PLANET ETHIOPIA.com

ትዝብት


 • "እህቴ በቅርቡ የምትፈታ አይመስለኝም" የመብት ተሟጋቿ ንግሥት ይርጋ ወንድም - "I Do Not Think My Sister Will be Released Soon." The Human Right Activist Nigist Yirga's Brother Said

                                                     

  የእህቴ ንግሥት ይርጋን የህይወት መንገድ በአዲስ አቅጣጫ የዘወሩት ተከታታይ ክስተቶች የተፈጠሩት በወርሃ ሐምሌ 2008 ዓ.ም ነው።

  ከዚያ በፊት ምንም ዓይነት የፖለቲካ ዝንባሌ ኖሯት የማታውቀው እህቴ ቀጣዮቹን ጥቂት ወራት በጎንደር ከተማ በነበሩ የተቃውሞ ሰልፎች ላይ በመሳተፍ፤በኋላም ሊይዟት ከሚፈልጓት የፀጥታ ኃይሎች በመሸሽ አሳልፋቸዋለች።

  በመስከረም 2009 የትውልድ እና የመኖሪያ ከተማዋን የኋሊት ትታ ከተደበቀችበት የታች አርማጭሆ ገጠራማ አካባቢ በቁጥጥር ሥር ስትውል ሃያ አምስት ዓመቷ ነበር።

  አሁን አዲስ አበባ በሚገኘው የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ሆና የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአማራ ክልል ተቀስቅሶ የነበረውን ሕዝባዊ አመፅ አስተባብረሻል፤ ከሕገ-ወጥ ድርጅት ጋርም ግንኙነት መስርተሻል በሚል የመሰረተባትን ክስ በመከታተል ላይ ስትሆን ለመጨረሻ ጊዜ በአካል ያየኋትም ከመታሰሯ ሁለት ሳምንታት ቀደም ብሎ ነው።

  ለአፍታ ያህል እንኳ ስቧት የማያውቀው የአካባቢዋ እና በአጠቃላይም የአገሪቷ የፖለቲካ ነባራዊ ሁኔታ እንደድንገት ቀልቧን ያጠመደው የወልቃይት ማንነት ኮሜቴ አመራሮች እና አባላት ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ግጭት ውስጥ ሲገቡና በተለይም የኮሚቴው አስተባባሪ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ሊይዟቸው የሞከሩትን የፀጥታ ኃይሎች በተኩስ ከመለሱ በኋላ ነው።

  በወቅቱ ይህንን ጉዳይ በአትኩሮት መከታተል መጀመሯ የሚገርም አልነበረም፤ እጅግ ብዙ የከተማዋ ወጣቶች የኮሎኔሉን ሰፈር ማዘውተር የያዙት ከተኩስ ልውውጡ ማግስት አንስቶ ነው።

  ከዚሁ ጋር ተያይዞ የፀጥታ ኃይሎች ከወጣቶቹ ጋር ግጭት ውስጥ መግባታቸውም አልቀረም። በአንድ አጋጣሚ አጠገቧ የነበረ አንድ ወጣት በጥይት ተመትቶ ሲወድቅ ማየቷ ይበልጥ የነካት ይመስለኛል።

  ፖለቲካ ጠገብ ያለመሆኗ እና ሰልፍን ከመሳሰሉ ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች ጋር የጠለቀ ትውውቅ ያለማዳበሯ ከብዙሃን ጎልታ እንድትታይና ዓይን ውስጥ እንድትገባ አድርጎታል፤ ይህን በታላቅ ወንድም ዓይን ሳየው ምነው ጠንቀቅ ባለች ኖሮ እያልኩ አስባለሁ።

  ሆኖም እንደዜጋ ሳጤነው ቁጭት ሳይሆን ኩራት ያሸንፈኛል፤ ላመነችበት ነገር ያላትን ሁሉ ያለምንም ቁጥብነት ፤ ያለምንም ማስመሰል መስጠቷ ያኮረኛል።

                                             

  ከምግብ ቤት እስከማረሚያ ቤት

  በአባት በኩል ብቻ የምዛመዳት ንግሥት ፤ በእናቷ በኩል ያሉ ሁለት እህቶቿን እና ከሐምሌው ክስተት በኋላ እንዲሁ ታስሮ የነበረ ወንድሟን ታስተዳድር ነበር።

  በሃያዎቹ የመጀመሪያ ዕድሜዋ ወደአረብ አገር በማቅናት ዱባይ ውስጥ ጥቂት ዓመታትን አሳልፋለች። አዋጭ ሥራ ፍለጋ በአካባቢው ወዳለ ትንሽ ከተማ አቅንታም ነበር።

  ከዚህ በኋላ ነው ወደጎንደር ከተማ ተመልሳ ተወዳጅ የሆነ የምግብ እና የመጠጥ መሸጫን የከፈተችው።

  ምግብ ቤቷ በወጣቶች በተለይም በከተማዋ የመጓጓዣ አገልግሎት በሚሰጡ ባለሦስት ጎማ ተሽከርካሪ ሾፌሮች ይዘወተር የነበረ መሆኑ፤ እሷም ከብዙሃኑ ጋር መልካም ግንኙነት ማዳበር መቻሏ በኋላ ከተማዋ በተቃውሞ ሰልፎች ስትናጥ በብዙዎች እንድትከበብ አስችሏታል።

  ከታሰረች በኋላ የንግድ ሥራዋ ሙሉ በሙሉ የቆመ ሲሆን ፤ ቤተሰቦቿም ኑሮን ለማሸነፍ በግቢያቸው ውስጥ ያሉ ሁለት ክፍሎችን ለማከራየት ተገድደዋል።

  ከዘመድ ከሚገኝ ድጋፍ ባሻገር አሁን ብቸኛው የገቢ ምንጫቸው ይኼው ነው።

  የእርሷን ክስ እና ደህንነት በተቻለን መጠን ከመከታተል ባሻገር ለእናቷ የሚደርሱ መረጃዎችንም መቆጣጠር ሌላኛው ፈተናችን ነው።

  ከተቃውሞዎቹ ጋር በተገናኘ ታስራ የነበረው እና በቅርቡ የተፈታችው አስቴር ስዩም እናት የልጃቸውን መፈታት ሳያዩ መሞታቸውን ማወቃችን ይበልጥ ጥንቁቅ እንድንሆን አስገድዶናል።

  የአስቴር እናት ልጃቸውን ለመጠየቅ ወደአዲስ አበባ ካመሩ በኋላ፤ አስቴር ክፉኛ ተጎሳቁላ ስላዩዋት ሲመለሱ ወዲያውኑ ነበር ጤናቸው የታወከው።

  እናም ንግሥት ጉስቁልቁል ብላ እንደነበር የተረዳን ሰሞን ሰውነቷ እስኪያገግም ድረስ የተለያዩ ሰበብ አስባቦችን በመደርደር እናቷ ወደአዲስ አበባ እንዳትሄድ ከመከልከል ውጭ አማራጭ አልነበረንም።

  አንዴ ደግሞ በምርመራ ወቅት ንግሥት እጅግ የከፉ አካላዊ ጉዳቶች እንደደረሰባት፤ ስብዕናን በሚነካ መልኩም ራቁቷን እንድትቆይ መደረጉን እንዲሁም ጥፍሮቿ ሁሉ መመንገላቸውን የሚናገሩ መረጃዎች በማኅበራዊ ሚዲያ በተሰራጩበት ወቅት እናቷ ሙሉ በሙሉ አቅሏን አጥታ ወደአዲስ አበባ ስትከንፍ ሄዳለች። እዚያ ስትደርስ ግን የተባሉት ነገሮች የተጋነኑ መሆናቸውን ለመረዳት ትችላለች።

  እርግጥ ንግሥት ማንነትን የሚነኩ ስድቦችን እንደምታስተናግድ እና ለረጅም ሰዓታት ቆማ እንደምትመረመር መረጃ አለን።

  ሆኖም በማኅበራዊ ሚዲያ የሚለቀቁ በግነት የተሞሉ መረጃዎች ለእናቷ እንዳይደርሱ መቆጣጠርም ሌላኛው ሥራችን ነው። በአንድ በኩል ሳየው ንግሥት ብቻዋን አይደለም የታሰረችው፤ እናቷንም ጨምራ እንጅ።

                                                  

  የእስረኞች መለቀቅ

  የኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባዊን ጨርሶ ሊቀ መናብርቱ በፖለቲካ ምክንያት የታሰሩ እስረኞች እንደሚለቀቁ መናገራቸውን ስንሰማ በመጀመሪያ እጅጉን ፈንድቀን ነበር። ነገር ግን ቀስ እያለ እውነታው ደስታችን እያተነነው መጣ።

  እንደሚገባኝ እርምጃው የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ከማባበል የዘለለ ሚና የለውም።

  መንግስት በአንድ በኩል እርቅና መግባባትን እፈልጋለሁ፤ የፖለቲካ ምኅዳሩን ማስፋት እሻለሁ ይላል። በሌላ ሁሉንም ከፖለቲካ ጋር በተገናኘ ያሰራቸውን እስረኞች ላለመፍታት ሰበቦችና መስፈርቶች ይደረድራል።

  እስካሁን ለናሙና ያህል የተወሰኑት ተፈቱ እንጅ ሁሉም ከእስር አልተለቀቁም፤ ከዚህ የተሻለ ነገር እንደማይኖር ስጋት አለኝ። እውነቱን ለመናገር ንግሥት በቅርብ ጊዜ የምትፈታ አይመስለኝም።

  ከእኔ ጋር በጣም ነበር የምንቀራረበው። በመቀሌ ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያ ዲግሪየን ስጨርስ እርሷው ናት መጥታ ያስመረቀችኝ።

  ቤተሰባዊ ጉዳዮችንም የምማከረው ከእርሷው ጋር ነበር። ነገር ግን እስር ዕጣችን ሆነ። እኔ ከአንድ ወር በኋላ ብፈታም እርሷ ግን አሁንም ክሷ አላለቀም። ዘመዶች እና ጎረቤቶች አንዳንድ ጊዜ "ተይ አንገትሽን ደፍተሽ ኑሪ እያልናት አልሰማ ብላ እንዲህ ሆነች" ሲሉ እሰማለሁ።

  እኔ ግን አንገቷን ያለመድፋቷ መቼም ሊያስፀፅተኝ አይችልም።

  ምንጭ፦ ቢቢሲ

  Read more »

 • ''አዝማሪዎቻችን የሙዚቃ ሳይንቲስቶች ናቸው" - "Our Azmaris Are Musicologists"

                                              

  ከአምሳ ሁለት ዓመታት በፊት ኒውዮርክ ባለች በትንሽ ስቱዲዮ ውስጥ የተፈጠረው ኢትዮ-ጃዝ ከአይፎን 8 ማስተዋወቂያነት በጀርመን ውስጥ እስካለ መንደር ስያሜ ሊሆን ችሏል።

  የሰሩት ሙዚቃ ለአይፎን 8 ማስተዋወቂያ ከመሆን ጋር ተያይዞም የተወሳሰቡ ጉዳዮች እንዳሉና ከእሳቸው ፈቃድ ውጭ ሙዚቃው እንደተሰጡ የሚናገሩት ሙላቱ ከወኪሎቻቸው ጋር በድርድር ላይ መሆናቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

  ይህ ቢሆንም ለአይፎን 8 ማስተዋወቂያነት መብቃቱ ኢትዮ-ጃዝ የፈጠረውን ተፅዕኖ ማሳያ ነው የሚሉት አቶ ሙላቱ "ለሙላቱ ወይም ለኢትዮ-ጃዝ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ሙዚቃ እዚህ ደረጃ ላይ መድረሱ ትልቅ ነገር ነው" በማለት ይናገራሉ።

  በመላው ዓለም ተደማጭነትን ማግኘት የቻለው ኢትዮ-ጃዝ እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ ያደረገው ትግሉ ግን ቀላል አልነበረም ይላሉ አቶ ሙላቱ።

  የሙላቱ ስኬቶች

  በተለያዩ ትላልቅ መድረኮችም ላይ የመታየት እድልን አግኝቷል። ከነዚህም መካከል የኢትዮ-ጃዝ ውጤት የሆነው የሙዚቃ ሥራ ለኦስካር ሽልማት ታጭቶ ለነበረው "ብሮክን ፍላወርስ" ለተሰኘው ፊልም ማጀቢያነት ውሎ ነበር።

  በተጨማሪም በሂፕ ሆፕ ሙዚቃ ታላቅ ስፍራ ያላቸው አሜሪካዊው ናስና የሬጌ ሙዚቃ ተጫዋቹ ዴሚየን ማርሌይ "የግሌ ትዝታን" ''ዲስታንት ሪላቲቭስ'' በሚለው አልበማቸው ውስጥ አካትተውታል።

  ሙላቱ አስታጥቄ በሙዚቃ ትምህርት ታላቅ በሚባለው በርክሌይ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬትም ያገኙ የመጀመaሪያው ጥቁር አፍሪካዊ ናቸው።

  "በርክሌይ ዩኒቨርሲቲ ለጃዝ ሙዚቃ ታላቅ ዩኒቨርሲቲ ነው። በዚህ ዩኒቨርሲቲም ተቀባይነትንና ዕውቅናን ማግኘት ክብር ነው። በጃዝ ውስጥ ከፍተኛ ስም ካላቸው እንደነ ዱክ ኤሊንግተን፣ ኩዊንሲ ጆንስ፣ አሪታ ፍራንክሊን ያገኙትን አንድ አፍሪካዊ ማግኘት ትልቅ እውቅና ነው" ይላል ሙላቱ።

  በቅርቡም ጃፓን ውስጥ በተደረገው የፉጂስ ኮንሰርት ላይ ከ120 ሺህ ሰዎች በላይ በተገኙበት ሥራቸውን ያቀረቡ ሲሆን ስኮትላንድ በሚገኘው ታላቁ ፌስቲቫል ግላስተንቤሪ ከ140 ሺህ ሰዎች በላይ በታደሙበት መድረክ ላይ ተሳትፈዋል።

  ከዚህ በተጨማሪ በጀርመን ሀገር በፖፕ ሲቲ በኢትዮ-ጃዝና በሙላቱ አስታጥቄ ስም መንደር ተሰይሟል። ከእሳቸው ሌላም ለሙዚቃ ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክተዋል ለሚባሉት ለእነ ኤልቪስ ፕሪስሊ፣ ማይክል ጃክሰን እንዲሁም ማሪያ ማኬባም ዕድሉ ደርሷቸዋል።

  እነዚህ ሁሉ የኢትዮ-ጃዝ ትሩፋት ናቸው የሚሉት ሙላቱ፤ ከዚህም በተጨማሪ የዘመናዊው ጃዝ ፈጣሪ በሆነው ቻርሊ ፓርከር ስም በየዓመቱ ኒውዮርክ ውስጥ በሚካሄድ ፌስቲቫል ላይ መጫወታቸው ለኢትዮ-ጃዝ ያገኘውን ትልቅ ክብር ማሳያ እንደሆነ ይናገራሉ።

  "ይሄ ሁሉ ለኢትዮ-ጃዝ ትልቅ ዕውቅና ነው፤ ሁልጊዜም እምፈልገውና የማልመው ደረጃ ላይ እየደረሰ ነው። የትም ቦታ ብሄድ ያለው የህዝቡ ፍላጎትና ፍቅርም ትልቅ ነው'' ይላሉ።

  ጥናቶችና አዳዲስ ሥራዎች

  ሁልጊዜም ቢሆን አዳዲስ ሥራዎችን ከመፍጠር አላቆምም የሚሉት ሙላቱ፤ በአሁኑ ወቅትም በኢትዮጵያዊው የዜማ ቀማሪ በቅዱስ ያሬድ ሥራዎች ላይ የኦፔራ እያዘጋጁ ነው።

  ይህ ሥራ ኢትዮጵያ በባህል ዘርፍ ለዓለም ያበረከተችውን አስተዋፅኦ የሚዘክር ነው። በዚህም ጥናት ውስጥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን በምትጠቀመው መቋሚያ ላይም ምርምሮችን አድርገዋል።

  ይህንን ምርምራቸውን እያካሄዱ ያሉት በሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የማሳቹሴትስ ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ ስር ነው።

  "ሙዚቃን መምራት ኢትዮጵያ ለዓለም ያበረከተችው አስተዋፅኦ ነው" (ኮንደክቲንግ ኢዝ ኢትዮፕያን ኮንትሪቦዩሽን ቱ ዘ ወርልድ) በሚል ርዕስ የጥናት ፅሁፍ ያቀረቡ ሲሆን በዚህም ኢትዮጵያ ከሌሎች ቀድማ መቋሚያን በመጠቀም ሙዚቃን መምራት እንዳስተማረች ይዘረዝራል።

