PLANET ETHIOPIA.com

ቴክኖሎጂ Technology


 • ጄ.አይ.ኦ ሲም ካርድ የሚቀበል ላፕቶፕ ኮምፒውተር ሊሰራ መሆኑን አስታወቀ

                  

  ሬላይንስ ጄ.አይ.ኦ ኩባንያ 4G ሲም ካርድ የሚቀበል ላፕቶፕ ኮምፒውተር ሊሰራ መሆኑን አስታውቋል።

  ኩባንያው አዲስ ይዞት የመጣው ባለ ሲምካርድ ላፕቶፕ ሀሳብም በገበያው ላይ ተቀባይ እንደሚተታደርገው ተገምቷል።

  ሬላይንስ ጄ.አይ.ኦ ኩባንያ 4G ሲም ካርድ የሚቀበል ላፕቶፕ ኮምፒውተር ዊንዶውስ 10 ኦፕሬቲንግ ሲስተም የሚጠቀም መሆኑም ታውቋል።

  ኩባንያው “ጄ.አይ.ኦ ፎን” በሚል በህንድ ውስጥ ለገበያ ያቀረበው 4G ሲም ካርድ የሚቀበለው ስማርት ስልኩ ከፍተኛ ተቀባይነት አግኝቷል ነው የተባለው።

  እንደ ኢኮኖሚክ ታይምስ ዘገባ ሬላይንስ ጄ.አይ.ኦ ኩባንያ ለገበያ ለማቅረብ ባሰበው ባለሲም ካርድ ላፕቶፕ ኮምፒውተር ዙሪያ ከአሜሪካው የቴክኖሎጂ ኩባንያ ኩዋልኮም ጋር እየተነጋገረ ነው።

  ሁለቱ ኩባንያዎችም በባለ ሲም ካርድ ላፕቶፕ ኮምፑውተሩ ስራ ላይ ተስማምተዋል የተባለ ሲሆን፥ በቀርቡን የሲም ካርድ ማስገቢያ ያለው ላፕቶፕ ምርት ይጀመራል ነው የተባለው።

  ላፕቶፑ መቼ ተመርቶ ለገበያ ይቀርባል በሚለው ዙሪያ ግን አስካሁን የተባለ ነገር የለም።

  ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

  Read more »

 • ህዋዌ በስማርት ሞባይል ስልክ የሚነዳ መኪና ሰራ

                      

  የቻይናው ትልቁ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ድርጅት ህዋዌ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን በስማርት ሞባይል ስልክ የሚነዳ መኪና መስራቱን በባርሴሎና እየተካሄደ ባለው ዓለም አቀፍ የሞባይል ጉባዔ ላይ አስታወቀ።

  "ሮድ ሪደር" ወይንም መንገድ ቃኚ የተባለው ይህ ቴክኖሎጂ የህዋዌ ምርት የሆነውን ሜት 10 ስልክን በመጠቀም መኪናን ይቆጣጠራል እንዲሁም በመንገድ ላይ የሚያጋጥሙ እንቅፋቶችን መለየት ይችላል። 

  መኪናው የሚያጋጥመውን ነገር የመረዳት፣ የመለየት እንዲሁም ትክክለኛውን ውሳኔ የመወሰን አቅም እንዳለውም ነው የተገለፀው።

  ስልክ ላይ የተገጠመው ካሜራ መንገድ ላይ የሚያጋጥሙትን አካላት ምስልን በመያዝ የተገጠመለትን ዋይፋይ በመጠቀም መረጃውን ወደ መኪናው እንደሚልክ ገልጸዋል።

  የህዋዌ ስራ አስኪያጅ መኪናው 1 ሺህ የተለያዩ አካላትን የመለየት ብቃት እንዳለው በጉባኤው ላይ የገለጹ ሲሆን፥ ከእነዚህም ውስጥ ድመት፣ ውሻ፣ ኳስ፣ ብስክሌት እና ሌሎች ነገሮችን የማስታወስ ብቃት አለው ነው ያሉት። 

  በተጨማሪም ሰው ሰራሽ የማሰብ አቅም ያለው መሳሪያ አስፈላጊነት ላይም በጉባዔ ላይ አንስተው ተወያይተዋል።

  በባርሴሎናው ጉባኤ ላይ ከ108 ሺህ በላይ ጎብኚዎች ይታደማሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፥ ከ2 ሺህ 300 በላይ ድርጅቶች ስራዎቻቸውን ማቅረባቸው ተገልጿል።

  ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

  Read more »

 • የአዲሱ ሳምሰንግ ጋላክሲ S9 በካሜራ ብቃት ላይ አተኩሯል - The New Samsung Galaxy S9 Model Focused on Camera Capabilities

                                          

  የጋላክሲ S9 እንዲሁም S9+ ካሜራዎች አቅም ከፍተኛ እንዲሆን ማድረግ የአዳዲሶቹ የሳምሰንግ ምርቶች መገለጫዎች ናቸው።

  የሁነቶችን እንቅስቃሴ መቅረፅ የሚያስችል ካሜራ አሰራር እንዲሁም አነስተኛ ብርሃንን ማሻሻል የሚችሉ ሌንሶች የእነዚህ ስልኮች መለያ ነው።

  እንደ አውሮፓውያኑ በ2017 የሳምሰንግ ሽያጭ ጨምሮ የነበረ ቢሆንም እንደ ሌሎቹ ተቀናቃኝ የቻይና ኩባንያዎች ግን ሽያጩ በጣም አልጨመረም።

  ኤክስፐርቶች እንደሚሉት አሁን ምርቶቹ ላይ የተደረጉት ማሻሻያዎችም ቀላል እንጂ ጉልህ የሚባሉ አደሉም።

  ይሁንና የs9 ቅርፅ ከ s8 ጋር እጅግ የሚመሳሰል መሆኑ ለአዲሶቹ ስልኮች ሽያጭ ችግር ሊሆን እንደሚችልም ይናገራሉ። S9+ ብቻ ከ S8+ በደንብ ይለያል።

