PLANET ETHIOPIA
Advertisment

Poems and Writings ግጥምና ወግ


 • በውቀቱ ስዩም-ሲያትል በተደረገው የዲያስፖራ የግርኳስ ውድድር አስመልክቶ የከተባት ወግ

  በውቀቱ ስዩም

  ©2017

  To be honest with you ሲያትል በተደረገው የዲያስፖራ የግርኳስ ውድድር ወደ ሚደረበት ስቴዲየም የሄድኩት ከማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት ጋር ሳልነካካ መፅሃፌን ሸጬ አገሬ ለመግባት ነበር፤

  (ከመፅሃፍ ሻጭ የሚገኘው ገቢ አስር በመቶ ለእኔ ሲሆን ፤ ቀሪው ለቤት አከራየ ለጋሽ ጣሰው መጦርያ ይሆናል)

  እና እዚያ ስደርስ፡ ከመላው አሜሪካ የመጣ ህዝበ -ዲያስፖራ ወደ ስቴድየሙ በር ይንቆረቆራል፤

  የስደት ወዳጁን ለማግኘት የመጣ! ያበሻ ፊት ናፍቆት የመጣ! የነገስታት ፊት የታተመበት ካናቴራ ሊቸበችብ የመጣ! የመጨረሻ የጠበሳ ሙከራ ለማድረግ የመጣ! የእግኳስ ፍቅር ነድቶት የመጣ::ዝምብሎ መሄጂያ አጥቶ የመጣ:: በየፍላጎቱ ተመርቶ የመጣ ያገርሰው -ስቴድየሙን ወረሰው::

  ከሜዳው ራስጌ ላይ ባለው ስፍራ ላይ የሸቀጥ መሸጫ ድንኳኖች ተደርድረዋል፡፡

  አንዱ ድንኳን አጠገብ ሄጄ ቆምኩ፡፡ ወደ ድንኳኑ በር ስመለከት”የኢሳት ቲሌቭዥን ጊዚያዊ ጣቢያ “የሚል ፅሁፍ ጋር ተገጣጠምሁ:: ፈጠን ብየ ስልታዊ ማፈግፈግ አረግሁ:: አፈግፍጌ የተጠለልኩበትን ድንኳን ቀና ብየ ሾፍ ሳረግ” ኢህአፓ” የሚል ተፅፎበታል:: አጥብቄ ሮጥሁ :: በመስኩ ላይ እንደቄጤማ የተነሰነሰ” ቦይኮት ጎሳየ ተስፋየ” የሚል ማሳደሚያ ፖስተር እየደቀደቅሁ ሮጥሁ:: ግን ብዙ አልሮጥኩም:: የብሬ ነጋ መልክ የታተመበት ቲሸርት የለበሰ ወጣት ጋር ተላተምኩ:: ወጣቱ ማጅር ግንዴን ይዞ ሰልፊ ሊነሳ ሲጥር አምልጨው ሸሸሁ:: በዚህ አይነት ሳፈገፍግ ከስቴድየሙ ልወጣ ትንሽ ነበር የቀረኝ::

  በመጨረሻ “በውቄ ከፈለግህ ይህን ጠረጴዛ መጠቀም ትችላለህ” የሚል ድምፅ ሰማሁ፤

  ዞር ስል የፌስቡክ ባለንጀራየ አዲስ ናት:: ከባለቤቷ ጋር ሆነው አንድ ጠረጴዛ አዋሱኝ:: ጠረጴዛው ላይ መፃህፎቼን ዘርግቼ ሸማች መጠባበቅ ጀመርሁ::

  ብጠብቅ ብጠብቅ ብጠብቅ መጣፌን አደለም የሚገዛ ዞር ብሎ የሚያይ የለም::

  ፒፕሉ ተጉዳይ ሳይጥፈኝ ተፊትለፊቴ እየተጋፋ ይነጉዳል:: በጋ ስለሆነ ወንዱም ሴቱም ባለቁምጣ ነው:: ለምን እንደሆን እንጃ ከሰሜ ባላገሩ በቀር ቁምጣ የሚያምርበት ያበሻ ወንድ ገጥሞኝ አያውቅም:: ሰሜ ባላገሩ ያን የመሰለ አርበ -ሰፊ ቅልጥም ይዞ ለምን ለብሄራዊ ቡድናችን እንደማይጫወት አይገባኝም:: ያብዛኞቻችን እግር በቁምጣ ማሃል ሲታይ የመፈክር እጀታ ይመስላል:: ቁምጣን ሴቶቻችን ይታጠቋት!! የተልባ ማሻው ሚካየል ያለህ! ያንዲቱ እግር ላይ አይኔን ተክየ ያለሁበትን ረሳሁ:: የድሃ አገር ተወላጅ መሆኔን ረሳሁ:: ከነጋ አንዲት መፃፍ እንኳን አለመሸጤን ረሳሁ:: ልጂቱ ይባስ ብሎ በታፋዋ ላይ የይሁዳ አንበሳን ተነቅሳዋለች:: ተራማጁ ሰውየ በሰኮንድ የድሮ ናፋቂ ሆንሁ:: ወያኔ ነፍስህ አይማርም! ስንት መንደፍያ እግር በቸርቺል ጎዳና እየተርመሰመሰ አሁን ይህን የመሰለ ታፋ መሰደድ ነበረበት?

  ዞር ስል አንድ ጎረምሳ ሚጢጢ ባንዲራ በሁለት ሁለት ዶላር ሲቸበችብ ሾፍኩት:: ግዞተኛው እየተጋፋ ይሸምታል::

  ባንዲራ ሻጩ በግራ እጁ የኪሱን ተርዚና በዶላር እየወጠረ በቀኝ እጁ በያዘው ማይክ ” እንዲህ ነው ኢትጵያዊነት !” እያለ ያሟሙቃል::

  ከሁለት ሰአት ጥበቃ በኃላ አንዱ መጥቶ መፅሀፍ ገዛኝ:: ማመን አቃተኝ::

  እጄን ትከሻው ላይ ጭኘ እንዲህ ስል መረቅሁት::

  “እጅህን ከቁርጥማት -ጉሮሮህን ከቢራ ጥማት ይሰውረው:: ከይሉኝታ ቢስ ቀፋይ- ጠላ ጋብዞ ውስኪ ከሚያስከፍል ግብር አስከፋይ -ይሰውርህ!