  መቋሚያን ብቻ ሳይሆን ፀናፅሉን፣ ከበሮውን በአጠቃላይ ንዋየ-ማህሌት ተብሎ የሚጠራውን ሥርዓት እንዳጠኑም ይናገራሉ። "ይህ ክላሲካል ሙዚቃ ተብሎ ለሚጠራው የሙዚቃ ሳይንስ መሰረት ነው፤ ይህም ኢትዮጵያ ለዓለም ያበረከተችውን ያሳያል እላለሁ" ይላሉ።

  ከዚህም በተጨማሪ ደግሞ የተለያዩ የሙዚቃ መሳሪያዎችን የፈጠሩትንና "የሙዚቃ ሳይንቲስቶች" ብለው በሚጠሯቸው እንደነ ደራሼ ባሉት ህዝቦች ሙዚቃም ላይ ምርምር እያደረጉም ነው።

  "በታሪክ ስናጠናው እነዚህ ሕዝቦች ለበርካታ የአውሮፓውያን የሙዚቃ መሳሪያዎች መሰረቶች ናቸው። ትራምፔትንና ትሮምቦንን የሚመስሉ የሙዚቃ መሳሪያዎች አሉ። ከነዚህም ውስጥ አንዱ የቤኒንሻንጉል የሙዚቃ መሳሪያ የሆነው ዙምባራ ነው" ይላሉ።

  ሸራተን አዲስ ተደርጎ በነበረው የሙላቱ የሙዚቃ ኮንሰርትም ላይ ሙዚቀኞቹንና እነዚህን የሙዚቃ መሳሪያዎች አካተዋል። በብዙ አጋጣሚዎች ስለደራሼ ህዝብ ሙዚቃ ጥልቀትም ሆነ ጥበብ አውርተው የማይጠግቡት ሙላቱ የደራሼ ሙዚቃ ከኢትዮጵያ ቅኝት ውጭ የሆነ ሙዚቃ ነው በማለት ይናገራሉ።

  ከአውሮፓውያኑ በላይ እንደ ደራሼ ላሉ አገር በቀል ሙዚቃዎች ክብርም ሆነ ዕውቅና መስጠት ይገባል ብለው የሚያምኑት ሙላቱ፤ "ምንም እንኳን ለቀረው ዓለም የጃዝ ሙዚቃ ያበረከቱት አስተዋፅኦ ከፍተኛ ቢሆንም በኢትዮጵያ ውስጥ ሥራዎቻቸው ላይ ጥናትና ምርምር የለም። ይህ ሁኔታ ደግሞ ሊቀየር ይገባል'' ይላሉ።

                                                 

  ኢትዮ-ጃዝ እንዴት ተፈጠረ?

  ሙዚቃን በበርክሌይ ያጠኑት ሙላቱ "ወደራስ መመልከት ወይም ማየት" ለሚለው መነሻቸውም የሆነው በዚሁ ትምህርት ቤት የሙዚቃ መምህር በነበረ ሰው አማካኝነት እንደሆነ ይናገራሉ።

  ይህ መምህር "ራሳችሁን ሁኑ" የሚል ምክርም በተደጋጋሚ ለግሷቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። ከትምህርት ቤት ወጥተውም ኒውዮርክ በሚኖሩበት ወቅት ስለኢትዮጵያ መመራመራቸውን ቀጠሉ።

  "እነዚህ ቅኝቶች ላይ ተመስርቼ ቀለምና መልካቸውን ሳይቀይር ከአውሮፓውያኑ አስራ ሁለት ድምፆች ጋር እንዴት አዋህጄ አዲስ ድምፅ መፍጠር እንደምችል እየተመራመርኩ ነበር" ይላሉ ሙላቱ።

  ከብዙ ጥናትና ምርምር በኋላም የሁለቱ ጥምረት ኢትዮ-ጃዝን መፍጠር ቻለ። ይህንንም ጥምረት ሙላቱ ''የቅኝቶች ፍንዳታ" (ኢምፕሮቫይዜሽንን) ይሉታል።

  ወደ ኢትዮጵያም ሲመለሱ ሁሉ ነገር አልጋ ባልጋ አልነበረም።

  ከሚያስታውሱትም አንዱ የፀጋየ ገብረ-መድህን ቲያትር ድርሰት ለሆነው 'ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት' ሙዚቃ በገናን፣ ፒያኖን፣ጊታርና ሌሎች ሙዚቃ መሳሪያዎችን በመጠቀም ቅንብሩን ሰሩ።

  በዚያን ወቅት የጥላሁን ገሰሰ "ኩሉን ማን ኳለሽ" በጣም ታዋቂ ዘፈን የነበረ ሲሆን ይህንን ሙዚቃ እንዲጠቀሙ ብዙዎች ቢፈልጉም የራሴን ቅንብር ነው የምጫወተው በማለት ሙላቱ በሀሳባቸው እንደፀኑ ይናገራሉ።

  በአምባሳደር ቲያትር ቤት ዝግጅታቸውን አቀረቡ። "መቼም ቢሆን አልረሳውም፤ ሙዚቃውም ከበገና ወደሌሎች ሙዚቃ መሳሪያዎች ሲሄድ ብዙዎች ውረድ አሉኝ። ውረድ የሚለው ድምፅ ቢበረታም ሳልጨርስ አልወረድኩም" የሚሉት ሙላቱ "ሁልጊዜም ቢሆን የምናገረው ያን ጊዜ ተስፋ ቆርጨ ሙዚቃ ማቆም እችል ነበር፤ መታገልን የመሰለ ነገር የለም። እንዲያውም እሱ የበለጠ ብርታትና እልህ ሰጥቶኛል። 'ተስፋ አትቁረጡ ሁልጊዜም ታገሉ፤ አዲስ ነገር ፍጠሩ' በማለት እመክራለሁ'' ይላሉ።

  ከዓመታት በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ ኢትዮ-ጃዝ ታዋቂነትን እያገኘና ተከታዮችን እያፈራ ቢመጣም አሁንም ቢሆን በከፍተኛ ደረጃ ተቀባይነት ያለው በአውሮፓና በሌሎች ሀገራት እንደሆነ ሙላቱ ይናገራሉ።

  ስለአዝማሪዎች

  ኢትዮ-ጃዝ በለውጥ ሂደት ውስጥ እንደሆነ የሚናገሩት ሙላቱ በዓመታት ውስጥ ብዙ የምርምር ሥራዎች እንደተጨመረበት ይናገራሉ።

  "አሁን ደግሞ ዋናው የኢትዮ-ጃዝ አላማ የሙዚቃ ሳይንቲስቶቻችንና ፈጣሪዎቻችን ላይ ተመስርተን፤ ያሉን መሳሪያዎች መልካቸውና ዲዛይናቸው ሳይቀይር እንዴት አድርጎ የሌላውን ዓለም ሙዚቃ መጫወት ይችላል የሚል ነው" ይላሉ።

  ''አዝማሪዎቻችን የሙዚቃ ሳይንቲስቶች ናቸው" የሚሉት ሙላቱ፤ ያሉትን የኢትዮጵያ ሙዚቃ መሳሪያዎችንና ሙዚቃን ፈጥረው እዚህ ካደረሱ ቀጣዩ ትውልድ ደግሞ ሊያሻሽለው እንደሚገባ ይናገራሉ።

  ሥራዎቻቸው መካከልም አዝማሪን ወደ 21ኛው ክፍለ-ዘመን ማምጣት በሚል በክራር ላይ የሰሩት ይገኝበታል። "እነዚህ ሥራዎች ቀላል አይደሉም። ማድመጥና መውደድን የሚፈልጉ ሰዎችን ይጠይቃል። በግለሰብ ደረጃ ብቻ የሚሰራ አይደለም'' ይላሉ ሙላቱ።

  ከምርምርና ከሙዚቃ ሥራው በተጨማሪ አፍሪካን ጃዝ ቪሌጅ (የአፍሪካ ጃዝ መንደር) የሚባል የሙዚቃ ትምህርት ቤት፣ የሬድዮ ፕሮግራም የነበራቸው ሲሆኑ ለሀርቫርድ ጥናት በሄዱበት ወቅት ተቋረጦ የነበረ ቢሆንም የሬድዮ ፕሮግራሙ አሁን ወደ አየር ተመልሷል።

  ምንጭ:- ቢቢሲ

  Read more »

 • ሩዋንዳን በጨረፍታ - Rwanda at a Glance

                                                 

  By (Aweke Abreham)

  ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ግዙፍ ቦይንግ አውሮፕላን ወርጄ አነስተኛዋን የኪጋሊ አየር ማረፍያ እግሬ ሲረግጥ ስለ ሩዋንዳ ያለኝ ምስል እንደነበረ ነው። ለአመታት ስለ ሃገሪቱ ከሰማሁት ካነበብኩትና በፊልም ካየሁት ተጠራቅሞ የተሰራው ምስል። እ.አ.አ በ1994 በቱትሲዎችና ለዘብተኛ ሁቱዎች ላይ ከተካሄደው ዘር ማጥፋት ጋር የተያያዘ አሉታዊ የሆነ ምስል ።  ከሀገሪቱ አጠቃላይ ህዝብ 84 በመቶውን ከሚይዙት ሁቱ ወገን የነበሩት የሀገሪቱ መሪ ጁቬኒል ሀቢያሪማና እና ሁቱው የቡሩንዲው ፕሬዚዳንት ሳይፕርዬን ንታርያሚራ የሚበሩበት አውሮፕላን ኪጋሊ አቅራቢያ ተመትቶ ከተገደሉ በኋላ ለአመታት በአክራሪ ሁቱዎች ሲጠበቅ የኖረው የሞት ቀጠሮ ደረሰ። የሁቱ ኢንተርሃምዌ ሚሊሻዎች አናሳዎቹ ቱትሲዎች ላይ በከፈቱት የዘር ማጥፋት ዘመቻ እስከ አንድ ሚሊየን የሚጠጉ ሩዋንዳዊያን ካለቁ በኋላ የሩዋንዳ መታወቂያ ሆቴል ሩዋንዳ በሚለውፊልምላይ እንዳሉ ዘግናኝ ትዕይንቶች አስፈሪ ነው። ይህን ምስል በአዕምሮዬ እንደታተመ ነው እንግዲህ ኪጋሊ የገባሁት።

  የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ጨዋታ ባደረገባቸው ቡታሬ እና ኪጋሊ ከተሞች ላይ በድምሩ አስራ አራት ቀናት ስቆይ እኔም የስራ ባልደረቦቼ የተገረምነው በህዝቡ ስርዓት እና ትህትና ነው። እንዲህ አይነት ትሁት ህዝብ እንዴት በገጀራ ለመተራረድ በቃ? የለሚው መልስ የማይገኝለት ጥያቄ ነው።ትህትናቸው ልዩ ነው።ቅንነታቸው ያስቀናል። ሩዋንዳዊያን ሃያ አመት ስላለፈው እልቂት ሲያስታውሱ ፊታቸው ላይ ሃዘን ይነበባል።በተቀረው ዓለም የሃገራቸው መታወቂያ መሆኑም ያማቸዋል። ትናንት የጨፈጨፉትም የተጨፈጨፉትም ወገኖች ዛሬ ይቅር ተባብለው በፍቅር ይኖራሉ።እንደ ጎሳ ሳይሆን እንደ ሀገር ነው የሚያስቡት።ካለፈው ተምረዋል።

  በሩዋንዳ ቆይታዬ ከተዋወቅኳቸው ሩዋንዳዊን አንዱ ንጋቦ ከሁቱ ወይስ ከቱትሲ ወገን ነህ ብዬ ስጠይቀው historically I'm Hutu ብሎ ነበር የመለሰልኝ።በጎሳ መከፋፈል አሁን ቦታ የለውም የሚል አንድምታ ነው ያለው መልሱ። አሁን የጎሳ ግጭት አይኑር እንጂ አብዛኛውን የሃገሪቱን የስልጣንና የሃብት ከፍታ የተቆጣጠሩት የፖል ካጋሜ ወገን የሆኑት አናሳዎቹ ቱትሲዎች ናቸው የሚል ቅሬታ ከሁቱዎች ወገን ይሰማል። የቅኝ ገዢዎች 'ቱትሲዎች ከኢትዮጵያ ነው የፈለሳችሁት በውበትም በእውቀትም ከሁቱዎች ትበልጣላችሁና ስልጣን የሚገባው ለናንተ ነው' በሚል የጀመሩት የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ ውጤት ነው ዘር ማጥፋቱ። የቡታሬ ከተማ ነዋሪ አንድ መቶ ሺህ ይገመታል።ከተማዋ ከኛዎቹ ሃዋሳ አልያም አዳማ ጋር ለንፅፅር አትቀርብም።ትንሽ ናት።በፅዳት ግን ታስከነዳቸዋለች።

  ኪጋሊ ከአፍሪካ ፅዱ ከተሞች አንዷ ናት።በፈረንጆቹ አቆጣጠር 2008 ላይ ፌስታልና መሰል የማይበሰብሱና አካባቢን የሚበክሉ የፕላስቲክ ምርቶችን መጠቀም በመላ ሃገሪቱ በአዋጅ ከተከለከለ በኋላ የኪጋሊ ውበት እና ፅዳት ትልቅ ለውጥ እንዳመጣ ነዋሪዎች ነግረውኛል። ከአህጉሪቱ ለኑሮ ምቹ የሆኑ ከተሞች ዝርዝርም ላይም ከመጀመሪያው ረድፍ የምትቀመጥ ናት ኪጋሊ።ከተማ ለማማር የግድ ከላይ እስከታች በመስታወት በተጀቦኑ ህንፃዎች መታጀብ እንደሌለበት ጥሩ ማሳያ መሆን ትችላለች። በሰፋፊና አረንጓዴ መናፈሻዎች የተሞላች እና በየቦታው ዛፎች የሚታዩባት ውብ ከተማ ናት። ኪጋሊም ሆነ ቡታሬ ላይ ከቦታ ቦታ ለመዘዋወር እኛጋ በተለምዶ ላዳ እያልን የምንጠራቸው አይነት የኮንትራት ታክሲዎችና የከተማ አውቶቡሶች ቢኖሩም አብዛኛው ሰው አንድ ሰው የሚያፈናጥጡ የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ ሞተር ብስክሌቶችን ይጠቀማል። አሽከርካሪዎቹ ከላይ የደንብ ልብሳቸውን ደርበው አናታቸው ላይ ከአደጋ መከላከያ ቆብ ማድረግና ለተሳፋሪዎችም ቆብ ማዘጋጀት ግዴታቸው ነው።

  ስለ ሩዋንዳ ውበት አንስቶ ስለ ሃገሬው ቆነጃጅት ሳይጠቅሱ ማለፍ አይገባምና በየቦታው አዲስ አበባ ያሉ እስኪመስል ኢትዮጵያዊያን ውብ ሴቶችን የመሰሉ ማየት መጀመሪያ ያልጠበቅነው ኋላ ላይ የለመድነው ሆነ። ኪጋሊ ወደሚገኘው ላሊበላ የኢትዮጵያ ምግብ ቤት ስንገባ ኢትዮጵያዊ መስላን በአማርኛ ያናገርናት አስተናጋጅ ሩዋንዳዊት ኖራ በሃገሬው ቋንቋ ኪኛሩዋንዳ መልሳ አስደንግጣናለች። ለኢትዮዽያዊያን ያላቸው ፍቅር ልዩ ነው።ሃገራችሁ የሃገራችን ወዳጅ የክፉ ቀን ደራሽ ናት ይላሉ።ደማችን አንድ ነው የውብ ሴቶች መገኛ መሆናችንም ያመሳስለናል የሚለው ከብዙ ሩዋንዳዊያን አንደበት የሚደመጥ ነው። ቢሾፍቱ ከተማ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ብዙ ሲቪል እና ወታደር የሆኑ ሩዋንዳዊያንን አግኝቼ በሚሰባበር አማርኛ አዋርተውኛል። ስለ ኢትዮጵያ ምን እንደሚያውቁ ሲጠየቁ ቴዲ አፍሮን የሚጠሩ ጥቂት አይደሉም።ላንባዲና የሚለው ዘፈኑን ከልጅ እስከ አዋቂ ተወዳጅ ነው።

  ሩዋንዳ አሁንም ጦርነት ያለ ይመስል በቀልድ መልክ 'ስትመጣ ሁለት ክላሽንኮቭ ይዘህልኝ ና' የሚል ወዳጅ ጥይት እንደ ቲማቲም በየቦታው የሚሸጥ የሚመስለው አይጠፋም። ሃገሬዎቹ ሲናገሩ እንኳን በጎሳ ተቧድኖ በግለሰብ ደረጃም ቢሆን ፀብ የተለመደ አይደለም።ፀብ፣ግጭትን መሸሽን ከጠባሳቸው ተምረዋል።አዲስ አበባ ላይ ቦክስ የሚያሰነዝር ነገር ኪጋሊ ላይ በዝምታ ይታለፋል።

  ወደ ኪጋሊ የሚወስደኝ አውሮፕላን ውስጥ ሆኜ ስለ ሩዋንዳ ሳስብ ጭንቅላቴ ውስጥ የነበሩት ምስሎች ቤተኛ ከመሆኑ የተነሳ ቡና ፈልቶአል ተብሎ ቢጠራ እንኳን አዲስ አበባ የሚመጣ የሚመስለኝ የሃገራቸው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ፣ሆቴል ሩዋንዳ ፊልም ያሉ ዘግናኝ ትዕይንቶ ብቻ ነበሩ። ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ ኪጋሊን ስለቅ ግን የሩዋንዳ ምስል በሌላ ተተክቶአል። በትላንት ፀባቸው መቃብር ላይ የዛሬ ፍቅርና መቻቻልን ያነፁ መልካም ሰዎች ባሉባት ሩዋንዳ!!