  ሁለቱ የካሜራ ሌንሶች የተያዩ እይታዎችን ይሰጣሉ፤ ትኩረት ከሚደረግበት ነገር ውጭ ያለን ነገር ገፅታንም እንደተፈለገው ለማድረግ ያስችላሉ።

  "የተደረጉት ማሻሻያዎች ሰዎች ስልካቸውን ለመለወጥና አዳዲሶቹን ለመግዛት የሚገፋፉ አይመስለኝም" ይላል አይዲሲ በተሰኘው ኩባንያ የገበያ ጥናት ኤክስፐርት የሆነው ፍራንሲስኮ ጀሮሚዮ።

  የስልኮቹ ካሜራ መሻሻል በርካቶች አዲሶቹን ስልኮች እንዲገዙ ሊያደርጉ ቢችሉም ይጠብቅ የነበረው ማሻሻያ ከዚህ የበለጠ እንደነበር ኤክስፐርቱ ያስረዳል።

  ከጠበቃቸው ማሻሻያዎች መካከል ለምሳሌ የኢንተርኔት ቀጥታ ትርጉም አንዱ ነበር። በተቃራኒው አዲሱ የቺፕ ቴክኖሎጂያቸው ምስጋና ይግባውና ያለ ኢንተርኔት ቃላት የሚተረጉሙትን የህዋዌ አዳዲስ ስልኮች ያደንቃል።

  ምንጭ፦ ቢቢሲ

  Read more »

 • ፕሮጀክተር የተገጠመለት ስማርት ሰዓት - Smartwatch With Skin-Touch Projector!

  የ                              

  ቻይናው ሀይር ኩባንያ ፕሮጀክተር የተገጠመለት ስማርት የእጅ ሰዓት አስተዋውቋል።

  ኩባንያው ስማርት ሰዓቱን በስፔን ባርሴሎና በተካሄደው የሞባይል ኮንግረስ የቴክኖሎጂ አውደ ርዕይ ላይ ነው ይዞ የቀረበው።

  ልክ እንደ ሌሎች ስማርት ሰዓቶች ሁሉ የጤና ሁኔታን ጨምሮ በርካታ አገልግሎቶች የሚሰጠው ይህ የእጅ ሰዓት፥ በላዩ ላይ ፕሮጀክተር ተገጥሞለታል ነው የተባለው።

  ስማርት ሰዓቱ ላይ የተገጠመው ፕሮጀክተር እጃችንን ልክ እንደ ሌላ ተጨማሪ ስክሪን ሊያስጠቅመን የሚችል ነው።

  በዚህም እንደ ፎቶግራፍ ያሉ ነገሮችን ጨምሮ ሌሎች ስማርት ሰዓቱ ላይ የምንጠቀማቸውን አገልግሎቶች ከፕሮጀክተሩ በሚወጣው ጨረር አማካኝነት በእጃችን ላይ መመልከት እንችላለን ነው የተባለው።

  ሀይር ስማርት ሰዓት በቀጣይ ሶስት ወይም አራት ወራት ውስጥ በቻይና ውስጥ ለገበያ መቅረብ እንደሚቸምርም ተነግሯል።

  ስለተቆረጠለት የመሸጫ ዋጋ ግን እስካሁን የተባለው ነገር የለም።

  ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

  Read more »

 • ካሊፎርኒያ አሽከርካሪ አልባ ተሽከርካሪዎችን በጎዳናዎች ላይ ልትሞክር ነው - California Green Lights Fully Driverless Cars For Testing on Public Roads

                                          

  ካሊፎርኒያ አሽከርካሪ አልባ ተሽከርካሪዎችን ከመጭው ሚያዚያ ወር ጀምሮ በጎዳናዎች ላይ ልትሞክር ነው።

  የተሽከርካሪዎቹ ሙከራ ያለምንም አሽከርካሪ ብቻ የሚደረግ ሲሆን፥ ኩባንያዎች ለዚህ የሚያገለግሉ ተሽከርካሪዎችን የማዘጋጀት ሃላፊነት አለባቸው ተብሏል።

  ከመጭው ሚያዚያ ወር በሚጀምረው ሙከራ በመላው የካሊፎርኒያ ግዛት ጥቅም ላይ ለመዋል የሚቀርቡ አሽከርካሪ አልባ ተሽከርካሪዎች ያለ አሽከርካሪ የመንገድ ላይ ሙከራቸውን ያደርጋሉ።

  ይህን ሙከራ ማድረግ የፈለጉ አሽከርካሪ አምራቾች ታዲያ ከግዛቲቱ የተሽከርካሪ መምሪያ ክፍል ፈቃድ ማግኘት ይኖርባቸዋል።

  የግዛቲቱ የተሽከርካሪ መምሪያ ክፍል ሁሉም ተሽከርካሪዎች ያለ አሽከርካሪ በጎዳና ላይ ሙከራቸውን እንዲያደርጉ የሚያደርግ መመሪያ ትናንት አድቋል።

  እስከዛሬ ድረስ አዲስ የሚሰሩ አሽከርካሪ አልባ ተሽከርካሪዎች ራሳቸውን ችለው የመንገድ ላይ ሙከራ ቢያደርጉም፥ ሁኔታውን በቅርበት የሚከታተል አሽከርካሪ ግን እንዲኖር ይደረግ ነበር።

  በአዲሱ መመሪያ መሰረት ግን ከፈረንጆቹ ሚያዚያ 2 ጀምሮ ሁሉም አሽከርካሪ አልባ ተሽከርካሪዎች ያለ አሽከርካሪ እንዲሞከሩ ይደረጋል ነው የተባለው።

  ተሽከርካሪ አምራቾችም በተሽከርካሪውና በተቆጣጣሪው መካከል መግባባት ይኖር ዘንድ የሚያስችል መገናኛ ቴክኖሎጅን ማመቻቸት ይጠበቅባቸዋል።

