆነ ጊዜ በቀን ውስጥ በቻሉት መጠን መስራት።

  በሳምንትም እስከ አራት ጊዜ ይህንኑ መደጋገም እና መከወን።

  መዳፍዎን መሬት ላይ በማድረግ እግርን ማፈራረቅ፦ በመጀመሪያ ፑሺ አፕ በሚሰራበት አኳኋን ሰውነትን ማዘጋጀትና መዳፍዎን በትክሻዎ ትይዩ መሬት ላይ ማድረግ።

   

  mount_climber.jpg

  ከዚያም እግርዎን ከፈት አድርገው መዘጋጀት እና፥ እግርዎን ተራ በተራ ወደ ደረትዎ እያስጠጉ መመለስ።

  ይህን እንቅስቃሴ በቻሉት መጠን ከ5 እስከ 10 ደቂቃ ለሚሆን ጊዜ በየቀኑ መስራት።

  በሲት አፕ ቅርጽ በመሆን እግርን በጥቂቱ ማንሳት፦ እግር ሳይታጠፍ በጀርባዎ መተኛትና ጭንቅላትዎን በሁለት እጅዎ በመያዝ በጣም በጥቂቱ ከጭንቅላትዎ ቀና ማለት።

   

  Flutter_Kicks.png

  ከዚያም እግርዎን ከመሬት ከአንድ ስንዝር ያነሰ ከፍታ በማንሳት በጣም ሳይከፈት እያፈራራቁ ላይና ታች ማድረግ።

  እስከቻሉት ድረስ በመስራት ሲደክመዎት አረፍ እያሉ በቀን ውስጥ እስከ 8 ጊዜ ለሚደርስ ድግግሞሽ መስራት።

  ሳምንቱን ሙሉ በዚህ መልኩ መስራት፤ ከላይ የተጠቀሱትን መስራት ከቻሉ የተጠራቀመ የስብ ክምችትን ለማስወገድና የተሻለ ቅርጽ ለመያዝ ይረዳዎታል።

  በተጨማሪም ጤንነትዎን ይጠብቃሉና ዛሬውኑ ጀምረው ሳይሰላቹ ይስሩት።

  ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

  Read more »

 • በወር አበባ ጊዜ ሊደረጉ የሚገቡ የንጽህና እና ተያያዥ ጥንቃቄዎች::

                                          

  የወር አበባ የሴቶች ወርሀዊ ኡደት ሲሆን አንድ ሴት የመራቢያ እንቁሎችን ሰውነቷ ማምርት ከሚጀምርበት የእድሜ ክልል ጀምሮ እስከ ማረጥ ወይም ሰውነቷ እንቁላልን ማምረት እስከሚያቆምበት ጊዜ ድረስ በየወሩ የሚመጣ ነው።

  ታዲያ ይህ የወር አበባ በየወሩ በሴቶች ላይ በሚከሰትበት ጊዜ ተገቢውን ጥንቃቄ ካልተደረገ ብዙ የጎንዮሽ ጉዳቶች ሊያስከትል እንደሚችል ያውቃሉ።
  በዚህ ኡደት ጊዜ ሴቶች ለኢንፌክሽን የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ ሲሆን፥ ይህ ኢንፌክሽን የሽንት መሽኚያ ቱቦዎችን እንዲሁም መሀፀንን ያጠቃል በጊዜው ተገቢውን ህክምና ካላገኘም ከፍተኛ ህመምን ሊያስከትል ይችላል።

  ሰለዚህም በወር አበባ ጊዜ ሊደረጉ የሚገቡ የንጽህና እና ተያያዥ ጥንቃቄዎችን እናካፍላችሁ

  1 በየጊዜው መታጠብ
  ሴቶች በወር አበባ ጊዜ መታጠብ ወይም ዝናብ ላይ መውጣት የለባቸውም የሚል አባባል እንዳለ ይነገራል፤ እንደ ጤና ባለሙያዎች ገለፃ ግን ይህ ፈፅሞ ከእውነት የራቀ ነው።

  የህክምን ባለሙያዎች አንዲት ሴት የወር አበባዋ ላይ በምትሆነበት ጊዜ በየጊዜው መታጠብ እንዲሁም ቢያንስ በቀን አንዴ ገላዋን መታጠብ እንዳለባት ይመክራሉ።

  ይህም ሊመጣ የሚችልን መጥፎ ጠረን እንዲሁም የሰውነታችንን ንፅህና ለመጠበቅ ይረዳል፤ ከዚህ በተጨማሪ ሽንት ቤት ተገብቶ በሚወጣት ጊዜ እጅን በሳሙና መታጠብ ይኖርብናል።

  2 ትክክለኛውን የልብስ አይነት መምረጥ
  አንዳንዶች በወር አበባ ጊዜ ከነጭ ልብስ ውጪ የትኛውንም አይንት ልብስ መልበስ እንደሚቻል ሲናገሩ ይሰማል።

  በእርግጥም ነጭ ልብስ በወር አበባ ጊዜ መልበሱ አይመከርም ሆኖም እንደ ጤና ባለሙያዎች በጣም አስፈላጊ የሆነው ጥንቃቄ በጣም ጠባብ እና ሰውነት ላይ የሚጣበቁ ልብሶችን፣ የጨርቃቸው አይነት ሰውነት ላይ እርጥበትን የሚፈጥሩ የልብስ አይነቶችን፣ ሙቀት እና የማሳከክ ስሜት ያላቸውን የልብስ አይንቶችን አለመልበስን ይመከራል።

  ከጥጥ ጨርቅ የተሰሩ የውስጥ ፓንቶችን እንዲሁም ሰፊ ልብሶችን መልበስ እርጥበት እንዳይፈጠር ከመርዳቱም ባሻገር ጥሩ ስሜት እንዲኖረን ያደርጋል።

  3 በየጊዜው የንፅህና መጠበቂያ ሞዴስን በአግባቡ መቀየር

  በየጊዜው የንፅህንና መጠበቂያ ሞዴስን መቀየር ከንፅህና ጉድለት ከሚፈጠር የኢንፌክሽን ችግር ከመጠበቁም ባሻገር በዚህ ምክንያት የሚመጡ በሽታዎችን ማስቀረት ያስችላል።

  4 ትክክለኛውን የሞዴስ አይነት መምረጥ

  ሞዴሶችን በምንጠቀምበት ጊዜ ትክክለኛውን የመምጠጥ አቅም ያለውን የሞዴስ አይነት እንድንመርጥ ይመከራል።

  ጥናቶች እንደሚጠቁሙት የመምጠጥ ባህሪያቸው ዝቅተኛ ያልሆነ ሞዴሶችን መጠቀም ይመከራል።

  5 በወር አበባ ጊዜ የሚከሰት ህመምን በተለያዩ መንገዶች ማስወገድ

  በወር አበባ መጀመሪያ እና መጨረሻ አካባቢ አንዳንዴ በመሀል ብዙ ሴቶች የሆድ እና የተለያዩ የሰውነት አካላት ህመም ያጋጥማቸዋል።