  ምዊሪዌ~መልካም ውሎ የዛሬ ሁለት ዓመት በዚሁ ቀን የተለጠፈ

  ምንጭ:-  ሸ.ነ.ግ - Sheneg

  Read more »

 • ከአለት ተፈልፍለው የተሰሩ ድንቅ አብያተ-ክርስቲያናት - The Incredible Rock-Hewn Churches

                                                                      

  በሰሜን ኢትዮጵያ የምትገኘው ላሊበላ ከአለት ተፈልፍለው የተሰሩት ድንቅ አብያተ-ክርስቲያናት የሚገኙባት ከተማ ናት። ለየት ያሉት እነዚህ አብያተ-ክርስቲያናት አሁን በዩኔስኮ ከተመዘገቡት የዓለማችን ድንቅ ታሪካዊ ስፍራዎች መካከል ይገኛሉ።

  ከአንድ ወጥ አለት በርና መስኮት እንዲኖራቸው ተደርገው የተሰሩት እነዚህ አብያተ-ክርስቲያናት አንዳንዶቹ እስከ 50 ሜትር የሚደርስ ጥልቀት አላቸው። የተገነቡትም በ12ኛው እና በ13ኛው ክፍለ ዘመን ነበር።

  በርካታ ምሁራንና የታሪክ አጥኚዎች እንደሚሉት ይህ ከአለት አብያተ-ክርስቲያናትን በመፈልፍል የመገንባት ጥበብ ከ500 ዓመታት ቀደም ብሎ የቀረ እንደሆነ ያምናሉ።

  ነገር ግን አሁን ባለንበት ዘመንም ከአንድ ወጥ አለት አብያተ-ክርስቲያናትን የመቅረፁ ሥራ በሰሜናዊ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተከናወነ መሆኑ ታውቋል። የቢቢሲው ዘጋቢ ኢማኑኤል ኢጉንዛ ወደ ስፍራው ተጉዞ ነበር።

  "እነዚህን አብያተ-ክርስቲያናትን የመስራቱ ጥሪና አጠቃላይ ቅርፁ ከእግዚአብሄር ዘንድ ተገልፆልኝ ነው'' ይላሉ የአርባ ዓመቱ ጎልማሳ አባ ገብረመስቀል ተሰማ ከአለት ፈልፍለው የሰሩትን አዲሱን ቤተክርስቲያ ተዘዋውረው እያሳዩ።

  በስፍራው በአጠቃላዩ አራት አብያተ-ክርስቲያናት ሲኖሩ እያንዳንዳቸው እርስበርሳቸው በሚያገናኝ ዋሻዎች ተያይዘዋል። የውስጥ ግድግዳቸውም በጥንቃቄ በተሰሩ ውብ ስዕሎች ተውበዋል።

  አባ ገብረመስቀል ተሰማ የኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን ቄስ ሲሆኑ፤ ከሌሎች ሦስት ሰራተኞች ጋር በመሆን በዙሪያቸው ያሉ ምዕመናን የአምልኮት ሥነ-ሥርዓት ለማከናወን ሊጠቀሙበት የሚችሉባቸውን አብያተ-ክርስቲያናት ከአለት ለመፈልፈል ሙሉ ጊዜያቸውን ሰውተዋል።

  "አዲሱ ላሊበላ ብዬ ብሰይመው ደስ የሚለኝን ይህን የውቅር የአብያተ-ክርስቲያናት ስብስብን ሰርቶ ለማጠናቀቅ አራት ዓመታትን ፈጅቶብናል'' ይላሉ።

  በእሳተ-ገሞራ የተፈጠረውን አለት ለመፈልፈልና ቅርፅ ለማበጀት በቅርብ የሚገኙትን መሮ፣ መጥረቢያና አካፋን ተጠቅመዋል። በዚህ ሂደት ከባዱ ሥራ የሚጀምረው ከግዙፍ አለት ጫፍ ላይ በመሆን እየጠረቡ ወደታች በመውረድ ነው። ይህም መስኮቶችን፣ በሮችንና መተላለፊያዎችን መጥረብን ይጨምራል።

                                                                   

  አብያተ ክርስቲያናቱ ከተቀረፁበት ቦታ ለመድረስ ቀላል አይደለም። አንደኛው ቤተክርስቲያን እየተቀረፀ ያለበት ስፍራ ለመድረስ ድንጋያማ የሆነ መንገድን ተከትሎ ለአንድ ሰዓት ያህል መጓዝን ይጠይቃል። አንዳንዶቹም በጣም የራቀ ቦታ ላይ ከመገኘታቸው የተነሳ የአካባቢው ባለስልጣናት ሳይቀሩ አብያተ-ክርስቲያናት መሰራታቸውን ሲሰሙ ተደንቀዋል።

  አዳዲሶቹ አብያተ-ክርስቲያናት የሚገኙት አስደናቂ ኮረብታዎች ባሉበትና ታዋቂዎቹ ከአለት የተፈለፈሉ የላሊበላ አብኣተክርስቲያናትን ለማየት በሚኣስችለው የሰሜን ኢትዮጵያ ክፍል ወሎ አካባቢ ነው።

  አስራአንዱ ከወጥ አለት የተፈለፈሉት የላሊበላ ውቅር አብያተ-ክርስቲያናት ለኢትዮጵያ ክርስትና ዋነኛ ሥፍራ በሆነው ቦታ ላይ በ12ኛው ክፍለዘመን ነበር የተሰሩት።

  ተፈልፍለው የተሰሩትም ወደ ኢየሩሳሌም ለመጓዝ ለሚቸገሩ ኢትዮጵያዊያን ምዕመናን ሲል አዲሲቱን ኢየሩሳሌም በቅርብ ለመገንባት በተነሳው በንጉሥ ላሊበላ ዘመን ነው።

  ረጅም ዘመንን ካስቆጠሩት የላሊበላ አብያተ-ክርስቲያናት መካከል ጣሪያው በመስቀል ቅርፅ የተሰራው ታዋቂው የቅዱስ ጊዮርጊስ ወይም ቤተ-ጊዮርጊስ እንዲሁም ከአንድ ወጥ አለት በመቀረፅ በዓለም ትልቁ የሆነው የቤተ-ማሪያም አብያተ-ክርስቲያናትን ጨምሮ አንዳንዶቹ ከመሬት በታች እስከ 40 ሜትር ይጠልቃሉ።

  አንዳንድ አፈ-ታሪኮች እንደሚሉት አብያተ-ክርስቲያናቱ በሚፈለፈሉበት ጊዜ በንጉሥ ላሊበላ ከውጪ እንዲመጡ የተደረጉ ሰራተኞች ቀን ቀን ሲሰሩ ይውሉና ሌሊት ደግሞ መላዕክት ሥራውን ያከናውኑ እንደነበር ይተርካሉ።

  ነገር ግን አባ ገብረመስቀል ይህንን አይቀበሉትም፤ አዲሶቹን ውቅር አብያተ-ክርስቲያናት ለመስራት የተነሳሱትም የላሊበላን አብያተ-ክርስቲያናት በእግዚአብሄር የተመሩ ኢትዮጰያዊያን የሰሩት መሆኑን ለማስመስከር እንደሆነ ይናገራሉ።

                                                                       

  "ኢትዮጵያዊያን ይህን መሰለ ተግባርን ለማከናወን የሚያበቃ እውቀትና ክህሎት አልነበራቸውም ብለው የሚያምኑ አንዳንዶች አሉ። ቢሆንም ግን አሁን እኔ በምሰራበት ጊዜ ማንም አንዳች ነገር አላሳየኝም፤ ይህን ድንቅ ሥራ እውን ያደረኩት በመንፈስ-ቅዱስ አማካይነት ነው'' ይላሉ።

  "በሰሜናዊው ኢትዮጵያ እየተገኙ ላሉት አዳዲስ አብያተ-ክርስቲያናት መንፈሳዊነት ዋነኛው መሰረት ነው'' ሲሉ የሚያብራሩት የቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር ማይክል ገርቨርስ ናቸው።

  ፕሮፌሰር ማይክል ከሥነ-ህንፃ እና ከፊልም ባለሙያዎች ጋር በመሆን ይህንን እየጠፋ ያለውን የግንባታ ጥበብ መዝግቦ ለማስቀመጥ አንድ ሥራ ጀምረዋል። በዩናይትድ ኪንግደሙ አርኬዲያ ፈንድ ቢደገፈው እቅዳቸውም ዘመናዊ የመረጃ ቋት በማዘጋጀት ለሕዝብ ክፍት ማድረግ ነው።

  "ከድንጋይ የሚፈለፈሉ አብያተ-ክርስቲያናትን መስራቱ የሚቀጥል ከሆነ ዘመናዊነት እየተስፋፋ በሚመጣበት ጊዜ መፈልፈያ መሳሪያዎችን መጠቀም ስለሚጀመር፤ በእጅ የመስራቱ ጥበብ ሙሉ ለሙሉ ይጠፋል'' ይላሉ።

  "ስለሆነም ከአንድ የግንባታ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ እየሄድን የግንባታውን ጥበብ የሚያውቁትን ባለሙያዎችን በማነጋገር ሥራቸውን እንዴት እንደሚያከናውኑ ያላቸውን የግል ዕውቀት እንመዘግባለን። አላማችንም ያገኘውን መረጃ ለሕዝብ ክፍት ማድረግ ነው።

  ቡድኑ እስካሁን 20 አዳዲስ አብያተ-ክርስቲያናትን በተራራማዎቹ በሰሜናዊ የአማራና የትግራይ ክፍሎች ውስጥ አግኝቷል።

  "የበለጠ በፈለግን ቁጥር ተጨማሪ እናገኛለን። በርካታ አብያተ-ክርስቲያናት እንዳሉ ስለማምን ሌሎች በርካቶቸን አግኝተን እንደምንመዘግባቸው ተስፋ አደርጋለሁ። ከአለት የተፈለፈሉ አብያተ-ክርስቲያናት አንድ ጊዜ አገልግሎት መስጠት ከጀመሩ በኋላ ብዙም ጥገና የሚፈልጉ አይደሉም። ለሺህ ዓመታት አገልግኦት ሊሰጡ ይችላሉ'' ሲሉ ፕሮፌሰር ገርቨርስ ይጨምራሉ።

  ለአባ ገብረመስቀል ሥራቸው አብያተ-ክርስቲያናቱን የገነቡበት ጥበብ መኖሩን ከማረጋገጥ በእጅጉ የበለጠ ነው።

  "አብያተ-ክርስቲያናቱበይፋ ተከፍተው በአካባቢዬ ያለው ሕብረተሰብ የሐይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓቶችን ሲያከናውን ለማየት ጓጉቻለሁ። በቅርቡ... በጣም በቅርቡ እነዚህ የእግዚአብሄር ቤቶች በደስተኛ ሰዎች ይሞላሉ'' ብለዋል ገፃቸው በፈገግታ በርቶ።

  ምንጭ: ቢቢሲ

   

  Read more »

 • የዲቪ ነገር - DV Lottery

                                                                 

  ኤፍሬም እንዳለ

  ያለፈው ቅዳሜ ነው፡፡ ጠዋት ላይ በከተማችን አንዱ ክፍል በተለያዩ የእድሜ ደረጃዎች ያሉ ሀያ አምስት፣ ሠላሳ የሚሆኑ ሰዎች ሰብሰብ ብለው ይቁነጠነጣሉ፣ ይንጎራደዳሉ፡፡ ምን ተፈጠረ? የተፈጠረውማ ገና በጠዋቱ መብራቱ እንደለመደው ድርግም ብሎ ጠፍቷል፡፡

  እና ደግሞ ለአዲስ አበባ መብራት መጥፋት ምን አዲስ ነገር አለው! አዲአለው!ማ እነኚሀ ሰዎች በሌሊት የመጡት ለአንድ አስቸኳይ ጉዳይ ነበር … የዲቪ ፎርም ለመሙላት፡፡

  አዎ የሌሊት ህልማቸውን አቋርጥው የእውን ህልማቸውን ሊያሳድዱ የመጡ ናቸው … ዲቪ ሞልተው፣ እጣ ደርሷቸው እዛቹ አሜሪካ የሚሏት ሁሉም የሚሮጥባት አገር ለመሄድ፡፡

  እናማ፣ እንደተለመደው ገና በማለዳው መብራቱ ድርግም ሲል፣ ለጥቂት ሰዓታትም ቢሆን ተስፋቸውን አጨልሞባቸዋል፡፡ ወይም ልክ በዓል ሲደርስ በበዓሉ ወቅት “ምንም አይነት የሀይል መቆራራጥ እንዳይደርስ ዝግጅት ተደርጓል እንደሚባለው ሁሉ “የዲቪ ሎተሪ ፎርም መሙያ ጊዜ እስኪጠናቀቅ ምንም አይነት የሀይል መቆራረጥ እንዳይኖር ዝግጅት ተደርጓል” ይባልልን፡፡

  በነገራችን ላይ፣ አሁን ኢንተርኔት ካፌውም በዝቶ፣ ሰዉ በየመሥሪያ ቤቱም፣ በየመኖሪያ ቤቱ ኮምፒዩተሩ በዝቶ አንድ ሰሞን እናይ የነበረውን ግርግር ባናይም ህዝባችን እንደ ጉድ የዲቪ ፎረም እየሞላ ነው፡፡ የቀይ ባህርንና የሜዲቴራኒያንን አሰቃቂ አደጋዎች እንኳን ሳይፈራ የሚፈልስ ህዝባችን እንደ ዲቪ አይነት አድል ማግኘት ቀላል አይደለም፡፡ በነገራችን ላይ ከጠቅላላችን በየዓመቱ ስንታችን እንሆን ፎርም የምንሞላው!

  ለምሳሌ በላይቤሪያና በሌሎች የምእራብ አፍሪካ አገሮች ከመላው ህብረተሰብ ወደ 10% የሚጠጋው ዲቪ ፎርም ይሞላል ነው የሚባለው፡፡ በጣም ብዙ ቁጥር ነው ይላሉ፡፡ እኛ ዘንድ አሥር በመቶ ቢባል ወደ አስር ሚሊዮን ህዝብ ማለት ነው፡፡ አሥር ሚሊዮናችንም ሞላን አርባ ሚሊዮናችን፣ አንዱ ሀቅ ዘንድሮ ብዙ ነገሮች የሰዉን ልብ እያሸፈቱት ነው፣ ውጪ፣ ወጪ እያስባሉት ነው፣ የማያውቀውን አገር እያስናፈቁት ነው፡፡

  እንደ በፊቱ “ሠርቶ መኖር አገር ውስጥ!” ብሎ ነገር ከመልካም ምክርነት ይልቅ ወደ ፌዝ የተጠጋ ይሆናል፡፡ ስንት ዓመት ሙሉ ራሳቸውን ለሥራ ብቁ ለማድረግ ናላቸውን ሲያዞሩ የኖሩ የከፍተኛ ደረጃ ትምህርት ተመራቂዎች ሥራ እያጡ አራትና አምስት ዓመት በሚንከራተቱበት ዘመን አንዳንድ የለመድናቸው አባባሎች ፌዝ ይሆናሉ፡፡ በሌለ ሥራ፣ ባልተፈጠረ የሥራ መስክ…

  “አገር ውስጥ ሠርቶ አይኖርም!” 
  “ሰው አገር ከመሄድ አንዱ መሥሪያ ቤት ብትቀጠር አይሻላትም!”