  ከዚህ ባለፈም ተሽከርካሪዎች በእንቅስቃሴ ወቅት በመረጃ መረብ ጠላፊዎች አማካኝነት አደጋ እንዳያስተናግዱ መከላከልም የእነርሱ ድርሻ ይሆናል።

  በሙከራ ወቅት የሚያጋጥምን ማንኛውንም ሁኔታ ማሳወቅና ማስረዳትም ሌላው ሃላፊነት ይሆናል።

  አሽከርካሪ አልባ ተሽከርካሪዎችን መገጣጠም አሁን በአውቶሞቢል ኢንዱስትሪው ውስጥ ትልቁን ድርሻ እየያዘ ነው።

  ኩባንያዎችም መሰል ቴክኖሎጅዎችን በመጠቀም ሙከራዎችን በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

  የመረጃ ማፈላለጊያ ገጽ የሆነው ጎግል አሽከርካሪ አልባ ተሽከርካሪዎችን ከሶስት ሚሊየን ማይል በላይ ሲሞክር፥ ኡበር ደግሞ ከአንድ ሚሊየን ማይል በላይ በጎዳና ላይ ሞክሯል።

  ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

  Read more »

 • ናሳ ከ6 ነጥብ 2 ቢሊየን ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ፎቶ ማንሳት መቻሉን ገለፀ

                           

  ናሳ ከምድራችን በ6 ነጥብ 2 ቢሊየን ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገኝን አካል ፎቶ ማንሳቱን አስታወቀ።
  ይህም ከዚህ ቀደም ከተነሳው በስልሳ ሚሊየን ኪሎ ሜትር በመላቅ አዲስ ሪከርድ ሆኖ መመዝገቡን ነው ያመለከተው።
  ድርጅቱ ሐሙስ የለቀቀውንም ተከትሎ ካሜራው በምድራችን ላይ ከሚገኙት ሁሉ የላቀ መሆኑን ገልጿል።
  ፎቶው የተነሳው በታህሳስ ወር ላይ እንደነበረ ተነግሯል።
  ፎቶ ተነሳ የተባለው አካል እጅብ ያሉ “ዊሺንግ ዌል’’ በመባል የሚጠሩ ከዋክብት መሆናቸውን ናሳ አስታውቋል።

   

  ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

   

   

  Read more »

 • ስልክን ቻርጅ በሚያደርጉ ጊዜ ማስተዋል ያለብዎት ጉዳይ - Things You Should Take a look Seriously When you Charge Your Phone

                                                                          

  ዘመናዊ ስልኮች ከስሪታቸው አንጻር ባትሪያቸው ቶሎ የሚያልቅና አጭር ጊዜን የሚያስጠቅሙ ናቸው።

  ከዚህ አንጻርም ተጠቃሚዎች ባትሪውን ቶሎ ቶሎ ሃይል ለመሙላት (ቻርጅ ለማድረግ) ሲሞክሩ ይስተዋላል።

  ይህ ሁኔታ ደግሞ ምናልባትም የባትሪን እድሜ ሊያሳጥር እና ሙሉ በሙሉ ሊያበላሸውም ይችላል።

  ስልክን ከመጠቀም ባለፈ ግን የባትሪ እድሜን ማራዘምና በአግባቡ ቻርጅ በማድረግ መጠቀም ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው።

  ስልክዎን ቻርጅ በሚያደርጉበት ጊዜ ምናልባት ያላስተዋሏቸው ነገሮች ይኖራሉና እነዚህን የባለሙያ ምክረ ሃሳቦች እናካፍልዎ።

  ቻርጅ እያደረጉ ስልክን በጭራሽ አለመጠቀም፦ አንዳንድ ጊዜ አስቸኳይ ጉዳይ ቢያጋጥም እንኳን ስልክን ቻርጅ እያደረጉ ባይጠቀሙ ይመረጣል።

  ምናልባት የግድ ከሆነ ደግሞ ስልኩ ከተሰራበት ኩባንያ አብሮ የተዘጋጀን ቻርጀር እየተጠቀሙ ቢሆን ይመረጣል ይላሉ ባለሙያዎች።

  ጥራት ያላቸውን ባለማራዘሚያ ቻርጀሮች መጠቀም፦ ባለማራዘሚያና በአብዛኛው በነጭ መደብ የተሰሩ እውነተኛ ቻርጀሮችን መጠቀም የባትሪን እድሜ ለማራዘም ይረዳልና ይጠቀሙበት።

  ሌሊቱን ሙሉ ቻርጅ ከማድረግ መቆጠብ፦ ወደ መኝታ ሲያመሩ ስልክዎን ቻርጀር ላይ ሰክተው ማሳደርዎ አደጋ አለው።

  ይህም ባትሪው ከመጠን በላይ ቻርጅ በማድረግ ማዳከም ይጀምራል፥ በአብዛኛው ስልክን በ40 እና በ80 ፐርሰንት መካከል ቻርጅ ማድረግ መልካም መሆኑንም ይመክራሉ።

  ምክንያታቸው ደግሞ 40 ፐርሰንት ከደረሰ ቻርጅ ማድረጉ ግዴታ ሲሆን 80 ከሆነ በኋላ ነቅለው ቢገለገሉበት ችግር የለውም የሚል ነው።

  ስልክን ለተወሰነ ጊዜ ማጥፋት፦ ሰው ሰርቶ ማረፍ እንደሚፈልገው ሁሉ ስልክን ማጥፋትም ለባትሪው መልካም እንደሆነ ነው ባለሙያዎች የሚገልጹት።

  ለዚህ ደግሞ ቢያንስ በሳምንት አንድ ቀን በተለይም ወደ መኝታ ሲያመሩ በማጥፋት እረፍት መስጠት።

  ይህ ሲሆን ደግሞ የስልኩ ባትሪ እድሜ እንዳያጥርና ረዘም ላለ ጊዜ እንዲያገለግልዎ ይረዳል።

  ባትሪው እስከሚያልቅ ጠብቆ ቻርጅ አለማድረግ፦ ሌላውና በብዙ ሰዎች የተለመደው ጉዳይ ደግሞ የስልክ ባትሪ እስከሚያልቅ ጠብቆ ቻርጅ ማድረግ ነው።

