PLANET ETHIOPIA.com

Lifestyle አኗኗር


 • የኢትዮጵያ ገና ለምን ታህሳስ 29 ይከበራል? - Why Ethiopian Celebrate Ethiopian Christmas on January 7?

                                                                      

  የአውሮፓውያንን የጊዜ ቀመር በሚከተሉ ሃገራት የክርስቶስ ልደት ዲሴምበር 25 (ታህሳስ 16) ይከበራል። ኢትዮጵያዊንን ጨምሮ ከ10 በላይ ሃገራት ደግሞ ከ12 ቀናት በኋላ ታህሳስ 29 ያከብራሉ። ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ ስንል የኃይማኖት ሊቃውንትን ጠይቀናል።

  "የጎርጎሮሳውያን የዘመን አቆጣጠር ያመጣው ፍልሰት"

  የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን የዘመን አቆጣጠር ከአውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር የተለየ ነው።

  አንደኛ ሰባት ዓመት ከስምንት ወር ከአስር ቀን ልዩነት አለ። ሁለተኛ እያንዳንዱ ወር የሚይዛቸው ቀናት ልዩነት አላቸው። ''በእያንዳንዱ ወር ውስጥ ከስድስት እስከ አስር ቀናት የሚደርሱ ልዩነቶች አሉ'' ይላሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን የዘመን ቀመር (ባህረ ሃሳብ) ዙሪያ መጽሃፍ ያሳተሙት መጋቤ ጥበብ በእምነት ምትኩ ።

  "የጎርጎሮሳውያኑ የዘመን አቆጣጠር እስከተጀመረበት ድረስ መላው ዓለም ተመሳሳይ የዘመን አቆጣጠር እንደነበረው ይታመናል"የሚሉት መጋቤ ጥበብ በእምነት" ነገር ግን በ1382 ዓ.ም የካቶሊክ ቤተክርስትያን ጳጳስ የነበረው ጎርጎሪዮስ የዘመን አቆጣጠሩ ችግር አለበት በሚል እንደገና እንዲሰላ ወሰነ። ከዚያም በአንድ ዓመት ውስጥ 365 ቀን ከ6 ሰዓት ነው ያለው የሚለውን ሃሳብ በማንሳት በየዓመቱ አንድ አንድ ሰዓት ተጨምሮብናል'' ይላሉ።

  ስለዚህ እንደ መጋቤ ጥበብ በእምነት ይህ አንድ ሰዓት ተጠራቅሞ መጨመር አለበት በማለት ከኒቂያ ጉባኤ ጀምሮ ያለውን አስልቶ በማሳሰብ 10 ቀን በመሙላቱ ኦክቶበር 5 የነበረውን ኦክቶበር 15 ነው ሲል አውጇል።

  "ስለዚህ በእኛና በእነሱ መካከል እየቀነሰ የሚሄድ ቢሆንም የ10 ቀን ያህል ልዩነት አለን።"

  እንግዲህ የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ከኖህ ዘመን ጀምሮ የነበራትን የቀን አቆጣጠር ጠብቃ ይዛ የቀጠለችና ምንም ነገር ያላሻሻለች በመሆኑ የነበረው እንዳለ ነው ሲሉ ያስረዳሉ።

  "በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ብቻ ሳትሆን የግብፅ ቤተክርስትያንም ምንም አይነት ማሻሻያ አላደረገችም።''

  "ዘመን በአንድ ክብ ላይ አንድ ነጥቡን መነሻ አድርጎ ክቡን የመቁጠር ሂደት ነው" የሚሉት ደግሞ መጋቢ ሰለሞን አበበ ገ/መድህን ናቸው ።

  ዘመን መቁጠር የጀመረው ክርስትናው አይደለም የሚሉት መጋቢ ሰለሞን ክርስትናው ከመጣ በኋላ ታላቁን ክስተት የጌታን የኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ መነሻ አደረጉ ብለዋል።

  "ይህም በአንድ ክብ ላይ የትኛው ነጥብ ላይ ሄጄ ነው መቁጠር የምጀምረው እንደማለት ነው። ምክንያቱም ዞረው በሚገጥሙ በማያቋርጡ ተፈጥሯዊ ሁኔታዎች የምድርን ዙረት መሠረት አድርጎ ዘመናችን ስለሚለዋወጥ ነው የምንቆጥረው።"

  ስለዚህ እንደ መጋቢ ሰለሞን በጁሊያን አቆጣጠር ለቆጠራ እንዲመቸውና እንዲሞላለት በዘፈቀደ ያስገባቸው ወደ 44 ደቂቃ እና 56 ቁርጥራጭ ሰከንዶች ተጨምረዋል።

  "በኋላ ላይ ጎርጎሪዮስ ሲያርመው ከዓመታት በኋላ ተጠራቅመው እነዛ ድቃቂዎች አስር ተጨማሪ ቀናት ወልደው ተገኙ።"

  ጎርጎሪዮስ እነዚህ አስር ቀናት ከናካቴው ተጎርደው ይውጡ የሚል አቋም ወሰደ ሲሉ ያስረዳሉ መጋቢ ሰለሞን።

  እርማቱ ሲካሄድ ለጊዜው በዓመት፣ በአስር ዓመት የማይታሰቡ ቁርጥራጭ ደቂቃዎች ቀን በመውለዳቸው ልዩነቱ እንደፈጠረ የሚናገሩት መጋቢ ሰለሞን "እኛ እንግዲህ የጁሊያን ሳይታረም የቀረውን ይዘን በመሄዳችን በወራቱ ላይና በቀናቱ ላይ አስርም ስምንትም እንዲሁም በዓመታቱ ላይ ልዩነቶችን እየፈጠረ መጣ። ስለዚህ የመጀመሪያው ልዩነት ሲታረም የታረመውን አለማካተታችን ነው።"

                                                                            

  የክርስቶስ ልደት መጽሐፍ ቅዱሳዊና ታሪካዊ መሠረቶች

  እንደ መጋቤ ጥበብ በእምነት የአውሮፓውያኑ የቀን አቆጣጠር መሠረት ያደረገው በ735 ዓ.ም የተከሰተውን የሮም መቃጠልን ነው። "ከዛ ተነስተው ነው የአዲስ ኪዳን ዓመተ ምህረታቸውን የቀመሩት።"

  የኢትዮጵያ ቤተ-ክርስትያን ግን እንዲህ ዓይነት ክስተቶችን መሠረት እንዳላደረገች የሚናገሩት መጋቤ ጥበብ በእምነት ምክንያቱ ደግሞ እንዲህ ዓይነት ክስተቶች የዓመት ልዩነት ሊፈጥሩ ስለሚችሉ እንደሆነ ይገልፃሉ።

  "የኢትዮጵያ ቤተ-ክርስትያን ለልደተ-ክርስቶስ መነሻ የምታደርገው መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ይኸውም የሉቃስ መጽሐፍ ምዕራፍ አንድ ላይ ቅዱስ ገብርኤል በስድስተኛው ወር ወደ ድንግል ማርያም ተላከ ይላል። ስድስት ወር ማለት ከዛ በፊት አንድ ታሪክ አለ ማለት ነው።"

  "በዚያው ምዕራፍ ላይ ቅዱስ ገብርኤል ወደ ዘካርያስ ሄዶ ዮሐንስ እንደሚፀነስ ብስራት ነግሮታል። የዮሐንስ ፅንሰት ከተከናወነ ከስድስተኛው ወር በኋላ ቅዱስ ገብርኤል ወደ እመቤታችን ሄደ ማለት ነው።"

  "ስለዚህ የጌታ ልደት መነሻ የሆነው የዮሐንስ ፅንሰት ወይም ልደት ነው። ዮሐንስ ደግሞ መቼ ነው የተፀነሰው የሚለውን ስናይ ዘካርያስ በቤተመቅደስ ገብቶ ያጥን ነበር ይላል። ይህ ሥርዓት ደግሞ በዓመት አንዴ የሚፈፀም ነው።"

  እንደ መጋቤ ጥበብ በእምነት ያንን ጊዜ ለማወቅ ደግሞ ብሉይ ኪዳን ላይ ዘካርያስ ገብቶ ቤተ መቅደሱን ያጠነበት ቀን በሰባተኛው ወር ከቀኑም በአስረኛው ቀን ነው (ዘሌ 16፥29፣ ዘሌ 23፥27 ) የሚለውን ማየት ያስፈልጋል።

  በተጨማሪም የአይሁዳውያን የቀን አቆጣጠር ደግሞ የሚጀምረው ከመጋቢት ነው። ከዚያ ተነስተን መስከረም ድረስ ስንቆጥር ሰባተኛው ወር ላይ እንደርሳለን። ስለዚህ ካህኑ ለሕዝቡ ስርየተ-ኃጢዓት የሚለምነው በመስከረም ወር ነው ማለት ነው ይላሉ መጋቤ ጥበብ።

  "ስለዚህ በቤተክርስትያናችን የብስራቱ ቀን መስከረም 27 ነው። ከዛ በኋላ ደግሞ ከሦስት ቀናት በኋላ ለሚስቱ ሄዶ ነግሯት ዮሐንስ ተፀነሰ። ከዚህ ከስድስት ወር በኋላ ቅዱስ ገብርኤል ወደ እመቤታችን የሄደበትን ቀን ስንቆጥረው መጋቢት 29 ቀን ይሆናል። ከዛ ደግሞ ተነስተን ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ስንቆጥር ታህሳስ 29 ላይ እንደርሳለን" ይላሉ።

  የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት መቼ ነው በትክክል መከበር ያለበት? የሚለውን ለመመለስ ቤተ-ክርስትያን በይፋ በሚታወቅ መልኩ ልደቱን ማክበር የጀመረችው መቼ ነው? የሚለውን ማየት አስፈላጊ እንደሆነ ደግሞ መጋቢ ሰለሞን ይናገራሉ።

  ቅዱስ መጽሐፍ የጌታን ልደት እንጂ የተወለደበትን ቀን አይነግረንም የሚሉት መጋቢ ሰለሞን በይፋ የተመዘገበ ታሪክ የምናገኘው በ4ኛው ምዕተ-ዓመት ላይ ነው ይላሉ።

  "አንዳንዶች በሦስተኛው ምዕተ-ዓመትም የመከበሩ ምልክቶች አሉ የሚል ዘገባ ያቀርባሉ። ይህ ከሆነ በዚህ የቀን ፍለጋው ውስጥ አሁንም ልዩነቶች ተፈጥረዋል።"

  የተለያዩ ምሁራን የቀን ቆጠራን ለማካሄድ ባህረ-ሃሳብም ሆነ ጎሪጎሪያውያን ወደ ኋላ ሲሄዱ ስህተት መፈፀማቸውን የሚናገሩት መጋቢ ሰለሞን፤ ከዛ ይልቅ ከኢየሱስ ልደት ጋር ያለውን ቀን ለመለየት መጽሐፍ ቅዱስን መመልከት ይሻላል ይላሉ።

  ኢየሱስ በተወለደ ጊዜ የነበሩ ምልክቶች የታላቁ ቄሳር መኖር፣ የሕዝብ ቆጠራ እንዲካሄድ ማዘዙ፣ የኮከቡ መታየት (ስነ-ከዋክብት ተመራማሪዎች ወደ ኋላ ሄደው አንዲመረምሩ ስለሚያስችላቸው)፣ በይሁዳ ላይ ሄሮድስ የሚባል ንጉስ መኖሩ፣ ጴንጤናዊው ጲላጦስ በሮም ላይ ገዢ ሆኖ መሾሙ፣ እነዚህ ታሪካዊ ክስተቶችን ከመፅሐፍ ቅዱስ ውጪ ካሉ ሰነዶች ጋር አያይዘን ካየን ሁለቱም የዘመን አቆጣጠሮች ወደኋላ ተሄዶ ሲመረመሩ ስህተት አለባቸው ሲሉም ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ።

  "በጎሪጎሪዮሳውያኑ 7 ዓመት ወደ ኋላ፤ በእኛ ደግሞ 15 ዓመት ወደኋላ ተመልሶ ነው የታሪካዊ ሁነቶች የተከሰቱት የሚሉ ጥናቶች ወጥተዋል" ይላሉ መጋቢ ሰለሞን።

                                                                  

  የኢትዮጵያ ወንጌላውያንና ካቶሊኮች

  እንደ መጋቢ ሰለሞን ከሆነ የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን ክርስትያኖች ልደት፣ ሞትና ትንሳዔን አበይት በዓላት አድርገው የሚቆጥሩ ናቸው።

  "በኢትዮጵያ ውስጥ ቀደምት ክርስትና ነበር። ቀዳሚውም ክርስትና ወደ 2000 ዓመት ኖሯል። ይህ ሃገር የክርስትና ውርስና ቅርስ አለው" ይላሉ።

  "...ምንም እንኳ ወንጌል አማኞች በአንዳንድ አስተምህሮዎች እና ትውፊታቸው ከቀዳሚቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስትያን ቢለዩም ነገር ግን የጌታን ልደት በማክበሩ ላይ ያንኑ የቀዳሚውን ይዞ መሄዱን መርጠዋል" ሲሉም ያስረዳሉ።