  ይህን ህመም ለማስወገድ ሊወሰዱ የሚችሉ መድሀኒቶች ቢኖሩም በቀላሉ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ህመሙን ማስወገድ ይቻላል።

  ምንጭ:- ጤናችን

  Read more »

 • ሻይ መጠጣት ለጉንፋን እንዳንጋለጥ ይከላከላል::

                                              

  ሻይ መጠጣት ለጉንፋን እንዳንጋለጥ እንደሚካላከል አዲስ የወጣ ጥናት አመልክቷል።

  ጥናቱን ያካሄዱት ተመራማሪዎች በሻይ፣ ቀይ ወይንና የመሳሰሉት መጠጦች ውስጥ የሚገኘው “ፍላቭኖይድስ” የላይኛውን የመተንፈሻ አካላችንን የሚያጠቁ ባክቴሪያዎችን የመከላከል አቅም አለው ይላሉ።

  ከዚህ ቀደም የነበሩ ማስረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከሆነ በአንጀታችን ውስጥ የሚገኙ ማይክሮባክቴሪያዎች እንደ ጉንፋን ላሉ በሽታዎች በቀላሉ እንዳንጋለጥ ይከላከላሉ።

  ተመራማሪዎችም በአንጀታችን ውስጥ ከሚገኙ ማይክሮ ባክቴሪያዎች ውስጥ የትኛው ለጉንፋን ያለንን ተጋላጭነት ይቀንሳል የሚለውን ለመለየት ጥናት ሲያካሂዲ ቆይተዋል።

  “ለዓመታት ፍላቭኖይድስ የተባለው ንጥረ ነገር የሰውነታችንን በሽታ የመከላከል ስርዓት በማጠናከር ለጉንፋን እና ለተለያዩ ኢንፌክሽኖች እንዳንጋለጥ እንደሚያደርግ ይታወቃል” ይላሉ በአሜሪካው የሴንት ሉዊስ የህጻናት ሆስፒታል የጥናት ቡድን መሪ አሽሊይ ስቲድ።

  “ፍላቭኖይድ ንጥረ ነገር በእለት ተእለት ምግባችን ውስጥ በቋሚነት የሚገኝ ንጥረ ነገር ነው፤ ስለዚህ ዋናው የጥናታችን አላማ የትኛው የአንጀታችን ባክቴሪያ ከፍላቭኖይደስ ጋር ተዋህዶ ለጉንፋን እና ሌሎችኢንፌክሽኖች ተጋላጭነትን ይቀንሳል የሚለው ነው፤ አሁንም ቢሆን በዚህ ለይ የሚቀረን ስራ አለ” ብለዋል።

  በዋሽንግተን ዩኒቨርሲቱ የጤና ሳይንስ ትምህርት ቤት የሴንት ሉዊስ ሆስፒታል ተመራማሪዎች የትኛው የአንጀት ባክቴሪያ ከፍላቭኖይደስ ጋር ሊስማማ ይችላል የሚለውን ለመለየት የሰዎች የአንጀት ባክቴሪያ ላይ የተለያዩ ምርምሮችን አካሂደዋል።

  በዚህ ምርምራቸውም “ክሎስትሪድየም ኦርቢሳይንደንስ” የተባለ ማይክሮ ባክቴሪያ ያገኙ ሲሆን፥ ይህም ፍላቭኖይድስ የተባለውን ንጥረ ነገር በመስበር የሰውነታችንን በሽታ የመከላከል አቅም እንዲያጠናክር የሚያድርግ ነው ብለዋል። 

  ለዚህም የእለት ተእለት ምግባችን ውስጥ ፍላቭኖድስን ማካተት እንደ ጉንፋን ላሉ በትንፋሽ የሚተላለፉ በሽታዎች የመጋለጥ እድላችንን እንደሚቀንስም ነው ተመራማሪዎቭቸ ያስታወቁት።

  በፍላቭኖድስ ንጥረ ነገር ከበለፀጉ ምግቦች እና መጠጦች ውስጥም፦

  ሻይ (በተለምዶ ቀይ ሻይ በማለት የምንጠራው)

  ወይን (በተለይም ቀይ ወይን) 

  ለውዝ 

  እንዲሁም እንደ ብርቱካን እና ሎሚ ያሉ በሲትሪክ አሲድ በውስጣቸው ያላቸው ፍራፍሬዎች ተጠቃሽ ናቸው።

  ምንጭ:- ጤናችን

  Read more »