  ይህ ደግሞ ለባትሪ እድሜ የመጀመሪያውና ዋናው ጠር ነውና፥ ባትሪው 40 ፐርሰንት ላይ ሲደርስ ቻርጅ ማድረጉን ይመክራሉ።

  ይህ ባይሆን እና በጣም ከወረደ በኋላ ቻርጅ ለማድረግ መሞከሩ ግን ባትሪን በመግደል ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላልና ይህን ልማድ ያስወግዱም ይላሉ።

  ከዚህ ባለፈም ቻርጀሩን ከቀጥተኛው ሶኬት ላይ አለመሰካት እና ከፍተኛ ሙቀት ባላቸው ቻርጀሮች አለመጠቀም መልካም ነው።

  ለስልኩ መከላከያ የገጠሟቸውን ነገሮች ማስወገድ፦ ስልክ ቻርጅ ሲደረግ ቀስ እያለ መሞቁ የተለመደ ጉዳይ ነው።

  ይሁን እንጅ ስልኩን ከአደጋ ለመከላከል በሚል የለጠፏቸው መከላከያዎችን ቻርጅ በሚያደርጉ ጊዜ አለመንቀል ባትሪው ከመጠን በላይ እንዲግልና በጊዜ አገልግሎት መስጠት እንዲያቆም ሊያደርገው ይችላል።

  ፈጣን ቻርጀሮችን አይጠቀሙ፦ ምናልባት አንዳንድ ጊዜ ከመቸኮል የተነሳ ቶሎ ሃይል የሚሞሉ ፈጣን ቻርጀሮችን መጠቀምና እነሱኑ አማራጭ ማድረጉ አይመከርም።

  ምክንያቱም እነዚህ ቻርጀሮች በፍጥነት ሃይል ስለሚለቁ ባትሪው ላይ ከፍተኛ መጠን ያለው የኤሌክትሪክ ፍሰት እንዲኖር በማድረግ ከልክ በላይ እንዲግል ያደርጉታል።

  ይህም በባትሪው እድሜ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል፤ ከልክ በላይ መጋሉ ባትሪውን የማቃጠል እድሉ ከፍተኛ ነው።

  የባትሪ መተግበሪያዎችን ማጥፋት፦ ከኢንተርኔት አውርደው የሚጠቀሙባቸውን አንዳንድ “የባትሪ እድሜ ማራዘሚያ” መተግበሪያዎችን በዚህ ጊዜ መዝጋት ይመከራል፤ ከዚህ ባለፈም በየጊዜው ቻርጅ አለማድረግ።

  ቻርጅ ሲያደርጉ 80 በመቶ ከደረሰ በኋላም መንቀልና መጠቀም ይቻላል፥ ይህን ሲያደርጉ ባትሪው ቶሎ ቶሎ እንዳይጨርስ ይረዳዋል።

  ቻርጅ እያደረጉ ስልኩን አለመጠቀም ሌላው ጠቃሚ ምክረ ሃሳብ ነው።

  ከዚህ ባለፈም የባትሪውን እድሜ ለማራዘም የማይጠቀሙባቸውን መተግበሪያዎችን መዝጋት፦ ይህን ማድረግዎ ባትሪው ስልክዎን በሚጠቀሙበት መጠን እንዲሰራ በማድረግ የተሻለ መቆጠብ እና መጠቀም ያስችልወታል። 

  የስልኩን ንዝረት መቀነስ፦ ስልኩ በሚጠራ ጊዜ ያለው ንዝረት ከፍተኛ መጠን ያለው ሃይል ይጠቀማል፤ ይህ ደግሞ የስልኩን ባትሪ ቶሎ እንዲያልቅ ያደርገዋል።

  የስክሪኑን የብርሃን መጠን መቀነስ፦ የስልኩ የብርሃን መጠን ከፍተኛ ሲሆን ባትሪው ቶሎ እንዲያልቅ ያደርገዋልና በተቻለ መጠን የስልኩን ስክሪን ብርሃን መጠን (screen brightness) መቀነስዎን አይዘንጉ።

  ብሉቱዝ እና ዋይፋይ መዝጋት፦ የስልኩን ብሉቱዝ መዝጋት ስልኩ በአቅራቢያው ካሉና ብሉቱዛቸወን ከከፈቱ ስልኮች ጋር ሲገናኝ ባትሪውን በብዛት ስለሚጠቀም ቶሎ የመጨረስ እድሉ ከፍተኛ ነው።

  ከዚህ ባለፈም ገመድ አልባ ኢንተርኔት (ዋይ ፋይ) በሌለበት ቦታ ኔትዎርኩን መዝጋት ስልኩ ኔት ዎርክ ፍለጋ የሚያጠፋውን ባትሪ እንዲቀንስ ያስችለዋል። 

  ኢንተርኔቱን ማጥፋት፦ የስልኩ ኢንተርኔት (ሞባይል ዳታ) ክፍት ከሆነ ኢንተርኔት በሚጠቀም ጊዜ ብዙ ባትሪ ስለሚወስድ ኢንተርኔቱን ቢያጠፉ ይመከራል። 

  ስልኩን ለመነጋገሪያ ብቻ ቢጠቀሙበት፦ በስልክዎ ፊልሞችን መመልከትና የተለያዩ ጨዋታዎችን (ጌም) መጫዎት ለባትሪ እድሜ ጠር ነውና ያነን ያስወግዱ።

  ብዙ መተግበሪያዎችን በአንድ ጊዜ ከመዝጋትና መክፈት መቆጠብ

  ብዙ ጊዜ እንደነ ኦፔራ ሚኒ፣ ፌስቡክ የመሳሰሉ መተግበሪያዎችን ተጠቅመን ስንጨርስ ዘግተን ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ መልሰን እንከፍታለን፡፡