  ምክንያታቸው ደግሞ የትኛውንም ለመምረጥ ምንም የተለየ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የለም የሚል ነው። "ይልቁንም ትውፊትን ነው የመረጥነው ማለት ነው" ብለዋል።

  የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስትያን በሄደችበት ሃገር ያለውን ባህል እና አካሄድ በመከተል የእምነት ስብከቷን እንደምታካሂድ የሚናገሩት መጋቤ ጥበብ በእምነት፤ በዚህ የተነሳም የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስትያን የተለየ የቀን አቆጣጠር አትከተልም ብለዋል።

  ምንጭ: ቢቢሲ

  Read more »

 • የግሉ ዘርፍ ሠራተኞች ለመውለድ ምን ያህል ይጠብቁ? - Private Company Female Employees and Pregnancy

  የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ረቡዕ ህዳር 26 ቀን 2010 ዓ.ም ባካሄደው የሶስተኛ ዓመት 7ኛ መደበኛ ስብሰባ የተሻሻለውን የመንግሥት ሠራተኞች አዋጅ በማፅደቅ የመንግሥት ሰራተኞችን የወሊድ ፈቃድ ከሦስት ወደ አራት ወር ከፍ እንዲል አድርጓል።

  አዋጁ በብዙዎች እሰይ የተባለለት ቢሆንም የአዋጁን መፅደቅ ተከትሎ በግሉ ዘርፍ ያሉ እናቶችስ? የሚል ጥያቄ እየተነሳ ነው።

  አንድ አገር ላይ እየሰሩና እኩል ግብር እየከፈሉ እንዴት የዚህ ዓይነት ልዩነት ይኖራል በሚል አስተያየታቸውን የሰነዘሩ ብዙዎች ናቸው።

  በግሉ ዘርፍ ያሉ ሴቶችን ጉዳይ በተመለከተ ከቢቢሲ ጥያቄ የቀረበላቸው የፌደራል የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ሚኒስቴር ህግ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ተክይበሉ በግሉ ዘርፍና በመንግሥት በጀት በማይተዳደሩ የልማት ድርጅቶች የአሰሪና ሠራተኛ ግንኙነትን የሚመለከት ሌላ አዋጅ መኖሩን በማስታወስ ይህ አዋጅም ተሻሽሎ ተመሳሳይ ውጤት እንደሚኖር ገልፀዋል።

  "የአሰሪና ሠራተኛ አዋጁ በመሻሻል ላይ ነው። በመሰረታዊነት የሚታየው ወሊድ ሴት ልጅ ትውልድን የመተካት ሃላፊነት የምትወጣበት ተፈጥሯዊ ነገር መሆኑ ነው። ስለዚህ ተመሳሳይ የሆነ የፖሊሲ አቋም ይኖራል ተብሎ ነው የሚጠበቀው። እስከዛሬም የነበረው ነገር ተመሳሳይ ነው" ብለዋል አቶ ደረጀ።

  ነገር ግን ይህ በግሉ ዘርፍ ያሉ ሴቶች የወሊድ ፈቃድን የሚመለከተው አዋጅን የማሻሻል ሂደት ገና በጅምር ላይ ነው።

  አቶ ደረጀ እንደሚሉት በአሁኑ ወቅት ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ማሻሻያውን እያየውና እየመከረበት ሲሆን ለውሳኔ አልደረሰም።

  እዚህ ጋር ሊነሳ የሚችለው ጥያቄ ለግል ዘርፍ ሠራተኞች የተዘጋነው አዋጅ በትክክል መቼ ይፀድቃል የሚለው ነው።

  ለመንግሥት ሠራተኞች የፀደቀው አዋጅ በተጨማሪም የመንግሥት መስሪያ ቤቶች የህፃናት ማቆያ እንዲያዘጋጁም ይደነግጋል።

  ያነጋገርናቸው እናቶች እርምጃው በጣም ጥሩ እንደሆነ ሲገልፁ ስድስት ወር ጡት ከማጥባት አንፃር አሁንም የወሊድ ፈቃድ ሊሻሻል እንደሚገባ የሚናገሩም አሉ።

  በተመሳሳይ የኢትዮጵያ የማህፀንና ፅንስ ሃኪሞች ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ደረጀ ንጉሴ ከእናቶች ከወሊድ ማገገም እንዲሁም ስድስት ወር ከማጥባት አንፃር ማህበራቸው የወሊድ ፍቃድ መርዘምን እንደሚደግፍ ይናገራሉ።

  ይህ ማለት ፍቃዱ ከዚህም በላይ ከፍ ቢል እንደ ህክምና ባለሙያ የሚደግፉት ነው።

  በተቃራኒው በአገሪቱ ነባራዊ የኢኮኖሚ ሁኔታ የወሊድ ፍቃድን መጨመር የሴቶችን ሥራ የመቀጠር እድል ይቀንሳል የሚል አስተያየት የሰጡን ሴቶችም አሉ።

  በፌስቡክና በተለያዩ ገፆች ሴቶችን የሚመለከቱ ነገሮችን የምትፅፈው ቤተልሄም ነጋሽ ቀደም ሲል የወሊድ ፈቃድ እንዲጨመር በማህበራዊ ድረ ገፆች ቅስቀሳ እናድርግ የሚል ጥያቄ ቀርቦላት የነበረ ቢሆንም፤ መጀመሪያ የኢኮኖሚው ሁኔታና የቀጣሪዎች አመለካከት ከግምት ውስጥ መግባት አለበት ብላ በማመን በቅስቀሳው ከመሳተፍ መቆጠቧን ትናገራለች።

  "ማህበረሰቡ መጀመሪያ መውለድ ዘር መተካት መሆኑን በመረዳት በወሊድ ምክንያት እናቶች ላይ የሚፈጠረውን ጫና ለመካፈል ፈቃደኛ መሆን አለበት። የድርጅት ባለቤቶች የወሊድ ፍቃድ ሲሰጡ ቀጣዩን ትውልደ እየተንከባከቡና እያሳደጉ መሆኑን ማወቅ አለባቸው" ትላለች።

  የቀድሞዋ ጋዜጠኛ ሮዝ መስቲካ ሥራዋን ያቆመችው የመጀመሪያ ልጇን ስትወልድ እንደነበር ታስታውሳለች።

  የወሊድ ፍቃድ ስድስት ወር መሆን አለበት በማለት በማህበራዊ ድረ ገፅ ቅስቀሳ ስታደርግ በመቆየቷ በአዋጁ መሻሻል ደስተኛ መሆኗን ትናገራለች።

  "ስድስት ወር ይጨመር የምለው አንድም ስድስት ወር ለማጥባት፤ ሌላው ደግሞ እናት በቂ እረፍት እንድታደርግ ነው። ቢሆንም ግን የተገኘው አንድ ወርም ቀላል ባለመሆኑ ደስተኛ ነኝ። ብዙ እናቶች እንደሚያደርጉት ከራሳቸው ፍቃድ ጨምረው ስድስት ወር ሊያጠቡ ይችላሉ" ብላለች።

  በመጀመሪያው የመንግስት ሰራተኞች አዋጅ 515/1999 መሰረት የወሊድ ፍቃድ ሦስት ወር ነበር።

  Read more »

 • የመንግስት ሰራተኞች የወሊድ ፈቃድ ወደ አራት ወር ከፍ አለ - Maternity Leave

                                                                 

  የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሻሻለውን የመንግስት ሰራተኞች ረቂቅ አዋጅ አጸደቀ።

  ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 7ኛ መደበኛ ስብሰባ የተሻሻለውን የመንግስት ሰራተኞች አዋጅን ጨምሮ ሌሎች ሁለት አዋጆችንም አፅድቋል።
  የተሻሻለው የመንግስት ሰራተኞች አዋጅ ሀገሪቷ ከደረሰችበት የዕድገት ደረጃ ጋር የተጣጣመና የመንግስት ሰራተኛውን መብት የሚያስጠብቁ ድንጋጌዎችን ያካተተ መሆኑ ተገልጿል።
  የሰው ኃብት ልማት እና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች ረቂቅ አዋጁን በዝርዝር በማየት የውሳኔ ሀሳባቸውን ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።
  በዚህም ረቂቅ አዋጁ በዓለም አቀፍ ደረጃ የታዩ ምርጥ ተሞክሮዎችን መሰረት ያደረገና አገሪቷ እያስመዘገበች ያለውን ዕድገት ማስቀጠል የሚያስችል ፐብሊክ ሰርቪስ ለመገንባት የሚረዳ መሆኑን የቋሚ ኮሚቴዎቹ በውሳኔ ሀሳባቸው አብራርተዋል።
  የመጀመሪያው የመንግስት ሰራተኞች አዋጅ 515/1999 በትግበራ ወቅት ያጋጥሙትን ችግሮች የሚፈታ እና አዋጁ የነበሩበትን ክፍተቶች የሚሞላ መሆኑም ተብራርቷል።
  የተሻሻለው አዋጅ ለሴት ሰራተኞች የአራት ወራት የወሊድ ፍቃድ ከመስጠቱም ባለፈ በመንግስት መስሪያ ቤቶች የህጻናት ማቆያ ቦታዎች እንዲዘጋጁ የሚያደርጉ ድንጋጌዎችን ይዟል።
  በቀድሞው አዋጅ የወሊድ ፍቃድ 90 ቀናት ወይም 3 ወር የነበረ ሲሆን፥ በተሻሻለው አዋጅ ወደ 120 ቀናት ወይም 4 ወር ከፍ ብሏል።
  የወሊድ ፈቃዱ ፅንስ የተቋረጠባቸው ሴቶችንም የሚያካትት መሆኑ ተገልጿል።
  አንድ የመንግስት ሰራተኛ የዓመት ፍቃድ በገንዘብ ሲለወጥ የሰራተኛው የአንድ ቀን ደመወዝ የሚታሰበው ያልተጣራ የወር ደመወዙን በ30 ቀናት በማካፈል መሆኑንም አዋጁ ይደነግጋል።
  በሌላ በኩል የህመም ፈቃድ የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ከሙሉ ደመወዝ ጋር፣ለተከታዮቹ ሶስት ወራት ደግሞ ከግማሽ ደመወዝ ጋር እንዲሁም ለሚቀጥሉት ሁለት ወራት ያለደመወዝ እንደሚሰጥ ነባሩ አዋጅ ይደነግጋል።
  በአዲሱ አዋጅ ግን የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ከሙሉ ደመወዝ ጋር፣ ለተከታዮቹ ሁለት ወራት ደግሞ ከግማሽ ደመወዝ ጋር እንዲሰጣቸው በሚል ተሻሽሏል።
  የምክር ቤቱ አባላት አዋጁ አገሪቷ አሁን ከደረሰችበት የዕድገት ደረጃ ጋር የሚጣጣምና የመንግስት ሰራተኞችን መብት የሚያስጠብቁ ድንጋጌዎችን ያካተተተ ነው በማለት በአንድ ድምፀ ተአቅቦና በአብላጫ ድምፅ አፅድቀውታል።
  ምክር ቤቱ በዛሬው ውሎው የተፈጥሮ ኃብት ልማትና አካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የደን ልማት ጥበቃና ረቂቅ አዋጅን በተመለከተ ያቀረበወን የውሳኔ ሀሳብ መርምሮ በአብላጫ ድምፅና በ13 ድምፀ ተአቅቦ አፅድቋል።
  በኢትዮጵያ መንግስትና በአለምአቀፍ የልማት ማህበር መካከል ለፍትሃዊ የመሰረታዊ አገልግሎቶች ማስፋፊያ ፕሮግራም ማስፈጸሚያ የሚውል ተጨማሪ ብድር ለማግኘት የተደረገውን ስምምነት ለማፅደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅንም በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።
  ምንጭ፦ ኢዜአ

  Read more »

 • ስለ ጠልሰም ወይም በተለምዶ የአስማት ጥበብ ተብሎ ስለሚጠራው ምን ያህል ያውቃሉ? - "Telsem" Or Magical Wisdom of Art

                                                       

  ጠልሰም አስማታዊ ጥበብ ነው ፤ ትርጉሙ ደግሞ አምሳል፣ውክልና እንዲሁም ማስዋብ ማለት ነው።

  ጠልሰም የተለየ ኀይል ያለው ጥበብ ነው።

  ኢትዮጵያውያን ከሁለተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ይሰሩት የነበረ ጥበብ መሆኑም ይነገራል።

  ይህም ጥበብ በየገዳማቱ በብራናዎች ላይ አርፏል።

  የጠልሰም ጥበብ ኃይል ያላቸውን ቃላት፣ዕፅዋት እንዲሁም ምልክቶችን ይይዛል።

  ጠልሰም የመፈወስ ኃይል አለው ስለሚባል በክታብነት የሚጠቀሙበት አሉ።

  ይህ ጥበብ በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ አካባቢዎች ብቻ ተወስኗል።

  የጠልሰም ስዕልም እነዚህን ኃይል ያላቸውን ቃላቶች፣ ምልክቶችና ዕፅዋት በመጠቀም የሚሳል ነው።

  ጠልሰም ከመፈወስ በተጨማሪ ሰውን የመሰወር፤ ግርማ ሞገስን መስጠት፤ በሰዎች ጫንቃ ላይ ለመስፈር የሚዳዳውን ሰይጣን ጋሻና ጦር በመሆን መከላከልና ማስጣል የሚያስችል ኃይል አለው ተብሎ ይታመናል፤ ይህም ዓቃቤ ርዕስ ተብሎ ይጠራል።