 • 10 አስደንጋጭ የህክምና ስህተቶች

                                                          
  የህክምና ስህተቶች በየጊዜው ይከሰታሉ፡፡ እንደውም በአገረ አሜሪካ በየዓመቱ 200 ሺህ ሰዎች ይሞታሉ፡፡ አንዳንዶች በአጋጣሚ የአካል ጉዳት ያገኛቸዋል፤ ወይም ደግሞ ህይወታቸው ሊያልፍ ይችላል፡፡ በእርግጥ ከሰው ስህተት ከብረት ዝገት እንደማይጠፋ ሁሉ ሐኪሞችና ነርሶችም ሰዎች ናቸውና ሊሳሳቱ ይችላሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ በጣም የማይሆኑ ስህተቶች ወይም ደግሞ በቀላል ጥንቃቄ ሊወገዱ የሚችሉ አስገራሚ ክስተቶች ሲፈፅሙ ይስተዋላል፡፡ ታዲያ ይህ የጤና ነው ማለት ይቻል ይሆን? እስኪ በታሪክ ውስጥ የማይረሱ የሚባሉትን እናንሳ እና የየራሳችንን አስተያየት እንሰንዝር፡፡
  1. ቆለጥ ያሳጣ ስህተት
  ቤንጃሚን ሁትን በመባል የሚጠራ የአየር ኃይል ባልደረባ ወደ ህክምና ያመራው ከሁለቱ የቆለጥ ፍሬዎቹ ውስጥ የግራው በመሟሸሹና በውስጡም የካንሰር ሕዋስ ሳይዝ እንዳልቀረ በሐኪም ስለተጠረጠረ ነበር፡፡ ይህ የቆለጥ ፍሬ ቢወገድም በአንዱ መውለድ ይችላል፤ የወንድ የዘር ፍሬም (sperm) ማምረት ያስችለዋል፡፡ በመሆኑም በቀዶ ጥገና እንዲወገድለት ቆዶ ህክምና ተደርጎለት ሲወጣ ግን የተወገደው የቆለጥ ፍሬ የግራው ሳይሆን ጤናማውን የቀኙ ሆኖ ነበር የተገኘው፡፡ በዚህም ስህተት ይህ ግለሰብና ሚስቱ የሎስ አንጀለስን ሆስፒታል በመክሰሳቸው 200 ሺህ ዶላር ካሳ አስከፍለዋል፡፡ እዚህ እኛ አገርም በማደንዘዣ ፋንታ የሬሳ ማድረቂያ መርፌ የተወጋ ታካሚ የአንድ ሰሞን መወያያ አጀንዳ ሆኖ እንደነበር ያስታውሷል፡፡
  2. በተሳሳተ ጭንቅላት በኩል የተደረገ ቀዶ ጥገና፡-
  በ2007 እንኳን በሮድ አይላንድ ሆስፒታል በሶስት ሰዎች ላይ ትክክለኛ ባልሆነ የጭንቅላት አቅጣጫ ላይ ቀዶ ጥገና ተደርጎላቸዋል፡፡ እንግዲህ ይታያችሁ በአንጎል ላይ መሳሳት ማለት ምን ማለት ሊሆን እንደሚችል፡፡ ሁለቱ ስህተቶች ወዲያውኑ በመታወቃቸው ፈጣን ማስተካከያ ተደርጎላቸዋል፡፡ የሶስተኛው ታማሚ ግን ወዲያው ባለመታወቁ ከሶስት ሳምንት በኋላ በ86 ዓመታቸው ለህልፈት በቅተዋል፡፡ በዚህ የተነሳም የሐኪሞቹ ፈቃድ ለሁለት ወራት ያህል እንዲታገድ ሆኗል፡፡
  3. የተሳሳተ የልብ ዝውውር፡-
  በ2003 በዲውክ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ውስጥ የተደረገው ስህተት ደግሞ ጄሲካ ሳንቲለን እየተባለ ለሚጠራው የ17 ዓመት ልጅ የተደረገና ከደም አይነቱ ጋር የማይሄድና የተሳሳተ የልብ ዝውውር ነበር፡፡ በዚህ የተነሳም የልጁ ሰውነት ወዲያውኑ መስራት አቆመ፤ ከፍተኛ የአንጎል ጉዳትም ደረሰበት፡፡ ይሁን እንጂ ወዲያውኑ በትክክለኛ ልብና ሳንባ ለመተካትና ችግሩን ለማስተካከል ጥረት ቢደረግም ልጁን ከሞት ማትረፍ አልተቻለም፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ሆስፒታሉ የትኛውንም አይነት ዝውውር ከማድረጉ በፊት ሁለት ጊዜ የማረጋገጥ ደንብን ተግባራዊ አድርጓል፡፡
  4. የሁለት ልጆችን ደም ያፈሰሰ መድኃኒት
  በፊልም አክተሩ ዴኒስ ኩይድና ሚስቱ ኪምበርሌዊ ባፊንግተን መንትያ ልጆችን መታቀፋቸው አስደሳች ቢሆንም ከፍተኛ የሚዲያ ትኩረትን የሳበው ግን ልጆቹ ከፍተኛ መጠን ያለውና ሔፓሪን የተባለውን አደገኛ መድኃኒት በስህተት መውሰዳቸውን ተከትሎ ባጋጠማቸው አደጋ የተነሳ ነበር፡፡ እነዚህ መንትያ ህፃናት እንደተወለዱ ላደረባቸው ኢንፌክሽን በደም ስር የሚወሰድ አንቲባዮቲክ ተሰጥቷቸው የነበረ ሲሆን የደም ስራቸው አካባቢ የደም መጓጎል እንዳይፈጠር 10 ዩኒት ሔፓሪን መውሰድ ሲገባቸው ለትልልቅ ሰዎች የሚሰጥ 10,000 ዩኒት ሔፓሪን በስህተት እንዲወስዱ ተደርጓል፡፡ በዚህ የተነሳም ደማቸው በከፍተኛ ደረጃ በመቅጠኑ ከሰውነታቸው ውጭም ሆነ ውስጥ የደም ፍሰት አጋጥሟቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ በሚገርም ገጠመኝ ከ41 ሰዓታት በኋላ ደማቸው መወፈር በመቻሉ ከሞት ተርፈዋል፡፡ ስህተቱ የተፈጠረው በሐኪም የታዘዘውን የልጆች ሔፓሪን አሳስታ የሰጠችው በፋርማሲዋ ምክንያት ነው፡፡ የልጆችም ሆነ የአዋቂዎች ሔፓሪን ብልቃጥ ደግሞ ተመሳሳይ በመሆኑ ነርሷ ልብ እንዳትል አድርጓል ይላል ዘገባው፡፡
  5. እግር እግር የሚል ስህተት
  እጅግ አስገራሚ የተባለውና የ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ግራ አጋቢ ስህተት የተፈጠረው በ52 ዓመቱ ደሊኪንግ ላይ ነበር፡፡ በ1995 በጣም ለተጎዳው እግሩ መቆረጥ እንዳለበት የተነገረው ኪንግ በቀዳጁ ሐኪሙ ስህተት የተነሳ ግን የተቆረጠው ሌላኛው እግሩ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ኪንግ በመጨረሻ ሁለቱንም እግሩን እንዲያጠያ ሆኗል፡፡ ስህተቱ የተፈጠረው ግለሰቡን ለቀዶ ህክምና ዝግጁ እንዲሆን ባደረጉት ነርሶች ነበር፡፡ ለቀዶ ህክምና ዝግጁ እንዲሆንና አስፈላጊው አጠባና ምልክት የተደረገው በጤናማው ላይ በመሆኑ ሐኪሙ በስህተት ሊቆርጡት በቅተዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ፈቃዳቸው ለ6 ወር የታገደ ሲሆን ለኪንግም የ250 ሺህ ዶላር ካሳ ከፍለዋል፡፡ በነገራችን ላይ በእኛም አገር ይህ መሰል ስህተት አጋጥሟል፤ በአዲስ አበባ ውስጥ፡፡
  6. በተሳሳተ ወንድ ያረገዘችው ሴት
  ሁለት ባልና ሚስት በተለመደው የግበረ ስጋ ግንኙነት መውለድ ያልቻሉ በመሆናቸው በልዩ የሰው ሰራሽ አረባብ ቴክኖሎጂ፣ እንዲፀንሱ ወደስነ ተዋልዶ ክሊኒክ ይሄዳሉ፡፡ እነዚህ ባልና ሚስት ቶማስና ናንሲ በመባል የሚጠሩ ሲሆን የሀኪሙ ኃላፊነት ቶማስን የዘር ሕዋስ (sperm) ከናንሲ የዘር ህዋስ (ova) ጋር በብልቃጥ ውስጥ በማደባለቅና ፅንስን እንዲፈጠር በማገዝ በመጨረሻ ወደናንሲ ማህፀን እንዲረገዝ ማዛወር ነበር፡፡ በዚህም ጥበብ ያረገዘችው ናንሲ የወለደቻት ልጅ የቆዳ ቀለሟ ጠይም መሆኑ ግራ አጋባት፡፡ ናንሲም ሆነች ባሏ በዘራቸው ፈረንጅ እንጂ ጥቁር አልነበሩም፡፡ በዚህ የተነሳ የአባትነት የደም ምርመራ (DNA) ለሶስት ጊዜ ሲደረግ በሁሉም ላይ ያሳየው ጄሲካ የተባለችው ህፃን አባቷ የእናቷ ባል አልነበረም፡፡ ማለትም ጄሲካ አንድሪው ልጅ አይደለችም፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያትም ሐኪሙ የናንሲን እንቁላል ሲያዋህድ የተጠቀመው የባሏን ሳይሆን በተመሳሳይ ችግር የመጣን የአንድ ጥቁር ስፐርምን በስህተት በመጠቀም ነበር፡፡ ይህም የሚያሳየው የአንድሪው ስፐርም የጥቁሩን ሚስት አስረግዟል ማለት ነው፡፡ በስህተት የተቀያየሩ ባሎች እንበላቸው ይሆን?
  7. አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ
  ይህ ደግሞ በ84 ዓመቷ አዛውንት ላይ የተደረገ ስህተት ሲሆን በቀዶ ጥገና እንዲወገድ የተወሰነው የሐሞት ከረጢቷ ሆኖ ሳለ ተቆርጦ የተጣለው ግን የቀኝ ኩላሊቷ ነበር፡፡ ይህ የሆነው የላብራቶሪ ውጤቱን አሳስቶ በማንበቡ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ሳይቆረጥ የተተወው የሐሞት ከረጢት በራሱ ጊዜ ድኖ ጤነኛ መሆኑም ሌላኛው አስገራሚ ክስተት ነበር፡፡ መጀመሪያውኑም ቀዶ ጥገና አያስፈልገውም ነበርና፡፡ በዚህ ተነሳም ሐኪሙ ከፍተኛ ካሳ የከፈለ ሲሆን ከዚህ ክስተት በኋላ ያለ ሌላ ሐኪም የበላይ ተመልካችነት ቀዶ ጥገና እንዳያከናውን ታግዷል፡፡
  8. በሆድ ውስጥ የተረሳ መጎተቻ
  በሲያትል በሚገኘው የዋሽንግተን ሜዲካል ሴንተር የተደረገው ስህተት ደግሞ በሆድ ውስጥ ዕጢ ለማውጣት በተደረገ ቀዶ ጥገና 30 ሳንቲ ሜትር የሚረዝም አጋዥ መጎተቻ (retractor) መሳሪያ ሊረሳ መቻሉ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ወዲያው ስህተት መፈጠሩ በመታወቁ መሳሪያው እንዲወጣ ቢደረግም ለታካሚው ግን 97 ሺህ ዶላር ካሳ ከመክፈል አልዳኑም፡፡
  9. በስህተት ራሱን ያጠፋው ግለሰብ
  ሼርማን ሲሞር የተባለ ግለሰብ በከፍተኛ የሆድ ህመም ሲሰቃይ የነበረ ሲሆን ለዚህም ሲባል ሆዱን በግልፅ ለማየትና መነሻውን ለማወቅ ቀዶ ህክምና ይደረግለታል፡፡ ይሁን እንጂ ቀዶ ጥገናው ከተካሄደ እስከ መጀመሪያዎቹ 16 ደቂቃዎች የሰመመን ማደንዘዣ አልተሰጠውም፡፡ ማደንዘዣው ከተሰጠው በኋላ ወዲያው ሊያደነዝዘው ባለመቻሉ ለከፍተኛ ህመም ይጋለጣል፡፡ ይሁን እንጂ በተወሰነ መልኩ ስለደነዘዘ ከሐኪሞቹ ጋር መነጋገርና ስቃዩን ማስረዳት አልቻለም ነበር፡፡ ከሆስፒታል ከወጣ በኋላ ቀዶ ጥገናውን እያስታወሰ በመረበሹ የተነሳ ክፉኛ በመሰቃየቱ ራሱን ሊያጠፋ ችሏል፡፡
  10. ጡት አልባ ያደረገ ውሳኔ
  ዳሪ ኤሰን በመባል የምትጠራ የ35 ዓመት ሴት ጡቶቿ ካንሰር አለባቸው በሚል ምርመራ የተነሳ ሁለቱም እንዲቆረጡ ይታዘዛል፡፡ ይሁን እንጂ ኤሰን አይቆረጡብኝም ብትልም ከሐኪም በላይ አይደለሽም በሚል በመጨረሻ እንዲቆረጡ ይደረጋል፡፡ ይሁን እንጂ ሁለቱም ጡቶቿ ምንም አይነት ካንሰር አልነበረባቸውም፡፡ በዚህ ስህተት የተነሳ ክስ የመሰረተችው ኤሰን ከፍተኛ ካሳ ተቀብላለች፡፡ ጡቶቿንም በንዘቡ ማስመለስ ችላለች፤ ሰው ሰራሽ ጡቶች በማስገጠም፡፡ምንጫቸችን የሳይቴክ ደህረገፅ ነዉ፡፡