  ስለሆነም ከተጠቀምን በኋላ የ“ሆም” ቁልፉን ተጠቅመን መውጣት ሌላ ጊዜ መጠቀም ስንፈልግ ሞባይላችን ካቆመበት እንዲቀጥል ያደርገዋል፡፡
  ይህም የሞባይላችንን ባትሪ እድሜን ያስቀጥላል።

  እርስዎም ከላይ የተጠቀሱትን የባለሙያ ምክረ ሃሳቦች በመተግበር የስልክዎን ባትሪ እድሜ ያራዝሙ።

  ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

  Read more »

 • ማይክሮሶፍት ኦፊስ 2019 በዊንዶውስ 10 ላይ ብቻ እንደሚሰራ ተገለፀ - Microsoft Office 2019 Will Only Work on Windows 10

                                                     

  አዲሱ የማይክሮሶፍት መገለግለያ የሆነው “ማይክሮሶፍት ኦፊስ 2019” ሶፍትዌር በዊንዶውስ 10 ኦፕሬቲንግ ሲስተም ላይ ብቻ የሚሰራ መሆኑ ተነገረ።

  እንደ ማይክሮሶፍት ኩባንያ ገለጻ፥ በዴስክ ቶፕ እና ላፕቶፕ ኮምፒውተሮች ለላይ ለፅሁፍ እና ለሌሎች አገልግሎቶች የሚያገለግለው “ማይክሮሶፍት ኦፊስ 2019” በያዝነው

  የፈረንጆቹ 2018 አጋማሽ ላይ ተጠቃሚዎች ዘንድ መድረስ ይጀምራል።

  ሆኖም ግን “ማይክሮሶፍት ኦፊስ 2019” ዊንዶውስ 10 ኦፕሬቲንግ ሲስተም በሚጠቀሙ ኮምፒውተሮች ላይ ብቻ እንደሚሰራ ነው የማይክሮሶፍት ኩባንያ ያስታወቀው።

  አዲሱ ማይክሮሶፍት ኦፊስ 2019 ወርድ፣ ኤክሴል፣ ፓወር ፖይንት፣ የቢዝነስ ስካይፒ እና ሼር ፖይንት የተባሉ አገልግሎቶችን ያካተተ ነው።

  “ማይክሮሶፍት ኦፊስ 2019” ለ5 ዓመታት ዋና ዋና የሚባሉ አገልግሎቶችን የሚሰጥ ሲሆን፥ ለተጨማሪ ሁለት ዓመት ደግሞ የማራዘሚያ ድጋፎች እንደሚደረጉበትን ኩባንያው ገልጿል።

  በአሁኑ ጊዜ ለማይክሮሶፍት ኦፊስ 2016 የተሰጠው የማራዘሚያ የድጋፍ ጊዜ በአውሮፓውያኑ 2025 ላይ እንደሚጠናቀቅም ተነግሯል።

  ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

  Read more »

 • ቻይና በ2020 በሰዓት 600 ኪሎ ሜትር የሚጓዝ ባቡር ገንብታ ለሙከራ እንደምታበቃ ገለፀች - China To Test 600 km/h Maglev Train by 2020

                                                                     

  ቻይና በአውሮፓውያኑ 2020 በሰዓት እስከ 600 ኪሎ ሜትር የሚጓዝ ባቡር ገንብታ ለሙከራ ዝግጁ ለማድረግ ማቀዷን አስታወቀች።

  የሀገሪቱ የባቡር ማምረቻ ኢንዳስትሪ እንዳስታወቀው ሊገነባ የታቀደው ባቡሩ የቴክኒክ ክፍል በእቅድ ደረጃ ከሲ አር አር ሲ ኩባንያ በተውጣጡ 19 ባለሙያዎች ፀድቋል።                                                                               

  የኩባንያው ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ዲንግ ሳንሳን እንዳስታቁት፥ እቅዱ የተገመገመ እንደመሆኑ ስራው ወደ ዲዛይን ግንባታ ይሸጋገራል።

  በዚህም "በተያዘው እቅድ መሰረት በአውሮፓውያኑ 2018 አንድ ናሙና ይሰራል፤ የባቡሩ ሙሉ ተሽከርካሪ ደግሞ በ2020 በአምስት ኪሎ ሜትር ሀዲድ ላይ ይሞከራል" ብለዋል። 

  የከፍተኛ ፍጥነት የባቡር ትራንስፖርት ስርዓት የማስተዋወቅ ሂደቱ፥ በሀገሪቱ የሳይንስና ቴክኖሎጂ 13ኛው የአምስት ዓመት ዕቅድ (2016-2020) ከተያዙት ቁልፍ ፕሮጀክቶች አንዱ መሆኑ ተገልጿል።

  የፕሮጀክቱ አላማ ቻይና በከፍተኛ ፍጥነት የሚንቀሳቀሱ ትላልቅ የባቡር ቴክኖሎጂ ንድፍ፣ ማምረቻ፣ ማስተካከያ እና ግምገማ ስርዓቱን በመቆጣጠር የራሷ የሆነ አቅም እንዲኖራት ለማድረግ ነው ተብሏል።

  ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

  Read more »

 • ለተማሪዎች የሚጠቅሙ 7 የስማርት ስልክ መተግበሪያዎች - 7 Top Android Apps For Students

                                                                      
  ኮሌጅና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የቤት ስራ እና መሰል በርካታ ስራዎች ያከናውናሉ።

  ተማሪዎቹ ጊዜያቸውን በመቆጠብ የተሰጣቸውን የቤት ስራዎች እና ሌሎች ስራዎች ለመስራት የሚያስችሉ የተለያዩ የሞባይል ስልክ ኦፖሬቲንግ ሲስተም ለአይፎን ኦፕሬቲንግ ሲስተም እና አንድሮይድ መተግበሪያዎችን ይፋ ተደርገዋል።