  ለዛሬም ከአንድ ኢትዮጵያዊ ጠልሰምን የሚጠቀም ሰዓሊ እናስተዋውቃችሁ።

  ተወልደብርሃን ኪዳነ አስመራ ከተማ ውስጥ ማይ ጃሕጃሕ በተባለ ልዩ ስፍራ ነው የተወለደው። የአንድ ዓመት ህፃን ልጅ ሆኖም ወደ ኢትዮጵያ መጣ።

  በመቐለ የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተክርስትያን ውስጥ የአብነት ትምህርቱን የተማረው ከመርጌታ አርአያ ሲሆን በተጨማሪም ጥንታዊና እየጠፋ ያለውንም የጠልሰምን ዕውቀት አስተምረውታል።

  የመደበኛ ትምህርቱን 8ኛ ክፍል ከደረሰ በኃላ ሁሉንም ነገር ጥሎ ወደ ጐጃም ጣና ቂርቆስ ገዳም ገባ።

  ገዳሙ ውስጥ ለሦስት ዓመታት ያህል የጠልሰም ጥበብን ከሊቃውንት አባቶች ተማረ።

                                                           

  የጠልሰምን ጥበብ ከአፈር፣ ከዕፅዋት፣ከቅጠልና ከአበባ እንዴት መሳል እንደሚቻልም ለዓመታት አጠና።

  ወደ ሰሜን ወሎ በማቅናትም በአቡነ ይምርሃነ ክርስቶስ ገዳም ውስጥ ስለ ጠልሰም አንድ ዓመት ተምሯል።

  ከዚያም በኃላ ሰሜን ሸዋ በሚገኘው የደብረ ሊባኖስ ገዳም በመሄድ የጠልሰምን ጥበብ ለአንድ ዓመት ተኩል ያህል አጥንቷል።

  ተወልደብርሃን በዚህ አላበቃም ወደ ቢሾፍቱም በመሄድ በቤተ ሩፋኤል ገዳም ውስጥ አንድ ዓመት ከሦስት ወር በመቆየት በጠልሰም ዙሪያ ላይ ቁፋሮና ምርምር አካሂዷል።

  ወጣቱ በነዚህ የምርምርና የጥናት ጊዜው ጠልሰም ትልቅ የኢትዮጵያውያን ስልጣኔ መሆኑን እንደተረዳ ይናገራል።

                                                               

  "የመጀመርያው ሰዓሊ ራሱ ፈጣሪ ነው፤የሰው ልጅ የፈጣሪ የጠልሰም ጥበብ ውጤት ነው። የሰው ልጅም ከፈጣሪው የወረሰውን የጥበብ ኅይል ተጠቅሞ የጠልሰምን ጥበብ መከወን ችሏል። በዚሁ ዘዴ ከመላዕክት ጋር ይነጋገራል። ሲያሰኘው ደግሞ ጥበቡ እየረቀቀ በሄደ ቁጥር ከአጋንንት ጋርም ያወራል" በማለት ተወልደብርሃን ስለ ጠልሰም አፈጣጠርና መንፈሳዊ ግንኙነት ይገልፃል ።

  በኢትዮጵያ የጠልሰም ጥበብና ሐረግ በየገዳማቱ ብራና ላይ ይገኛሉ። ተወልደብርሃን በጠልሰም ምርምር ዘልቆ የገባ ሲሆን የራሱን የፈጠራ ውጤት በማከል የተለያዩ ስዕሎችን ያዘጋጃል።

  እስከ አሁን ድረስ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ሰዓሊያን ጋር በመሆን በአዲስ አበባ የአሜሪካ ኤምባሲ፣ብሔራዊ ቴአትር፣ነፃ አርት ቪሌጅ፣ሸራተን ሆቴል፣እንዲሁም በመቐለ ከተማ፣ በዓዲ ግራትና አክሱም ዩኒቨርሲቲዎች በተለያየ ጊዜ የጠልሰም ስዕሎች ዓውደ ርእይ አቅርቧል።

  በመቶዎች የሚቆጠሩ የጠልሰም ስዕሎችንም ሰርቷል።

  "ኢትዮጵያውያን ከጠልሰም በፊት የነበረውና 'ርስተ ጌታ' በሚል ይታወቅ የነበረው የጥበብ ጸጋ አጥተነዋል። 'ርስተ ጌታ' በስነ ፍጥረት ዙሪያ የሚያጠነጥን የስዕል ጥበብ ነበረ። በአሁኑ ሰዓት የዚህ ጥበብ አሻራ በደብረ ዳሞ ገዳም (ትግራይ) እንዲሁም በይምርሃነ ክርስቶስ ገዳም (ላልይበላ) ይገኛል" በማለት ተወልደብርሃን ይናገራል።

  ይህንን ጥበብ ወደ ቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ዕቅድ ያለው ተወልደብርሃን ትግራይ ክልል ውስጥ ከክልሉ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር በአምስት አካባቢዎች በጠልሰም ጥበብ ዙሪያ ለወጣቶች ስልጠና ለመስጠት አቅዶ እንዳልተሳካለት ይናገራል።

  "ጠልሰም ደግሞ ምንድን ነው? አሉኝ። ብራና ላይ ስዬ አሳየሁዋቸው፤ሊቀበሉት አልቻሉም፤ይኸው ቤቴን ዘግቼ እስላለሁ" ሲል ሁኔታው ምን ያህል እንዳልተመቻቸለት ገልጿል።

                                                        

  ተወልደብርሃን ማታ እስከ እኩለ ሌሊት ሲስል ሻማ ማብራትና ዕጣን ማጨስ ይወዳል።

  ባለፈው ዓመት ዘጠኙን ቅዱሳን ለመሳል 78 ሻማዎችን አብርቷል።

  በኢትዮጵያ የጠልሰም ጥበብ ውስጥ ሴቶች አይሳተፉበትም ምክንያቱም ይህ ጥበብ የአስማት ነው ተብሎ ስለሚታወቅ ከባድ ተፅዕኖ ስለሚደርስባቸው ነው በማለት ተወልደብርሃን ይገልፃል።

  ተወልደብርሃን በአሁኑ ሰዓት መቐለ በሚገኝ አንድ የሥነጥበብ ጥምህርት ቤት ዘመናዊ የስዕል ጥበብ ያስተምራል።

  በቀጣይ አንድ ትልቅ የጠልሰም ጥበብ ውጤቶችን የሚያሳይ ዓውደ ርዕይ ለማዘጋጀት አቅዷል።

  "ኢትዮጵያ ውስጥ ጠልሰም አደጋ ላይ ነው፤ሌላው ቀርቶ በውል ተጠንቶ አልተሰነደም። እኔ ያጠናሁትና የሰበሰብኩትን ዕውቀት በመፅሃፍ አሳትሜ ወደ ህዝቡ እንዳላቀርብ አጋዥ በማጣት ይኸው አቋረጥኩት" ሲል ተወልደ ብርሃን በምሬት ይናገራል።

  ምንጭ: ቢቢሲ

  Read more »

 • ውቅያኖስን እንታደግ በሚል መፈክር ከ4 ሺህ በላይ ሰዎች በአሸዋ ላይ በመወዳደራቸው በድንቃድንቅ መዝገብ ሰፍረዋል - Thousands Take Part in Record-breaking Beach Race to Help "save the ocean"

                                                              

  ውቅያኖስ እንታደግ በሚል መፈክር ከ4 ሺህ በላይ ሰዎች በአሸዋ ላይ በመወዳደራቸው በዓለም የድንቃድንቅ መዝገብ ሰፍረዋል።

  መሰረቱን ካሊፎርኒያ ያደረገው “ሰርፊንግ ማዶና ኦሺንስ ፕሮጀክት” ድርጅት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በባህር ዳርቻ በአሸዋ ላይ ሩጫ በማወዳደር የዓለም ግዙፉን የአሸዋ ላይ ውድድር ያዘጋጀ በሚል ተመዝግቧል።

  ድርጅቱ ለየት ያለውን ውድድር ያዘጋጀው ውቅያኖስን እንጠብቅ እንታደግ የሚል ንቅናቄን ለመፍጠር ነው ተብሏል።

                                                                                             

  ውድድሩ በሳንዲያጎ በውቧ ኢንቺኒታስ የባህር ዳርቻ የተካሄደ ሲሆን፥ 4 ሺህ 288 ሰዎችን የመለማመጃ ጫማቸውን ተጫምተው እንዲሮጡ በማድረግ ነው በዓለም የድንቃ ድንቅ መዝገብ ላይ የሰፈሩት።

  የተወሰኑ ተወዳዳሪዎች ራሳቸውን ፎቶ ለማንሳት ሲሉ ለአፍታ ውድድሩን በማቆማቸው በድንቃድንቅ መዝገብ ስማቸው ሳይሰፍር ቀርቷል።

  ሆኖም በድንቃድንቅ መዝገቡ ላይ ለመስፈር በትንሹ 1 ሺህ ሰዎችን ማሳተፍ ያስፈልግ የነበረ ሲሆን፥ ከዚያ በላይ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ውድድሩን በማጠናቀቃቸው ለድሉ በቅተዋል።

                                                         

  ተሳታፊዎቹ በአሸዋ ላይ በትንሹ 100 ሜትሮችን መሮጥ የሚጠበቅናቸው ቢሆንም የሰርፊንግ ማዶና ኦሺንስ ፕሮጀክት ድርጅት ግን ለአዋቂዎች በ5 ሺህ በ10 ሺህ እና በ15 ሺህ ኪሎ ሜትር የተለያየ የርቀት ሩጫን በግዴታ አስቀምጧል።

  ለታዳጊዎች ደግሞ 1 ሺህ ሜትርን መሮጥ ግዴታ ተጥሎባቸዋል።

  በዚህም በርካቶች የተጣለባቸውን ነየርቀት ወሰን በአሸዋ ላይ ሩጠው ጨርሰዋል።

  ምንጭ፦ www.guinnessworldrecords.com

  Read more »

 • የልጆችዎን የሞባይል አጠቃቀም ይከታተሉ ይሆን? - Will You Monitor Your Kids' Mobile Usage?

                                                                         

  ዲስ አበባ፣ ህዳር 1፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ወላጆች የልጆችን የሞባይል ስልክ በርቀት ለመቀየር እና የስክሪን አጠቃቀም ጊዜ ገደብ ማስቀመጥ የሚችሉበት መተግበሪያ ይፋ ሆኗል።

  በጎግል በተደረገ ጥናት መሠረት በአውስትራሊያ ውስጥ ዕድሜያቸው ከ2 እስከ 12 ዓመት ያሉት 50 በመቶ የሚሆኑ ልጆች የራሳቸው ሞባይል ስልክ አላቸው።

  ታዲያ አብዛኛዎቹ ቤተሰቦች የልጆቻቸውን ኢንተርኔት አጠቃቀም በመቆጣጠር ረገድ ንቁ ተሳትፎ ቢያደርጉም፥ ጊዜ ገደብ ማስቀመጥ ግን አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል ነው የተባለው።

  ስለዚህ ይሄን ችግር መፍታት የሚችል “”ፋሚልይ ሊንክ” የተሰኘ በጎግል ኩባንያ የተገነባ አዲስ መተግበሪያ መጀመሩን ተጠቁሟል።

  ይህ መተግበሪያ ዓላማው ወላጆች የልጆቻቸውን የሞባይል አጠቃቀም ለመወሰን እና መረጃን ለማዳረስ ነው ተብሏል።

  መተግበሪያው በአንድሮይድ ኦፕሬቲንግ ሲስተም መሣሪያዎች ላይ ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን፥ ወላጆች ወይም ተንከባካቢዎች የልጆችን የሞባይል ስልክ ስክሪን የመመልከቻ ጊዜ ገደብ፣ የሚጠቀሙባቸውን መተግበሪያዎች ለመከታተል እና የመኝታ ሰዓት ማቀናጀትን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ባህሪዎችን እንዲቆጣጠሩ ያግዛቸዋል ነው የተባለው።

  አዲሱ “ፋሚሊ ሊንክ” መተግበሪያ፥ ወላጆች ህጻናት የሞባይል ስልኮቻቸውን እንዴት እንደሚጠቀሙበት በመመልከት የአጠቃቀም ደንቦችን ለማቀናጀት እንደሚረዳም ኩባንያው ተናገሯል።

  ይህም ልጆች ቴክኖሎጂን በደህንነት እንዲጠቀሙ የሚያግዝ መሆኑ ነው የተጠቆመው።

  የጎግል ቃል አቀባይ እንደገለጹት ከሆነ፥ ቴክኖሎጂው ወላጆች የልጆቻቸውን ፍላጎት ለማወቅ፣ በቀጥታ መስመር( online) ላይ እያወሩ ያሉትን እና ምን ዓይነት መረጃ እያጋሩ እንደሆነ ለመመልከት ይረዳል። 