  ደስታህ ፍፃሜ አይኑረው:: ሞትህን ያስቀረው:: ካልሆነ አሟሟትህን ያሳምረው- እግርህን በቀይ ምንጣፍ ላይ ያውለው- ስንቅህን ያክብደው እዳህን ያቅለለው- አለባበስህን ፋሺን-ኪስህን ATM ማሺን ያርግልህ-ምቀኛህን ለዘብጥያ ይዳርግልህ..

  ጠላቶችህ እንደባዘቶ ይዳመጡ-ሽንት ቤት ሲቀመጡ-ይበርታባቸው ምጡ-“

  በመጨረሻ ያትላንታው ወዳጄ ፊደል -ኮስታሮ ከፊቴ መጥቶ ተገተረ::

  “ይሄ ነገር ተዝፍዝፎ ቀረ እንዴ?” አለኝ ወደ መፃፌ ባገጩ እየጠቆመ::

  እንግዲህ ምን ማድረግ ይቻላል ?! በሚል አይነት እጄን ዘረጋሁ::

  “ለመጣፍ ሽያጭ ማስታወቂያ ወሳኝ ነው!! አሁን ተመልከት እንዴት እንደምቀውጠው!” አለና ከመፃፌ መካከል ሁለት አንስቶ ያዘ:: ከዚያ በቀኝ እጁ ይዞት የነበረውን ጥሩንባ አውጥቶ ድብልቅልቅ አድርጎ ነፍቶ ” እንዳያመልጣችሁ” ብሎ ጮኸ::

  የጥሩባውን ልፈፋ ተከትሎ ብዙ አጃቢ ከበበን:: ከከባቢዎች አንዱ ጠጋ አለና እንዲህ አለ::

  “ነፍሴ! እሱን ጥሩንባ ስንት ትሸጥልኛለህ?”

   

  Read more »

 • ፓንክረስት ሞተ ይላሉ

                                            በዳንኤል ክብረት    
                                            
  ፓንክረስት ሞተ ይላሉ
  አያፍሩም ደግሞ ይዋሻሉ፤
  ታሪክን እንደነዳጅ ቆፍሮ
  ለቅርስ እንደ ውርስ ተከራክሮ
  ላልተወለደባት ምድር ከተወላጅ በላይ ለፍቶ
  በደም ከወረሷት በላይ በፍቅር ልቧ ውስጥ ገብቶ
  ከእናቱ እስከ ልጁ - ለጦቢያ ልቡን ሠውቶ
  በትውልድ ማማ ላይ ቆሞ የጸናውን ጌታ
  ሞቷል እያለ ይዋሻል ታሪክ የጠላ ቱማታ፡፡
  ኢትዮጵያዊነት ቅኔ ነው
  ብርቱ እንደ ፓንክረስት የሚነጥቀው
  ሞኝ እንደ ከመዳፉ የሚቀማው፡፡
  ኢትዮጵያዊነት ጸጋ ነው
  ልባም እንደ ዐሉላ የሚቀባው
  ሞኝ እንደ ባንዳ የሚነሣው፤
  ስንቱ ከማዕዘናተ ዓለም
  እንደ ኦሎምፒክ ከትሞባት
  ባተወለደባት ምድር
  እትብቱን አምጥቶ ሲቀብርባት
  ከደጁ ሞፈር ሲቆረጥ
  ጅላጅል ቆሞ አንጎላጀ
  ኢትዮጵያ ውስጥ ተወልዶ
  ሐበሻ ሳይሆን አረጀ፡፡
  እንዲህ ያለው ልብ አልባ
  ልባሙን ሞተ ይለዋል
  በትውልድ ማማ ላይ ያለ
  መቼ ልብ ሰጥቶ ይሰማዋል፡፡
  ፓንክረስትማ አልሞተም
  በኢትዮጵያ ልብ ይኖራል
  በዐጸደ ነፍስ ሆኖ
  ጠላቷ ፍግም ሲል ያያል፡፡
  የካቲት 10 ቀን 2009 ዓም
  Read more »

 • ሕዝብ ለመሪው በሦስት ደረጃ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል፡፡ (ከዳንኤል ክብረት) - People's Three Stages of Warning for Their Leaders by The People

   
   
   
   
  ከዳንኤል ክብረት
  ሕዝብ ለመሪው በሦስት ደረጃ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል፡፡ የመጀመሪያው ‹አርም› የሚል ነው፡፡ በዚህ ደረጃ ሕዝቡ ሦስት ነገሮችን አምኗል ማለት ነው፡፡ አንድም መሪው በጎ ኅሊና አለው፤ ለማረም የሚችል ዐቅም አለው፤ ችግሩ የተፈጠረው ከአሠራሩ ላይ ነው ብሏል፡፡ አንድም ደግሞ ሕዝቡ መሪው እንደማንኛውም ፍጡር ተሳሳተ እንጂ ራሱ ስሕተት አይደለም፡፡ ስለዚህ ሊያርም ይችላል ብሎ አምኗል፡፡ በመጨረሻም ሕዝብ መሪውን ይወዳል፣ ስሕተቱን ግን ይጠላል ማለት ነው፡፡
   
  እዚህ ላይ የደረሰ መሪ የታደለ የሚሆነው ስሕተቶቹን ነቅሶ ‹ሳይርቅ በቅርቡ፣ ሳይደርቅ በርጥቡ› ለማረም ከቻለ ነው፡፡ የሚሳሳት ፈጣሪ እንደሌለ ሁሉ የማይሳሳት መሪ የለም፡፡  መሪዎችን ታላቅና ታናሽ የሚያደርጋቸው ስሕተታቸውን ለማመንና አምነውም ለማረም ያላቸው ዐቅምና ቁርጠኛነት ነው፡፡ መሪ የሕዝቡን ጥቆማ ሰምቶ፣ የሕዝቡንም ልብ አድምጦ ችግሩን በጊዜ ካረመ ስሕተቱ ከሥራ የመጣ እንጂ ከመሪው ጠባይ የመነጨ አይደለም ብሎ ሕዝብ በመሪው እንዲተማመን ያደርገዋል፡፡ ‹ከሰው ስሕተት፣ ከብረት ዝገት አይጠፋም› ብሎ ያልፈዋል፡፡ ሕዝብ የነገረውን ስሕተት ከማረም ይልቅ ‹እኔ ደኅና ነኝ ችግሩ ከአፈጻጸሜ የመጣ ነው› እያለ ችላ ካለው ሕዝብ ወደ ሁለተኛው ደረጃ ይሻገራል፡፡ ጃን ሜዳ ሠፍሮ እያደመ ራስ ተፈሪን ወደ ዙፋን ያመጣው መሐል ሠፋሪ ጦር (ሠራዊቱ) ነበር፡፡ በኋላም አርሙ ቢላቸው አላርም ሲሉ በ1953 መፈንቅለ መንግሥት ያደረገው ይኼው ሠራዊት ነው፡፡
   