  እነዚህ መተግበሪያዎች የተዘጋጁት ለተማሪዎች ድጋፍ ለመስጠት ተብሎ ሲሆን፥ መተግበሪያዎቹም እንደሚከተለው ይፋ ተደርገዋል።

  1) ለዊንዶውስ፣ አንድሮይድ እና ኦፖሬቲንግ ሲስተም በነፃ የሚገኝ “Office Lens” መተግበሪያ

  ይህ መተግበሪያ ለመፅሔቶች፣ በጥቁር እና ነጭ ሰሌዳ ለሚቀርቡ ፅሁፎች እና ለሰነዶች የሚሆን ፎቶግራፍ ለማንሳት የሚጠቅም ነው። 

  በመተግበሪያው በመታገዝ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ፎቶዎችን ማንሳት ስለሚቻል፣ ምስሎቹ በፓወር ፖይንት፣ በወረድ ወይም ፒዲኤፍ ፎርማት ለማስቀመጥ ይጠቅማል ነው የተባለው። 

  2) “Alarm Clock Sleep Cycle” መተግበሪያ

  ይህ መተግበሪያ ያለ ክፍያ የሚገኝ ሲሆን፥ ለአንድሮይድ እና ኦፖሬቲንግ ሲስተም ሞባይሎች የሚያገለግል ነው።

  ተማሪዎች ከእንቅልፋቸው በመንቃት የሚሰሩት ነገር ሲኖራቸው በሚፈልጉት ሰዓት ለማንቃት ይጠቅማል።

  3) “Dragon Dictation”መተግበሪያ

  ይህ መተግበሪያ ለአይፎን (አይ.ኦ.ኤስ) ስማርት ስልኮች የሚሰራ ነው።

  በእጅዎ ሲፅፉ ድካም፣ ከዛምአለፍ ሲል ጉዳት ሊያስከትል ይችላል፤ ይህንን ሁኔታ ለማስወገድ ከፈለጉ Dragon Dictation ከኢንተርኔት በማውረድ መጠቀም ይችላሉ። 
  በዚህም የቤት ስራዎን በመተግበሪው በመፃፍ ጊዜዎን እና ድካምዎን ማቃለል እንደሚችሉ ነው የተገለፀው።

  4) Student Homework Planner መተግበሪያ

  መተግበሪያው ለዊንዶውስ፣ አንድሮይድ እና አይ.ኦ.ኤስ ኦፕሬቲን ሲስተም ለሚጠቀሙ ስማርት ስልኮች እና ሌሎች መገልገያዎች በነፃ ይገኛል።

  በዚህ መተግበሪያ አማካይነት ተማሪዎች የቤት ስራቸውን እና የክፍል መርሃ ግብራቸውን መከታተል እንዲሁም የፈተና ማስታወሻዎችን ማግኘት ይችላሉ።

  5) Wonderlist መተግበሪያ

  መተግበሪያው ለዊንዶውስ፣ አንድሮይድ እና አይ.ኦ.ኤስ ኦፕሬቲን ሲስተም ለሚጠቀሙ ስማርት ስልኮች እና ሌሎች መገልገያዎች በነፃ ይገኛል።

  ይህ መተግበሪያ የትምህርት ቤት ፕሮጀክቶችን፣ የኮሌጅ ፕሮጄክቶችን ወይም የሱቅ ዝርዝር ክንዋኔ መከታተል የሚያስችል ነው። 

  Wunderlist ፍጥነቱ ከኮምፒተር እና ታብሌቶች በመሳሰሉት መሳሪያዎች የሚመሳሰል ነው።

  በዚህም ማንኛውንም ችግር ለማስወገድ አስታዋሾችን እና ቀነ ገደቦችን ለማውጣት ነፃነት የሚሰጥ ነው።

  6) Tasker መተግበሪያ

  ይህ መተግበሪያ ለአንድሮይድ ሞባይል ስልክ የሚሆን ሲሆን፥ ዋጋውም 2 ነጥብ 99 የአሜሪካን ዶላር ነው።

  የአንድሮይድ ስልክዎን ለመቆጣጠር እና ለተለያዩ ስራዎች በራሱ ጊዜ ለማስኬድ የሚጠቅም መተግበሪያ ነው።

  አንዳንድ መተግበሪያዎችን ለመቆለፍ የይለፍ ኮድ መጠቀም መጠቀም የሚያስችል ነው።

  በተጨማሪም የሞባይል ካሜራ ቁልፍን ለመቀየር እና የስልክ ጥሪዎችዎን ወድያውኑ ለመቅዳት ያስችላል።

  7) Flashcards Deluxe መተግበሪያ

  ይህ መተግበሪያ ለአንድሮይድ እና አይ ኦ ኤስ ሞባይል ኦፕሬቲንግ ሲስተሞች የሚያገለግል ሲሆን፥ ዋጋውም 3 ነጥብ 99 የአሜሪካ ዶላር ይደርሳል።

  መተግበሪያው ለጥናት እና መረጃ ለመያዝ የሚያስች ነው።

  የዚህ መተግበሪያ ተጠቃሚዎች የጋራ የሆነ የቤተ መጽሐፍትን ማግኘት ይችላሉ።

  ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

  Read more »

 • ሳምሰንግ ተጣጣፊ አዲስ የስልክ ዓይነቱን በ2019 ይፋ እንደሚያደርግ ገለፀ - Samsung Reviles to Release Folding Smartphone in 2019

                                                 

  ሳምሰንግ ኤሌክትሮኒክስ ኩባንያ በአውሮፓውያኑ 2019 ተጣጣፊ ስማርት የሞባይል ስልክን ይፋ እንደሚያደርግ ገለፀ።

  ኩባንያው የሚተጣጠፍ የመመልከቻ ስክሪን ያለው ይህ ስልክ ይፋ ይደረጋል ከተባለ ረዥም ጊዜ አስቆጥሯል።

  በተለይም ከተጠቃሚዎች ዘንድ ያለ ፍላጎት ይህን አዲስ የስልክ ሞዴል ይፋ ማድረጊያ ጊዜን እንዳራዘመው ነው ኩባንያው የጠቆመው።

  samsung_folding2_15012018.jpg

  ሆኖም በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት መጨረሻ ላይ ስልኩን ወደ ማምረት እንደሚገባ ነው ኩባንያው ያስታወቀው።