  በተጨማሪም ወላጆች መረጃን ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ እንዴት እንደሚጠቀሙ ከልጆቻቸው ጋር ግልጽ ውይይት ማድረግ እንደሚያስችላቸው ተነግሯል።

  “ፋሚሊ ሊንክ” መተግበሪያ አንድሮይድ ኦፕሬቲንግ ሲስተም በሚጠቀሙ የስልክ መሳሪያዎች ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን፥ የአፕል ስማርት ስልኮች ያላቸው ሰዎችም ተመሳሳይ አገልግሎት መጠቀም ይችላሉ ተብሏል።

  ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

  Read more »

 • 10 የአለማችን አስገራሚ ሰዎች - 10 Amazing People Of The World

  ሁላችንም ከሌላው ሰው ጋር ለየት የሚያደርገን በህሪያትና ችሎታዎች የታደልን ነን፡፡ ይሁንና የአንዳንድ ሰዎች የተሰጣችው ልዩ ችሎታ በጣም የሚገርምና ጉድ የሚያሰኝ ነው፡፡ ከዚህ በመቀጠል በአለማችን በጣም አስገራሚ የሆኑ  ሰዎችን ተፈጥሮ ካደለቻቸው ልዩ ብቃታቸው ጋር እናያለን፣

   

  1. ወገበ-ቀጭ እመቤት

   

                                                        

  የ26 አመቷ ጀርመናዊት ሚሸል ኮብከ በአለማችን ወገበ-ቀጭኗ እመቤት ስትሆን፤ የወገቧ መጠነ-ዙሪያ 40.64 ሳንቲ ማትር ወይም 16 ኢንች ነው፡፡ ሚሸል የወገቧን መጠነ-ዙሪያ ከዚህም በታች ወደ 35.56 ሳንቲ ማትር ወይም 14 ኢንች  የማሳነስ ዕቅድ እንዳላት ትናገራለች፡፡ “ችቦ አይሞላም ወገቧ ማር እሸት ነው ቀለቧ” የተባለው ለዚች አይነቷ ቆንጆ ሳይሆን አይቀርም፡፡

   

  1. ብረት-በሉ ሰው

                                                                                 

  ይህ ግለሰብ ሚቸል ሎቲቶ ይባላል የፈረንሳይ ዜግነት ያለው ሲሆን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ሠኔ 15 ቀን 1950 ነበር የተወለደው፡፡ ሚቸል ሎቲቶ  አንድን አውሮፕላን በሁለት አመታት ውስጥ አጣጥሞ እንደበላ ይነገርለታል፡፡ በ40 አመት ጊዜ ውስጥ ሚቸል ሎቲቶ ከዘጠኝ ቶን በላይ ክብደት የሚመዝን ብረት ተመግቧል፡፡ መቸም ሰው በጤናው ብረትን አይመገብምና “ይህ ሚቸል የተባለ ግለሰብ ግን ጤነኛ ነው?” ብለው ሳይጠይቁ አይቀሩም:: ሚሸል ፒካ የተባለ የአእምሮ ህመም ተጠቂ ሲሆን፣ የህመሙ ዋነኛ ባህሪይ ሰዎች በተለምዶ የማይመገቧቸውን ነገሮች (ብረትና ፕላስቲክ የመሳሰሉትን) እንድንመገብ የሚያደርግ ነው፡፡

   

  1. ፂመ-ረጅሙ ሰው

                                                                             

  ራም ሲንግ ቹዋሃን ይባላል ህንዳዊ ነው በአለማችን ፂመ-ረጅሙ ሰው ለመባል በቅቷል፡፡ የራም ፂም 4.29 ሜትር የሚረዝም ሲሆን በቀን ውስጥ አንድ ሰዓት የሚሆነውን ጊዜ ፂሙን በማጽዳትና በማበጠር ያሳልፋል፡፡ አሪፍ ጊዜ ማሳለፊያ ያገኘ ይመስላል፡፡

   

  1. እድሜ-ጠገቡ ፓይለት

                                                                          

  አቶ ፒተር ዌበር ጁኒየር የተባሉት አሜሪካዊ በአለማችን እድሜ ጠገቡ አውሮፕላን አብራሪ መሆናውን አለምአቀፋዊው የክበረ ወሰን መዝገብ ያስረዳል፡፡ አቶ ፒተር የ96 አመት ወጣት ሲሆኑ ላለፉት 72 አመታት አውሮፕላን ሲያበሩ ቆይተዋቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት በወር ቢያንስ ለሁለት ጊዜ የሰማይ ላይ ጉዟቸውን እንደሚያከናውኑ አቶ ፒተር ይናገራሉ፡፡

   

  1. እድሜ-ጠገቧ የዮጋ መምህርት

                                                                         

  አሁን ደግሞ ከእድሜ ጠገቡ አውሮፕላን አብራሪ ወደ እድሜ-ጠገቧ የዮጋ መምህርት እንሸጋገር፡፡ ወይዘሮ ታኦ ፖርቸን-ሊንች የ96 አመት እድሜ ባለጸጋ ናቸው፡፡ ለ70 አመታት የዮጋ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ዘወትር ከሌሊቱ 11 ሰዓት ላይ ወይዘሮዋ ተማሪዎቻቸውን ሰብስበው እንዴት ሰውነታቸውን ማጠፍና መዘርጋት እንደሚችሉና ሌሎችን የዮጋ ዘዴዎች ያስተምራሉ፡፡

   

  1. አፈ-ሰፊው ሰው

   

                                                                       

  ፍራንሲስኮ ዶሚነጎ ጃኩይም ይባላል በአለማችን ትልቅ የሆነውን አፍ በመያዝ ክብረ ወሰኑን ሰብሮ ይገኛል:: የጃኩይም አፍ ከዳር እስከዳር 17ሳንቲ ማትር ወይም 6.69 ኢንች ያህል ይሰፋል፡፡

   

  1. ብረ ንግስት

                                                                        

  አሻ ራኒ የሁለት የአለም ክበረ-ወሰኖች ባለቤት ነች፤ ከባድ ነገሮችን በጸጉሯና በጆሮዋ በመጎተት ብቃቷ፡፡ የ23 አመቷ አሻ በዚህ ለዩ ችሎታዋ ብረቷ ንግስት የሚል ቅጽል ስም ተሰጥቷታል፡፡

   

  1. ቀንዳሟ ወይዘሮ

                                                                          

  ይህ ደግሞ ከወደ ቻይና የተገኘ አስገራሚ ዜና ነው፡፡ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 2010 ዣንግ ሩይፋንግ የተባሉ ወይዘሮ ግንባራቸው ላይ ቀንድ በማብቀል አለምን አስደምመዋል፡፡ ወይ ጉድ!!

   

  1. የብርቱ ሳንባ ባለቤት

   

                                                                      

  እርስዎ ምን ያህል መጠን ያለውን ፊኛ መንፋት ይችላሉ? ማንጂት ሲንግ የተባለው ግለሰብ ግን 2.5 ሜትር መጠነ-ዙሪያ ያለውን ፊኛ በ42 ድቂቃ ውስጥ በመንፋት በአለማችን የጠንካራ ሳነባ ባለቤት መሆኑን አስመስክሯል፡፡

   

  1. እጁን እንዳነሳ የቀረው ሰው

                                                                       

  ይህ ሰው የሂንዱ እምነት ተከታይ ነው፡፡ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1973 ሳደሁ አማር ባራቲ የተባለ ግለሰብ የሂንዱ አምላክ ክብር ሲል ቀኝ እጁን አነሳ፤ ከዛን ቀን ጀምሮ ለአምላኩ ክብር ያነሳውን እጁን አላወረደም፡፡

  ምንጭ:- የሸገር FM 102.1 ሬዲዮ

   

   

   

  Read more »

 • ህፃናትን በበጉዲፈቻ ወደ ውጭ አገር መላክ የሚፈቅደው አንቀጽ ከኢትዮጵያ ቤተሰብ ሕግ እንዲሠረዝ ተወሰነ

                                                          

  የውጭ አገር ጉዲፈቻ የተፈጥሮ ቤተሰብ ፍቅርና እንክብካቤን ሙሉ በሙሉ የማይተካና ከዚህ ቀደም በጉዲፈቻ ወደ ውጭ አገራት የሄዱ ህፃናት ላይ የማንነት ቀውስ በማስከተሉ፣ ይህን አሠራር የሚፈቅደው የሕግ ድንጋጌ ከቤተሰብ ሕጉ እንዲሠረዝ መንግሥት ወሰነ።

  በዚህም መሠረት የቤተሰብ ሕጉ ላይ ማሻሻያ የሚያደርግ ረቂቅ ሕግ ዛሬ ለፓርላማ ቀርቦ ለዝርዝር እይታ ተመርቷል ። የውጭ ጉዲፈቻን በሚፈቅደው ሕግ አማካይነት ተጀምረው በፍርድ ቤት ሂደት ላይ የሚገኙ እንዲቀጥሉ ማሻሻያው ይፈቅዳል።

  በሌላ በኩል የመንግሥት ሠራተኞች አዋጅ የተለያዩ ማሻሻያዎችን አካቶ ለፓርላማ የቀረበ ሲሆን፣ ለእናቶች ከወሊድ በኋላ ይፈቀድ የነበረው የሁለት ወር ዕረፍት ሦስት ወር እንዲሆን፣ በድምሩ እናቶች ለቅድመና ድህረ ወሊድ የአራት ወር እረፍት እንዲያገኙ በረቂቅ ሕጉ ተካቶ ቀርቧል።

  ምንጭ:- ሪፖርተር

  Read more »

 • የሰውነት ክብደትን መቀነስ በርካታ ገንዘብ ለመቆጠብ ያግዛል

                                                            

  ከልክ በላይ የሆነ አላስፈላጊ ውፍረት ለመላው ጤንነት ጎጅ መሆኑን የህክምና ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ይገልጻሉ።

  ከልክ በላይ መወፈር የልብና ተያያዥ የጤና እክሎች፣ የስኳር በሽታ እና የካንሰር ተጋላጭነትን ይጨምራል።

  ይህ እንዳይሆን ታዲያ ክብደትን መቆጣጠርና ከሰውነት ቁመት ጋር የተመጣጠነ ክብደት ሊኖር እንደሚገባም ያነሳሉ።

  ከዚህ ጋር ተያይዞም በተደረገ ጥናትም ከሰውነት ቁመት ጋር የተመጣጠነ የሰውነት ክብደት መያዝና አላስፈላጊ ውፍረትን መቀነስ በሺዎች የሚቆጠር ዶላርን ለመቆጠብ እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

  በአሜሪካ የጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ ተመራማሪዎች ባደረጉት ጥናት፥ ከልክ በላይ ውፍረትን መቆጣጠር መቻል በአመት ከላይ ለተጠቀሱት በሽታዎች የሚወጣን የህክምና ወጪን በመቆጠብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትም ለማሳደግ እንደሚረዳ ገልጸዋል።

  ተመራማሪዎቹ በጥናታቸው እንደገለጹት በተለይም በ50ዎቹ የእድሜ ክልል የሚገኝ ሰው የሰውነት ክብደቱን መቆጣጠርና መቀነስ ከቻለ በርካታ ገንዘብ መቆጠብ ይችላል።

  አንድ የ50 አመት ሰው ክብደቱ ከሰውነት ቁመቱ ጋር ያለውን ምጣኔ (ባዮ ማስ ኢንዴክስ) በ5 በመቶና ከዚያ በላይ መቀነስ ከቻለ በአመት 36 ሺህ 278 የአሜሪካ ዶላር መቆጠብ ይችላል ብለዋል፤ (የህክምና ወጪው ጥናቱ በተደረገበት ሃገር ያለውን የሚገልጽ ነው)።

  ይህ ገንዘብ ግለሰቡ/ግለሰቧ ክብደታቸውን መቆጣጠርና ከላይ ለተጠቀሱት በሽታዎች ተጋላጭነታቸውን መቀነስ በመቻላቸው የመጣ መሆኑንም ተመራማሪዎች ይገልጻሉ።

  እናም የሰውነት ክብደታቸው ከሰውነት ቁመታቸው ጋር ያለው ምጣኔ አነስ ያለ ከሆነ፥ ለበሽታ የመጋለጥ እድላቸው አነስተኛ ስለሚሆን የህክምና ወጪያቸውም ይቀንሳል ብለዋል ተመራማሪዎቹ።

  ክብደቱ ከሰውነት ቁመቱ ጋር ያለው ምጣኔ 25 የሆነ ሰው ጤናማና የተስተካከለ የሰውነት ክብደት እንዳለው ሲታሰብ፥ ከ25 እስከ 30 ያለው ደግሞ ወፍራም ተብሎ ይታሰባል።

  ከ30 በላይ መሆን ደግሞ ከልክ በላይ የሆነ አላስፈላጊ ውፍረት በሚለው ምድብ ይካተታል።

  ታዲያ በዚህ ጥናታቸው አንድ የ20 አመት ወጣት ሰው ከአላስፈላጊ ውፍረት (ከ30 በላይ) ወፍራም (እስከ 30 ባለው) ወደሚለው ምድብ በመምጣት ክብደቱን ማስተካከል ከቻለ፥ በአመት ውስጥ 17 ሺህ 655 የአሜሪካ ዶላር መቆጠብ ይችላል ነው ያሉት።