  ሁለተኛው የሕዝብ ማስጠንቀቂያ ‹ታረም› የሚል ነው፡፡ ሕዝብ  መሪውን ‹ታረም› ካለ ሁለት ነገሮችን አስቧል፡፡ ‹መሪው ልክ ነበር ነገር ግን  እንደማንኛውም ፍጡር ተሳስቷል› የሚለው ሐሳቡን ቀይሯል፡፡ ‹መሪው ስሕተቱን ሊያርም ይችላል› ከሚለው ወጥቷል፡፡ ይህንን ዕድል ላይመለስበት አልፎ መሪው ስሕተት የሚሠራ ሳይሆን ስሑት (የተሳሳተ) መሪ ነው፡፡ ስሕተቱ ከሥራ ሂደት ሳይሆን ከአመራሩ፣ ከአስተሳሰቡና ከአካሄዱ የመጣ ነው፡፡ ተግባሩ እንዲስተካከል መሪው መስተካከል አለበት ብሎ ሕዝቡ አምኗል ማለት ነው፡፡ ከኩርንችት በለስ፣ ከአጋምም ወይን ሊለቀም አይችልም፡፡ ውኃው እንዲስተካከል ምንጩ መስተካከል አለበት ብሎ ሕዝብ ማሰብ ጀምሯል፡፡ እንደዚያም ቢሆን ግን መሪው ራሱን ሊያረም የሚችል መሪ ነው ብሎ አምኗል፡፡
   
  በዚህ እከን ላይ የደረሰ መሪ ራሱን ፈትሾ፣ መርምሮና አንጥሮ እንደ ወይን ግንድ እየገረዘ ሸለፈቱን መጣል አለበት፡፡ ሌላውን ሰውነት ለማዳን ሲባል ሕመምተኛው የሰውነት አካል እንደሚቆረጠው ሁሉ ሀገርን ለማዳን ሲባል የሚቆረጡ አሠራሮች፣ አስተሳሰቦች፣ አካሄዶች፣ መሪዎች፣ ፖሊሲዎችና መርሖች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ‹ታረም› የተባለ መሪ እነዚህን አርሞ እንደ እባብ ሳይሆን እንደ ንሥር ታድሶ ከመጣ፤ ጥፋቱ ከአፈጻጸሜ የመጣ ነው፣ ሕዝቡ ስላልገባው ነው፣ ስላልተማረ ነው፣ ስላልሠለጠነ ነው፣ እያለ የመሥዋዕት በግ ፍለጋ ካልኳተነ፤ ‹ችግሩ እኔ  ነኝ፤ መፍትሔውም የእኔ መለወጥ ነው› ብሎ ካመነ፤ አምኖም ከሠራ፤ ሠርቶም ከተለወጠ፡፡ ሕዝቡ፡-
  ‹አሁን ወጣች ጀንበር
  ተሸሽጋ ነበር› ብሎ ይቀበለዋል፡፡
  ይህንን ሁሉ ትቶ መሪው በሕዝቡ ትዕግሥት ላይ ከቀለደ፤ ሕዝብም ለትዕግሥቱ ምላሹ ካለፈው የባሰ፣ ከተስፋው ያነሰ ሲሆንበት፤ ሕዝብ አመለካከቱን ይቀይራል፡፡ አርም፣ ታረም ማለት ዋጋ አልባ መሆኑን ይረዳል፡፡ ሊያርም ሊታረም የሚችል መሪና አመራር የለም ብሎ ያምናል፡፡ ችግሩ መሠረታዊ ነው ብሎ ይረዳል፡፡ በዚህ ጊዜ ሦስተኛውንና የመጨረሻ ማስጠንቀቂያውን ይሰጣል፡፡ ንጉሥ ኃይለ ሥላሴን ሆ ብሎ ወደ ሥልጣን ያመጣው ወታደር፣ ስሕተቶቻቸውን ማረም ሲያቅታቸው በ1953 መፈንቅለ መንግሥት ያደረገው ወታደር፤ በ1966 ደግሞ ሥልጣናቸውን አሳጣቸው፡፡ የ1953ቱ መፈንቅለ መንግሥት ‹ታረም› የሚል መልእክት እንዳለው ንጉሡ ቢረዱ ኖሮ የ66ቱን ነገር ያስቀሩት ነበር፡፡ ግን አልሆነም፡፡ ‹ታረም› የሚለውን አልረዳ ሲሉ ‹ተወገድ› የሚለው የመጨረሻው ማስጠንቀቂያ መጣ፡፡ 
   
  ደርግም እንዲህ ነበር፡፡ በ66 አብዮቱ ሲፈነዳ፣ መሬት ላራሹ ሲታወጅ የሕዝብ ድጋፍ ነበረው፡፡ ቆይቶ ስሕተት ሲያበዛ ‹አርም› የሚለው መልእክት ከያቅጣጫው መጣ፡፡ ሰልፎች፣ ወረቀቶች፣ ተቃውሞዎች መጡ፡፡ ከማረም ይልቅ ‹መረምረም› ስለመረጠ የመጀመሪያውን ዕድል አሳለፈው፡፡ ከውስጥና ከውጭ ጠብመንጃ አንሥተው ግራ ቀኝ የወጠሩት ኃይሎች ‹ታረም› ቢሉትም መታረም ትቶ ማውደምን መረጠ፡፡ የ1981 ዓም መፈንቅለ መንግሥት ‹ተወገድ› የሚለውን መለከት ነፋ፡፡ ደርግ የሚተርፍ መስሎት ለፋ፡፡ ግን ተወገድ ከተባለ በኋላ መትረፍ በተአምር ብቻ ነበርና ሊተርፍ አልቻለም፡፡
   
  ይህ ‹ተወገድ› የሚለው ሦስተኛው  ማስጠንቀቂያ የመጨረሻው የሕዝብ ጥያቄ ነው፡፡ መሪው ታምሞ አይደለም፡፡ ራሱ በሽታ ነው፡፡ ተቸግሮ አይደለም፡፡ ራሱ ችግር ነው፡፡ ደክሞ አይደለም፡፡ ራሱ ደካም ነው፡፡ ተፈትኖ አይደለም፤ ራሱ ፈተና ነው ብሎ አምኗል፡፡ ስለዚህም መፍትሔው መወገድ ብቻ ነው ብሎ ይቆርጧል፡፡ ቆርጦም ይሠራል፡፡ ሕዝብ እዚህ ደረጃ ከደረሰ በኋላ መመለስ ብዙ ጊዜ ከባድ ነው፡፡ ማረምንም መታረምንም ከሚቀበልበት እርከን አልፏልና ቀሪው ዕድል የሚሆነው በሰላም መሰናበት ነው፡፡
   