  ኩባንያው ሊሰራ ያቀደውን ስማርት ስልክ ለተመረጡ ደንበኞቹም በ2018 ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።

  ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

  Read more »

 • ኤል ጂ እንደ ወረቀት የሚጠቀለል ባለ 65 ኢንች ቴሌቪዥን ይፋ አደረገ - LG Unveils Stunning OLED TV That Can Be Rolled Up Like Paper

                                                                        

  ኤል ጂ እንደ ወረቀት የሚጠቀለል አዲስ ባለ 65 ኢንች ቴሌቪዥን ይፋ ማድረጉ ተነግሯል።

  የተጣጣፊ የቴሌቪዥን የስክሪኑ የመዝጊያ ቁልፉን በምንጫንበት ጊዜ የሚጠቀለል ሲሆን፥ በሳሎናቸው ውስጥ ቴሌቪዥን ሰፊ ቦታን እንዳይዝ ለሚፈልጉ ሰዎች መልካም ዜና ነው ተብሏል።

  ቴሌቪዥኑን በምንጠቀምበት ጊዜ በ “OLED 4K TV” ስክሪኑ በጣም ጥራት ያለው ምስልን የሚያሳየን መሆኑም ተነግሯል።

  ሆኖም ግን በማናይበት ጊዜ እንደ ሌሎች ቴሌቪዥኖች ቦታ ይዞ አይቀመጥም፤ ልክ እንደ ወረቀጥ ተጠቅልሎ የተዘጋጀለት ሳጥን ውስጥ ይገባል እንጂ ተብሏል።

                                                             

  በእርግጥ ታጣፊ ስክሪኖች ለኤል ጂ አዲስ ነገር አይደለም የተባለ ሲሆን፥ ኩባንያው ከጥቂት ዓመታት በፊትም ስክሪናቸው የሚታጠፍ ቴሌቪዥን ሰርቶ ነበር ነው የተባለው።

  እዚህ ጋር የተቀየረው ነገር ቢኖር የስክሪን መጠኑ መሆኑም ተነግሯል።

  ኩባንያው ከዚህ ቀደም ይፋ አድርጎት የነበረው ተጠቅላይ ቴሌቪዥን ባለ 18 ኢንች እንደነበረም ይታወሳል።

  ተጠቅላይ ቴሌቪዥኖቹ ከ1 ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ተመርተው ተጠቃሚዎች ዘንድ መቅረብ እንደሚጀምሩም ተነግሯል።

  ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

   

  Read more »

 • 8 ፕላኔቶች የሚሽከረከሯት ኮኮብ ነገር - Hidden Planet System Found Orbiting Nearest Star to Our Solar System

                                                           

  (ግሩም ተበጀ)

  የሥነ ሕዋ ተመራማሪዎች ያለንበትን የፀሐይ ሥርዓት የሚመስል፤ 8 ፕላኔቶች በዙሪያዋ የሚሽከረከሯት ኮከብ አገኘን ብለዋል፡፡

  ተመራማሪዎች እንዳሉት በኮኮቧ ዙሪያ ያሉት ፕላኔቶችና መላ ስርዓቱ የፀሐይ ሥርዓታንን ይመስላል፡፡ ልክ እንደፀሐይ ስርዓታችን ሁሉ በዚህች ኮከብ ዙሪያም ትናንሾቹ ፕላኔቶች ቀረብ ብለው ሲገኙ ትላልቆቹ ደግሞ ራቅ ብለው ነው የሚገኙት፡፡

  ልዩነቱ በፀሐይ ሥርዓታችን ውስጥ ያሉት ፕላኔቶች ተራርቀው የመገኘታቸው ጉዳይ ሲሆን በዚህች ኮከብ ዙሪያ ያሉት ፕላኔቶች ግን እጅግ ተቀራርበው ነው የሚገኙት፡፡ ለምሳሌ ያህል በዚህች ኮከብ ዙሪያ ከሚሽከረከሩት ፕላኔቶች በመጨረሻ ላይ የሚገኘው ፕላኔት በፀሐይ ስርዓታችን ምድር ያለችበት ርቀት ላይ የሚገኝ ነው፡፡

  እስከዛሬ የስነ ሕዋ ተመራማሪዎች በሌሎች ክዋክብት ዙሪያ 3500 ያህል ፕላኔቶች ቢያገኙም በአንድ ኮከብ ዙሪያ ይህን ያህል የበዙ 8 ፕላኔቶችን ሲያገኙ ግን ይህ የመጀመሪያው ነው ተብሏል፡፡

                                                                                                                                                                                                                                                   

  2,545 የብርሃን አመት ርቀት ላይ የምትገኘው ይህች Kepler-90 ተብላ የተሰየመችው ኮከብ ከእኛዋ ፀሀይ በግዝፈትም በሙቀትም ትበልጣለች ይለናል የቢቢሲው ድረገፅ ዘገባ፡፡

  በኮከቧ ዙሪያ 7 ፕላኔቶች መኖራቸውን ያውቁ የነበሩት ሳይንቲስቶች የጉግል ኢንጂነሮችን machine learning የተሰኘ የአርቴፊሺያል ኢንተለጀንስ ስልት በመጠቀም ነው ተጨማሪዋን ፕላኔት ማግኘት የቻሉት፡፡ ስልቱ በከዚህ ቀደም ፍለጋ የታለፉ ፕላኔቶችን ለማግኘት ረድቷል፡፡