  ከልክ በላይ ከሆነ ውፍረት (ከ30 በላይ) ወደ ጤነኛ ውፍረት (እስከ 25 ባለው) ከመጣ ደግሞ የሚቆጥበውን የገንዘብ መጠን ወደ 28 ሺህ 20 ዶላር ማሳደግ እንደሚችልም ይገልጻሉ።

  ይህ የገንዘብ ቁጠባ ደግሞ ወጪን ከመቀነስ ባሻገር ምርታማነትንም ይጨምራል ነው የሚሉት ተመራማሪዎቹ፤ ምክንያቱም በህመም ሳቢያ ቤት በመዋል ያለ ስራ የሚባክንን ጊዜ መቅረፍ ያስችላልና።

  ከልክ በላይ ሲወፍሩ ለበሽታ መጋለጥ፣ ለህክምና በርካታ ገንዘብ ማውጣት እና ቤት ውስጥ በመዋል ከስራ መራቅ ይመጣል፤ ይህ ደግሞ ገንዘብን አባክኖ ምርታማነትን በመቀነስ ከፍ ያለ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ያስከትላል።

  ይህ የግለሰቦች አመታዊ የህክምና ወጪ ታዲያ እንደ ሃገር ሲታሰብም ከፍ ያለ ጠቀሜታ ያለው ነውና አላስፈላጊ ውፍረትን መከላከል ቀዳሚው ትኩረት ሊሆን እንደሚገባ አጽንኦት ይሰጣሉ።

   

  ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

   

   

   

  Read more »

 • የአትክልት ተመጋቢ መሆን ወይም አትክልትን አዘውትሮ በመመገብ የምናገኛቸውን የጤና ጥቅሞች

                                                 

  የአትክልት ተመጋቢ መሆን ወይም አትክልትን አዘውትሮ በመመገብ የምናገኛቸውን የጤና ጥቅሞች ብለው ተመራማሪዎቹ የጠቀሷቸውን እናካፍልዎ።

  1.ለስኳር በሽታ የመጋለጥ እድላችንን ይቀንሳል፦ ጥናቱ እንዳመላከተው ስጋን ከመመገብ ይልቅ አትክልትን አዘውትረው የሚመገቡ ሰዎች ለስኳር በሽታ ያላቸው የተጋላጭነት መጠን ዝቅተኛ ነው ይላሉ።

  2.ለልብ ህመም እንዳንጋለጥ ይረዳናል፦ የአትክልት ተመጋቢ ወይም አትክልትን አዘውትረን ይምንጠቀም ከሆነ ልባችን በቀላሉ እንዳይታመም እና ጤነኛ እንዲሆን ይረዳናል።

  እንደ ስጋ ያሉ መግቦች በውስጣቸው ያለው የስብ መጠን ከፍተኛ በመሆኑ በደማቸን ውስጥ የኮሌስትሮል መጠን እንዲበዛ በማደረግ በቀላሉ ለልብ ህመም ሊዳርጉን ስለሚችሉ ስጋ ነክ ከሆኑ ምግቦች ይልቅ አትክልትን አዘውትሮ መመገብ ይመከራልም ብለዋል ተመራማሪዎቹ።

  3.ለደም ግፊት እንዳንጋለጥ ይረዳናል፦ የአትክልት ተመጋቢ ወይም አትክልትን አዘውትረን የምንጠቀም ከሆነ ለደም ግፊት ያለን ተጋላጭነት እጅጉን ይቀንሳል ተብሏል።

  4.ክብደትን ለመቀነስ ይረዳል፦ የአትክልት ተመጋቢ ወይም አትክልትን አዘውትረን የምንጠቀም ከሆነም ክብደትን በቀላሉ ለመቀነስ ያስችለናልም ብለዋል ተመራማሪዎቹ።

  ተመራማሪዎቹ ባደረጉት ጥናትም ከመጠን በላይ ውፍረት ያላቸው ሰዎችን በሁለት ቡድን ካካፈሉ በኋላ አንድኛውን ቡድን አትክልት ሌላኛውን ደግሞ ስጋ ነክ ምግቦችን እንዲመገቡ ካደረጉ በኋላ ባገኙት ውጤት አትክልት ተመጋቢዎች ብዙ ኪሎ ግራም ቀንሰው ተገኝተዋል።

  5.ለካንሰር እንዳንጋለጥ ይረዳናል፦ አትክልትን አዘውትረን በተመገብን ቁጥር ለካንሰር በሽታ የመጋለጥ እድላችን እንደሚቀንስ ተነግሯል።

  6.ያማረ የሰውነት ቆዳ እንዲኖረን ያደርጋል፦ አትክልት ተመጋቢነት ለቆዳችን ማማር ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው ተብሏል።

  አትክልትን አዘውትረን በመመገባችንም በቀላሉ እንደ የቆዳ መሸብሸብ እና ከሌሎች ከቆዳ ጋር ተያያዥነት ላላቸው ችግሮች እንዳንጋለጥ ይረዳናል።

  ምንጭ፦ healthdigezt.com

  ተቶርጉሞ የተጫነው፦ በሙለታ መንገሻ

  Read more »

 • ድብርትን ለማስወገድ በሳምንት ለ1 ሰዓት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ይጠቅማል

                                                 

  የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ በርካታ የጤና ጠቀሜታዎች አንዳሉት ይታወቃል፤ በቅርቡ የወጣ ጥናት ደግሞ የአካል ብቃት አንቅስቃሴ ከድብርት ለመላቀቅ ፍቱን ነው ይላል።

  ተመራማሪዎች ለ30 ዓመታት ተካሄደ ባሉት ጥናታቸው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ድብርትን በማስወገዱ ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አመላክተዋል።

  በአውስትራሊያ ተመራማሪዎች የተመራው እና በአሜሪካ ጆርናል ኦፍ ሳይካትሪ ላይ በታተመው የጥናት ውጤት እንደተገለጸው፥ በጥናቱ በ22 ሺህ 500 ኖርዌያውያን ላይ ክተትል ተደርጓል።

  በዚህም በሰዎች ላይ ከሚከሰቱ አዳዲስ ድብርቶች ወስጥ 12 በመቶ ያክሉ በሳምንት ለ1 ሰዓት ብቻ በሚሰራ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መከላከል እንደሚቻል ተለይቷል።

  በኤን.ኤስ.ደብሊው ዩኒቨርሲቲ ብላክ ዶግ ኢኒስቲቲዩት ሳይካትሪስት እና ኢፒዲሞሎጂስት የሆኑት የጥናት ቡድኑ መሪ ሳም ሀርቬይ፥ የምንሰራው የአካል ብቃት መጠን እና አይነት ምንም ችገር የለውም ይላሉ።

  ዋናው ጥቅም የሚገኘው ሰዎች በሳምን ውስጥ ምንም ካለመስራት ወደ የአንድ እና የሁለት ሰዓት አካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲሰሩ በማሸጋገር ነው ብለዋል።

  በጥናቱም የአካል ብቃት እንቅስቃሴን አዘውትረው የሚሰሩ ሰዎች ለድብርት የመጋለጥ አድላቸው በ41 በመቶ የቀነሰ መሆኑም ተለይቷል ብለዋል።

  ይህም በዓመት 100 ሺህ የሚደርሱ የድብርት ህክምናዎችን ሊያስቀር ይችላል የተባለ ሲሆን፥ ለጤና የሚወጣን በቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የሚቆጠሩ ገንዘቦችንም ለመቆጠብ ያስችላል ነው የተባለው።

  ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

  Read more »

 • አረም - ጥቅሙ ያልታወቀለት ተክል

                                            

  እምቦጭ አረምን ለተዋቡ ቁሳቁሶች መስሪያ በማዋል ለአካባቢዋ ሕዝብ ገቢ ማግኛ ቢዝነስ የፈጠረችው ናይጄሪያዊት አቼንዮ አዳቻባ ታሪክ…


  አዳቻባ የተማረችው ኮምፕዩተር ሳይንስ ነው፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት፣ ከውጭ ሐገር ቆይታዋ ወደ ናይጄሪያ ተመልሳ ሌጎስ ውስጥ ባለ አንድ ድልድይ ላይ ስታልፍ ያየችው ትዕይንት ‘አሃ’ አስባላት፡፡

  በዛው ቅፅበት ችግሩም እድሉም ታየኝ ትላለች አዳቻባ፡፡

  አዳጃባ በድልድዩ ላይ ሰታልፍ ከድልድዩ ስር ያለው ወንዝ በአረም ተሞልቶ የአሳ አጥማጅ ጀልባዎች ለማለፍ ተቸግረው አየች፡፡

  ይህን ችግር ሳይ አብሮ ያለው መልካም አጋጣሚም ታየኝ የምትለው አዳጃባ በአካባቢ የሚገኙ የእድ ጥበብ ባለሞያዎች ከአረሙ አንዳች ጥቅም ያለው ነገር እንዲሰሩ አበረታታች፡፡ ዘወትር ቅዳሜ እየሄደችም ከአረሙ የቤት ቁሳቁስ የመስራት ጥበቡን ተማረች፡፡

  በመቀጠል MitiMeth የተባለ አረሙን ለጥቅም የሚያውል አትራፊ ድርጅት መመስረቷን የምትናገረው አዳጃባ ድርጅቷ ሁለት አይነት ተግባር እንደሚያከናውን ትናገራለች፡፡

  አንደኛው አረሙን እንዴት ለጥቅም ማዋል እንደሚቻል የሚያሰለጥን ወርክሾፕ የሚሰጥ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከአረሙ ጠቃሚ ቁሳቁሶችን እያመረተ ይሸጣል፡፡

  ከ5 እስከ 10 ቀናት የሚቆየውን ወርክሾፕ የሚደጉሙት በማህበረሰብ ደህንነት ጉዳይ ላይ የሚሰሩ መንግሥታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ናቸው፡፡

  ከአረሙ ጠቃሚ ቁሶች የሚያመርተው የድርጅቱ አካል ደግሞ ለፅህፈት መሳሪያ፣ ለቤት ቁሳቁስ እና ለምግብ ማዘጋጃነት የሚያገለግሉ እቃዎችን እያመረተ ለሽያጭ ያቀርባል፡፡

  “ከቻይና ከሚገቡ ርካሽ ዋጋ ካላቸው እቃዎች አንፃር ተወዳድሮ ማሸነፍ ፈታኝ መሆኑን አውቃለሁ” የምትለው አዳጃባ “ቢሆንም ግን ለሕዝቡ በእጅ የተመረተ እቃ በማሽን ከተመረተ ይልቅ ዋጋ ያለው መሆኑን አስተምረናል፡፡ ናይጄሪያ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ውስጥ በመሆኗም ከውጭ እቃ ማስገባት እየከበደ በመምጣቱ ተጠቃሚ ሆንን” ብላለች ለቢቢሲ ስትናገር፡፡

  አረሙን ሰብስበው የሚያመጡት አሳ አጥማጆችም ሆኑ በአረሙ ቁስ የሚያመርቱት ኑሯቸውን የሚደጉሙበት ተጨማሪ ገቢ አግኝተዋል፡፡ ይህ አካባቢን ከጥፋት አድኖ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ የሚያደርግ ዘዴ የብዙዎች አድናቆት ተችሮታል፡፡

  በተመሳሳይ መረጃ … በቅርቡ ሸገር እንደ አረም ይቆጠር ስለነበረውና አሁን ላይ ግን ትልቅ ጥቅም እንዳለው ስለተደረሰበት የዳክዬ አረም (Duckweed) ስለተባለው ተክል አንድ መልካም ወሬ አስደምጦ ነበር፡፡

  ዶሮዎች የሚወዱት ይህ ተክል ዶሮዎች ሲበሉት በእንቁላላቸው ውስጥ ያለውን የፕሮቲን መጠን የሚጨምር ነው፡፡

  ላሞች ሲበሉትም ወተታቸው ውስጥ ያለው የፕሮቲን መጠን ሲጨምር ታይቷል፡፡ በአሳዎችም እንዲሁ…

  ይህ ተክል በለተይ ለነፍሰጡሮች እና እናቶች ያለውን ጥቅም በመረዳት በዚህ ዙሪያ ለሚሰራ ፕሮጀክት ዩ ኤስ ኤይድ ለ3 ዓመታት የሚውል የ2 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ማድረጉ ተነግሯል፡፡ አምቦ ዩኒቨርሲቲ በዚህ ተክል ላይ ምርምር እያካሄደ ሲሆን 1 200 እናቶችም በዚህ ተክል ተጠቃሚ መሆናቸውን አስደምጠናችሁ ነበር::

  ምንጭ:- የሸገር FM 102.1 ሬዲዮ

  Read more »

 • ሀሰተኛ የከንፈር ውበት መጠበቂያ ቀለሞች ለከፋ የጤና ጉዳት ስለሚያስከትሉ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል

                                                             