  ምንጭ:- ጤናችን

  Read more »

 • ሲያስመልስዎት መወሰድ ያለባቸው የመፍትሄ እርምጃዎች::

                                                

  ማስመለስ በጤና መታወክም ይሁን በሌላ ምክንያት ሊከሰት የሚችል የጤና ችግር ነው።

  የምግብ አለመስማማት፣ የምግብ መመረዝ፣ አዕምሮ ላይ የሚከሰት ጉዳት፣ ከልክ በላይ መመገብ፣ እርግዝና፣ የመድሃኒቶች የጎንዮሽ ጉዳት፣ ከልክ በላይ አልኮል መጠጣት ለዚህ ችግር ይዳርጋሉ።

  ይህ ችግር ሲከሰት ደግሞ ከህክምና በፊት በራስ አቅም መወሰድ የሚገባቸው የመፍትሄ እርምጃዎች ይኖራሉ።

  በጥልቅ መተንፈስ፦ በጣም አየር ወደ ውስጥ እየሳቡ በአፍንጫ በጥልቅ መተንፈስ ሲያስመልስዎ የመኮማተር አይነት ስሜት ላይ የነበረውን ሆድ የተሻለ የመለጠጥ አቅም እንዲያገኝ ይረዳዋል።

  ይህንን በመደጋገምም የሆድ አካባቢ መጨናነቅና መኮማተርን በማስወገድ ነጻ የሆነ ስሜት እንዲሰማው ማደረግ ይቻላል።

  ከመዳፍ በታች ባለው የእጅ አንጓ ላይ የደም ስር አካባቢ ያለበትን ቦታ ጫን በማለት መያዝም ለዚህ መፈትሄ እንደሆነ የቻይና ባህላዊ ህክምና አዋቂዎችን ዋቢ ያደረጉ መረጃዎች ያሳያሉ።