  የአንድ መሪ ብስለት በሁለት ደረጃ ይለካል፡፡ የመጀመሪያው ሲቻል በፊተኛው፣ ሳይቻል በቀጣዩ ደረጃ ላይ መንቃት፣ ነቅቶም  ተገቢውን ማድረግ፡፡ ያም ዘመን ካለፈና ጀንበር ካዘቀዘቀች ደግሞ ራሱንም ሀገሩንም ሳያጠፋ መልካም የወንድ በር ማዘጋጀት ነው፡፡
  ዘቦ እዝን ሰሚዐ ለይስማዕ፡፡  
  Read more »

 • ዋ.....ተማሪ መሆን

   

                                      

            ኣንደኛ ክፍል ትምርት ስጀምር፤ የመማርያ ክፍላችን ተሠርቶ ኣልተጠናቀቀም ነበር፡፡ እና ከክፍሉ በር ተነስተን መቀመጫ ወንበራችን ላይ እስክንደርስ ድረስ ጉቶ ያደናቅፈን፣ ሰርዶም ይጠልፈን ነበር፡፡

  መምህሩ ከታች እያስተማረ ከሰሌዳው ራስጌ፤ ኣንድ ቀጫጫ ኣናጢ መሠላል ላይ ቆሞ ጣራውን መመዶሻ ሲወቅር ኣይቸዋለሁ፡፡

  መምህራችን ኢትዮጵያ በቀንድ ከብት ካፍሪካ ኣንደኛ መሆኗን ሲተርክልን ከላይ ያለው ኣናጢ”ምነው ዲስኩሩን ትተህ ተጠመኔው ኣጠገብ ያለችትን ቢስማር ብታቀብለኝ“ እያለ ያናጥበዋል፡፡

  ተማሪ ቤትን ሳስብ ትዝ የሚለኝ ዩኒፎርም ነው፡፡ የዩኒፎርም ዓላማ በደሃና በሃብታም ተማሪዎች መካከል ያለውን ልዩነት ማጥበብ ነው፡፡ግን ሃብታሞች ሁሌም ብልጫቸውን ኣስጠብቀው መቆየት ይፈልጋሉ፡፡ ለዚህም በረቂቅ መንገድ ይፋለማሉ፡፡

  ትምርት ቤቱ ሁላችንም ደማቅ ሰማያዊ ቀለም ያለው ዩኒፎርም እንድለብስ ያስገድድ ነበር፡፡ ሃብታሞች በቀለሙ ተስማምተው ለልጆቻቸው ኣንደኛ ደረጃ ጨርቅ ይመርጡላቸዋል፡፡ በሚይዙት የደብተር ቦርሳ በሚጫሟት ጫማ ለየት ብለው እንዲታዩ ያደርጓቸዋል፡፡

  እኛ የድሃ ልጆች ዩኒፎርማችን ለትምርት ቀሰማ ብቻ ሳይሆን ለእንጨት ለቀማም ስለምንጠቀምበት ከሁለት ወር በኋላ ቀለሙን ይቀይራል፡፡ ቁልፉ ረግፎ በድዱ ብቻ ይቀራል፡፡ እነ መርፌ ቁልፍ የረገፈውን ቁልፍ ተክተው ኣገልግሎት ለመስጠት ይታገላሉ፡፡

  በጊዜው ተሽከርካሪ ወንበር ስላልነበረ በሰለቸን ቁጥር እኛው ራሳችን ወንበራችን ላይ ከመሽከርከር ውጭ ኣማራጭ ኣልነበረንም፡፡ ኣሁን ሳስበው ፤ ክፍል ውስጥ እንጎለትበት የነበረው ነገር ኣግዳሚ ወንበር የሚል ስም ይበዛበታል፡፡ ሁለት እግር ያለው የወደቀ የብሳና ግንድ ተብሎ ቢጠራ ያምርበታል፡፡ ግማሽ ቀን ተቀምጨበት ስነሳ መሃረብ የሚያክል ጨርቅ ከሱሪዬ ላይ ቆርሶ ያስቀራል፡፡ የፊዚክስ መምህር ሰለ ሰበቃ friction ባሰተማረ ቁጥር ለምሳሌነት የሚጠቅሰው የኔን ሱሪ ነበር፡፡ የሰፈራችን እውቅ ልብስ ሰፊ የተለያየ ቀለምና የጥራት ደረጃ ባላቸው ትርፍራፊ ጨርቆች በመጣጣፍ በነተበው ሱሪዬ ላይ ነፍስ ለመዝራት ሞከሩ፡፡ ሙከራው መቀመጫዬ ኣካባቢ የጥንቱን ያለም ካርታ የሚመስል የጨርቅ ምስል በመሳል ተጠናቀቀ፡፡

  ተማሪ ቤት ሲነሣ ጋሽ ዮሴፍ ያቆብን ሳላነሣ ማለፍ ኣይሆንልኝም፡፡ጋሽ ዮሴፍ ወፍራም ነበሩ፡፡ ቦርጭን ወደ ደብረማርቆስ ለመጀመርያ ጊዜ ያስገቡት ጋሽ ዮሴፍ ይመስሉኛል፡፡ ተዝያ በፊት ቦርጭ ምን እንደሆነ ያየነው መስከረም በተባለው መጽሄት ላይ በሚሳለው የኢምፔሪያሊዝም ካርቱን ስእል ላይ ነው፡፡ በመጽሄቱ የመጨረሻ ገጽ ላይ ኢምፒየሪያሊዝም ከትንሽ ህጻን ልጅ ኣፍ ጡጦ ቀምቶ ሲጠባ ይታያል፡፡ ደርግ፤ ቦርጭ ካድሃሪው ስርኣት የተወረሰ ኣካል ነው ብሎ ስለሚያምን ቦርጭ ማውጣትን በህገመንግስቱ ከልክሎ ነበር፡፡ጋሽ ዮሴፍ ከሶስት መቶ ብር ደመወዝተኛ የማይጠበቅ ቀፈት በማውጣታቸው ኣቃቤህግ ከሰሳቸው፡፡ ክቡር ፍርድቤቱ የግራና የቀኙን ክርክር ኣዳምጦ የኣምስት ወር ጂምናስቲክ ፈረደባቸው፡፡