  የትክክለኛነት ማረጋገጫ የሌላቸው ሀሰተኛ የከንፈር ውበት መጠበቂያ ቀለሞችን መጠቀም ለከፋ የጤና ጉዳት እንደሚያጋልጥ ተነግሯል።

  በብሪታኒያ ፓርላማ የሰብዓዊ እና ማህበራዊ ደህንነት ጉዳዮች ኮሚቴ ሀሰተኛ የከንፈር ውበት መጠበቂያ ቀለሞች ከጤና ጥበቃ መመሪያ ውጭ የሆኑ እና ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያደርሱ በክትትል ደርሼበታለሁ ብሏል።

  በፌስቡክ እና በኢ-ቤይ አማካኝነት ለ300 ደንበኞች ሀሰተኛ ምርቶችን የሸጠ ግለሰብም ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት አምርቶ በእስራት እንዲቀጣ ተደርጓል።

  ሀሰተኛ የከንፈር ውብት መጠበቂያ ቀለሞችን በመደበኛ ሁኔታ የሚጠቀሙ ከሆነ፥ ለከፍተኛ የደም ግፊት፣ ለመራቢያ አካል ችግር፣ ለአዕምሮ እና ለልብ ህመም ያጋልጣል ነው የተባለው።

  በተለይም ነፍሰጡር ሴቶች ቀለሞቹን በሚጠቀሟቸው ጊዜ በማህፀን ውስጥ ላሉ ህፃናት የአዕምሮ ህዋሳት መውደም ይዳርጋል።

  ሀሰተኛ ምርቶችን ገዝተው የሚጠቀሙ ሰዎች የከፋ የጤና ጉዳት ሳይደርስባቸው በፊት ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው ተብሏል።

  በመሆኑም በየመንገዱ ወይም በማንኛውም ሱቅ በቅናሽ ዋጋ ያለማብራሪያ እና ያልምንም የትክክለኝነት ማረጋገጫ የሚሸጡ የከንፈር ማስዋቢያዎችን ከመግዛት መቆጠብ እንዲያስፈልግ ተመክሯል።

  በተለይም የከንፈር ውበት መጠበቂያ ቀለሞችን መጠቀም የሚፈልግ ሰው ካለ ወደ ኮስሞቲክስ ሱቆች ወይም መድሃኒት ቤቶች ጎራ በማለት ማማከር እና የሚያስፈልገውን ምርት መግዛት እና በአጠቃቀሙ መሰረት መጠቀም ይግባል ነው የተባለው።

  የንግድ እና የጤና ተቋማትም ሀሰተኛ የከንፈር ውበት መጠበቂያ በሚሸጡ ሰዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር መስራት እና የግንዛቤ በቀለሞቹ ጉዳት ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን መስራት እንንዳለባቸውም ተመክሯል።

  ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

  Read more »

 • የቡሄ በዓል…

                                                    buhe_1.jpg

  በሙለታ መንገሻ

  ቡሄመላው ሀገራችን በየዓመቱ ነሐሴ 13 ቀን የሚከበር በዓል ሲሆን፥ በዓሉ ሀይማኖታዊ እና ባህላዊ ትውፊቶች አሉት።

  በዓሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታተቶች ዘንድ የደብረ ታቦር በዓል በሚል ነው በየዓመቱ ነሃሴ 13 የሚከበረው።

  ይህም ኢየሱስ ክርስቶስ በማስተማር ላይ በነበረበት ጊዜ በደብረ ታቦር ላይ ብርሃነ መለኮቱን የገለፀበት ዕለትን ለማስታወስ ነው የሚከበረው።

  በዓሉ ባህላዊ ትውፊቶችም ያሉት ሲሆን፥ በዚህም ቡሄ በዓል የሚል መጠሪያ አለው።

  ቡሄ ማለት መላጣ ወይም ገላጣ ማለት ሲሆን፥ በሀገራችን ክረምቱ ተገባዶ ብርሃን በሚታይበት ወቅት የሚከበር በዓል ስለሆነ ቡሄ የሚባል መጠሪያ እንደተሰጠው ይነገራል።

  በቀደምት ጊዜያት የቡሄ በዓልን መዳረሻ ተከትሎ በገጠርም ሆነ በየከተማው ልጆች ጅራፋቸውን ገምደው ሲያጮሁ ይሰነብታሉ፤ እናቶችም ለበዓሉ ዝግጅት ስንዴ ሲለቅሙ፣ ሲፈትጉ እና ሲፈጩ ይሰነብታሉ።

  በነሐሴ 13 ዋዜማ በእያንዳንዱ ቤተሰብ ደጃፍ እጅብ ብለው የታሰሩት ችቦዎች የሚቀጣጠሉበት ቀንም ነው።

  ችቦ የማቀጣጥሉን ሥርዓት የሚያዘጋጁትም ሆነ የሚመሩት እንደጨዋታው ልጆች ሳይሆኑ አዋቂዎች እና አባቶች ናቸው።

  በቡሄ በዓል አከባባርም ከዋዜማው ጀምሮ ህፃናት በየቤቱ ደጃፍ “ቡሄ በሉ” እያሉ ግጥም እየደረደሩ በዜማ ይጨፍራሉ።

  ቡሄ ጭፈራ በቡድን የሚጨፈር ሲሆን፥ እያንዳንዱ ቡድን የራሱ መሪ ይኖረዋል፣ ይሄ መሪ አውራጅ በመባል ይታወቃል።

  አውራጁ ዋናው ዘፋኝ ነው፤ ግጥሞቹን በዜማ በማቀናጀት ያወርድላቸዋል፤ ጓደኞቹም በወግ ይቀበሉታል፣ ከልባቸው ላባቸው እስኪንጠፈጠፍ ያስነኩታል።

  ሽልማታቸው ሙልሙል ዳቦ ነውና እሱን ሲያገኙ ምርቃት መርቀው ወደሚቀጥለው ቤት ያመራሉ።

  ከቡሄ ጭፈራ ግጥም ውስጥ፦

  ቡሄ በሉ፣ ልጆች ሁሉ

  ቡሄ መጣ፤ ያ መላጣ

  ቅቤ ቀቡት፣ እንዳይነጣ…

  በማለት በሚጨፍሩበት ጊዜ እናቶች ካዘጋጁት ዳቦ ይሰጧቸውና እየገመጡ ጅራፋቸውን ሲያጮሁ ያመሻሉ።

  የቡሄ በዓል አከባበር አሁን አሁን በከተሞች ባህላዊ ቀለሙን እየለቀቀ መምጣቱ የሚስተዋል ሲሆን፥ በገጠሩ የኢትዮጵያ ክፍል ግን አሁንም ባህሉን ጠብቆ እንደሚከበር እሙን ነው።

   

  ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

   

  Read more »

 • የቡሄ በዓል ጭፈራ ግጥም

                                           

   

   

  ቡሄ በሉ ሆ! ልጆች ሁሉ ሆ
  የኛማ ጌታ ሆ የአለም ፈጣሪ ሆ
  የሰላም አምላክ ሆ ትሁት መሐሪ ሆ
  በደብረ ታቦር ሆ የተገለጠው ሆ
  ፊቱ እንደ ፀሐይ ሆ ያንፀባረቀው ሆ
  ....................በርቶ የታየው ሆ
  ድምፅህን ሰማና በብሩ ደመና/፪/
  የቡሄ ብርሃን ለእኛ መጣን/፪/
  ያዕቆብ ዮሐንስ እንዲሁምጴጥሮስ

  አምላክን አዮት ሆ ሙሴ ኤልያስ ሆ
  አባትም አለ ልጄን ስሙት ሆ
  ቃሌ ነውና የወለድኩት ሆ
  አዝ
  ታቦር አርሞንየም እንኩን ደስ አላቸው
  ከቅዱስ ተራራ ስምህ ደስ አላቸው
  ሰላም ሰላም የ ታቦር ተራራ
  ብርሃነ መለኮት ባንቺ ላይ አበራ
  አዝ
  በተዋህዶ ሆ ወልድ የከበረው ሆ
  የእግዚአብሔር አብ ልጅ ሆ
  ወልደ ማርያም ነው ሆ
  ቡሄ በሉ ቡሄ በሉ ሆ
  የአዳም ልጆች ሆ ብርሃን ተቀበሉ ሆ
  አዝ
  ድምፅህን ሰማና በብሩ ደመና
  አባቴም ቤት ሆ አለኝ ለከት ሆ
  እናቴም ቤት ሆ አለኝ ለከት ሆ
  አጎቴም ቤት ሆአለኝ ለከት ሆ
  አክስቴም ቤት ሆ አለኝ ለከት ሆ
  ተከምሮአል ሆ! እንደ ኩበት ሆ!
  ...... .. . እዝ................

  Read more »

 • በስራ ቦታ የሚያጋጥምን ከፍተኛ ጭንቀት በ10 ደቂቃ ውስጥ ሊያስወግዱ የሚችሉ 10 ተግባራት

                                                               

  በዚህ ዘመን በርካታ ሰዎች ለጭንቀት እንደሚጋለጡ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

  ከፍተኛ ጭንቀት እና ትካዜ ወደ አዕምሯችን በሚመጡ የግል ወይም ማህበራዊ ችግሮች ሊከሰት ይችላል፡፡

  የዋተርሉ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች በዚህ ዓመት በቢሮ ውስጥ ብዙ ጊዜ የሚያሳልፉና ለጭንቀት የሚዳረጉ በርካታ ሰዎችን ጠይቀው በሰሩት ጥናት ካጋጠማቸው መጥፎ ስሜት ለመራቅ በርካታ ተግባራትን እንደሚከያናውኑ ጠቅሰዋል፡፡

  በቢሮ ውስጥ የሚያጋጥሙ የስራ ጭንቀቶችን በ10 ደቂቃ ውስጥ ለማስወገድ የሚጠቅሙ 10 ተግባራትን እነሆ ብሏል ጥናቱ፡፡

  1. ስዕል መሞከር

  የዋተርሉ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች እንደሚመክሩት ከሆነ በቢሮ ውስጥ ከፍተኛ ጭንቀት በሚያጋጥመን ጊዜ ወረቀት እና እርሳስን በማገናኘት ስለሚያስጨንቀን ነገር ለመሳል ብንሞከር ተመራጭ ነው፡፡

  በአንጎል ውስጥ የሚገኘው ጭንቀት፣ ትካዜ እና ፍርሃት በምስል ሲታይ ቀለል ይለናል ይላሉ ተመራማሪዎች፡፡

  2. ጭንቀት እና ውጥረትን ለመቀነስ የተሰሩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን መጠቀም

  በበለፀጉት ሀገራት ዜጎችን ከጭንቀት እና ከድብርት የሚያወጡ በርካታ መተግበሪያዎች ተሰርተው ጥቅም ላይ እየዋሉ ይገኛሉ፡፡

  እነዚህ መተግበሪዎች ከፍተኛ ጭንቀትን እንዴት ማስወገድ እንደሚገባ በማስገንዘብ እና ለራስ መልካም ነገርን ማሰብ ያለውን ጥቅም በማሳወቅ በርካቶችን ታድገዋል፡፡

  3. ከፍተኛ ጭንቀት ሲያጋጥም አንድ ብርጭቆ ውሃ መጠጣት

  በአዕምሮ ውስጥ ያለው የጭንቀት ነበልባል ቀዝቀዝ እንዲል በአንድ ትንፋሽ አንድ የብርጭቆ ውሃን መጠጣት ይመከራል፡፡

  በተለይም እስትንፋስ መረጋጋትን እና የሰውነት መሞቅን እንዲሁም የአዕምሮ መወጠርን ለማርገብ ጥቅሙ ላቅ ያለ ነው ተብሏል፡፡

  4. የሚወዱትን ዜማ ወይም ሙዚቃ ማዳመጥ

  አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ሙዚቃ ሕይወቴ ይላሉ፤ የስነ ልቦና ባለሙያዎች ደግሞ በስራ ቦታ ላይ ለሚያጋጥም ጭንቀት የሚወዱትን ሙዚቃ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ማዳመጥ መፍትሔ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

  ለአብነትም ወከባ በሚበዛበት ቢሮ ውስጥ ሆነው በግል የጆሮ ማዳመጫዎ አይንዎን ጨፍነው ሙዚቃ ወይም መዝሙርን ለአምስት ደቂቃ ቢያዳምጡ ትካዜ እና ጭንቀት ከአዕምሮ እንዲርቅ ያደርጋል ተብሏል፡፡

  በተለይም ለተመስጦ የሚረዱ ሙዚቃዎችን ማዳመጥ መልካም መሆኑ ነው የተነገረው፡፡

  5. የእንቆቅልሽ ይዘት ያላቸውን ጨዋታዎች መጫዎት

  ብዙ ጊዜ እንቆቅልሽ የልጆችን አዕምሮ ለማጎልበት አካባቢያዊ ነገሮችን መነሻ በማድረግ በጥያቄና መልስ መልኩ አዝናኝ ሆኖ ይቀርባል፡፡