  ብሎ ነገር ከመልካም ምኞትነት የማያልፍበት ዘመን ላይ እየደረስን ነው፡፡ እናማ… ሰዋችን የዲቪ ፎርም ለመሙላት ይህን ያህል የሚጨነቀው ልበ ደረቅ ስለሆነ፣ አገሩን ስለጠላ ምናምን አይደለም፡፡

  በተለየ ወጣቱ እንደ መስቀል አደባባይ ሰልፍ በኢንተርኔት ካፌዎች ቢኮለኮል አይገርምም፡፡ ስንት ዓመት ለፍተው ከተመረቁ በኋላ አራትና አምስት ዓመታት ሥራ በማይገኝበት ጊዜ ሰዉ ‘ዲቪ መዳኛዬ’ ቢል አይገርምም፡፡

  አሁን ግን ዲቪ ከባድ ጠላት ተነስቶበታል፣ ክንዳቸው ሀያል የሆኑ ጠላት፣ ዶናልድ ትረምፕ የሚባሉ ጠላት፡፡ ኮንግረስን “ይሄንን ዲቪ የሚሉትን ነገር ሰርዙልኝ፣” እያሉ ነው፡፡ በርካታ ደጋፊዎች አሏቸው - ከሪፐብሊካን ፓርቲው ብቻ ሳይሆን ከዴሞክራቲክ ፓርቲውም፡፡ በዚህም የተነሳ ‘የዲቪ ሎተሪ ዘመን ሊያጥር ይሆን እንዴ!” እየተባለ ነው፡፡

  የዲቪ ሎተሪ ተቃዋሚዎች አንዱ ትልቅ ምክንያት ሽብርተኞች ሰተት ብለው አገራችን እንዲገቡ ማድረግ ይሆናል የሚል ነው፡፡ “ሽብርተኛ ድርጅት ከሆንክ ከበርካታ ሀገራት በመቶዎች የሚቆጠሩ አባላቶችህ ፎርም እንዲሞሉ ታደርጋለህ … ከእነዚህም አንዱ ወይም ሁለቱ እጣው ሊደርሳቸው ይችላል” ብለዋለ አንድ የዲቪ ተቃዋሚ የኮንግረስ አባል፡፡

  “ዲቪ ሎተሪ ሸፍጥ የበዛበት፣ ምንም አይነት ኤኮኖሚያዊ ወይንም ሰብአዊ ጠቀሜታ የሌለው ነው” ብለዋል ሌላኛው የምክር ቤት አባል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በሪፐብሊካኖቹ ቁጥጥር ስር ባለው በአሜሪካ ኮንግረስ ውስጥ ዲቪ ሎተሪን ለማስቆም ያለሙ ቢያንስ ሁለት የውሳኔ ረቂቆች አሉ፡፡

  ሄሻም መሀመድ ሃዳዬት የተባለ ግብጻዊ በሎስ አንጀለስ አውሮፕላን ጣቢያ ተኩስ ከፍቶ ሰዎች ይገድላል፡፡ ግብጻዊው ከጥቂት ዓመታት በፊት በዲቪ ሎተሪ ነበር አሜሪካ የገባው፡፡ ድርጊቱ አቧራ አስነስቶ ነበር፡፡ “ይኸው ሎተሪ፣ እጣ እያላችሁ አሸባሪዎችን እያስገባችሁ ልታስጨርሱን ነው!” አይነት ክርክር ተነስቶ ነበር፡፡

  በቀደም እለት ደግሞ ኒው ዮርክ ውስጥ በመኪና ብዙ ሰዎች ገጭቶ የገደለው ሳይፉሎ ሳይፖቭ እንዲሁ በዲቪ ሎተሪ የገባ ነው፡፡ በ2009 ከኡዝቤክስታን እድል ካገኙት 3‚284 ሰዎ አንዱ ነው፡፡ እንደውም እሱ ከገባ በኋላ መአት ሰዎች ጎትቷል ነው የሚባለው፡፡

  በነገራችን ላይ ብዙዎች ዲቪን ዘመናዊ ባርነት ይሉታል፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ አብዛኞቹ በዲቪ ከየደሀ ሀገራት የሚሄዱ ሰዎች ዝቅተኛ በሚባሉ ሥራዎች ላይ መውደቃቸው ነው፡፡ “አሜሪካውያን ዝቅተኛዎቹን ሥራዎች እነሱ መሥራት ስለማይፈልጉ የዘየዱት ዘዴ ነው፣” ይላሉ፡፡

  በተለይም ከአፍሪካ ሀገራት ወደላይ የሚፈናጠሩ ብዙ አይደሉም ነው የሚባለው፡፡ ብዙ የእኛ ልጆች ማጣፊያው አጥሯቸው ባክነው ቀርተዋል ይባላል፡፡ በሌላ በኩል ቢከፋም ቢለፋም የአቅማቸውን ያህል እየሠሩ ቤተሰቦቻቸውን የሚያስተዳደሩ ብዙ ናቸው፡፡

  “ህይወቴን ለውጦታል፣” ብሏል ቪክተር ኦቴ የተባለ የቬኑኒዙዌላ ተወላጅ፡፡ “እኔ ከአገር ከወጣሁ በኋላ ቬኑዙዌላ ምን እንደሆነች ተመልከቱ!” ግን ከመጭበርር አላመለጠም፡፡ ለአንድ ኩባንያ 150 ዶላር ከፍሏል፡፡ እጣ ሲደርስው ኩባንያው ተጨማሪ 3‚000 ዶላር ክፈል አለው፡፡ አንድ አሜሪካዊ ጓደኛው ነው “ምንም መክፈል የለብህም!” ብሎ ያተረፈው፡፡

  በቅርብ ዓመታት አብዛኞቹ የዲቪ አሸናፊዎች ከአፍሪካና ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ናቸው፡፡ ከእነኚህም መሀል እነኢራን፣ ግብጽ፣ ባንግላዴሽ፣ ኡዝቤክስታን፣ ቱርክ የመሳሰሉ ሙስሊም ሀገራት አሉባቸው፡፡ ባለፉት ዓመታት ከ77% በላይ ዲቪ አሸናፊዎች ከአፍሪካና ከእስያ ናቸው፡፡

  ለበርካታ ዓመታት ግብጽና ባንግላዴሽ በጣም ብዙ እድለኞች ልከዋል፡፡ ከ2001 ጀምሮ ባለው ጊዜ ከባንግላዴሽ ብቻ በዲቪ ሎተሪ 180‚000 በላይ እድለኞች አሜሪካ ገበተዋል፡፡ እንዲሁም ከ191‚000 በላይ ኢራናውያን በዚህ ጊዜ አሜሪካ ገብተዋል፡፡ የእኛ ስንት ይሆኑ ይሆን ! በነገራችን ለይ በዲቪ ሎተሪ 2019 ባለፉት ዓመታት 50‚000 ዜጎቻቸው ዲቪ ሎተሪ የደረሳቸው እንደ ካናዳ፣ ቻይና፣ ህንድ፣ ናይጄሪያና ሜክሲኮ በዘንድሮው እጣ አልተካተቱም፡፡

  በዓለም አቀፍ ደረጃ የዲቪ ፎርም የሚሞላው ሰው መአት ነው፡፡ ለምሳሌ ለዲቪ 2018 ያመለከቱት ሰዎች 14‚600 000 በላይ ናቸው፡፡ ያስመዘገቧቸው ቤተሰቦች ሲጨመሩ ደግሞ ቁጥሩ ከ23 ሚሊየን ያልፋል፡፡

  የተመረጡት 115 968 ናቸው፡፡ ከእነኚህ ነው እንግዲህ በኢንተርቪውም በምኑም እየተቀነሱ 50‚000ዎቹ ብቻ የሚቀሩት፡፡ ማንኛውም አገር ከ7% በላይ የዲቪ ሎተሪ ቪዛዎች አይሰጡትም፡፡ ይህም ማለት 3‚500 ቪዛዎች ማለት ነው፡፡

  በዚህ ላይ ደግሞ አጭበርባሪው በጸጉር ልክ ነው፡፡ በብዙ ሀገራት በአሜሪካ መንግሥት አካላት የተከፈቱ በሚመስሉ ድረ ገጾች ብዙዎች ይታለላሉ፡፡ ብዙዎቹ በተለያያ ሰበብ ገንዘብ ይጠይቃሉ፡፡ ብዙ አመልካቾች ዝርዝሩን ሰለማያውቁትና አሜሪካ ለመግባት ባላቸው ከፍተኛ ጉጉት ገንዘባቸውን ይከስራሉ ነው የሚባለው፡፡

  እድሉ ደርሶ ወደዛ ሲኬድ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ይሆናል ብለው ብዙ ችግር ውስጥ የሚገቡ አሉ፡፡ ሁሉም ነገር እንደቤታችው እየመሰላቸው፣ እዚህ በየመዝናኛው፣ በየሞሉ ረብጣ ብር እየመዘዙ እንደሚሸለለው እዛም በየቦታው ረብጣ ብር መምዝዝ የሚያስጨበጭብና የሚያስቀና እየመሰላቸው ችግር ላይ የሚወድቁ ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡

  አሜሪካ ለሀያ ዓመታት በላይ የኖረ አንድ ወዳጃችን የነገረን ታሪከ አለ፡፡ ልጁ እዚህ ቅልጥ ያለ አራዳ የሚባል አይነት ነው፡፡ ምንም እንኳን ዘንድሮ የአራድነት ትርጉም ራሱ የሚሊዮን ዶላር ጥያቄ ቢሆንም፡፡ እየተጣጠፉ፣ እየተገለባባጡ ምን እያሉ ገንዘበ መሥራት ይችልበታል፡፡ አሜሪካ ይሄድና እንዲሁ እዚህ በለመደው መንገድ ይገለባበጥ፣ ይተጠጣፍ ጀመር፡፡ ደግሞ ተሳካለትና ዶላረ ሰበሰበ፡፡

  አንድ ቀን መኪና ለመግዛት ይሄዳል፡፡ የሠላሳ ሺህ ዶላር መኪና ሊገዛ ከተስማማ በኋላ “እሺ ክሬዲት ካርድ፣” ሲሉት፣ ልምድ አይለቅም አይደል፣ “አይ በካሽ ነው የምከፍለው” ይላቸዋል፡፡ ከዛም የመኪና መሸጫው ባለቤት “እሺ ጠብቀኝ” ብሎት ቢሮው ይገባል፡፡ ምንም ያሀል ሳይቆይ በመኪና ከች አሉለት … የአገር ውስጥ ገቢ ሰዎች፡፡

  “ይሄን ሁሉ ገንዘብ ከየት አመጣህ?” አይነት ማፋጠጥ ጀመሩ፡፡ መንተባተብ ሲጀመር “የምናቀርብልህ ጥያቄዎች አሉ” ተብሎ ተወሰደ፡፡ ታሪኩን በሰማን ጊዜ ገና መከራ ውስጥ ነበር፡፡
  እናማ ዜጎቻችን እድል ደርሷቸው ያለ በቂ መረጃ እየሄዱ ችግር እንዳይደርስባቸው እውነተኛ መረጃ የሚያገኙበት ስርአት መዘርጋት ብልህነት ይሆናል፡፡

  ባልና ሚስቱ ጥሩ ሥራ፣ ጥሩ ገቢ አላቸው፡፡ የራሳቸው አሪፍ ቤት፣ መኪና ምናምን አላቸው፡፡ በእኛ አገር ደረጃ ከፍተኛ ኑሮ ካላቸው የሚጠጉ ናቸው፡፡ እና በአንድ ወቅት ባልየው ዲቪ ሎተሪ ይደርሰዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ዘመድ አዝማድ “መቼም ይሄን ሁሉ ነገር ጥለው አይሄዱም” ምናምን ይላል፡፡ ሰው አሜሪካ የሚሄደው ለተሻለ ኑሮ፣ ለተሻለ ገቢ አይደል እንዴ ! እነሱ እንዲሀ አይነት ኑሮ እየኖሩ ምን ጎደለባቸወና ይሄዳሉ ! ዘመድ፣ አዝማድ መከረ፣ “እንደው እንዲች ብላችሁ እግራችሁን እንዳታነሱ !” ተባሉ፡፡

  አልሰሙም፡፡

  ያላቸውን ንብረት ሁሉ ቸበቸቡት፡፡ “ደህና ሁኚ አንቺ ምናምን አገር፣” ብለው ሄዱ፡፡ ዓመታት አለፉ፡፡ ከዛም ድንገት ሳይታሰብ ሁለቱም አዲስ አበባ ከች አሉ፡፡ አሜሪካ አልሆነችላቸውም፡፡ ቢሉ፣ ቢለፉ ምንም ሊሳካ አልቻለም፡፡ እዚህ የተለማመዱት የማሪንጌቻቻ ኑሮ አሜሪካ ፊልም ላይ ብቻ የሚያዩዋት ሆነ፡፡ እዚህም ሲመጡ ምኑም ምናምኑም አልሆነ፡፡ ትዳር ፈረሰ፣ ከዛ በኋላ ሁለቱም የት ይግቡ፣ የት ይውጡ የሚያውቅ የለም፡፡

  እነኚህ አይነት ሰዎች አጠቃላይ ስዕሉን ማሳያ አይሆኑም፡፡ በጣም ብዙ ወገኖቻችን ጥርሳቸውን ነክሰው ጥሩ ደረጃ ከመድረስም አልፈው ለቤተሰቦቻቸውና ለጓደኞቻቸው ሳይቀር ተርፈዋል፡፡ ዶላሩን ወደ አገር ውስጥ የሚያጎርፉት ብዙዎች በዲቪ የሄዱና በዲቪ በሄዱ ዘመዶቻቸው ብርታት አሜሪከ የገቡ ናቸው፡፡

  እናም ይሄ ‘ዲቪ ይሰረዝ’ የሚባለው ነገር ተቀባይነትን አግኝቶ ትረምፕና የአላማው ደጋፊዎች የልባቸው ከሞላ በእርግጥም እኛም እንጎዳለን ማለቱ ማጋነን አይሆንም፡፡ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ምናልባትም ከዛ በላይ የሚሆን ህዝብ ከውጪ ከዘመድ አዝማድ በሚላክለት ገንዘብ ትንፋሹን የሚያቆይባት አገር እንዲህ አይነት እድሎች ሲታጠፉባት “እሰይ” የሚያሰኝ አይሆንም፡፡

  ለአሁኑ ግን መብራቶችም እባካችሁ ተባበሩ፡፡ ግዴለም፣ መብራት ባይኖርም የቀዘቀዘ ሹሯችንን ግጥም አድርገን እንበላለን፡፡ የሰዋችንን የዲቪ ህልም ግን አታቀዝቀዙበት፡፡

  እስከዛው ድረስ ዲቪ ፎርም ለሞሉና ለሚሞሉ ሁሉ መልካሙ ይግጠማቸው እንጂ ሌላ ምን ይባላል

  ምንጭ:- የሸገር FM 102.1 ሬዲዮ

   

  Read more »