  ጋሽ ዮሴፍ ሁሌም በግራ ብብታቸው ስር የተጣጠፈ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ይይዛሉ፡፡ በዚያች ጋዜጣ ኣምስተኛ ገጽ ላይ ታላቅ ልጃቸው ፤ ወላጅን ስለማክበር የጻፈው ግጥም ታትሟል፡፡ የትምርት ምኒስትር የመደባቸው ጂኦግራፊ እንዲያስተምሩ ነበር፡፡ ልጃቸው ግጥም ካወጣ በኋላ በራሳቸው ጊዜ የስነግጥም መምህር ሆኑ፡፡ ፈርዶብን የሳቸውን ልጅ ግጥም በቃል ስንወጣ ውለን ወደ ቤታችን እንሄዳለን፡፡ ያንን የቸከ ግጥም ስሸመድድ ኖሬ ግጥም ኣለመጥላቴን ሳስብ ይገርመኛል፡፡

  ጋሽ ዮሴፍ “መኣድን” የተባለ ትንሽ ልጅ ነበራቸው፡፡ መኣድን የተባለው ወድቆ ስለተገኝ ነው፡፡ ክፍል ሲመጡ እንደ ቡችላ ተከትሏቸው ይመጣል፡፡ ከኛጋ ትንሽ ሲማር ከቆየ በኋላ ይሰለቸዋል፡፡ ከዚያ ብድግ ይልና ከተማሪዎች መካከል ትንሽ ኣናት ያለውን ተማሪ መርጦ በቴስታ በመምታት ይዝናናል፡፡ ኣልፎ ኣልፎ ኣባቱ እያስተማሩ እሱ ድምጡን ከፍ ኣድርጎ ይዘምራል፡፡ መዝሙሪቱ...
  “ሰባትና ሰባት ሲደመር ኣስራ ኣራት
  መንግስቷይለማርያም የጨለማ መብራት”
  የምትል፤የሂሳብ ስሌትን እና የግለሰብ ኣምልኮን ኣስተባብራ የያዘች መዝሙር ነበረች፡፡

  እስከ ሶስተኛ ክፍል በሂሳብ ጎበዝ ተማሪ ነበርሁ፡፡ ሶስተኛ ክፍል ስደርስ እትየ ስለናት የተባለች መምህር ገጠመችኝና በሂሳብ ብቻ ሳይሆን በሰው ልጅ ካለኝ እምነት ጋር ኣቆራረጠችኝ፡፡ የሆነ ብዜት ትጠይቀኝና ስሳሳት ና ወዲህ ውጣ ትለኛለች ፡፡ ገና እንደወጣሁ ከስጋና ከጅማት የተሰራ መንሽ በሚያክል መዳፏ በጥፊ ትከድንብኛለች፡፡ ኪራላይሶ ! የሰው ልጅ ሳይወልድ ኣይኑን ባይኑ ማየት እንደሚችል የተረዳሁት ለመጀመርያ ጊዜ የትየ ስለናት ጥፊ ፊቴ ላይ ሲያርፍ ነው፡፡

  እትየ ስለናት ከማስተማር ውጭ ያለውን ጊዜዋን የምታሳልፈው ሻረው የተባለውን ጓደኛየን በመግረፍ ነበር፡፡ ”የምትገረፍበትን ለበቅ ቆርጠህ ኣምጣ “ ትለዋለች፡፡ ሻረው ከክፍል ይወጣና ጓሮ በበቀለው ጫካ ውስጥ ገብቶ ይንጎራደዳል፡፡ እጁን ወገቡ ላይ ኣድርጎ እያንዳንዱን ቅርንጫፍና ቅጠል በጽሞና ሲቃኝ በእጽዋት ላይ ምርምር የሚሰራ እንጂ ኣርጩሜ የሚቆርጥ ኣይመስልም፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ በመስኮቱ ብቅ ብሎ እጩ ኣርጩሜውን እያሳየ ”ይቺ ትሁን እትየ?“እያለ ያማርጣታል፡፡ እሷም እንደ ሸማች "ትንሽ ጨምርበት" ምናምን ብላ ተከራክራ ስትጨርስ ኣንበርክካ ታበራየዋለች፡፡ ኣሁን ሳስበው፤ ትምርት ቤታችን በትምህርት ሚኒስትር ስር የሚተዳደደር ራሱን የቻለ የቶርች ካምፕ ኑሯል፡፡ የወህኒ ቤት ገራፊዎች ስርኣት ሲለወጥ ለፍርድ ይቀርባሉ፡፡ የትምርት ቤት ገራፊዎች ግን መምህር በሚል የክብር ልብስ ተሸፍነው ተከብረው ይኖራሉ፡፡

  ኣረጋ ተሰማ የተባለ ቀውላላ ላይበራሪያን ያደረገኝን እንዴት ረሳዋለሁ፡፡ ጋሽ ኣረጋ በላይበራሪያንነት የተመደበው ከትልቅ መደርደርያ ላይ መጽሃፍ ለማውረድ የሚያስችል ቁመት ስላለው መሆን ኣለበት፡፡ ኣብማ ትምርትቤት ስማር በሳምንት ኣንድ ቀን የንባብ ክፍለጊዜ ነበረን፡፡ ወይ ንባብ! ክፍለጊዜው ኣርባ ደቂቃ ብቻ ቢሆንም ከሰላሳ ደቂቃ በላይ ያለውን ጊዜ የምናጠፋው ያረጋ ተሰማን ኣሰልቺ መመሪያ በመስማት ነው፡፡

  "መመሪያ ኣንድ ! ጸጥታ! ማንኛውም የላይበራሪው ተጠቃሚ ማውራትም ሆነ ማንሾካሾክ ኣይጠበቅበትም፡፡ እደግመዋለሁ ማውራትም ሆነ ማንሾካሾክ ኣይጠበቅበትም"

  "መመርያ ሁለት ጽሞና፡፡ ማንኛውም ተማሪ ጽሞና ማሳየት ይጠበቅበታል”

  ትዛዙ ስድሳ ድረስ ይዘልቃል፡፡ መመሪያውን ተጠናቆ የመጀመርያውን ገጽ ስንገልጥ ክፍለጊዜው ማለቁን የሚያረዳው ደወል ይደወላል፡፡

  ኣንድ ቀን ኣላስችለኝ ስላለ ጋሽ ኣረጋ ሲዘበዝብ እኔ ከፊቴ የተቀመጠውን ”ለምለምና ጎሹ” የተባለ መጽሃፍ ገለጥ ኣርጌ ማንበብ ጀመርሁ፡፡