  ይህ ልምድ በስራ ቦታ ቢተገበር ሰዎች የሚጋጥማቸውን ጭንቀትና ትካዜ ለመቅረፍ ወሳኝ ነው፡፡

  በተለይም በቢሮ ውስጥ በጠጴዛችን ላይ በቀላሉ በተዘጋጁ ቅርጾች ላይ ቃላትን፣ ቁጥሮችን ወይም የተቆራረጡ ምስሎችን በማገጣጠም መጫወት ከፍተኛ የሆነውን የአዕምሮ ጭንቀት ከ10 ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለማስወገድ ያግዛል፡፡

  6. የስራ ጠረጴዛችንን ጽዱ እና አቀማማጡን የተስተካከለ ማድረግ

  ቤታችን ንጹህ ሲሆን ደስ የሚለንን ያህል ቢሮ ውስጥም ጠረጴዛችን ንጹህና ማራኪ አቀማመጡም የተስተካከለ ሲሆን በስራ ላይ የሚያጋጥምን ጭንቀት እንደሚቀንስ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

  የስራ መደራረብ ሲያጋጥም በአግባቡ ለመምራትም ያመቻል፡፡

  7. ለ10 ደቂቃዎች መመሰጥ

  በስራ ሰዓት ካለን ጊዜ ውጥ 10 ደቂቃ ያህል ከቢሮ ወጣ ብሎ ፀጥታ በነገሰበት ቦታ ተመስጦ አድርጎ ወደ ስራ መመለስ ጭንቀትን አስወግዶ ብሩህ መንፈስን ያላብሳል፡፡

  በተመስጦው ጊዜም ዓይንን መጨፈን፣ ትኩረትን መሰብሰብ፣ አተነፋፈስን ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡

  8. በረዥሙ አየር ወደ ውስጥ ማስገባትና ማስወጣት

  አንድ ሰው በስራ ገበታው ላይ እያለ ለትከዜ ወይም ለጭንቀት የሚዳርግ ሀሳብ ወደ አዕምሮው ከመጣ ስራውን ለአፍታ አቁሞ አየር ወደ ሳንባ በጥልቁ ማስገባት ለመረጋጋት ቢሞክር የተሻለ መሆኑን የስታንፎርድ ዩኒቨርስቲ የባዮኬሚስትሪ ፕሮፌሰሩ ማርክ ክራስኖው ይናገራሉ፡፡

  አተነፋፈስን ማረጋጋት አዕምሮን ለማረጋጋት ወሳኝ ነው ብለዋል ፕሮፌሰር ክራስኖው፡፡

  9. ጭንቀት ሲፈጠር የሚሰማንን በሙሉ መጻፍ

  አስጨናቂ ነገሮች ወደ አንጎላችን በሚመጡበት ጊዜ ያለውን ስሜት በሙሉ በወረቀት ወይም በማስታወሻችን ማስፈር ይገባል፡፡

  ስለምናስበው ነገር በምንጽፍበት ጊዜ ሁሉም ነገር በየመስመሩ ይቀመጣል፤ ይህ ደግሞ ለአዕምሮ እረፍትን ያመጣል ነው የሚሉት የስነ ልቦና ባለሙያዎቹ፡፡

  10. በእግር ጉዞ ማድረግ

  አንዳንድ ጊዜ ከቢሮ ወጣ ብሎ ለ10 ደቂቃ ያህል በእግር እንቅስቃሴ ማድረግ የመንፈስ መታደስን ለማምጣት ይረዳል፡፡

  የእግር ጉዞ ማድረግ አዕምሮን በማረጋጋት በስራችን ላይ ውጤታማ እንድንሆን እንደሚያግዝም ተጠቁሟል፡፡

  በአጠቃላይ ከላይ የተገለፁት ተግባራት በአማራጭነት የሚተገበሩ ሲሆኑ ከ10 ደቂቃ ውስጥ ባነሰ ጊዜ ከፍተኛ የሆነ ጭንቀትን ለማስወገድ ቁልፍ መፍትሔ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡

  ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

  Read more »

 • በውጭ ሀገራት ለሚኖሩ ልጆች ምቹ የሆኑ ዘጠኝ ሀገራት ይፋ ሆኑ::

                                                

  ሰዎች በአዲስ ስራ ፍለጋ ወይም በሌላ የህይወት አጋጣሚ ምክንያት ወደ ሌላ ሀገር ሊጓዙ ይችላሉ፡፡

  የተጓዙበት ሀገር ማህበረሰብ፣ የአየር ሁኔታ፣ ማህበራዊ አገልግሎቶችም ምቾት ሊሰጧቸው ወይም “ሀገሬ ማሪኝ” ሊያስብሏቸው ይችላሉ፡፡

  በዓለም ደረጃ በውጭ ሀገር ከሚኖሩ ሰዎች መካከል 46 በመቶዎቹ ቤተሰብ መስርተው ልጆች የወለዱ ሲሆን፥ ከዚህ ውስጥ 21 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው ልጆቻቸውን እየኖሩበት ባለው ሀገር እያሳደጉ የሚገኙት፡፡

  ኢንተር ኔሽንስ የተሰኘ የጥናት ቡድን በውጭ ሀገር በሚኖሩ 3 ሺህ ቤተሰቦች ላይ ቅኝት በማድረግ ቤተሰብ ለመመስረት እና ልጆችን ለማሳደግ ምቹ የሆኑ ሀገራትን ደረጃ ለማውጣት ሞክሯል።

  በጥናቱም ስዊዘርላንድ፣ ሩሲያ እና አውስትራሊያ ከውጭ ሀገር ለመጡ ቤተሰቦች ምቹ ባለመሆን የመጨረሻዎቹን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡

  በአንጻሩ በውጭ ሀገር ልጆችን ለማሳደግ ምቹ የተባሉ ዘጠኝ ሀገራት ከዚህ ቀጥሎ ቀርበዋል፡፡

  1. ኡጋንዳ

  በኡጋንዳ የሚኖሩ የውጭ ዜጎች በሚኖሩበት አካባቢ ያለው የሀገሪቱ ማህበረሰብ ለኑሮ ምቹ ለልጆቻቸውም መልካም አቀራረብ ያለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

  በሀገሪቱ ከሚገኙ የውጭ ቤተሰቦች መካከል 68 በመቶዎቹ ልጆቻቸውን በኡጋንዳ በማሳደጋቸው እና ቤተሰብ መስርተው በመኖራቸው ሙሉ በሙሉ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

  2. እስራኤል

  በጥናቱ መሰረት እስራኤል ልጆች ላሏቸው የውጭ ሀገር ዜጎች ምቹ በመሆን ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡

  ቴል አቪቭ በተለይም ሀገሪቱ ለውጭ ዜጎች እና ለልጆቻቸው ባላት የጤና እና የትምህርት ፖሊሲ ነው ተመራጭ የሆነችው፡፡

  3. ታይዋን

  ታይዋን ከውጭ ሀገር መጥተው ኑሯቸውን በሀገሪቱ ለመሰረቱ ቤተሰቦች ከእለታዊ ህይወት ጀምሮ እስከ ፋይናንስ ጉዳዮች ድረስ በጥሩ ኑሮ ላይ እንዲገኙ በማድረግ ትጠቀሳለች፡፡

  በጥናቱ ከተካተቱ በሀገሪቱ የሚኖሩ የውጭ ሀገር ዜጎች መካከል 97 በመቶ ያህሉ መላሾች ታይዋናውያን ለልጆቻቸው ጥሩ አመለካከት እንዳላቸውና የውጭ ሀገር ዜጋ ናቸው በሚል እንደማያገሏቸው ነው የገለፁት፡፡

  4. ኮስታሪካ

  ይህቺ ሀገር የውጭ ሀገር ዜጎች ለኑሮ ውድነት የማይዳረጉባት እና ሁሉ ነገር ርካሽ የሆነባት መሆኗ ይነገራል።

  በኮስታሪካ የሚኖሩ 74 በመቶ የውጭ ሀገር ዜጎች በሰጡት አስተያየት በሀገሪቱ ለልጆች ምቹ የመዝናኛ ስፍራዎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

  በጥናቱ ውስጥ 91 በመቶ ያህሉ የውጭ ዜጎች የአካባቢው ማህበረሰብ ልጆቻቸውን እንደሚያቀርቡ እና እንደዜጋ እንደሚመለከታቸው መስክረዋል፡፡

  5. ታይላንድ

  እስያዊቷ ሀገር ከሌሎች ሀገራት መጥተው ቤተሰብ ለመሰረቱ ሰዎችና ለልጆቻቸው ጤና ትኩረት በመስጠት የምትታወቅ ሲሆን በሀገሪቱ ከሚኖሩት የውጭ ዜጎች መካከል 76 በመቶዎቹ እርካታ እንደሚሰማቸው መስክረዋል፡፡

  6. ግሪክ

  ግሪክ ለውጭ ዜጎች ምቹ በመሆን ከቀዳሚዎቹ ሀገራት ተርታ ብትሰለፍም በትምህርት አገልግሎቷ ደካማ ናት ተብሏል።

  7. አውስትራሊያ 

  በአውስትራሊያ የሚኖሩ የውጭ ሀገር ዜጎች ለቤተሰባቸው ህይወት እና ለስራ ምቹ መሆኗን ቢጠቅሱም ልጆች የሚዝናኑባቸው ምቹ ቦታዎች ላይ ክፍተት መኖሩን ጠቁመዋል፡፡

  8. ሜክሲኮ

  ሜክሲኳዊያን ከሌሎች ሀገራት በስራ ወይም በሌሎች የህይወት አጋጣሚ ለሚመጡ ሰዎች አቀባበላቸው መልካም እንደሆነ፣ በኑሮም ተስማሚ መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡

  9. ቱርክ
  በቱርክ የሚኖሩ የውጭ ሀገር ዜጎች አንካራ ልጆቻቸውን በጥሩ ሁኔታ እንዲያሳድጉ እንደምታበራታታ ገልፀዋል፡፡

  ሆኖም በፖለቲካዊ አለመረጋጋት ምክንያት የልጆች እና የቤተሰባቸው ደህንነት ስጋት ውስጥ መውደቁን በደካማ ጎኗ አንስተውታል፡፡

  ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

   

  Read more »

 • ቡና ጠጡና “ዕድሜ ጥገቡ”

                                                                 

  አንዲት ስኒ ቡና! አቦል ካለበለዚያም እስከ በረካው - የብዙ ሰው ሱስና የለት ተለት ቀጠሮው ነው። በተለይ በጠዋት “ፉት” የተባለች እንደሁ አህ!!! መልካም ቀን ተጀመረ ማለት ነው…
  አንድ ሰሞኑን የወጣ አዲስ የጥናት ሪፖርት ደግሞ “ምን ቀን ብቻ? ዕድሜ ሙሉ እንጂ!” ይላል። በቀን ሦስት ስኒ ቡና የሚያጣጥሙ ሰዎች ከማይጠጡቱ ለተሻለ የዘመን ርዝማኔ እንዲሁ እንዳጣጣሙት ይኖራሉ፡፡
  ሳይንቲስቶቹ ጥናቱን ያደረጉት ዕድሜአቸው ከ35 ዓመት በላይ በሆነ ቁጥራቸው ከግማሽ ሚሊየን በበዛ በአሥር የአውሮፓ ሃገሮች ውስጥ በሚኖሩ ጤናማ ሰዎች ላይ መሆኑን ሪፖርታቸው አሳይቷል።
  “ባንዲት ስኒ ቡና ዋጋዋ ባነሰ፣ (የዛሬን አያድርገውና) ስንት ዕድሜ ረዘመ ስንቱ ሰው ታደሰ።” ብሎ ይፅፍ ይሆን ጠቃሽ?! ለማንኛውም “ቡና ጠጡ!”