  አዲስ የተገኘችው Kepler-90i የምትባለው ፕላኔት ወደ እናት ኮኮቧ በጣሙን ቀርባ ስለምትገኝ የወለሏ የሙቀት መጠን 425 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሲደርስ፤ በፀሐይዋ ዙሪያ አንድ ዙር ለማጠናቀቅ 14.4 ቀናት ብቻ ነው የሚፈጅባት፡፡

  ለግኝቱ የረዳው ምልከታ የተገኘው ከናሳ የኬፕለር የሕዋ ቴሌስኮፕ ሲሆን በዚህች ኮከብ ዙሪያ ካሉት 8 ፕላኔቶች 7ቱ መሬትን መሰል መሆናቸውም በሪከርድ ተመዝግቧል፡፡

  ምንጭ:- የሸገር FM 102.1 ሬዲዮ

   

  Read more »

 • ሞሮኮ የገነባችውን በአፍሪካ ፈጣኑን የባቡር መስመር በዚህ ሳምንት መሞከር ጀምራለች

                                                                     

  ሞሮኮ ገንብታ ያጠናቀቀችውን በአፍሪካ ፈጣን የተባለውን የባቡር መስመር መሞከር ጀመረች።

  ባቡሩ በሰዓት 320 ኪሎ ሜትር የሚጓዝ ነው።

  የባቡር መስመሩ ላይ ሰኞ እለት በተደረገ የሙከራ ጉዞ ባቡሩ በሰዓት 275 ኪሎ ሜትር ተጉዟል።

  ይህ ባቡር በካዛብላንካና ታንገርስ መካከል ይወስድ የነበረውን ሰዓት በሁለት ሶስተኛ የሚቀንስ ነው።

  ፕሮጀክቱ በአጠቃላይ 2 ነጥብ 4 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ወጪ የተደረገበት ሲሆን፥ 50 በመቶውን ወጪ አገሪቱ የሸፈነችው ከፈረንሳይ ባገኘችው ብድር ነው።

  በፈረንሳይ ኩባንያ የተገነባው ይህ የባቡር መስመር ሙሉ በሙሉ የሙከራ ጊዜውን አጠናቆ ወደ ስራ የሚገባው በፈረንጆቹ 2018 ነው ተብሏል።

  የሞሮኮ መንግስት በዓመት 6 ሚሊየን ሰዎችን የማመላለስ አቅም ያለው የባቡር መስመሩ መዘርጋት የአገሪቱን የመሰረተ ልማት የሚያዘምን መሆኑን ተገልጿል።

  ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

  Read more »

 • በኤሌክትሪክ ኃይል የሚንቀሳቀስ አውሮፕላን ሊሰራ ነው

                                                     

  ተቀማጭነቱን በአሜሪካ ሲያትል ያደረገ በቦይንግ እና ጄት አየር መንገዶች የሚደገፍ ዙኑም ኤሮ ኩባንያ በኤሌክትሪክ ኃይል የበርሩ አነስተኛ አውሮፕላኖች ለገበያ ለማቅረብ እየሰራ መሆኑን ገለፀ።

  ኩባንያው አውርፕላኖቹን በፈረንጆቹ 2022 ነው ይፋ ለማድረግ ያቀደው።

  በኤሌክትሪክ ኃይል የሚበርረው አውሮፕላን ከ1 ሺህ 600 ኪሎ ሜትር ርቀት ለመጓዝ ይፈጅ የነበረው ጊዜ እና የጉዞ ወጪን ለመቀነስ ታስቦ የተነደፈ መሆኑ ተገልጿል።

  ዙኑም ዲዛይን እያደረገው ያለው ሞተር በአውሮፕላኑ ተሽከርካሪ ላይ ካለው ነፋስ መስጫ ጋር ተመሳሳይነት ያለው በመሆኑ የሞተር ግለትን ለማቀዝቀዝ እንደሚጠቅም ተገልጿል።

  አዲሱ አውሮፕላን በሰዓት 544 ኪሎ ሜትር እና በ7 ሺህ 600 ሜትር ከፍታ ላይ ይጓዛል፤ ይህም ከተለመዱት ጀቶች ፍጥነቱ ያነሰ እና ከፍታውም ዝቅተኛ ነው ተብሏል።

  ኩባንያው የአውሮፕላኑን ቅርፅ በተመለከተ ከአምራቾች ጋር በመነጋገር ላይ ነው።

  የአዲሱ አውሮፕላን ባትሪዎች፣ የኤሌክትሪክ ስርዓቶች፣ ሶፍትዌሮችን እና ሌሎች ክፍሎችን ለመሞከር የሚያስችል የበረራ ላይ አምሳያዎች በመገንባት ላይ መሆኑን ጠቁሟል።

  ዙኑም በሀገራት ለሚደረጉ የአየር ጉዞዎች የገበያ ክፍተትን ለመሙላት፥ ብሎም የግል አየር መጓጓዣ እና የንግድ አውሮፕላኖች ጥቅም ላይ የሚውሉበትን ሁኔታ ለመፍጠር እየሰራሁ ነው ብሏል።

  በዚህም በትላልቅ ከተሞች አካባቢ በሚገኙ በሺዎች በሚቆጠሩ ትናንሽ የአውሮፕላን ማረፊያዎች በመገኘት የጉዞ ጊዜዎችን እና ወጪዎችን ለመቀነስ እንደሚያስችል ተጠቁሟል።

  ኩባንያው በሚቀጥሉት 10 ዓመታት መጨረሻ 50 ተሳፋሪዎችን ማጓጓዝ የሚያስችል እና በተሻሻለ የባትሪ ቴክኖሎጂ 1 ሺህ 600 ኪሎ ሜትር የሚጓዝ አውሮፕላን ይፋ ለማድረግ ማቀዱን ጠቁሟል።

  አዲሱ አውሮፕላን በባትሪ ኃይል የሚጓዝ ሲሆን አንድ አብራሪ ብቻ እንዲኖረው ተደርጎ የተነደፈ ነው ተብሏል።

  ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

  Read more »