  “ውጣና ተንበርከክ“ የሚል ድምጽ ኣናጠበኝ፡፡ ኣረጋ ተሰማ ወለሉ ላይ በጥንቃቄ ኣንበርክኮ ያገጨን ኣቅጣጫ ሲያስተካክል ሊሥለኝ ለሞዴልነት እያመቻቸኝ እንጂ ለግርፍያ የሚያሰናዳኝ ኣይመስልም፡፡ በኋላ ወድያ ወዲህ እየተንጎራደደ ትእዛዛቱን ማዝነብ ቀጠለ፡፡ድንገት ግን ዞር ሲል እና እግሩ ሲወናጨፍ ትዝ ይለኛል፡፡ ከዝያ ወድያ ትዝ የሚለኝ ነገር ቢኖር መለስተኛ ኣውሎ ነፋስ ያነሳው ኣቧራ ክፍሉን መሙላቱ ነው፡፡ በዚያ መጅ እግር የግድያ ሙከራ ተደርጎብኝ መትረፌ ተርፌም ይችን መጻፌ ይገርመኛል፡፡ የድመት ነፍስ እና የተርምኔተርን ኣካል የሰጠኝ የወንቃው ጊዮርጊስ የተመሰገነ ይሁን፡፡ በኤክስሬይ ቢታይ ጋሽ ኣረጋ የጫማ ምልክት ጉበቴ ላይ ሳይኖር ኣይቀርም፡፡

  ከእለታት ኣንድ ቀን ይመር የተባለ ጓደኛችን ወለላ ለተባለች ልጅ ኣፍቅሮ ደብዳቤ ጻፈላት፡፡ ደብዳቤው በደብተር ውስጥ ተሸሽጎ ከእጅ ወደ እጅ ሲዘል ቆይቶ ለተፈቃሪዋ ሳይደርስ በቁጥጥር ስር ዋለ፡፡

  ኣንድ ቀን ማለዳ ላይ ባንዲራ ከተሰቀለ በኋላ ይመርና ወለላ ወደ መድረኩ እንዲወጡ ተደረገና ደብዳቤው ለተማሪው ሁላ ተነበበ፡፡ ርእሰ-መምህራችን ደብዳቤውን ይዞት ወደ መደረኩ ሲወጣ ኣቤት ፊቱ ላይ ይታይ የነበረው ኩራት! የመፈንቅለ መንግስት ሴራ ያከሸፈ እንጂ የሁለት ምስኪኖችን የፍቅር ደብዳቤ የዘረፈ ኣይመስልም፡፡ ከደብዳቤው ውስጥ ኣንድ ሃረግ በተነበበ ቁጥር ተማሪው ሲያወካ ከውካታው እኔም ያቅሜን ኣዋጥቻለሁ፡፡ በጊዜው በይመርና ወለላ “ብልግና” ተቆጥቸ በውርደታቸውም ረክቼ ነበር፡፡ የሁለቱ ፍቅረኛሞችን ግላዊነት ከደፈሩት ጋር መተባበሬ ፤ህሊናን ቶርች ከሚያደርጉት ጋር ማበሬ የገባኝ ኣሁን ነው፡፡

  ይህ በእውነተኛ ገጠመኝ ላይ የተመሰረተ ኩሸት ነው፡፡ 
  ግን ብዙዎቻችሁ ያሳለፋችሁት ልጅነት ከዚህ መንፈስ እንደማይወጣ እገምታለሁ፡፡

  በተማሪ ቤት ያስተዋልነው የጉልበተኛ መምህሮችና ያቅመቢስ ተማሪዎች ግኑኝነት ከትምርት ቤት ስንወጣ የቀረ ከመሰለን ተሳስተናል፡፡

  ባለቃና በምንዝር መካከል ያለው ግኑኝነት፤
  በኣከራይና በተከራይ መካከል ያለው ግኑኝነት፤ 
  በመንግስትና በገባሩ መካክል ያለው ግኑኝነት፤ 
  በዚህ ብሄርተኛና በዚያኛው ብሄርተኛ መካከል ያለው ግኑኝነት ፤ በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ያለው ግኑኝነት በትምርትቤታችን ኣምሳል የተዋቀረ ይመስለኛል፡፡
  .
  በ በዕውቀቱ ስዩም

  Read more »

 • እኔ ስለአቢሲኒያ.....

  እኔ ስለአቢሲኒያ.....

  እኔ ስለአቢሲኒያ.....
  ችጋር ስጠይቅዎ......

  ‹‹መራብ ያጋጥማል፣አይዞሽ አታልቅሺ
  ይልቅ እናስታውስ፣ታጠቂ ተነሺ

  እነንትና መችለት ፣ በብዙ ተርበው
  ንጉስ ዘንድ ቀረቡ፣እጣኑን ልጅ በልተው!!

  እኒያ ነጫጮቹ ፣ የሚቀምሱት ጠፍቶ
  ውሀ ነክረው ጋጡ፣ ጫማና ቀበቶ ››

  ያሉኝን ሰምቼ ፣ ምኞቴ በረታ
  እግሬ ጫማ የለው፣ልብሴም የተፈታ

  እንኩዋን ልጅ ሊኖረኝ ፣ ፋፍቶ የሚበላ
  ውሽማዬም ሞተ ፣ ሳይቀምስ የኔን ገላ

  ባሌ እግረ ቀጭን ፣ ሲበሉት ያቅራል
  እንኳን ቀን ሊያሳልፍ ፣ በትንታ ይገላል

  እናማ ይንገሩኝ ፣ ምን ልሁን በሞቴ
  ለግመጥዎ መሰል ፣ አማሩኝ ቅባቴ!

  ጃስ!.....ይሩጡ...........

  (ከቤተልሄም ኒቆዲሞስ)

  Read more »

 • ይሄውልህ ስማኝ!