  ለዚህ ሶስት ጣትን በዚህ ክፍል ላይ በማስቀመጥ እና አውራ ጣትን በማስደገፍ እስከ ሶስት ደቂቃ ድረስ በማሸት ይህን ችግር ማስቆም ይቻላል።

  ይህን ማድረጉ ለደቂቃዎች የተስተጓገለውን የደም ዝውውር ስርዓት ለማስተካከልም ይረዳል።

  ዝንጅብልና ቅርፉንድ፦ ይህን በሻይ መልክ በማፍላት መጠቀምም ለዚህ ችግር ሌላው መፍትሄ ነው።

  ይህ ደግሞ በተለይም በእርግዝና ወቅትና በህክምና ወቅት ለሚከሰት የማስመለስ ችግር መፍትሄ መሆኑም ይነገራል።

  ከ5 እስከ 10 ደቂቃ ከሻይ ጋር በማፍላት ዝንጅብሉን መጠቀም፥ እንዲሁም ቅርፉንዱን ከሻይ ጋር በጥቂቱ በማፍላትና በመጠቀም በመፍትሄነት መጠቀም ይቻላል።

  ቅርንፉድ በውስጡ በያዘው ፀረ ባክቴሪያ ንጥረ ነገር አማካኝነት ይህን ችግር ለመቅረፍ ተመራጩ ነው።

  ውሃ መጠጣት፦ ካስመለሰዎት በኋላ አረፍ እያሉ በጥቂቱ ውሃ በብዛት መጠጣት ይኖርብዎታል።

  ከዚህ ባለፈም እንደ አረንጓዴ ሻይ ያሉ መጠጦን አፍልቶ መጠቀምም ይመከራል።

  ሎሚ መምጠጥም ከውሃ በኋላ ቢያደርጉት ይመከራል።

  ከዚህ ባለፈም የሜንት ቃና ያላቸውን ከረሜላዎች መጠቀምም በዚህ ወቅት ከዚያ ስሜት ለመውጣት ይረዳል።

  በቂ እረፍት ማድረግም ሰውነት ያጣውን ጉልበት እንዲያገኝ ይረዳዋል።

  ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ ወደ መድሃኒት ቤት በማምራት ቫይታሚን ቢ6 መግዛትና መጠቀም ቢችሉ መልካም ይሆናል።

  ይህ ምናልባት ማታ አልኮል በማብዛትዎ ምክንያት ካስመለሰዎት ያለውን የራስ ምታትና የመደንዘዝ ስሜት ለመቀነስ ይረዳል።

  ከዚህ በኋላም ቀለል ያለ ምግብ በጥቂቱ በመመገብ ሻይ ነገር መጠጣት ይመከራል።

  ምግብ ለመመገብ ግን እስከ 30 ደቂቃ መጠበቅና እስከዚያው ንጹህ ውሃ መጎንጨትና አረፍ ማለት።

  ከዚያ በፊት የሚወሰድ ምግብ በድጋሚ እንዲያስመልሱ ሊያደርግ ስለሚችል መውሰዱ አይመከርም፤ በተደጋጋሚ ማስመለስ ጨጓራን ለጉዳት ይዳርጋልና።

  ማስመለሱ ተደጋጋሚና የበዛ ከሆነ ደግሞ ሃኪም ዘንድ ጎራ ማለት ይኖርበዎታል።

  ማስመለሱ ከሳምንት በላይ የቆየ ከሆነ፣ ለእርጉዝ ሴቶች፣ ቤት ውስጥ የሞከሩት መንገድ መፍትሄ ካልሆነ፣ ከፍተኛ የሆነ የፈሳሽ እጥረት ሲከሰትና የተለየ ቀለም ያለው ፈሳሽ ከወጣ ወደ ሃኪም መሄድ ይኖርብዎታል።

  ችግሩ ህጻናት ላይ ከሆነ ግን የተመገቡትን ነገር መጠየቅና ማወቅ በተቻለ ፍጥነትም ወደ ህክምና ተቋም ማምራት አስፈላጊ ነው።

  ምንጭ:- ጤናችን

  Read more »

 • ጭንቀት አእምሯችንና ሰውነታችን ላይ ምን አይነት ችግር ይፈጠራል…?

                                               

  ጭንቀት የህይወት ውጣ ውረድ ውስጥ የሚያጋጥም ሲሆን፥ በርካቶቻችንም በተለያዩ ጊዜያት ተጨንቀን እንደምናውቅ እውን ነው።

  ጭንቀት በርካታ መንስኤዎች ሲኖሩት፥ ከምንኖርበት አካባቢ፣ ከሰውነታችን፣ ከምንናገረው ነገር እና ለምንኖርበት ዓለም ያለን አተያይ ጋር ተያይዞ ሊከሰት ይችላል።

  እንደ ፈተና ያሉ ነገሮች በሚያጋጥሙን ጊዜ ጭንቀት ተፈጥሯዊ ነገር ሲሆን፥ ሆኖም ግን በስነ ልቦናችን ጭንቀቱን የመቋቋም እና ምላሽ የመስጠት አቅምን ተፈጥሮ ለግሳናለች።

  ጫና ውስጥ ገብተን የጭንቀት ስሜት በሚሰማን ጊዜ የነርቭ ስርዓታችን ሰውነታችን የጭንቀት ሆርሞን የሆኑትን “አድሬናይል፣ ኖራድሬላይን እና ኮርቲሶል” እንዲለቅ ትእዛዝ ያስተላልፍለታል።

  ይህም ስነ ልቦናዊ ለውጥ እንዲመጣ በማድረግ በጭንቀት ምክንያት ሊከሰትብን የሚችለውን ጉዳት ለመመከት የሚያስችል ሲሆን፥ “የጭንቀት ምላሽ” ተብሎ ይነገራል። 

  ለጭንቀት ምላሽ የሚሰጠው የአካላችን ክፍል ሁሌም ንቁ ከሆነ፥ ጭንቀት ለምንሰራው ስራ ትኩረት እንድንሰጥ እና በተነሳሽነት እንድነሰራ ስለሚያደርግ ጠቀሜታ እንዳለው ይነገራል።

  ጭንቀት በሰውነታችን ላይ የሚያስከትለው የጤና እክል…

  ጭንቀት በተደጋጋሚ የሚከሰትብን ከሆነ እና ስሜቱ ለረጅም ሰዓት የሚቆየበን ከሆነ ወይም ደግሞ መጥፎ የሆነውን ስሜት ሰውነታችን መቆጣጣር ካቃጠው በዚህ ጊዜ ችግር እንደሚፈጠር ይነገራል።

  የነርቭ ስርዓታችን ለተከሰተብን የጭንቀት ስሜት ምላሽ መለቆጣጠር በሚል በተከታታይነት ምላሽ በሚሰጥበት ጊዜ ከፍተኛ ላብ ሰውነታችንን ሊያጠምቅ ይችላል።