 • ኮርያ ላይ ሆኜ አድዋን ሳስባት

                         
  ዋና ከተማ ሶኡል፣ ናምዮንግ ዶንግ፣ ዮንግሳን-ጉ (29 Itaewon-ro, Namyeong-dong, Yongsan-gu, Seoul) በሚገኘው የጦርነት መታሰቢያ ሙዝየም ግድግዳዎች ላይ በኮርያ ጦርነት ወቅት ከመላው ዓለም ተሰባስበው ሲዋጉ የተሠዉ ወታደሮች ስም ዝርዝሮች ተጽፈዋል፡፡ በዚህ ዝርዝር ውስጥ ኢትዮጵያ 121 ወታደሮቿን መሠዋቷ ተገልጧል፡፡ ከሁሉም ሀገሮች ብዙ ወታደሮችን ያሰለፈችውና ብዙ ወታደሮቿንም ያጣችው አሜሪካ ናት፡፡ የአሜሪካ ወታደሮች ዝርዝር በየግዛታቸው ረዥሙን ግድግዳ በሁለት እጥፍ ሞልቶታል፡፡
  ይህን ሙዝየም ስጎበኝ ሁለት ነገሮች በሐሳቤ ይመጡ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ሀገራችን በታሪኳ እጅግ ብዙ ጦርነቶችን አድርጋለች፡፡ በጦርነቱ ተጎድተናል፤ በጦርነቱም ተጠቅመናል፡፡ የሕይወት ጥፋት፣ የንብረት ጉዳት ደርሶብን፣ ማኅበራዊ ቀውሶችንም በተሸክመን የተጎዳነውን ያህል ሀገራችንን ከጠላት ጠብቀን በማወቆየታችን ነጻነት የሚያስገኘውን መንፈሳዊና ቁሳዊ ጥቅምም አግኝተናል፡፡ በነጻነታችን ላይ ቆመን ሌሎች ነጻ እንዲሆኑም ታግለናል፡፡ ጦርነቶቻችን የዛሬዋን ሀገራችንንና የዛሬዎቹን ሕዝቦቻችንን አሁን ባሉበት መልክ ሠርተዋቸዋል፡፡ ይህ ሁሉ ቢሆንም የኢትዮጵያን የጦርነት ታሪክ የሚያሳይ አንድም የጦርነት መታሰቢያ ሙዝየም ግን የለንም፡፡
  በኢትዮጵያ ምድር የነበሩ ጦርነቶችን፤ ጦርነቶቹ በሀገሪቱ ላይ ያደረሱትን አዎንታዊና አሉታዊ ተጽዕኖዎች፣ በጦርነቶቹ የነበረውን አሰላለፍ፣ ትጥቅ፣ ስንቅ፣ ወታደራዊ አደረጃጀት፣ የጦርነቱ መሪዎችንና ተሳታፊዎችን፣ የተሠዉ ጀግኖቻችንን፣ የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን፣ የወደመ ንብረታችንን፣ የተገኘ ነጻነታችንን ሊያሳይ የሚችል ብሔራዊ ሙዝየም ያስፈልገን ነበር፡፡
  በዚህ ሙዝየም ከጦርነት ጋር የተያያዙ መዛግብት ይቀመጡበታል፣ ከጦርነት ጋር የተያያዙ ቅርሶች ይሰበሰቡበታል፣ ከጦርነት ጋር የተያያዙ ፎቶዎች፣ ሥዕሎችና ቪዲዮዎች ይታዩበታል፤ ጀግኖቹ ይከበሩበታል፤ አጥፊዎቹ ይወቀሱበታል፤ ሀገርን ሀገር አድርጎ ለማቆየት የተከፈለው መሥዋዕት ይዘከርበታል፤ ካለፈው ትምህርት ይወሰድበታል፤ለወደፊቱ ጥንቃቄ ይደረግበታል፡፡ የጦርነት መታሰቢያ ሙዝየም ስለሌለን ከጥንት እስከ ዛሬ አባቶቻችን እንዴት ተጋድለው፣ በምን ተጋድለው፣ ምን ለብሰው ተጋድለው፣ ምን ሰንቀው ተጋድለው፣ እንዴት ዘምተው ተጋድለው፣ እንዴት ተደራጅተው ተጋድለው ይህችን ሀገር እንዳቆዩዋት መልክ ባለው ደረጃ ታሪኩን ለመዘከር አልቻልንም፡፡ የቀድሞ መሣሪያዎቻችን እየጠፉ፣ የቀድሞ ወታደራዊ ማዕረጎች እየተረሱ፣ የቀድሞ የስንቅ ማዘጋጃ ሞያዎችና ዕቃዎች እየቀሩ፣ የቀድሞ የጦርነት ዐውዶች ለሌላ ተግባር እየተቀየሩ ይገኛሉ፡፡ 
  ካለፈው ለመማር ባለመቻላችን ጦርነቶችን ደጋግመናቸዋል፤ ዛሬም ወደ ጦርነት የሚያመራው መንፈሳችን እንዳለ ነው፡፡ ለግጭቶች መፍቻ የሚሆኑ በቂ መንገዶችንም አልተለምንም፡፡ ካለፈው በሚገባ የማይማር የትናንቱን ስሕተት ለመድገም የተረገመ ነው ይባላልና፡፡
  ሌላው ጉዳይ ደግሞ ለሀገራቸው ሲሉ መሥዋዕት የከፈሉ ጀግኖቻችን ጉዳይ ነው፡፡ ለመሆኑ በአድዋ ጦርነት የተሰለፉ ጀግኖች ስም ዝርዝር ይታወቃል? ተጽፎ ሊገኝበት የሚችል ይፋዊ መዝገብስ አለን? አድዋን ከተራራነት ወደ ታሪካዊ ሙዝየምነት ሳንቀይረው 115 ዓመታት አለፉ፡፡ አድዋና ማይጨው ቦታ እንጂ ሥፍራ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡ በኮርያ ጦርነት ጊዜ አሜሪካ 36574 ወታደሮች ሞተውባታል፡፡ የእነዚህ ሁሉ ወታደሮች ስም ዝርዝር በጦርነት መታሰቢያ ሙዝየሙ ላይ ተጽፏል፡፡ በጉራዕ፣ በጉንዲት፣ በዶጋሊ፣ በአድዋ፣ በማይጨው፣ በመተማ፣ በሶማልያ፣ በባድሜ የተሠዉት ወታደሮቻችን ለመሆኑ ስንት ናቸው? እነማንስ ናቸው? መቼ ነው ይፋዊ ዝርዝራቸው የሚነገረው? የሰው ዋጋ ተከፍሎ እንደዋዛ የምናልፈውስ እስከ መቼ ነው? የኛን ጦርነቶች ተዋጊዎች ዝርዝር ሁሉን ማወቅ ያስቸግር ይሆናል፡፡ የምናውቃቸውን ዘርዝረን ለረሳናቸው ደግሞ ‹ያልታወቀው ወታደር› የተሰኘውን ሐውልት ማቆም እንችላለን፡፡ ያለፉትን የሚረሳ ሰው ራሱ የሚዘነጋበትን መንገድ የሚጠርግ ነው ይባላል፡፡ መታሰቢያችን ከዘመናችን ማለፍ የሚችለው የቀደሙትን መታሰቢያ ከዘመናቸው ማሳለፍ ከቻልን ነው፡፡ 
  የኮርያ የጦርነት ሙዝየም በጀግንነትና በኩራት የሚዘክራቸውን ኮርያውያንንና የየሀገሩን ባለውለታዎች ሳይ የሀገሬ ጀግኖች ያሳዝኑኛል፡፡ ዋጋ በከፈሉባት ሀገር እነርሱን የሚያስታውስና ታሪካቸውን በየትውልዱ ሊቀርጽ የሚችል ክብራቸውንና ደረጃቸውን የጠበቀ መታሰቢያ አላገኙም፡፡ ምናልባትም የሚያዝነው መንፈሳቸው ይሆን ሀገሪቱን በየዘመናቱ አዙሪት ላይ የሚጥላት?
  ምንጭ :- ከዳንኤል ክብረት
   
  Read more »

 • ኩሬአውያን

                                                      
  ከዳንኤል ክብረት
  ትውፊታውያን የሀገራችን ሰዓሊዎች የማያመዛዝንን ሰው ሲስሉ አንድ ዓይና አድርገው ይስሉት ነበር፡፡ ሰፋ አድርጎ የማያይ፤ እውነትን በከፊል ብቻ የሚቀበላት፤ ከሚያውቀው ውጭ ሌላ ነገር ያለ የማይመስለው ነው ማለታቸው ነው፡፡ ‹እልፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል› የሚል አባባልም አለ፡፡ ዕውቀትህን፣ አመለካከትህንና አካሄድህን ባሻሻልክ ቁጥር ያላየኸውን ታያለህ፣ ያልሰማኸውን ትሰማለህ፤ ያልተገለጠልህ ይገለጥልሃል፤ የረቀቀው ይጨበጥልሃል፤ እውነት ነው ያልከው ውሸት፣ ውሸት ነው ያልከውም እውነት ሆኖ ልታገኘው ትችላለህ ሲሉ ነው፡፡
   
  ቀደምት ሊቃውንት ሁለት ዓይን የተሰጠን በአንዱ የራሳችን በሌላው የሌላውን ለማየት ነው፡፡ ሁለት ጆሮ የተሰጠን በአንዱ የራሳችንን በሌላው የሌላውን ለመስማት ነው፡፡ ሁለት እጅ የተሰጠን በአንዱ ለመስጠት በሌላው ለመቀበል ነው፡፡ ሁለት እግር የተሰጠን በአንዱ ወደራሳችን በሌላው ወደ ሌላው ለመሄድ ነው ይሉ ነበር፡፡  
   
  ሞንጎልያውያንም ከዚህ ጋር የሚሄድ ብሂል አላቸው፡፡ 
   
  በአንዲት የሞንጎልያ ትንሽ መንደር ውስጥ በምትገኝ ኩሬ አንዲት ዓይን ብቻ ያለቺው ዕንቁራሪት ይኖር ነበር፡፡ ለእርሱ ዓለም ማለት ያቺ ኩሬ፣ ንጉሥም ማለት እርሱ ነው፡፡ ከእርሱ ኩሬ የተሻለ ቦታ፣ ከእርሱም የበለጠ ዕድለኛ የለም፡፡ የሚመኘው ነገር ቢኖር እርሱ ያገኘውን ይህንን ታላቅ ነገር የሚካፈለው ጓደኛ እንዲያገኝ ብቻ ነበር፡፡
   
  አንድ ቀን በአካባቢው ከባድ ዝናም ጣለ፡፡ ምድሪቱንም የሚገለባብጣት መሰለ፡፡ ዕንቁራሪቱ በዚያች ለእርሱ ምርጥ በሆነችው ኩሬ ውስጥ በመሆኑ ምንም ነገር አይመጣብኝም ብሎ አመነ፡፡ ዝናቡ ግን አካባቢውን ደበላልቆ ከኩሬው ማዶ የሚገኘውንና ዕንቁራሪቱ መኖሩን የማያውቀውን ኡቩስ ኑር የተባለውን ጨዋማ ባሕር እንዲሞላ አደረገው፡፡ ባሕሩ ሲሞላ በውስጡ የነበሩትን እንስሳት ተፋቸው፡፡ አንዱ የባሕር ዔሊም በጎርፉ ተወስዶ የማያውቀው ቦታ ወደቀ፡፡
   
  ዔሊው የኡቩስ ኑር ባሕርን ሊያየው አልቻለም፡፡ የት ቦታ እንዳለም አላወቀም፡፡ ወደየት አቅጣጫ መሄድ እንዳለበትም ግራ ገባው፡፡ ነገር ግን በቆሙበት ቦታ ከመሞት እየሄዱ መሞት ይሻላል ብሎ መጓዝ ጀመረ፡፡ ቢሄድ፣ ቢሄድ፣ ቢሄድ መንገዱ ሊያልቅለት ባሕሩንም ሊያገኘው አልቻለም፡፡እንዲያውም እየደከመውና እየራበው መጣ፡፡ ሙቀቱንም መቋቋም አልቻለም፡፡ ወደ ኡቩስ ኑር ባሕር ሳልደርስ ልሞት እችላለሁ ብሎ ሠጋ፡፡ 
   
  ወደ ባሕሩ በቀላሉ ሊደርስ እንደማይችል የተረዳው ዔሊ ነፍሱን ሊያድንለት የሚችል አንዳች ውኃ እየፈለገ ሳለ የዕንቁራሪቱን ኩሬ ተመለከተ፡፡ በዔሊ ፍጥነት ተንከላውሶ እዚያ ኩሬ ውስጥ ተወርውሮ ዘፍ አለ፡፡ ዔሊው ኩሬው ውስጥ ዘፍ ሲል የኩሬው ውኃ ከጥፋት ውኃ ባልተናነሰ ተናወጠ፡፡ ዕንቁራሪቱም ሰምቶት የማያውቀውን በመስማቱና አይቶት የማያውቀውን በማየቱ በድንጋጤ ልቡ ቀጥ አለች፡፡ ከሰዓታት በኋላ ሲረጋጋ አንዳች የሚያህል ፍጡር በኩሬው ውስጥ ሲንከላወስ ተመለከተ፡፡
   
  ‹ለመሆኑ ማነህ? ከየትስ መጣህ? እዚህስ ምን ታደርጋለህ?› የጥያቄ መዓት አወረደበት፡፡ ዔሊው ጥሙን የሚያስታግሥለትን ውኃ ከተጋተ በኋላ ‹እኔ ዔሊ ነኝ፡፡ የመጣሁትም ከኡቩስ ኑር ባሕር ነው፡፡ እዚያ በተከሠተ ጎርፍ ከባሕሩ ወጥቼ ጠፋሁ፡፡ ወደ ባሕሩ እመለሳለሁ ብዬ ስጓዝ በውኃ ጥም ልሞት ደረስኩ፡፡ ፈጣሪ ይመስገን እዚህ ኩሬ ውስጥ ጣለኝ› አለው፡፡
   
  ‹ታድያ አሁን ምን እያሰብክ ነው?› አለው ዕንቁራሪቱ፡፡ ‹እኔ ወደ ባሕሩ መመለስ ነበር የምፈልገው፡፡ ነገር ግን መንገዱን አላውቀውም፡፡ በመካከልም በውኃ ጥም እንዳልሞት ፈራሁ፡፡ እናም ካላስቸገርኩህ በጋው እስኪያልፍ እዚህ አንተ ጋ ብከርም ምን ይመስልሃል?› አለው፡፡ ለብዙ ዘመናት ብቻውን የኖረው ዕንቁራሪት ጓደኛ ስላገኘ ደስ ብሎት ፈነጠዘ፡፡ ይህን እርሱ በኩሬው ውስጥ ያገኘውን ልዩ ደስታና ርካታ የሚያካፍለው ጓደኛ አገኘ፡፡
   
  ዔሊው የበጋውን ወቅት የሚያሳልፍበት ቦታ በማግኘቱ እፎይ ያለ ቢመስለውም ዕንቁራሪቱ ግን በጥያቄዎች ያጣድፈው ነበር፡፡ ከኩሬው ውጭ ያለውን ዓለም የማያውቀው፤ በዓለም የመጨረሻው፣ ትልቁና ምቹው ቦታ ኩሬው የሚመስለው ዕንቁራሪት የጥያቄ ናዳ አወረደበት፡፡ ‹ለመሆኑ ያንተ ባሕር እንደዚህ ኩሬ ውብና ምቹ ነው› አለው፡፡ ዔሊውም ዕንቁራሪቱን ላለማስከፋት ብሎ ‹ያንተ ኩሬ ውብና ምቹ ነው› አለው፡፡ ዕንቁራሪቱም በዚህ ተደሰተና ‹ለመሆኑ ያንተ ባሕር ከእኔ ኩሬ ይበልጣል› አለው፡፡ ዔሊውም ‹የኡቩስ ኑርን ባሕር ከዚህ ትንሽ ኩሬ ጋር ማነጻጻር የማይታሰብ ነው፡፡ ወርድና ቁመቱን ማንም ሊለካው አይችልም፤ አጅግ ሰፊ፣ ጥልቅና ምቹ ነው፡፡ አያሌ የባሕር እንስሳት ይገኙበታል› አለና መለሰለት፡፡
   
  ዕንቁራሪቱ ደነገጠ፡፡ እዚህ ኩሬ ውስጥ የገባው እጅግ ውሸታም ዔሊ ነው ብሎ አመነ፡፡ ከዚህ ኩሬ የበለጠ ነገር በዓለም ላይ ሊገኝ አይችልም፡፡ ዕንቁራሪቱ በአንድ ዓይኑ ሲያያት የእርሱ ኩሬ ለእርሱ እጅግ ሰፊ፣ ማንም ሊደርስባት የማይቻላት ናት፡፡ ለመሆኑ በዓለም ላይ ከዚህ የሚበልጥ ምን ምቹ ቦታ ይገኛል? ብሎ አሰበና ‹የኡቩስ ኑር ባሕር የሚባል ነገር የለም፡፤ ቢኖርም ከዚህ ኩሬ ፈጽሞ ሊበልጥ አይችልም፡፡ አንተ ውሸታም ነህ፡፡ ሆን ብለህ እኔን ለማስደነቅና ከዚህ እንድወጣ ለማድረግ ነው እንጂ ከዚህ የሚበልጥ ባሕር ፈጽሞ የለም፡፡ በዓለም ላይ ያለው ብቸኛው፣ ታላቁና ምቹው ውኃ ይሄ ኩሬ ነው› አለው፡፡ 
   
  ዔሊውም ‹ወዳጄ ሞኝ አትሁን፡፡ የማታውቀውን ነገር ሁሉ የለም አትበል፡፡ አንተ በአንድ ዓይንህ ስለምታያት ይቺ ኩሬ ትልቅ ትመስልሃለች እንጂ እንኳን ከዚህ ኩሬ ከኡቩስ ኑር ባሕር የሚበልጡም አሉ፡፡ እኔ የያዝኩት ብቻ የመጨረሻው ነው ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው፡፡ ዕውቀቴ የመጨረሻው ነው ብሎ እንደሚያስብ ፍጡር የሚጎዳ የለም› አለው፡፡ በዚህ ጊዜ ዕንቁራሪቱ ክፉኛ ተቆጣ ‹ሞኝ አልከኝ፡፡ አንተ ከሌላ ዓለም የመጣህ ፍጡር ነህ፡፡ ከዚህ ኩሬ የሚበልጥና የተሻለ ነገር አለ ብሎ የሚለኝ ለእኔ የመጨረሻው ውሸታም ነው፡፡ ይህን ኩሬ እስካሁን እኔ ዋኝቼ አልጨረስኩትም› እያለ አመናጨቀው፡፡
   