  (ከቤተልሄም ኒቆዲሞስ)

  ጣቴን አንጨብርሬ ፡ ጠጉሬንም ነጭቼ
  አንዴ በንብርክኬ ፡ አንዴ ተደፍቼ
  ለስልባቦት ቀኔ ፤ ከሞት ለሰፈፈች
  ሰላም አልባ ነፍሴ ፤ ፍቅር ለታመመች
  ለምኜህ ነበረ ፤ አቅፍ ሙሉ ደስታ
  አንዲት ጀንበር ስቄ ፤ ባጭር እንድፈታ
  ከኑሮ ሰቀቀን ፤ ከሃፍረት መኝታ
  ሰውረኝ እያልኩኝ ፤ ስከተልህ ጌታ
  አንተም ከዳመና ፤ እኔም ከምድር ላይ
  ገምቶ የከረፋ ፤ የሰው ክፋት ስናይ
  ምሬት ሲያደባየኝ ፤ በተራዬ ስሸት
  የኔን ክፋት አይተህ ፤ ፈገግታህ ሲከተት
  አቆምኩኝ ማነፍረቅ ፤ ጀመረኝ ስርቅታ
  የልጅነት ልቤ ፤ አምቶኝ ወደማታ
  እውነት ነው ፈጣሪ ፤ አንተማ ልክ ነህ
  ድሮስ እጣን እንጂ ፤ መች ካዋቂ ውለህ
  እንዲህ ውብ ከሆነ ፤ ልጅነት ሲጠራ
  አሮጌ ሰው ቀርቶ ፤ ትልቅ ህጻን ስራ!

   

  Read more »

 • ጠቦትና አንካሳ

  ጠቦትና አንካሳ

  ተሰብሮ ሲያነክስ ፤ ሚሄድበት እግሩ
  ድውይ ሆኖ ጎኑ ፤ ሲበዛበት ጣሩ
  ጠቦት ብላ አሉት ፤ አዋቂ ወጌሻ
  ለወደቀ አካሉ ፤ ከመኝታ ማንሻ
  እውነትም ተሻለው ፤ ዳነና ዘለለ
  በጠቦቷ ታምር ፤ አገሩ ጉድ አለ

  ሌላ በሽታ............
  ቀዳሚ አንካሳ ፤ ሌላ ቀን ታመመ
  የደም ትክትክ ይዞት ፤ በሴስ አዘገመ
  እላይ ታች ባዘነ ፤ ሄዋንን ፍለጋ
  የሞቀ ስጋውን ፤ በስጋ ሊያረጋ
  ድንገት ትዝ ቢለው ፤ የወጌሻው ምክር
  የሄዋን ጠቦቶች ፤ ያፈላልግ ጀመር
  አንዲቷን አገኘ ፤ ባለለምዷን ግልገል
  መቅኒዋን ሊጠጣ ፤ ጀመረ መከተል
  አወይ ውሸት ጠቦት ፤ አወይ ለምድ ክፉ
  እሷ ዶሮ ሆና ፤ እሱ መለከፉ
  ጠቦት መስላው ስቦ፤ ከቅፉ ከተተ
  ቀምሶ እንኳ ሳይጠግባት ፤ ፈንግል ይዞት ሞተ!

  ከቤተልሄም ኒቆዲሞስ

  Read more »

 • ሰበር ዜና

  ሰበር ዜና
  ልማታዊው መንግስታችን ተደጋጋሚ የመብራት መጥፋትን አስመልክቶ እየቆመ ያለውን ውብ እና ዘመናዊ ባቡር ለሰርግ አዳራሽነት በኪራይ እንዳቀረበው አስታወቀ፡፡ኢቲዮ ቴሌኮምም ባቡሩ ውስጥ ለሚሞሸሩ የመጀመሪያዎቹ ሀምሳ ጥንዶች የኔትዎርክ ሽልማት እሰጣለሁ ሲል ታዲያስ አዲስ ደግሞ ሰርጋቸውን ‹በሰሞነኛ ወሬ› እንደሚቸፈችፍ ቃል ገብቷል፡፡

  ከቤተልሄም ኒቆዲሞስ

  Read more »

 • ልማት አደናቃፊ ውሾች.......