  የመተንፈሻ አካል ላይ ጉዳት ያስከትላል፦ አብዝተን ስንጨነቅ ጠንከር ያለ እና ፍጥነት የተሞላበት አተነፋፈስ ይስተዋልብናል፤ ይህም ኦክሲጅን በብዛት እና በፍጥነት በደማችን ውስጥ እንዲሰራጭ ያደርጋል ተብሏል።

  ከዚህም በላይ እንደ አስም ያሉ የመተንፈሻ አካል የጤና እክል ላላቸው ሰዎች ላይም ጭንቀት የበለጠ ጉዳት ያስከትላል ነው የተባለው።

  የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅምን ያዳክማል፦ አብዝተን በምጨነቅበት ጊዜ የነርቭ ስርአታችን ጭንቀቱን ለመቆጣጣር የሚለቀው ኮርቲሶል የተባለ ሆርሚን የሰውነታችን በሽታ የመከላከል እቅም ላይ ጫና ያሳድራል።

  በዚህ ጊዜም ለኢንፌክሽኖች እና ለሌሎች የበሽታ አይነቶች የመጋለጥ እድላቸውን የሚጨምር ሲሆን፥ ሰውነታችን በሽታን ለመከላከል የሚያደርገው ጥረትም ይዳከማል ነው የተባለው።

  የልብ ጤንነት ላይ ችግር ያስከትላል፦ ጭንቀት በበዛ ቁጥር የልባችን ጤንነት ላይ እከል እንደሚፈጥርም ተነግሯል።

  የጭንቀት ስሜት በሚሰማን ጊዜ የልብ ምታችን እና የደማችን ዝውውር ፍጥነት የሚጨምር ሲሆን፥ ጭንቀቱ በሚወገድልን ጊዜ ሁሉም ወደ ነበረበት ቦታ ይመለሳል።

  ሆኖም ግን ጭንቀቱ በዘላቂነት ለረጀም ጊዜ የሚቆይብን ከሆነ የደም ቧንቧዎቻችን ላይ ጎዳት የሚያስከትል ሲሆን፥ይህም ለድንገተኛ የልብ ህመም፣ ለከፍተኛ የደም ግፊት እና ለስትሮክ የመጋለጥ እድላችንን ከፍ ያደርገዋል ተብሏል።

  የጨጓራ ህመም ሊያስከትል ይችላል፦ አብዝቶ መጨነት ለጨጓራ ህመም ሊዳርገን እንደሚችለም ተነግሯል።

  የመራቢያ ስርዓት ላይ እክል ይፈጥራል፦ አብዝቶ መጨነቅ ወንዶች ላይ የቴስቴስትሮን እና የወንድ ዘረ የማመንጨት ሂደትን ይጎዳል የተባለ ሲሆን፥ እንዲሁም ስንፈተ ወሲብ እና የብልት አለመቆምን ሊያስከትል እንደሚችልም ይነገራል።

  ጭንቀት በሴቶች ላይም የወር አበባ ኡደትን እንዲዛባ ያደርጋል የተባለ ሲሆን፥ የወር አበባ በሚመጣ ጊዜ የሚሰሙ የህመም ስሜቶች እንዲጨምሩ ያድረጋልም ተብሏል።

  ጭንቀት እና አእምሯችን…

  አብዝቶ መጨነቅ “ሀይሬራሮዡዋል” የተባለ እክል ሊያስከትልብን የሚችል ሲሆን፥ ይህም እንቅልፍ ቶሎ አለመተኛት፣ ለረጅም ሰዓት መተኛት አለመቻል እና በድካም የተሞላ ምሽትን ማሳለፍ ነው።

  ይህም ነገሮች ላይ ትኩረት የመስጠት፣ የመማር እና የማስታወስ አቅማችን ላይ ችግር ሊፈጥር እንደሚችል ነው የተነገረው። 

  ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

  Read more »

 • ፎሮፎርን በቤት ውስጥ እንዴት መከላከል ይቻላል

                                                           

  1.የወይራ ዘይትን መቀባት
  2.አንድ የክዳን ሰሀን የፖም አቼቶን ከ3 የሻይ ማንኪያ የሎሚ ጭማቂ እና ከ3 የሻይ ማንኪያ ቤኪንግ ሶዳ ጋር በማዋሃድ መቀባት እና ለ10 ደቂቃ ቆይቶ መታጠብ
  3.በቅድሚያ ፀጉርዎን ይታጠቡ በመቀጠል እርጎን መቀባት እና ለ15 ደቂቃ ቆይቶ መታጠብ
  4.ሁለት የእንቁላል አስኳል መቀባት እና በላስቲክ በመሸፈን ለአንድ ሰአት መቆየት እና መታጠብ ሽታው ቶሎ ሊለቅ ስለማይችል ደጋግሞ መታጠብ ተገቢ ነው
  5.ነጭ ሽንኩርት እና ማርን በደንብ በማዋሀድ መቀባት እና ለ15 ደቂቃ ቆይቶ መታጠብ
  6.የፖም ጭማቂን ከውሃ ጋር በማዋሀድ መቀባት እና ለ15 ደቂቃ ቆይቶ መታጠብ
  7.የጉሎ ዘይትን መቀባት እና ማሳደር ጠዋት ላይ መታጠብ
  8.የአሳ ዘይት መቀባት
  9.ፀጉርን ከመታጠብ በፊት በአጋባቡ ማበጠር የፎሮፎርን መጠን ይቀንሳል
  10. የፀጉርን ንፅህና በአግባቡ መጠበቅ
  11.ማበጠሪያ ፣ ቢጎዲን እና ሻሽ የመሳሰሉትን በጋራ አለመጠቀም
  12.በሚዋኙበት ወቅት የዋና ኮፍያ(shower cape) ይጠቀሙ

  Read more »

 • በብቸኝነት እንዴት መኖር ይችላሉ?