  ዔሊው ይህንን ንግግር ለማመን አልቻለም፡፡ የዕንቁራሪቱን ደኅነኛ ዓይን እያየ ‹አንተ ይህቺን ኩሬ የዓለም መጨረሻ አድርገህ ማየትህ አይገርመኝም፡፡ ያለህ አንድ ዓይን ብቻ ስለሆነ፡፡ የሚገርመው በሁለት ዓይኑ የሚያየውን ሁሉ መቃወምህ ነው፡፡ ሁላችንም በአንተ አንድ ዓይን ልናይ አንችልም፡፡ ላንተ ያልታየህ ሁሉ የለም፤ አንተ ያልደረስክበት ሁሉ አልተፈጠረም፤ አንተ ያልኖርክበት ሁሉ ምቹ አይደለም ብለህ ታስባለህ፡፡ ዓለምን በልክህ ቀደህ ሰፍተሃታል፡፡ ሁላችንም ደግሞ ባንተ ልክ እንድናሰፋት ታስባለህ፡፡ ይህ የመጨረሻው ሞኝነት ነው፡፡ እኔ ብቻ እና የኔ ብቻ ትክክል ነው ብሎ ማሰብ ነው ከዚህ ኩሬ እንዳትወጣ ያደረገህ፡፡ ሁሉንም ነገር በኩሬው ልክ ታስበዋለህ፡፡ በእውነትም አንተ የመጨረሻው ሞኝ ነህ፡፡ 
   
  ብልህ ብትሆን ኖሮ ስለ ሌላውና ሌላውንም ለመስማት ትፈልግ ነበር፡፡ ብልህ ብትሆን ኖሮ ካንተ የሚያንስም፣ ካንተ የሚስተካከልም፣ ካንተ የሚበልጥም መኖሩን አምነህ ትቀበል ነበር፡፡ ብልህ ብትሆን ኖሮ ስለ ሌላው ዐውቀህ ኅሊናህን ታሰፋው ነበር፡፡ ብልህ ብትሆን ኖሮ ካንተ የተለየ ዕውቀትና ልምድ ያላቸውን ታዳምጥ ነበር፡፡ ብልህ ብትሆን ኖሮ ለመናገር ብቻ ሳይሆን ለመስማት ዕድል ትሰጥ ነበር፡፡ በል ይመችህ፤ እዚሁ ኩሬህ ውስጥ ኑር፡፡ እውነትም ከዚህ የተሻለ ላንተ አይገኝም፡፡ እዚህ ኩሬ ውስጥ የምትኖረው ኩሬው ከሁሉም የሚበልጥ ስለሆነ ሳይሆን ላንተ ስለሚመጥንህ ነው፡፡ ቀሪ ሕይወቴን ከሞኝ ጋር ከምኖር ብልሆች ወዳሉበት እየሄድኩ ብሞት ይሻለኛል› ብሎ ከኩሬው ወጥቶ ሄደ፡፡
   
  ዕንቁራሪቱም በአንድ ዓይኑ ሲያይ የኩሬውን ግድግዳ ተመለከተው፡፡ ‹ይህ የዓለም ዳርቻ አይደለምን፡፡ ለመሆኑ ይህ ዔሊ ከዓለም ዳርቻ ውጭ የት ሊሄድ ነው› አለ ይባላል፡፡
  ምንጭ:- የዳንኤል ክብረት እይታዎች
  Read more »

 • ኑ! ሀገሬን እናዋልዳት

                                                              

   

  ከዳንኤል ክብረት

  አዋላጇ ጠፍታ ልጁም በእግሩ መጥቶ
  እናቲቱ ሞተች ልጅዬውም ሞቶ

  የሚል የልቅሶ ግጥም አለ። ነፍሰ ጡር እናት ስትወልድ ልጁ በእግሩ ከመጣ አደጋ ነው ይባላል። ጎበዝ አዋላጅ አግኝታ ልጁ በአናቱ እንዲመጣ ልታግዛት ይገባል። ያ ካልሆነ ግን ባልተስተካከለ መንገድ የመጣውን ልጅ ለመውለድ የምታምጠው እናት፣ ለረዥም ጊዜ በማማጧ የተነሣ ደክማ ለሞት ትዳረጋለች። ልጇም የመሞት ዕጣ ፈንታ ይገጥመዋል። መውለድ ደስታ የሚሆነው ልጁ በሰላም ተወልዶ፣ ለእናቱ ጤናና ደስታ ካመጣ ነው። መውለድ ካልተስተካከለ ማርገዝ ብቻውን ድካም ነው። ለዚህ ነው ነፍሰ ጡሮች በሕክምና እርዳታ ሲታገዙ ቆይተው፣ በሕክምና እርዳታ እንዲወልዱ የሚመከረው

  ሀገር ለውጥን ልትወልድ የምትችለው የለውጥን ጽንስ በጤናማ መልኩ አርግዛ በጤናማ መልኩ እንድትወልድ የሚረዷትን ሐኪሞች ካገኘች ነው። ጽንሱ ጤናማ መሆኑን በየጊዜው የሚከታተሉ፤ ችግር ሲፈጠር ወዲያው መፍትሔ የሚሰጡ። ስትወልድም ልጁም እናቲቱም ጤንነታቸው በተጠበቀበት መንገድ እንድትወልድ የሚረዱ አዋላጅ ሐኪሞች ያስፈልጓታል። ይህ ሲጠፋ ልጁም እናቲቱም ለሞት ይዳረጋሉ።
  ኢትዮጵያ ብዙ ጊዜ ለውጥን ፀንሳ ታውቃለች። ብዙ ጊዜ የማታገኘው ጎበዝ አዋላጅ ሐኪም ነው። በዚህ ምክንያትም ብዙ ጊዜ ልጇ ሞቶባታል። ያውም በእርሷም ላይ ከባድ አደጋ አድርሶ። ማኅፀኗን ጎድቷት ስለሚሄድ፣ ሌላ ልጅ ለመጸነስ ዘመናትን እንዲፈጅባት አድርጎ።

  የቅርቡ ታሪካችንን እንኳን ብንመለከተው፣የልጅ ኢያሱን ዘመን ፀንሳ ነበር። ነገር ግን ካለፉት ዘመናት በተለየ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሀገሪቱ ሂደት ባለቤት እንዲሆን ከዘመኑ በቀደመ ሐሳብ የተነሣውን ወጣቱ ንጉሥ ሐሳቡን የሚያዋልድለትና ፅንሱ በእግሩ መጥቶ እናቱንም ራሱንም እንዳይገድል የሚያደርግ ሐኪም አጥቶ፣ ሀገሪቱ ያንን ዕድል አመከነችው። የተገኙት አዋላጆች ሳይሆኑ አምካኞች ነበሩ። ልክ ፈርዖን በግብጽ፣እሥራኤላውያን ላይ አሠማርቷቸው እንደነበሩት የአዋላጅ አምካኞች።

  በ1953 ዓ.ም ኢትዮጵያ እንደገና ሌላ የለውጥ ልጅ ፀንሳ ነበር። ነባሩ ንጉሣዊ ሥርዓት ከመሠረቱ ሳይናጋ ነገር ግን ዘመኑ የሚጠይቀውን ሥርዓታዊ ለውጥ ለመውለድ ፀንሳ ነበር። አዋላጅ ግን አላገኘችም። ያንን ሐሳብ በሚገባ ፀንሳ በሚገባ እንድትወልድ የሚያደርጉ አዋላጆች ብታገኝ ኖሮ፣የጥንቱን ከዘመኑ ያጣጣመ ሥርዓት ገንብታ ለመጓዝ ትችል ነበር። ግን ምን ዋጋ አለው፤ ጨነገፈ።

  በ1966 ዓ.ም ሌላ የለውጥ ልጅ ፀነሰች። ሀገሪቱን ወደተሻለ ሥርዓት ሊወስድ የሚችል ተስፋ የሰነቀ ልጅ። ምን ዋጋ አለው። አዋላጆች አላገኘችም። ልጁን ጤናማ ሆኖ እንዲወለድ ከማገዝ ይልቅ አዋላጆቹ እርስ በርሳቸው ሲጨፋጨፉና ሲቧቀሱ፣ ልጁ ‹ታሪክ የጣለብንን ኃላፊነት ለመወጣት› ብለው በተነሡ የወታደር አጨናጋፊዎች እጅ ወደቀ። አንዲት የገጠር ሴት ለመውለድ ደርሳ አዋላጅ ጠራች። የቀን ጎደሎ ሆኖባት የማይችል ሰው እጅ ወደቀችና እርሷም ልጇም ሞቱ። አልቃሽ፡-

  እንዲህ ያል ክፉ ቀን ክፉ ሰው ላይ ጥሏት
  እንኳን ልጅ ልታገኝ እርሷንም ገደሏት፤

  ብላ ገጠመች ይባላል። ኢትዮጵያም በ66 እንዲህ ነው የሆነቺው። ሐኪሞች ልጆቿ፤ የራስዋን ልጅ ማዋለድና ማሳደግ ሲገባቸው፣ የማደጎ ልጅ ከሶቪየት አምጥተው ልጅሽ ይሄ ነው አሏት። በማኅፀንዋ የተፀነሰውን የራስዋን ልጅ ገድለው የሰው ልጅ አሳቀፏት። የአዋላጆቹ ጠብም ልጇን እንዴት እናዋልዳት? መሆኑ ቀርቶ፣የትኛውን ልጅ ትታቀፍ? የሚለው ላይ ሆነ። እንኳን አዲስ ልጅ ልትወልድ እርሷም በወሊድ ምክንያት በተከሠተ ሕመም ለዘመናት ትሰቃይ ጀመር።

  ያ ዘመን አልፎ 1983 ዓ.ም መጣ። ሁሉንም ያሳተፈ፤ የኅብረተሰብም የሐሳብም ብዝኃነትን የተቀበለ፤ ሀገሪቱ ስትመኘው የኖረቺውን ልጅ ልትወልድ የምትችልበት ዕድል ገጠማት። አሁንም ግን አዋላጆች ጠፉ። ያንን ለውጥ በፖለቲካ ብስለት፣ በዕውቀትና በትዕግሥት፣ በአመራርና በጥበብ አዋልደው፣ሀገሬ ዴሞክራሲና ዕድገትን ከነ ቃጭሉ ዱብ እንድታደርግ የሚያስችሉ አዋላጆች ጠፉ። ሁሉም የራሱን ብቻ ሲሰማና ‹ልጁ እንዲፀነስ የታገልኩት እኔ ነኝና እኔ ብቻ ልወስን› ሲል ሀገሬ ልጇን አጣችው። እርሷ ለመፅነስ እንጂ ለመውለድ ሳትታደል ቀረች።

  ከሕዝቡ አብራክ ተከፍሎ በኢትዮጵያ ማኅፀን የተፀነሰውን ያንኑ ልጇን ተባብሮ ከማዋለድና እርሱኑ ተከባክቦ ከማሳደግ ይልቅ አሁንም ኮሚኒዝሙን፣ ማኦኢዝሙን፣ ዴሞክራሲውን፣ ቀያይጠንን እንደ አሻንጉሊት ሰፍተን፣ ‹ልጅሽ ይሄ ነው› አልናት። የብሔረሰቦችን ጥያቄ ልንግባባበትና ሀገር ልንመሠርትበት በምንችለው መንገድ መፍትሔውን መውለድ ሲገባን፣ ዘወትር የሚያጣላንንና የሚያበጣብጠንን የማደጎ ልጅ አመጣን። ከራሳችን አብራክ በራሳችን ማኅፀን ለኛ የሚሆን የፌዴራሊዝም ልጅ ልንወልድ ሲገባን የማደጎ ልጅ አመጣን። ይኼው አሁን በሂደት ልጁ የኛ ልጅ አለመሆኑን፤ ኢትዮጵያ የወለደችው ልጅ አለመሆኑን እየነገረን ነው። ከኛ ፍላጎት፣ ባህል፣ አስተሳሰብና ታሪክ ጋር መኖር አቅቶታል። የገዛ ልጃችን ዕዳ ነው የሆነብን። ሀገሬ ልጅ አልወጣላትም።

  በ1997 ዓ.ም ሀገሬ ሌላ ልጅ ፀንሳ ነበር። ዴሞክራሲን። የአስተሳሰብ ብዙኅነትን ልትወልድ ነበር። እኛም ትወልዳለች ብለን የገንፎውንና የአጥሚቱን እህል አዘጋጅተን ነበር። ግን ምን ያደርጋል፤ ሐኪም አላገኘችም። ‹እኔ ብቻ› የሚል ሐኪም ገጥሟት፤ የዛሬውን እንጂ የነገውን የማያይ ስግብግብ አዋላጅ ገጥሟት፤ ምንጊዜም በሆስፒታሉ ውስጥ ‹ብቸኛው ስፔሻሊስት ሐኪም› እየተባለ መኖር የሚወድ ራስ ወዳድ ሐኪም ገጥሟት፤ ጊዜያዊ ችግሮችን ለዘላቂው ጥቅም ሲል መታገሥ የማይችል ሐኪም ገጥሟት፤ ወይ ‹ሁሉን ማግኘት አለያም ሁሉን ማጣት› የሚባል የማዋለጃ መሣሪያ የያዘ ሐኪም ገጥሟት ሀገሬ ልጇ ሞተባት።

  እርሷም ትፀንሳለች እኛም እንፈጫለን
  ለልቅሶ ነው እንጂ ለእልልታ አልታደልን፤

  አለ አሉ፤ ኀዘን የጎዳው ባል። ሚስቱ በፀነሰች ቁጥር ለአራሷ የሚሆን እህል በቤቱ ይፈጫል። ነገር ግን ወለደች ተብሎ እልል ሳይባል፣ ሞተባት ተብሎ ይለቀሳል። ይሄ ነበር ባልን እንዲህ እንዲያንጎራጉር ያደረገው። ሀገሬም እንዲህ ነው የሆነቺው።

  አሁንም ሀገሬ ፀንሳለች። እኛም ሊያግባባንና ሊያስማማን የሚችል ሥርዓተ መንግሥት፤ የብዙኃኑን ውክልና የሚያረጋግጥ ዴሞክራሲያዊ ሂደት፤ የትብብር መነሻ የሚሆን፣ ከአጥር ይልቅ ድልድይ የሚገነባ ፌዴራሊዝም፣ ሰብኣዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚያከብርና የሚጠብቅ የፖለቲካ ምኅዳር ትወልዳለች ብለን ተስፋ እያደረግን ነው። ይህ እንዲሆን ግን ማዋለድ ያስፈልጋል። ኃይልና ጉልበትን፣ ዘረኝነትና ጽንፈኝነትን፣ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀልና እኔ ብቻ ዐውቅላችኋለሁን፣ እኔን ምን አገባኝና እኔ የለሁበትምን፣ አግላይነትንና ጠቅላይነትን፣ ጥገናዊነትንና ጊዜያዊነትን ትተን ሀገሬ ለሁላችንም የሚሆን፣ ሁላችንም እልል ብለን የምንቀበለው፤ ሁላችንም የአራስ ጥሪ የምናመጣለት፣ ሁላችንም በመወለዱ ገንፎ የምንበላበት፣ ሁላችንም ልደቱን የምናከብርለት፣ ከሩቅ ያሉት እንደ ሰብአ ሰገል ገሥግሠው፣ ከቅርብ ያሉት እንደ እረኞቹ ነቅተው ሄደው የሚያመሰግኑት ልጅ እንዲወለድልን ማዋለድ አለብን። ምሁራኑ፣ የፖለቲካው ልሂቃን፣ ደጋፊዎች፣ ተቃዋሚዎች፣ የእምነት መሪዎች፣ የሚዲያ ተዋንያን፣ ነጋድያን፣ ወጣቶችና ሴቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ወታደራዊ አለቆች፤ ሀገራችን የፀነሰቺውን ልጅ በሰላም እንድትገላገል እንርዳት። አንዱ እግሩን፣ አንዱ እጁን፣ አንዱ ጆሮውን፣ አንዱ ጭንቅላቱን እየሳበ፣ ለራሱ ብቻ የሚጠቅመውን የየራሱን ልጅ ለማዋለድ ቢጥር ልጁ ይሞታል እንጂ ልጅ አይሆንም። ሀገሬም ፀንሳ በወለደች ቁጥር እየተጎዳች፣ እየደከመች ትሄዳለች።

  እናት በተደጋጋሚ ልጆች ሞተውባት በስተመጨረሻ ተወልዶ የሚያድግላትን ልጅ ‹ማስረሻ› ትለዋለች። ያለፈውን መከራና ስቃይ ሁሉ የሚያስረሳ ማለቷ ነው። ሀገሬ ማስረሻ የሆነ ልጅ ትፈልጋለች። እልህና ኃይለኝነት አልጠቀመንም። ዘረኝነትና መከፋፈል አልፈየደልንም፣ ጥላቻና ሽኩቻ አላሳደገንም፤ ግዴለሽነትና ራስ ወዳድነት አላራመደንም። አሁን ሰከን ብሎ፤ ከስሜታዊነትም ወጥቶ፣ሀገሬ የፀነሰቺውን ልጅ እንዴት በሰላም ልትገላገል እንደምትችል መነጋገር፣ መመካከርና መተባበር ያስፈልጋል። ኑ! ሀገሬን እናዋልዳት፤ ኑ፡፡ እስከ መቼ ልጅ ይሙትባት?