  ልማት አደናቃፊ ውሾች.......
  ትናንት ምሽት የሰፈራችን አየር በሚሰቀጥጥ የውሾች ለቅሶ ተመታ፡፡ ውሾቹ ወልደውና ተዋልደው አርባ አምስት ደርሰዋል፡፡ቆይ ቆይ እኔ የት እንደምኖር ለካ አልነገርኳችሁም....መጀመሪያ አዲስ አበቤ ሁላ ቆጥ ላይ ከምሰቀል ጭቃ ቤቴ ይግደለኝ ብሎ ንቆት አሁን ግን ከግድቡ ቀጥሎ እየተረባረበበት ባለው የኮንዶሚኒየም ህንጻ ላይ ነው፡፡እና ምን አለፋችሁ አንዱ ህንጻ በነፍስ ወከፍ በአርባ አምስት ውሾች ተከቦ ነው ምሽቱ የሚደራው፡፡ ተባእት ውሾች የቴዲ አፍሮን ‹ሰባ ደረጃ› እየዘፈኑ‹ሲመሽ ወደማታ ማታ ማታ አቤት ያንቺ ፍቅር ሲበረታ...› እያሉ(በውሽኛ) የቡችሎቻቸውን እናቶች ያሽኮረምማሉ፡፡ከድሪያው አለፍ ያለ ንቃተ ህሊና ያላቸው የማህበሩ አባል ውሾች ከመንጋቸው ነጠል ብለው የእግረኛ ውሾች መንገድ እንዲሰራላቸው ለሰፈሩ የሰው ኮሚቴዎች ደብዳቤ በመጻፍ ተጠምደው ለሊቱን ያጋምሱታል፡፡ስጋ ቤቶችን ‹በመጃለስ› ለአራስ ሚስቶቻቸው ቀለብ ያመጣሉ፡፡ቡችሎች ላልተፈለገ እርግዝና እንዳይጋለጡ እንዲሁም ውሻዊ ስነምግባርን ያልተከተለ የጾታ ግንኙነት እንዳይኖራቸው ደጋግመው ይመክራሉ፡፡ቡችሎቹም ከፋርማሲ ገብተው ‹ፖስት ፒል› መግዛት ስለማይችሉ አይቀብጡም፡፡ገና ተባእቶቹ ሲጠጓቸው ‹ሶሪ ካረገዝኩ ሼፔ ይበላሻል ...› እያሉ ወደ ቡድናቸው ይቀላቀላሉ፡፡እውነት ነዋ ውሻ አረገዘ ማለት ዶላር ወደብር ተመነዘረ ማለት ነው ፡፡ነፍ ነዋ የሚቀፈቅፉት!!
  የዛሬው ግን ለየት ያለ ነው፡፡መልአከ ሞትን ስኪኒ ሱሪ ለብሶ ሲመጣ ያዩታል የሚባሉት እኚህ ፍጡራን ማላዘን ጀመሩ፡፡እርግጥ ነው ጎረቤቴ ናቲ ሲመጣም አንዳንዴ በስህተት ያላዝናሉ፡፡ምክኒያቱን ከውሾቹ ጠይቄ እንደተረዳሁት ከሆነ የናቲ አቋምና ሱሪ ከፍንዳታው መልአከሞት ጋር በጣም ስለሚመሳሰልና የመንፈስ ራዳራቸው የቴክኒክ ብልሽት ስለገጠመው እንደሆነ ነበር፡፡ዛሬም ከሶስተኛው ቆጥ ላይ አንገቴን በመስኮቴ በኩል ብቅ አድርጌ የውሾችን ሰልፍ አይ ገባሁ፡፡ጆሮ ቆራጣው ‹አለም በቃኝ› የተለመደ ያስለቃሽነት ስራውን ጀምሮ በአንካሳ እግሩ እየተጎተተና በግራ አይኑ እያለቀሰ እዬዬውን ያስነካዋል፡፡ሌሎቹም አርባምናምን ውሾች ይቀበሉታል፡፡ድምጻቸው በጣም ስለመረረኝ ‹‹አንተ አለም በቃኝ ሰው ተኝቷልኮ! እንዴ ለደንቡስ ቢሆን ማለዳ ላይ ነውኮ መርዶ ሚነገረው!አሁን በጅቦች አየር ሰአት እየገባችሁ ሰፈሩን ለምን ትበጠብጣላችሁ?›› አልኩት አይኔን እያሻሸሁ፡፡‹‹አይይ ቢጩዬ ጉዳችሁን አላወቃችሁ ዛሬ አንድ ሰው እዚህ ሰፈር በህይወት አያድርም፡፡ሞት ከነሰራዊቱ ሲመጣ ይታየኛል ...ሳስበው ህንጻው ሊደረመስ ነው መሰለኝ..››አለና እዬዬውን ቀጠለ፡፡‹‹ስማ ...እና ህንጻው ይፈርሳል ነው የምትለኝ ... ምን ተሻለ?›› አልኩት ለክፉም ለደጉም የላጤ ቦርሳዬን በጀርባዬ አንግቤ ከቤቴ ለመውጣት እየተዘጋጀሁ፡፡እውነት ነዋ የአለም በቃኝ ውሻዊ ራዳር የመልአከሞትን ያገዳደል እቅድ አነፍንፎ ይሆናል፡፡ስለዚህ እውነትነቱን ካረጋገጥኩ መውጣቴ እዳው ገብስ ነው፡፡‹‹አይ እሱንኳ አልተረጋገጠም ግን ምን መሰለሽ አንዳንድ የግንባታ ግድፈቶች ስላሉበት ሰበብ እንዳይሆን ብዬ ነው፡፡አንቺ ግን አሪፍ ልጅ ነሽኮ ለምን ከኛ ጋር አትኖሪም?ከሰፊው ሟች ጋር ከመሞት ከኛ ጋር መቀየስ አያዋጣሽም? ››አለኝ ጭራውን እየወዘወዘ፡፡‹‹ኧረ ባክህ ብርዱንስ ማን ይችለዋል?››አልኩት በመስኮቴ በኩል የሚያጣፋኝን ውሽንፍር እየጠጣሁ፡፡‹‹እንዴ እኛ ምን ሆንን? ውሻ እንደሆነው ሆነሽ መዞር ነዋ! ›› አለኝ፡፡ ‹‹ኧ.....ረ! ውሻ እንደሆነው ሆኜ? አለም በቃኝ ትሰማለህ አሁን እኔ እንዳንተ ልሁን ብል ሰማይ ቤት ያሉት መላእክት ራሱ እንኳን ከሞት ሊያሰጥሉኝ ይቅርና ‹ደሞ እንደውሻ ከካፖርት የወፈረ ጸጉር የተገጫት መስሏት መላጣ እንብርቷን ይዛ ከቤት ወጣች› ብለው ሙድ ይይዙብኛል፡፡በዛ ላይ ከነሙቀቴና ወዜ ብሞት ይሻለኛል እንጂ ሸማቾች ሱቅ በር ላይ ለሊቱን በአስረሽ ምቺው ከንዳንተ አይነቶች ጋር መጨፈር አልፈልግም›› አልኩት፡፡እሱም በጣም ተስፋ በቆረጠ መንፈስ ‹‹አይይ ቢጩዬ ....ከሰው ሁሉ ያንቺ ሞት ቆጨኝ አውውውው.....›› ብሎ ማላዘን ሲጀምር ጀሌዎቹም ተከተሉት፡፡ድንገት ሁለተኛ ቆጥ ላይ የምትኖረው አልማዝ ነጭ ሽንኩርት ልትነለቅጥ ጠዋት ከኮብልስቶኑ መንገድ ላይ የነቀለቻቸውን ሁለት ድንጋዮች ይዛ በመስኮቱ በኩል ብቅ አለች፡፡ድንጋዮቹን በብርሀን ፍጥነት እነ‹አለም በቃኝ› ቡድን ላይ አዘነበቻቸው፡፡ውሾቹም‹‹አይ ...›› ብለው ተበተኑ፡፡‹‹ምናባታቸው ሟርተኛ ልማት አደናቃፊ ሁላ.....ከዚህ በኋላ ድርሽ ትሉና ደግሞ አመዳሞች!ልጄን እኮ አላስተኛ አሏት ...›› ብላ ተመልሳ መስኮቷን ዘጋች፡፡እኔም መጋረጃዬን ጋረድኩ፡፡ህይወት ይቀጥላል፡፡ እንደማልሞት ስለገባኝ ቦርሳዬን ከቤቴ ወለል አሳረፍኳት፡፡የአልማዝ‹ልማት አደናቃፊ› ውሾችም ሞትን ሊሰብኩ ወደሌላ ብሎክ ሄዱ፡፡እስኪነጋ ድረስ................

  ከቤተልሄም ኒቆዲሞስ
  (መታሰቢያነቱ ለእንትና እና አልቃሾ)

  Read more »

 • እምነት

  እምነት
  በቀቢጸ ተስፋ ፤ በተከፋ ኑሮ
  በተገፋ ፍቅር ፤ ባልተሰማ ሮሮ
  በተዳፈነ ህልም ፤ መሪ ባጣ መንገድ
  እኔው እኔ ልሆን ፤ ልቆም ስንገዳገድ
  አልቆርጥም ኖራለሁ ፤ ከሞት ይሻል ብዬ
  የሰማይ ላይ ኮኮብ ፤ ከምድር ተጥዬ!

  ከቤተልሄም ኒቆዲሞስ

  Read more »

Advertisment