  ምንጭ:- ቪ ኦ ኤ(VOA)

   

  Read more »

 • የአዕምሯችን ኃይል በመጠቀም ጤናችንን ለመጠበቅ የሚረዱ ስልቶች

         

         አዕምሯችን የሚያስበው እና ሰውነታችን የሚሰማን ነገር የቀጥታ ግንኙነት አላቸው።       

          በመሆኑም ስነ ልቦናዊ ጫናዎችን ለማቃለል የሰውነታችን እንቅስቃሴ ወሳኝ ፋይዳ አለው።

  አዕምሯችን በመጠቀምም የሰውነታችን ጤና ማጎልበት እንችላለን።

  በአጭሩ አተያያችን መቀየር እና አዕምሯችንን የተቆጣጠሩ መጥፎ ሀሳቦች ማስወገድ መልካም የሰውነት አቋም እንድናለበስ እና አጠቃላይ ጤናችንን ለመጠበቅ ይረዳል።

  ምንም እንኳን አዎንታዊ አስተሳሰብ ሁሉንም ችግር መፍታት ባይችልም ጤናማ አስተሳሰብ ለጤናማ ሰውነት ዋነኛው ግብአት ነው።

   

  ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ሰባት ስልቶችም አዕምሯችን በመጠቀም የሰውነታችን ጤና ለመጠበቅ ይረዳሉ ተብሏል።

  1. የምንወስዳቸው ህክምናዎች ውጤታማ እንደሚሆኑ መተማመን

  በርካታ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ለተለያዩ የህክምና አገልግሎቶች ውጤታማነት ታካሚው በሚሰጠው ህክምና ላይ ያለው መተማመን ከፍተኛ ድርሻ ይይዛል።

  ከባድ የራስ ምታት አሞን አንድ ሰው “ይሄ መድሃኒት ያድንሃል” ካለን እና እኛም እንደሚያድነን በሙሉ እምነት ከተማመንበት ምንም እንኳን መድሃኒቱ ከስኳር ብቻ የተሰራ ቢሆንም ያድነናል።

  ጉልበታችን አሞንም በባህላዊ መንገድም ይሁን በህክምና ተቋማት እየታሸን እያደረግናቸው ያሉት ህክምናዎች ፈውስ ይሆኑናል ወይም አያድኑንም በሚል ለአዕምሯችን የምንነግረው ነገር ከህክምናዎቹ በተሻለ በአጭሩ ለማገገም እንደሚረዳ ነው የሚነገረው።

   

  2. ከመኝታ በፊት የምስጋና ማስታወሻዎችን መፃፍ ለመልካም እንቅልፍ

  የእንቅልፍ ማጣት የሚያስቸግራችሁ ከሆነ የምስጋና ማስታወሻ መፃፍ ሁነኛ መፍትሄ ነው ተብሏል።

  የተለያዩ ጥናቶች አመስጋኝነት እና ጥሩ እንቅልፍ ግንኙነት እንዳላቸው አሳይተዋል።

  ከመኝታ በፊት ልናመሰግናቸው ስለምንፈልጋቸው ሰዎች መፃፍ በተለይም በእንቅልፍ ማጣት ለሚንገላቱ ሰዎች ጥሩ ዘዴ መሆኑ ተገልጿል።

   

  3. የመኖራችን ትርጉም ላይ ትኩረት ማድረግ

   

  በህይወት መኖራችን ትርጉም ያለው መሆኑን መረዳት ረጅም እድሜ የመኖር እድላችን ያሰፋል።

  ትርጉም ያለው ህይወት እየመሩ መሆኑን የሚተማመኑ ሰዎች የህይወት ዘመናቸው ጤናማ እና ረጅም እንደሚሆንም ጥናቶች ያመለክታሉ።

  ሁል ጊዜ ጠዋት ጠዋት ከአልጋችን እንደምንነሳበት ስሜት ሁሉ የመኖራችን ትርጉሙ ምንድን ነው ብለን ራሳችን ጠይቀን የምናገኘው ምላሽ ለስኬታማ እና ረጅም ህይወት ወሳኝ ነው ተብሏል።

   

  4. ተስፈኛ መሆን በሽታ የመከላከል አቅምን ያሳድጋል

  መጪውን ተስፋ የሚያደርጉ ሰዎች በበሽታ የመጠቃት እድላቸው አነስተኛ መሆኑ ይነገራል።

  በርካታ ተመራማሪዎች ለአስርት አመታት ባደረጉት ጥናት ተስፈኛ ሰዎች በሽታን የመከላከል አቅማቸው ከፍተኛ መሆኑን ደርሰንበታል ብለዋል።

  ለዚህም ነገ ጥሩ ይሆናል ብለው የሚያስቡ ሰዎች ጤንነታቸውን ለመጠበቅ ጥረት ያደርጋሉ የሚለውን በምክንያትነት አስቀምጠዋል።

  ነገር ግን በቅርብ የተደረጉ ጥናቶች ብሩህ አስተሳሰብ በራሱ በሽታ የመከላከል አቅምን በማሳደግ ረገድ አስተዋፅኦው ከፍ ያለ መሆኑን አሳይተዋል።

   

  5. ተመስጦ

  ጭንቀት በሰውነታችን ላይ የሚያደርሰውን ችግር ለመከላከል ተመስጦ(ሚዴሽን) ይመከራል።

  ተመስጦ በጭንቀት የተነሳ የሚመጣ በሽታን እና ከእድሜ ጋር የተያያዙ ህመሞችን ለመቀነስም ይረዳል።

  ተመራማሪዎች ህፃናትን በለጋ እድሜያቸው እንዴት ከራሳቸው ጋር መነጋገር (መመሰጥ) እንዳለባቸው ማስተማር እስከ ህይወታቸው ፍፃሜ የሚያስገኝላቸው የጤና በረከት ላቅ ያለ ነው ብለዋል።

   

  6. ስፖርታዊ እንቅስቃሴ እንዳደረግን በማሰብ ጡንቻችንን ማፈርጠም

  ምንም አይነት ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ሳናደርግ በአዕምሯችን እንቅስቃሴ እያደረግን መሆኑን በማሰብ ብቻ ጡንቻዎቻችን ማሳደግ እንደምንችል ነው ተመራማሪዎች የሚናገሩት።

   

  7. በመሳቅ የልብ ህመም ተጋላጭነትን መቀነስ

  ጤናማ ልብ እንዲኖርዎት ደስታን የሚፈጥሩ ነገሮች ላይ ትኩረት አድርጉ ተብሏል።

  ሳቅ የጭንቀት ሆርሞኖችን ይቀንሳል፤ ጠቃሚ የኮሊስትሮል መጠንንም ይጨምራል።

  ከዚህም ባለፈ የደም ማመላለሻ ቱቦዎች እብጠትን ይቀንሳል።

  ሳቅ በርካታ ጥቅሞች እንዳሉት እሙን ነው፤ ምንም አይነት ጉዳት የማያስከትል መሆኑም ሌላኛው አበርክቶው ነው።

   

  የአዕምሯችን ታላቅ ሀይል

  አዕምሯችን ምርጥ ሀብታችን አልያም ሁነኛ ጠላታችን ሊሆን ይችላል።

  እናም አዕምሯችን አጠቃላይ የሰውነታችንን ጤና ለመጠበቅ እንዴት እንጠቀምበት የሚለውን ከላይ የተዘረዘሩ ነጥቦች ያጢኗቸው።

  ማንኛውም ሰው የአዕምሮውን ጥንካሬን በልምምድ ማጎልበት ይችላል።

  ከላይ የጠቀስናቸው ስልቶችም የጤናማ እና ረጅም እድሜ ቁልፍ መሳሪያዎች ሊሆኑ ይችላሉ።

  ምንጭ: www.psychologytoday.com  በፋሲካው ታደሰ  ለ FBC  የተተረጎመ

  Read more »

 • በልዩ ዝግጅት ላይ ከመሳተፋችን በፊት ራሳችንን በመስታወት መመልከት የሚያስገኝልን 7 ጠቀሜታዎች::

                                               

  በአንድ ህዝባዊ ወይም ማህበራዊ ልዩ ዝግጅት ላይ ለመታደም በምንፈልግበት ጊዜ መስታወት መመልከት እና ራሳችንን መገምገም እየተለመደ መጥቷል፡፡

  በዝግጅቱ ላይ ለየት ብሎ እና ማራኪ ሆኖ ለመቅረብም መስታወት ይጠቅማል፡፡

  መስታወት መመልከታችን ከምናስበው በላይ ያሉትን ጥቅሞች ከዚህ ቀጥሎ አቅርበናል፡፡

  1. አካላዊ ገፅታን ለማስተካከል

  የሰውነታችን ቅርፅ እንዲሁም አለባበሳችን የተስተታከለ እንዲሆን እና በህዝባዊ ሁነቱ ሳቢ ሆኖ ለመታየት ወደ ስፍራው ከማቅናታችን በፊት መስታወት መጠቀም ወሳኝ ነው፡፡

  2. አተነፋፈሳችንን ለማወቅ

  የሰው ልጅ በሕይወት እንዲኖር የመተንፈሻ አካላቱ በሚገባ መስራት አለባቸው፡፡

  ከዚህ ባሻገር በትልቅ ማህበራዊ ዝግጅ ላይ ስንገኝ አተነፋፈሳችን የተረጋጋ እና ሌሎችን የማይረብሽ ቢሆን ይመረጣል፡፡

  ለዚህም ደግሞ በቤት ውስጥ ባለን መስታወት በምን የአተነፋፈስ ልክ እየተነፈስን እንደሆነ ማረጋገጥ እና ለመረጋጋት መሞከር ይገባል፡፡

  ለአብነትም ስራ ቆይተን፣ ወይም በብስጭት ስሜት ወስጥ ስንሆን ያለው አተነፋፈስ ጥሩ ያልሆነ ስሜት በአዕምሯችን ውስጥ መኖሩን በሚያሳውቅ መልኩ ፈጣን እና የተቆራረጠ ይሆናል፡፡

  በመሆኑም በመስታወት ፊት ለፊት ቆመን ራሳችንን እያየን አየር ወደ ውስጥ አስገብቶ በዝግታ ማስወጣትን ተለማምዶ ሲስተካከል ወደ ምንፈልገው ዝግጅት ማምራት ተገቢ መሆኑን ነው ጥናቶች የሚያሳዩት፡፡

  3. አመለካከት (ባህሪን) ለመገምገም እና ለማረጋገጥ

  ከሰው ልጅ ስሜታዊ እንቅስቀሴዎች መካከል 55 በመቶዎቹ ቃላዊ ያልሆኑ ወይም አካላዊ ናቸው፡፡

  ይህ ከሆነ ደግሞ፣ ብስጭት በፊት ገጽታ ይታወቃል፤ በመሆኑም ሰዎች ለራሳቸው በመታመን ባህሪያቸውን ለማስተካከል እና በልዩ ዝግጅቱ ላይ ተረጋግተው በጥ ስነ ምግባር እንዲያሳልፉ ራሳቸውን በመስታወት መመልከት ተመራጭ ነው፡፡

  4. በመስታወት ውስጥ የራስን ተስፋ መመልከት


  አንዳንድ ጊዜ በቀጣይ ይሳካል ስለምንለው ነገር ባይሳካስ በሚል ትኩርት ላንሰጠው እንችላለን፡፡

  ሆኖም ይላሉ በዚህ ረገድ የተሰሩ ጥናቶች፤ ሰዎች በአንድ አጋጣሚ ማሳከት የሚፈልጉትን ነገር ለምሳሌ በልዩ ዝግጅቶች ላይ ሊያሳኩት ስለፈለጉት ነገር ያላቸውን ተስፋ ለማጠናከር እና ግቡን ለመምታት በመስታወት ውስጥ ራስን በመመልከት ተስፋን መሰነቅ ተገቢ ይሆናል ይላሉ፡፡

  5. የፍርሃት ስሜትን ለማስወገድ

  ፍርሃትን እና ጭንቀትን ለማስወገድ ድግግሞሻዊ የመረጋጋት ልምምዶችን እና ራስን በተመስጦ መመልከትን ይጠይቃል፡፡

  ፍርሃት ወደ ሰዎች አዕምሮ በሚመጣት ጊዜ ሰዎች መፍራታቸውን አምነው ለማስወገድ ትረት መዳረግ አለባቸው፡፡

  ለአብነትም በመስታወት ውስጥ ራስን እያዩ አተነፋፈስን በማረጋጋት፣ እና ፍርሃቱ ወደ አዕምሮ የመጣው ያለምንም ምክንያት መሆኑን፣ በዝግጅቱ ላይ መገኘት እንደሚያኮራ ለአንጎላችን በመንገር የራስ መተማመንን ማጎልበት ይገባል፡፡

  6.ራስን ከመውቀስ ለማዳን

  ብዙ ጊዜ በሆነው ባልሆነው ነገር ራሳችንን በመውቀስ ከሰዎች ጋርም ስንገናኝ የጥፋተኝነት ስሜትን በሚያንፀባርቅ መልኩ እንቀርባለን፡፡

  እንደዚህ ዓይነቱ ልምድ በጣም ልዩ በሆኑ ዝግጅቶች እና የእኛን ድርሻ በሚፈልጉ ማህበራዊ ሁነቶች ላይ ጉዳት ያመጣብናል፡፡

  በመሆኑም ወደ ዝግጅቱ ከማምራታችን እና የስራ ድርሻችንን ከመረከባችን በፊት ራሳችንን ከምንም መጥፎ ስሜት እና ከወቀሳ አውጥተውን እንድንሄድ በመስታወት ውስጥ ከራሳችን ጋር መነጋገር እና ቀለል አድርጎ ማየት አስፈላጊ ነው፡፡

  እኛ ለራሳችን መልካም ነገርን መመገብ አለብን፡፡

  7. በትክክል የምንፈልገውን ነገር ለማወቅ

  ሰዎች ስለ አንድ ጉዳይ ሲያስቡ ከእውነት የሚፈልጉትን መሆኑ አለመሆኑን መለየት ያስልጋቸዋል፡፡

  መስታወት እየተመለከቱ ራስን እየጠየቁ፣ የምሳተፍበት ጉዳዩ በትክክልም ያስፈልኛል ወይስ አያስፈልገኝም የሚለውን ማረጋገጥ ግድ ይላል፡፡

  ይህ ደግሞ በሕይወት ውስጥ በራስ በመተማመን ስሜት ነገሮችን ለመወሰን እና የምንፈልገው እንዲሳካ ያግዛል፡፡

  በአጠቃላይ መስታወትን እየተመለከቱ ራስን መገምገም፣ ከፍርሃት እና ሌሎች አካላዊም ሆነ ስነልቦናዊ አሉታዊ ተጥፅዕኖዎች እንድንርቅ ያደርጋል፡፡

  ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

   

  Read more »