  ምንጭ:- የዳንኤል ክብረት እይታዎች

  Read more »

 • የብዝሃ- ሕይወት ስብጥር ጥናት

                                              

  በሸዋዬ ለገሠ እና አዜብ ታደሰ

  ኢትዮጵያ በብዝሃ ህይወት ስብጥር በተፈጥሮ የታደለች ሀገር መሆኗን ተመራማሪዎች ይናገራሉ። በሀገሪቱና በዉጭ ሳይንቲስቶች ትብብርም በእጽዋቱ ዘርፍ ሰፋ ያለ ጥናት ተካሂዷል፤ አሁንም እየተካሄደ ነዉ። የተገኙ የጥናት ዉጤቶችን መሠረት ያደረገ የጥበቃ ሥራ መሠራት እንደሚኖርበትም ተመራማሪዎቹ ያሳስባሉ።

  ላለፉት 38 ዓመታት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በእጽዋት ጥናት እና ምርምር ላይ ጊዜያቸዉን አሳልፈዋል። አሁንም በዚሁ መስክ ምርምራቸዉን ቀጥለዋል። አብዛኛዉን የዕድሜ ዘመናቸዉን በእጽዋት ምርምር ያሳለፉት ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰዉ፤ የጎርጎሪዮሳዊ 2016 ዓ,ምን የብሪታኒያዉ የሮያል ቦታኒክ ጋርደን ዓለም አቀፉን የኪዉ ሽልማት ለማግኘት በቅተዋል። ኩዉ ገልድ የተሰኘዉ ማኅበር በጎርጎሪዮሳዊዉ 1893ዓ,ም የተመሠረተ ሲሆን፤ ዋና ዓላማዉ የምድራችንን እጽዋት ዝርያ ማጥናት፣ መከታተል እና መጠበቅ ላይ ያነጣጠረ ነዉ። ለዚህም በዘርፉ የሚደረገዉን ጥናት ይደግፋል ያበረታታል።
  እሳቸዉ እንደሚሉት ከጎርጎሪዮሳዊዉ 1950ዎቹ እና ከዚያ በኋላ የኢትዮጵያን ብዝሃህይወት የሚመለከቱ ጥናቶች አልነበሩም። የኢትዮጵያን የብዝሃህይወት መረጃ ለማሰባሰብ ፕሮፌሰር ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር የጀመሩትን ፕሮፌሰር ሰብስቤ ከባልደረቦቻቸዉ ጋር ተረክበዉ ቀጥለዉበት ሥራዉን ማጠናቀቃቸዉንም ያስረዳሉ።  30 ዓመት በፈጀ  በዚህ ፕሮጀክትም ከኢትዮጵያዉያኑ በተጨማሪ ከ17 ሃገራት የተዉጣጡ ከ119 ሳይንቲስቶች በላይ መሳተፋቸዉንም ይገልጻሉ። የእጽዋቱን ምንነት ለማወቅ ስነምህዳሩን ማጥናት እንደሚያስፈልግ የሚናገሩት ተመራማሪ ካለፉት አምስት እና አራት ዓመታት በፊት ጀምሮም የኢትዮጵያን የስነምህዳር እጽዋት ሽፋን የሚያመለክት ዳጎስ ያለ የጥናት መጽሐፍ መዘጋጀቱንም አብራርተዋል። እንዲህ ያሉ ጥናቶች በመካሄዳቸዉም በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የሚገኙ 6,000 እጽዋት እጽዋቱ የት እንደሚገኙ ምን እንደሚመስሉ እና የመሳሰሉት አስፈላጊ ዝርዝር መረጃዎች፤ አሉ። ከእነዚህ ዉስጥም 600ዎቹ ኢትዮጵያ ዉስጥ ብቻ የሚገኙ ብርቅዬ እፅዋት መሆናቸዉን ፕሮፌሰር ሰብስቤ ገልጸዉልናል።ኢትዮጵያ የብዝሃ ሕይወት ቋት ናት የሚሉት ፕሮፌሰር ሰብስቤ የብዝሃ ህይወቱ መገኛ የሆነዉ የሀገሪቱ ደን እየተመናመ በመሄዱ ያላትን ሀብት በአግባቡ እንዳልተጠቀመችም ይናገራሉ።

  ዋና ሥራቸዉና ትኩረታቸዉ ምርምሩና ግኝቱ ላይ መሆኑን የሚናገሩት የእጽዋት ምርምር ባለሙያዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ ብቻ እንደሚገኙ የታወቀዉ ብርቅዬ የሆኑት እጽዋት ዝርያ እንዳይጠፋ ጥንቃቄ የማድረጉ ሥራ በቅንጅትና በጋራ መከናወን እንዳለበት ሳያሳስቡ አላለፉም።

  ከጥናትና ምርምሩ ዉጤት ኅብረተሰቡ መረጃዎች እንዲያገኝም በተለያዩ እጽዋት ላይ የተካሄዱ ጥናት እና ምርምሮች ታትመዉ በየዩኒቨርሲቲዎቹ እንዲሰራጩ፤ እንዲሁም ጥናቶቹን ለማየት ለሚፈልጉ እንዲዳረሱም ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ከባለሙያዉ ለመረዳት ተችሏል።የእጽዋት ሳይንስ ተመራማሪዉ ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰዉ እንደገለጹልን አንዴ የኢትዮጵያ የእጽዋት ዝርያ በሙሉ ከተጻፈ በኋላ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በክልላቸዉ ያለዉን የእጽዋት ዝርያ መጻፍ ይችላሉ። እንዲህ ማድረግ ሲቻል ደግሞ መረጃዉ ለኅብረተሰቡ የተሻለ ቅርበት ይኖረዋል ብለዉም ያምናሉ። የብዝሃ ሕይወት ቋት ያሏት ሀገር ኢትዮጵያም በዩኒቨርሲቲዉ ከሚከናወነዉ ምርምር በተጓዳኝ ሀብቷን የምትጠብቅበትን ስልት ማጠናከር እንደሚገባም ሳይመክሩ አላለፉም።

  ምንጭ :- DW

   

  Read more »

 • የአለም አቀፍ የቡና ቀንና ኢትዮጵያ

                                                                  

  ቡና ከማሳ ጀምሮ እስከ ተጠቃሚው እስኪደርስ ድረስ ያለውን ሂደት ማሰየትና ተወዳጅ የሆነውን ቡና አምራች የሆኑትን በአነስተኛ ማሳ ላይ የተመሰረቱ አምራቾችን ተገቢውን ክብር በመስጠት ዕለቱ እንደሚከበር በምህጻረ ቃል (ICO) የአለም አቀፉ ቡና ድርጅት ገልጿል፡፡

  በየአመቱ በፈረንጆቹ አቆጣጠር ጥቅምት 1 የሚከበረው አለም አቀፉ የቡና ቀን 77 አገራትን በአባልነት ባቀፈው የአለም አቀፉ የቡና ድርጅት አስተባባሪነት ይከበራል፡፡

  ባለፉት 50 ዓመታት የቡና በምርታማነትም ሆነ በፍጆታ ረገድ ዕድገት ማሳየቱን የአለም አቀፉ የምግብ ድርጅት (FAO) መረጃ ያመለክታል፡፡ ቡና በ70 ሀገራት ብቻ የሚመረት ሲሆን ብራዚል፣ ቬትናምና ኢንዲኖዥያ የጠቅላላ ሀገራት ምርትን 50 በመቶ ድርሻ ይይዛሉ፡፡

  የቡና ንግድ በምርቱ አቅርቦትና ጥራት ላይ ይወሰናል፡፡ የቡና አይነት አረቢካ ወይም ሮቦስታ መሆኑ፣ በቡናው ውስጥ ሰው ሰራሽ ማዳበሪያ መኖሩና ያለመኖሩ፣ የታጠበና ያልታጠበ መሆኑ እንዲሁም እሴት የተጨመረበትና ያልተጨመረበት መሆኑ በገበያው ላይ የራሱ ድርሻ አለው፡፡

  የቡና ምርትን በተለይም ለታዳጊ ሀገራት ዋንኛው የውጭ ምንዛሪ የሚያገኙበት ዘርፍ ነው፡፡ ቡና ላኪ ሀገራት በ2012 ወደ ውጭ ከላኩት 70 ሚልዮን ኩንታል የቡና ምርት 24 ቢልዮን ዶላር ማግኘት መቻላቸውን የአለም ምግብ ድርጅት መረጃ ያመለክታል፡፡ አኃዙ ከአስር አመታት በፊት ከነበረው አንጻር በምርት 25 በመቶ እና በውጭ ምንዛሪ ግኝት በ3 ዕጥፍ መላቁን ከተመሳሳይ ምንጭ የተገኘ መረጃ ያሳያል፡፡ በአለም ደረጃ ሁለት አይነት የቡና ዝርያዎች ይገኛሉ፡፡

  አረቢካና ሮቡስታ በመባል ይታወቃሉ፡፡ የቡና ዝርያዎቹ እንደየ ቅደም ተከላቸው 40 እና 60 በመቶ የአለም አቀፉን የቡና ጠቅላላ ምርት ድርሻን ይዛሉ፡፡ የአረቢካ የቡና ዝርያ በዋጋ ረገድ ከሮቡስታ የተሻለ ቢሆንም ከ2013 ወዲህ የሮቡስታ ቡና ምርት መጨመሩን ተከትሎ የአሪቢካ ቡና ዋጋ እያሽቆለቆለ መምጣቱን የአለም ምግብ ድርጅ መረጃ ያመለክታል፡፡

  የኢትዮጵያ የቡና፤ ምርትና ፍጆታ የቡና መገኛ እንደሆነች የምትታመነው ኢትዮጵያ በቡና ምርት በአፍሪካ ቀዳሚ ነች። በአለም ደግሞ 5 ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ የሀገሪቱ የቡና ምርት የአለምን 5 በመቶ የአፍሪካን ደግሞ 39 በመቶ ድረሻ እንደያዘ የአለም ቡና ድርጅት (ICO) መረጃ ያመለክታል፡፡ በኢትዮጵያ በቡና የተሸፈነው መሬት ለቡና አመቺ ከሆነው አንጻር በጣም አነስተኛ ነው፡፡

  በቡና የተሸፈነው መሬት መጠን ግማሽ ሚልዮን ሄክታር ገደማ ነው፡፡ የተሸፈነው መሬት ለቡና ምርት ምቹ ከሆነው 6 ሚልዮን ሄክታር አንጻር 3.8 በመቶ ብቻ ይሸፍናል (Mekuria.et)፡፡ ኢትዮጵያ በቡና ምርት ዕድገት መጠን ከአለም ቀደሚዋ ናት፡፡

  ምርቱ በየአመቱ 12 በመቶ በማስመዝገብ የአለምን የቡና ምርት ዕድገት መጠንን ይመራል፡፡ ብራዚል፣ ቬትናምና ኮሎምቢያ አንደ ቅደም ተከተላቸው 7፣ 5፣ እና 3 በመቶ በማስመዝገብ ኢትዮጵያን እንደሚከተሉ የአለም ምግብ ድርጅት FAO ሪፖርት ያስረዳል፡፡

  አብዛኛው የኢትዮጵያ ቡና ምርት አነስኛ ማሳን መሰረት ያደረገ ነው፡፡ ከአንድ ሄክታር በታች በሆነ ማሳ የሚያመርቱ አርሶ አደሮች የሀገሪቱን ጠቅላላ የቡና ምርት 90 በመቶ ድርሻ እንደሚሸፈኑ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ መረጃ ያመለክታል፡፡

  የተፈጥሮ ደን 5 በመቶ ድርሻ ሲኖረው ቀሪውን ሰፋፊ እርሻን መሰረት ያደረገ የቡና ምርት ይሸፍናል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ቡና በማምረት የተሰማራውን 15 ሚልዮን ያህል አርሶ አደር ተጠቃሚ ለማድረግ ከአለም አቀፉ ቡና ድርጅትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

  በተለይም ዕውቅና ካገኙት የይርጋ ጨፌ፣ ሲዳሞና ሀረር ስፔሻሊቲ ቡናዎች በተጨማሪ ሌሎችንም ለማስመዝገብ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡ ቡናን ጨምሮ በሀገሪቱ የሚመረቱ ምርቶች ግብይት ለማሳለጥ በአፍሪካ በአይነቱ የመጀመሪያው የሆነው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ድርጅት ቡና አምራቹ የለፋበትን ዋጋ እንዲያገኝ ያራሱን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል፡፡

  በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ቡና ፍጆታ ከፍተኛ እንደሆነ ይነገራል፡፡ አመታዊ ፍጆታው በነፍስ ወከፍ 2.4 ኪሎ ግራም መሆኑን የአለም አቀፉ ቡና ድርጅት መረጃ ያመለክታል፡፡ የጠቅላላ የሀገሪቱ የቡና ምርት ገሚሱ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚዉል ነው፡፡ ከጠቅላላ ምርት አንጻር የሀገሪቱ የቡና ፍጆታ ድርሻ፤ ኢትዮጵያን ከአለም አንጻር ቁጥር አንድ እንደሚያደርጋት የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (USAID) በዘርፉ ያደረገው ጥናት ያመለክታል፡፡

  በሌላ ጎኑ የሀገሪቱ ባህላዊ የቡና አፈላል በፍጥነት ወደ ንግድ እየተቀየረ መምጣቱን ተከትሎ ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል እየፈጠረ ይገኛል፡፡ የቡና ንግዱ ከትልቅ እስከ ትንሽ የሀገሪቱ ከተማዎች መስፋፋቱ የቡና ፍጆታውን በማሳደግ ረገድ ያራሱን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ ቡና ወጪ ንግድ የቡና ምርት ኢትዮጵያ ከፍተኛውን የውጭ ምንዛሪ የምታገኝበት ነው፡፡ እንደ ማዕከላዊ ስታስቲስክ ኤጀንሲ መረጃ፤ ቡና ሀገሪቱ 31 በመቶ የውጭ ምንዛሪ የምታገኝበት ምርት ነው፡፡

  ከ10 አመት በፊት የቡና ምርት የውጭ ምንዛሪ ግኝት 65 በመቶ ድርሻ እንደነበረው መረጃው ያመለክታል፡፡ ኢትዮጵያ ቡናን በመላክ የምታገኘው የውጭ ምንዛሪ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በጎርጎሮሳዊያኑ 1990ዎቹ ከተገኘው የውጭ ምንዛሪ አንጻር አሁን ያለው በ5 ዕጥፍ ገደማ ይልቃል፡፡ በተለይም ከ2003 ጀምሮ የቡና የአለም ገበያ ዋጋ እየተሻሻለ መምጣቱን ተከትሎ ከቡና የተገኘው ገቢ እያደገ መጥቷል፡፡

  የኢትዮጵያ የቡና ምርት ጥራትን ብቻ በማሳደግ አሁን እየተገኘ ያለውን የውጭ ምንዛሪ በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ እንደሚቻል የአለም ምግብ ድርጅት FAO ጥናት ያመልክታል፡፡ ሀገሪቱ ወደ ወጭ የምትልከው ቡና አብዛኛው ያልታጠበ ነው፡፡ ወደ ውጭ ከሚላከው ቡና የታጠበ ቡና 27 በመቶ ብቻ ድርሻን ይዛል፡፡ ቀሪው 73 በመቶ ሳይታጠብ የሚላክ ነው፡፡

  ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ በአለቀፍ ደረጃ ተወዳጅ የሆነውንና ተፈጥሯዊ (Organic) ቡናን ለአለም ገበያ በማቅረብ ትታወቃለች፡፡ በአለም ገበያ ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጣውን ከሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ነጻ የሆነ (Organic) ቡና በከፍተኛ ደረጃ በማቅረብ የምትቀድማት ሀገር ፔሩ ብቻ ናት፡፡ ኢትዮጵያ ለአለም ገበያ የምታቀርበው ከሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ነጻ የሆነ ቡና እስከ 20 በመቶ የሚደርስበት ወቅት አለ፡፡ ይህ ደግሞ ሀገሪቱ ከአለም ገበያ ካላት 5 በመቶ ድርሻ አንጻር ከፍተኛ የሚባል ነው፡፡ ይህ ሆኖም ከተፈጥሯዊ (Organic) ቡና የሀገሪቱን ጠቅላላ ኤክስፖርት 6 በመቶ ድርሻን ብቻ እንደሚይዝ የአለም ምግብ ድርጅት FAO መረጃ ያመለክታል፡፡