  ይብዛም ይነስ የሰው ልጅ በህይዎት እያለ የብቸኝነት ስሜት ማስተናገዱና የተወሰኑ ጊዜያቶችንም በብቸኝነት ማሳለፉ አይቀሬ ነው።

  ከቤተሰብ ተነጥሎ ለስራ አልያም በሌላ አጋጣሚ ከቤተሰብ መራቅ፣ ከአብሮ አደግና ከልጅነት ጓደኛ በህይዎት አጋጣሚ መነጠልና መለየት እንዲሁም መሰል አጋጣሚዎች ለብቸኝነት ሊዳርጉ ይችላሉ።

  የስነ ልቦና ባለሙያዎችም ብቸኝነት የሰው ልጅ አንዱ የህይዎት ገጽታ የመሆን አጋጣሚው የሰፋ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ይህን አጋጣሚ መቀበልና መላመድ እንደሚገባ ይገልጻሉ።

  ከዚህ አንጻርም አጋጣሚው እስከሚገኝ ድረስ ብቸኝነትን ከመጋፋት አምኖና ተቀብሎ መኖርን ይመክራሉ።

  ከብቸኝነት ጋር አብሮ ለመኖርና ስሜቱን ለመቀበል ደግሞ የሚከተሉትን መንገዶች ይጠቅሳሉ፤

  የአጭር ጊዜ መፍትሄ አለመውሰድና ራስን ማሳመን፦ አንዳንድ ጊዜ ብቸኝነትን ለማምለጥና የአጭር ጊዜ መፍትሄ ከመፈለግ አንጻር አላስፈላጊ ስሜት ውስጥ በመግባት የማይጠቅሙ እርምጃዎችን መውሰድ ይስተዋላል።

  አብዝቶ መጠጣትና ራስን በዚያ አጋጣሚ የመደበቅ አዝማሚያዎች ደግሞ በዚህ ወቅት የሚስተዋሉ አጋጣሚዎች ናቸው።

  ይህ ግን ራስን ለከፋ ጉዳት ከመዳረግና ከመሸነፍ ውጭ ሌላ መፍትሄ አያመጣም፥ ከዚያ ይልቅ የአጭር ጊዜ መፍትሄውን በመተው ያንን ህይዎት መላመድና ራስን ማሳመኑ መልካም ነው።

  የሚኖሩትን ህይዎት አምነው በመቀበል ወደውት ሲኖሩት ዘለቄታዊ ደስታና የአዕምሮ እረፍትም ያገኛሉና ነገሩን አምኖ መቀበልና መላመድን ይምረጡ።

  ባይመችዎትም እስካሉ ድረስ አምኖ መቀበል ከራስም ሆነ ኬሎች ጋር ተስማምቶና ተግባብቶ ለመኖር ቁልፉ ነውና ይጠቀሙበት።

  አጋጣሚውን መጋፈጥ፦ በልጅነት እያንዳንዱ እንቅስቃሴ በሌሎች ላይ በተለይም ቤተሰብ ላይ የተመሰረተና የተወሰነ ነበር።

  በዚያ ወቅት ለመመገብ፣ ለመጠጣትና ለመጫዎትም ሆነ ለመዝናናት የሌሎችን እርዳታ መሻትና መጠበቅ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል።

  ባለሙያዎቹ በልጅነት ዘመን የሚሰማ ብቸኝነት በወጣትነት ዘመን በህይዎት አጋጣሚ ከቤተሰብ ሲለዩ ሊከሰት እንደሚችል ያነሳሉ።

  በዚህ ወቅት ከቤተሰብ፣ ከፍቅረኛ፣ ከቅርብ ጓደኛና ወዳጅ ጋር ሊራራቁ እና በልጅነት ጊዜ ይሰማዎት የነበረው የብቸኝነት ስሜት ተመልሶ ሊመጣና ብቸኛ እንደሆኑም ሊያስቡ ይችላሉ።

  ይህ ግን ብቸኝነትን ከመፍራትና በቤተሰብና ጓደኛ ተከቦ መኖርን ከመፈለግ የመነጨ እንጅ ያን ያክል አስጨናቂና አስፈሪ አጋጣሚ አለመሆኑን ይገልጻሉ።

  በዚህ ወቅት እንደ ልጅነት ጊዜ ማሰብ ሳይሆን እንደ ትልቅ ሰው በርካታ አማራጮች እንዳሉ ማሰብና ራስዎን እንደቻሉ ማስታወስም ይገባወታል።

  ከዚህ አንጻርም እንደልጅነት ዘመን ብቻየን ነኝና ድረሱልኝ ሳይሆን፥ ብቸኝነትዎን መላመድና በምን መልኩ ህይወቴን መምራት አለብኝ በማለት ፈተናውን ለመወጣት መዘጋጀት ይኖርብዎታል።

  ለምን ብሎ አለመጠየቅ፦ አብዛኛዎቹ ራሳቸውን ብቸኛ ሆነው ሲያገኙት፤ ለምን ብቸኛ ሆንኩ? እና ለምን የብቸኝነት ስሜት ይሰማኛል? የሚል ጥያቄ ራሳቸውን ይጠይቃሉ።

  አንድ ነገር ከሆነ በኋላ ለምን የሚል ጥያቄ ራስን መጠየቅ ግን መፍትሄ ማግኛ መንገዶችን የሚያጠብበት አጋጣሚ ሰፊ ስለመሆኑም ይነገራል።

  ለምን ብለው መጠየቅ ሲጀምሩ ራስን መውቀስና አላስፈላጊ ቁጭት ውስጥ የመግባት አጋጣሚዎም የሰፋ ይሆናል።

  ለምን የሚል ጥያቄን በደጋሙ ቁጥርም ለነገሮች ወሰን በማበጀት ሰፋ ያለውን አማራጭ እንዳያስተውሉም ያግድዎታል፤ ከዚህ ባለፈም ከጉዳዩ ጋር የማይገናኙ ነገሮችን ፍለጋ ላይ እንዲያተኩሩም ሊያደርግዎት ይችላል።

  ይህን ጥያቄ በጠየቁ ቁጥርም የከፋ ስሜትን እንዲሰማዎት በማድረግ ነገሩን ከመቀበል ወደ መቃወም እንዲያመሩና ምናልባት መፍትሄ አልባ ያደርግዎታል።

  ከዚያ ይልቅ ምን ተፈጠረ? ከሆነው ነገር ምንስ አገኘሁ? በቀጣይስ ምን ያጋጥመኛል? ብሎ መጠየቁን የተሻለ መሆኑንም ነው ባለሙያዎች የሚመክሩት።

  ምክንያቱም ይህን ሲጠይቁ ለችግሩም ሆነ ለጠየቁት ነገር አዳዲስ ነገሮች በማግኘት ሰፋ ያሉ እይታዎች እንዲኖርዎት ያግዛልና።

  ስሜቱን እንደ ህይዎትዎ አንድ ክፍል መቀበል፦ ሁልጊዜም ቢሆን ህይዎት ላይ የሚከሰቱ ለውጦች ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ለብቸኝነት መዳረጋቸው አይቀሬ ነው።

  ከዚህ ቀደም የለመዱትን ህይዎት በመተው አዲስ ህይዎትን ለመጀመር ሲያስቡ ጀምሮ የብቸኝነት ስሜት ይከሰታል።

  አዲስ የሚገጥምዎትን ህይዎትና የአካባቢውን አጠቃላይ ሁኔታ ለማወቅ ከመጨነቅ አንጻር ለብቸኝነት ስሜት መዳረግዎም አይቀርም።

  እንዲህ ባለ ስሜት ራስን ማስጨነቅና ባልተገባ ስሜት ውስጥ መቆየቱ ግን ብዙም አስፈላጊ አይደለም፥ ከዚያ ይልቅ አጋጣሚውን የህይዎት አካል አድርጎ ማስቀጠል የተሻለው አማራጭ ነው።

  ዘወትር ህይዎትዎን በተለያዩ አቅጣጫዎች እንደሚመሩ ማሰቡም መልካም መሆኑን ያስረዳሉ የስነ ልቦና ባለሙያዎች።

  የመጣውን አምኖ መቀበል በሄዱበት ሁሉ ምቹ ከባቢን ለመፍጠርም ያግዛልና በዚያ መልኩ ህይዎትዎን ለመምራት ይሞክሩ።

  ከዚህ ጋር ተያይዞም ብቸኝነትን ከፍቅረኛዎም ቢለዩ እንኳን ሁኔታው የተለመደ እንደሆነ በማሰብ መቀበል ይገባዎታል።

  የመለየት ስሜት አንዳንድ ጊዜም ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ የሚመጣና ሊከሰት የሚችልበት አጋጣሚም ስላለ፥ ይህን አጋጣሚ ቀለል አድርጎ ማየትን መልመዱ መልካም መሆኑን ነው የስነ ልቦና ባለሙያዎች የሚያነሱት።

  በዚህ ወቅት ራስን ማግለል ሳይሆን በአካባቢዎ ካለ ማህበረሰብ ጋር መቀራረብ።

  ከወዳጅዎ ርቀው ሰው ሲቀርቡም የተፈጠረብዎትን ብቸኝነት መራቂያና መደበቂያ ለማድረግ ሳይሆን፥ ሰዎኛ ባህሪ ከመሆኑ አንጻር በብቸኝነት እንዳይጎዱ መሆን አለበት።

  ይህን መሰሉ ማህበራዊ መስተጋብር ዘወትር ብቸኛ ነኝ እያሉ የፍቅረኛዎን እገዛ ሳይጠብቁና ሳይፈልጉ ተራርቀውም ቢሆን መኖር መቻልዎን ማሳያ ነው።

  ሁሉም ብቸኝነት እንደሚሰማው ያስቡ፦ ይብዛም ይነስ ሁሉም ሰው የብቸኝነት ስሜት እንደሚሰማው ማስታወስ ይኖርብዎታል።

  በብቸኝነት ስሜት ብቻዎን እንዳልሆኑ ማሰብ ሲጀምሩ፥ በዚህ ስሜት እንደተጎዱ በማሰብ ራስዎን ከማህበረሰቡ የማግለል ስሜትዎ እንዲቀንስና ከሌሎች ጋር እንዲተሳሰሩ ይረዳወታል።

  በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት መጠኑ ይለያይ እንጅ አብዛኛው የሰው ልጅ በርካታ የሚጋራቸው ስሜቶች እንዳሉት ማስታወስም ይገባል።

  ይህ ደግሞ ለአብሮነትና ለአንድነት ስሜቱ መልካም ነውና ብቻየን አይደለሁም ብለው ያስቡ፤ ያንኑ ህይዎትም ይኑሩት።

  በዚህ ስሜት የተጠቁ ከሆነና ምናልባት ከተቸገሩ በአካባቢዎ በሚገኙ የማህበረሰብ አቀፍና መሰል ማህበራት ጎራ በማለት ከሰዎች ጋር ይገናኙ።

   

  ምንጭ:- ጤናችን

   

  Read more »

 • የዓለም ጡት የማጥባት ሳምንት

                                                             

  “ጡት የማጥባትን ባሕል በጋራ ዘላቂ እናድርግ!” በሚል መሪ ቃል ከሐምሌ 25 እስከ ነሐሴ 1 ቀን 2009 ዓ.ም እየተከበረ ነው፡፡

  የጡት ማጥባት ቁልፍ መልዕክቶች፡-
  1. ልጅዎን እንደ ወለዱ ወዲያውኑ በአንድ ሰዓት ውስጥ ጡትዎን ማጥባትዎ፡-
  ጡትዎ በደንብ ወተት እንዲያመነጭ ከወሊድ በኋላ የሚከሰትን የደም መፍሰስ ይቀንሳል፡፡
  2. የመጀመሪያውን ቢጫ መሰል የጡትዎን ወተት /እንገር/ ለልጅዎ ማጥባትዎ፡-
  እንገሩ ለሕጻኑ የሚያስፈልገውን የበለጸገ ንጥረ-ምግብ በበቂ ሁኔታ የያዘ በመሆኑ የሕጻኑን በተፈጥሮ በሽታ የመከላከል አቅሙን ያዳብርለታል፡፡ በተጨማሪም የሕጻኑን አንጀት በማለስልስ የመጀመሪያው አይነ ምድር እንዲወገድ ያደርጋል፡፡ 
  3. ልጅዎ መጥባት በፈለገ ጊዜ ሁሉ ያጥቡት፡፡ ቀንና ማታን ጨምሮ ከ10-12 ጊዜ ያጥቡት፡፡
  ይህን ማድረግዎ ጡትዎ በቂ ወተት እንዲያመነጭና እንዲያፈስ/እንዲዎጣና በእናትና በልጅ መካከል የሚኖረውን ፍቅር ያደረጃል
  4. ልጅዎን በሚያጠቡበት ጊዜ በአግባቡ ማቀፍና ጡትዎን ማጉረስ ያስፈልጋል፡፡
  ይህን ማድረገዎ ህጻኑ በደንብ ጡት እንዲስብና ምቾት እንዲሰማው ከማድረጉም በላይ የጡትዎ ጫፍ እንዳይሰነጠቅና እንዳይቆስል ይረዳል፡፡
  5. ልጅዎን ጡት ሲያጠቡ አንዱን ጡት ባዶ እስኪሆን ካጠቡ በኋላ ሌላውን ጡትዎን ያጥቡ፡፡
  ምክንያቱም ቀድሞ የሚወጣው ቀጭን ወተት የህጻኑን የውሀ ጥም/ ፍላጎት የሚያረካ ሲሆን በኋላ የሚመጣው ወፍራም ወተት ደግሞ የምግብ ፍላጎቱን የሚያሟላ በመሆኑ ነው
  6. ልጅዎ ስድስት ወር አስኪሞላው ድረስ ከጡት ወተት ሌላ ምንም ዓይነት ተጨማሪ ነገር አይስጡ፤ ውኃም ቢሆን፡፡
  - የጡት ወተት ለሕጻኑ እድገትና ጤንነት የሚያሰፈልገውን በቂ ውሃና ምግብ የያዘ ነው፡፡
  - ለሕጻኑ ውሃ ወይም ሌላ ፈሳሽና ምግብ ቢሰጡ ለተቅማጥና መሰል በሽታዎች ያጋልጠዋል፡፡

   

  ምንጭ:- ጤናችን

   

   

  Read more »

Advertisment