  ከ1990ዎቹ ዓ.ም ወዲህ የኢትዮጵያን ቡና በመግዛት ጀርመን (29 በመቶ) ጃፓን፣ (16 በመቶ) ሳውዲ አረቢያ (15) በመቶ ድርሻን በመያዝ ቀዳሚ ናቸው፡፡ አሜሪካ ከኢትዮጵያ የምትገዛው የቡና መጠን አነስተኛ ቢሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል፡፡ በ1992 ዓ.ም አሜሪካ ከኢትዮጵያ የምታስገባው ቡና 4 በመቶ የነበረ ሲሆን አኃዙ በዕጥፍ በማደግ በአሁኑ ወቅት 8 በመቶ ደርሷል፡፡ በየአመቱ እንደ አውሮፓዉያኑ አቆጣጠር ጥቅምት 1 የሚከበረው የአለም አቀፍ የቡና ቀን ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ባሻገር የዕለት ዕለት ማህበራዊ ግንኙነታችን ጋር ጥልቅ ትስስር ላለው አረንጓዴ ወርቃችን ትልቅ ትርጉም ያለው ነው፡፡

  ምንጭ:- EBC

  Read more »

 • ከአሸናፊዎች መዳፍ -ወደ- የተሸናፊዎች ወገብ

                                                                                 

  ከዳንኤል ክብረት

  ሰላም ከተሸናፊዎች ወገብ እንጂ ከአሸናፊዎች መዳፍ አትገኝም› የሚል ወርቃማ አባባል አላቸው የካናዳ ጥንታውያን ሕዝቦች (First Nations)፡፡ አደን ልዩ ችሎታቸው የነበረውና በዚህች ሀገር ከሺ ዓመታት በፊት ሠፍረው መኖር የጀመሩት እነዚህ ሕዝቦች አያሌ የእርስ በርስ ጦርነቶችንና ችግሮችን ለመፍታት የቻሉት በዚህ ምክንያት እንደነበረ ይነገራል፡፡ ሁለት ጎሳዎች በአደንና በእርሻ ቦታ ወይም በድንበር ምክንያት በተፈጠረ ችግር ወደ ጦርነት ይገባሉ፡፡ የእነዚህ ጥንታውያን ሕዝቦች ሽማግሌዎች ግን ጦርነቱ በአንደኛው አሸናፊነት እንዲጠናቀቅ አይፈቅዱም፡፡ ጦርነቱ ሲደረግ የተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው የሚታገሡት፡፡ የዚህን ምክንያቱን ሲያስረዱ ደግሞ ‹ሁለቱም ወገኖች የጦርነቱን አስከፊ ገጽታ መቅመስ አለባቸው› ይላሉ፡፡ የችግር መፍቻው መንገዳቸው ወደ ባሰ ችግር እየወሰዳቸው መሆኑን ከምክርና ከትምህርት ይልቅ በተግባር እንዲያዩት ጊዜ ይሰጧቸዋል፡፡ በኋላ ግን በመካከል ይገባሉ፡፡ ‹ጦርነቱ በአንደኛው ወገን አሸናፊነት መጠናቀቅ የለበትም› የሚል እምነት አላቸው፡፡ ሁለቱም ወገኖች ቀን ጣላቸው፤ ችግር ለያያቸው፤ መንገድ አጣላቸው እንጂ ወንድማማቾች ናቸው፡፡ የእነዚህ ወንድማማቾች ትግል በአንደኛው አሸናፊነት ከተጠናቀቀ ሰላም አይገኝም፡፡ አሸናፊው ጨቋኝ፣ በቀለኛ፣ ጉልበተኛና ዘራፊ ሆኖ ይቀራል፡፡ ተሸናፊው ደግሞ ቂመኛ፣ ቀን ጠባቂ፣ በጥላቻ የተሞላና ባዕድ ሆኖ ይኖራል፡፡ የጊዜ ጉዳይ ይሆናል እንጂ አሸናፊና ተሸናፊ ቦታ መቀያየራቸው አይቀርም፡፡ የሕዝቡም ችግር ይቀጥላል፡፡ ለካናዳ ጥንታውያን ሕዝቦች መፍትሔው አንድ አሸናፊ መፍጠር ሳይሆን ሁለት ተሸናፊ ማግኘት ነው፡፡ ሁለቱም ወገኖች ጦራቸውን መሬት ተክለው፤ እግራቸውን አጣጥፈው፣ ምንጣፍም ላይ ተቀምጠው መነጋገርና መደራደር አለባቸው፡፡ እስኪስማሙ ድረስ መነጋገር፤ እስኪግባቡ ድረስ መደራደር፡፡ ሲያቅታቸው በሽማግሌዎቹ እየታገዙ ወደ አንድ የመግባቢያ ሐሳብ መምጣት፡፡ ያን ጊዜ ሁለቱም ወገኖች ከሁለቱም ለተሻለ ሉዐላዊ ሐሳብ ተሸናፊ ሆነው ይወጣሉ፡፡ ለዚህ ነው ‹ሰላም ከተሸናፊዎች ወገብ እንጂ ከአሸናፊዎች መዳፍ አትወጣም› የሚሉት፡፡ ‹የተሸናፊዎች ወገብ› ሲሉ በባሕላቸው ስምምነቱ የሚፈጠረው ከወገብ ጎንበስ ብሎ በትኅትና የመጨረሻውን ሐሳብ በመቀበል ስለሆነ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታም ከተሸናፊዎች ወገብ እንጂ ከአሸናፊዎች መዳፍ መምጣት አይችልም፡፡ ሁሉም ወገን ለዚህች ሀገር የተሻለውን ሐሳብ ለማምጣትና በዚያም ለመመራት ወገቡን መስበር አለበት እንጂ የእርሱን ሐሳብ በሌሎች ላይ በአሸናፊነት ጭኖ ማለፍ የለበትም፡፡ ካለፈው ታሪካችን ይህን መማር አያቅተንም፡፡ የካናዳ ጥንታውያን ሕዝቦች እንዳሉት በኛም ሀገር የአንድ ወገን አሸናፊነት አሸናፊውን ጨቋኝ፣ በቀለኛ፣ ጉልበተኛና ዘራፊ ሆኖ እንዲቀር አድርጎታል፡፡ ተሸናፊውን ደግሞ ቂመኛ፣ ቀን ጠባቂ፣ በጥላቻ የተሞላና ባዕድ ሆኖ በየዘመናቱ የራሱን ጥያቄና የራሱን የነጻነት ትግል እንዲጀምር በር ከፍቶለታል፡፡ ምጣድ ላይ ጢቢኛ ተጋግሮ ላይኛው የዳቦው ክፍል ታችኛውን በእሳት በመለብለቡ ሲስቅበት ‹የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ስትገለበጥ ትቀምሰዋለህ› አለው ይባላል፡፡ ተጋድሏችንና ጥረታችን እገሌን አስወግደን፣ በእገሌ መቃብር ላይ ሐውልት ለመሥራት፤ አንዱን በሌላኛው ለመተካት፤ ከአንደኛው አገዛዝ ወደሌላኛው ለመሸጋገር ከሆነ በላሸቀ ጎማ በዳገት ጭቃ ላይ እንደመንዳት ይቆጠራል፡፡ ጎማው በተሽከረከረ ቁጥር ጭቃው እያንዳለጠው መኪናውን ወደኋላ እንጂ ወደፊት አይወስደውም፡፡ አሁንም ይቅደምና ይውደም የትግላችን መፈክር ከሆኑ ያለፉት ዘመናት ትግሎቻችን ካመጡልን ለውጥ የተሻለ አናመጣም፡፡ አሁንም ‹እኛ› እና ‹እናንተ› እየተባባልን አንዱ ለሌላው መብት ሰጭ፣ ዋስትና ሰጭ፣ ምሕረት ሰጭ ሆኖ ከቀረበ ሥጋት እንጂ ሰላምን ማምጣት አይቻልም፡፡ ጉዞው አንድ አሸናፊ ወገንን ከፈጠረ ጊዜ የሚያፈነዳውን ፈንጂ የመቅበር ሥነ ሥርዓት ይሆናል፡፡ ጉዞው አሸናፊ ሐሳብን ከፈጠረ ግን የፈንጂ ማምከኛ እንደመሥራት ይቆጠራል፡፡ የምንጋደለው ሁላችንም ወደ ውይይቱና ድርድሩ አዳራሽ ለመግባት እንድንችል፤ የሁላችንም ሐሳብ የሚፋጭበትና የተሻለው ሐሳብ አሸናፊ የሚሆንበትን ሥርዓት ለመዘርጋት እንድንበቃ፤ ከጭንቅላታቸው ይልቅ በጡንቻቸው፣ ከሐሳባቸው ይልቅ በመሣሪያቸው የሚተማመኑት ወገኖች ተሸንፈው ወደ ተሸናፊዎች መድረክ እንዲመጡ ለማድረግ ከሆነ ትግሉ ፈዋሽ ነው፡፡ በአፍሪካችን ታሪክ ውስጥ አስቸጋሪው ምዕራፍ በጦርነት ያሸነፉ ኃይሎች የአሸናፊነት ልምድ ብቻ ስለሚኖራቸው ሰላም የምትፈልገውን የተሸናፊነት ባሕርይ ለመያዝ አለመቻላቸው ነው፡፡ በናይጄርያ የሚኖሩ ዮሩባዎች ‹ከበሮን እንዲመታ አድርጎ መሥራትና ከበሮን ለኢሻይ ኦ ሉዋህ መምታት ይለያያሉ› የሚል አባባል አላቸው፡፡ [ኢ ሻ ኦሉዋህ - ‹የእግዚአብሔር ሥራ ሳይፈጸም አይቀርም› የሚል የዩሩባ ባሕላዊ ዘፈን ነው] ነጻነትን ማምጣትና በነጻነት የምትኖርን ሀገር መገንባት የተለያዩ መንገዶችንና ችሎታዎችን ይጠይቃሉ፡፡ የደቡብ ሱዳን ተዋጊዎች ከሰሜን ሱዳን ነጻ የሆነች ሀገር በዘመናት ትግል ፈጠሩ፡፡ በሰላምና በነጻነት የምትጓዝ ሀገር መፍጠር ግን አቃታቸው፡፡ ሰላም ከአሸናፊዎች መዳፍ ልትወጣ አትችልምና፡፡ ከአሸናፊዎች መዳፍ የምትወጣ ሰላም ሰላማዊነቷ ለአሸናፊዎቹ ብቻ ነው፡፡ ተሸናፊዎቹ ምንጊዜም በጦርነት ሥነ ልቡና ውስጥ ነው የሚኖሩት፡፡ የምንታገለው ለመሸነፍ መሆን አለበት፡፡ ኔልሰን ማንዴላ በአፓርታይድ የመጨረሻዎቹ ዘመናት የአፓርታይድ መሪዎች ለድርድር ሲጋብዙት ፈቃደኛ በመሆኑ ከሌሎች የኤ ኤን ሲ መሪዎች ክርክር ገጥሞት ነበር፡፡ የአፓርታይድን ፍጻሜ ‹በፈረስ አንገት፣ በጦር አንደበት› ማምጣት ስንችልና ሲገባን ለምን? የሚል ሙግት፡፡ የማንዴላ መልስ የተለየ ነበር፡፡ ‹የታገልነው በሁላችንም ፍላጎት ላይና በሁላችንም ድርድር የምትገነባ ደቡብ አፍሪካን ለማምጣት እንጂ የአንድ ወገን የነበረችውን ሀገር የሌላ ወገን ለማድረግ አይደለም፡፡ የሁላችንም የምትሆነውን ሀገር ሁላችንም እንድንፈጥራት ለማድረግ ነው› ነበር ያለው፡፡ ትግሉ ተሸናፊዎች ወደሚገቡበት አዳራሽ ለመግባት ማንም በማንም ላይ በሩን እንዳይዘጋ ለማድረግ መሆን አለበት፡፡ ሁሉም ወገቡን እንጂ መዳፉን ይዞ እንዳይመጣ ለማድረግ መሆን አለበት፡፡ መዳፍ የጨበጡትን አላቅቆ ወገብ እንዲይዙ ለማስቻል መሆን አለበት፡፡ ዮሐንስ ሐፂር ‹አንተ ስትገባ እርሱ ወጣ› እንዳለው አንዱ ሲገባ የሚወጣ ሌላ መኖር የለበትም፡፡ ሁሉም በገቢ ደረሰኝ የሚመዘገብበትን አካውንት ነው መክፈት ያለብን፡፡ የካናዳ ጥንታውያን ሕዝቦች ‹የጦርነቱን አስከፊ ገጽታ መቅመስ አለባቸው› ካሉት በላይ በአንድ ወገን አሸናፊነት የሚጠናቀቅ ትግልና አብዮት የሚያስከትለውን ጣጣ በሚገባ ቀምሰነዋል፡፡ ዩሩባዎች ‹የፀሐይ መጥለቂያ የጨረቃ መውጫ ነው› እንደሚሉት የአንዱ ወገን ትግል መጨረሻ ለሌላው ወገን የትግል መጀመሪያ እየሆነ ስንገላበጥ ኖረናል፡፡ የሺ ዓመታት ታሪክ አለን የምንል ሕዝቦች ስንት ጊዜ የነጻነት ቀን፣ ስንት ጊዜ የሕዝብ መዝሙር፣ ስንት ጊዜ የባንዴራ ዓርማ፣ ስንት ጊዜ ሕገ መንግሥት፣ ስንት ጊዜ የየአካባቢዎቻችንን ስያሜ እንደቀያየርን እናውቀዋለን፡፡ አንድ ጊዜ አንዱ ባላባት በሌላው ባላባት ርስት ይሾምና ይሄዳል፡፡የተሾመው ባላባት ግብር አውጥቶ ሕዝብ ይጋብዛል፡፡ በዚያ ግብር ላይ የተሿሚው ወገኖች ‹ዓይናማው ገዳየ› እያሉ ሲዘፍኑ የተሸናፊው ወገኖች ‹አሃው ገዳይ› በማለት ፋንታ ‹አለን ጉዳይ› ይሉ ነበር አሉ፡፡ ልባቸው እንደሸፈተ ሲናገሩ፡፡ የነገዋ ኢትዮጵያ ጉዞም ‹ዓይናማው ገዳይ› ብሎ አንዱ ሲዘፍን ሌላው ‹አለን ጉዳይ› የማይልበትን ሥርዓት ለመዘርጋት መሆን አለበት፡፡ ይህ የሚሆነው ደግሞ የአሸናፊነት መዳፋችንን አላቅቀን የተሸናፊነትን ወገብ ይዘን ወደ ውይይቱ አዳራሽ በነጻነት ከገባን ነው፡፡ የነገዋ ኢትዮጵያ ከአሸናፊዎች መዳፍ ሳይሆን ከተሸናፊዎች ወገብ መገኘት አለባት፡፡ 

  ምንጭ : የዳንኤል ክብረት እይታዎች

  Read more »

 • ሕዝብ ለመሪው በሦስት ደረጃ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል፡፡ (ከዳንኤል ክብረት) - People's Three Stages of Warning for Their Leaders by The People

   
   
   
   
  ከዳንኤል ክብረት
  ሕዝብ ለመሪው በሦስት ደረጃ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል፡፡ የመጀመሪያው ‹አርም› የሚል ነው፡፡ በዚህ ደረጃ ሕዝቡ ሦስት ነገሮችን አምኗል ማለት ነው፡፡ አንድም መሪው በጎ ኅሊና አለው፤ ለማረም የሚችል ዐቅም አለው፤ ችግሩ የተፈጠረው ከአሠራሩ ላይ ነው ብሏል፡፡ አንድም ደግሞ ሕዝቡ መሪው እንደማንኛውም ፍጡር ተሳሳተ እንጂ ራሱ ስሕተት አይደለም፡፡ ስለዚህ ሊያርም ይችላል ብሎ አምኗል፡፡ በመጨረሻም ሕዝብ መሪውን ይወዳል፣ ስሕተቱን ግን ይጠላል ማለት ነው፡፡
   
  እዚህ ላይ የደረሰ መሪ የታደለ የሚሆነው ስሕተቶቹን ነቅሶ ‹ሳይርቅ በቅርቡ፣ ሳይደርቅ በርጥቡ› ለማረም ከቻለ ነው፡፡ የሚሳሳት ፈጣሪ እንደሌለ ሁሉ የማይሳሳት መሪ የለም፡፡  መሪዎችን ታላቅና ታናሽ የሚያደርጋቸው ስሕተታቸውን ለማመንና አምነውም ለማረም ያላቸው ዐቅምና ቁርጠኛነት ነው፡፡ መሪ የሕዝቡን ጥቆማ ሰምቶ፣ የሕዝቡንም ልብ አድምጦ ችግሩን በጊዜ ካረመ ስሕተቱ ከሥራ የመጣ እንጂ ከመሪው ጠባይ የመነጨ አይደለም ብሎ ሕዝብ በመሪው እንዲተማመን ያደርገዋል፡፡ ‹ከሰው ስሕተት፣ ከብረት ዝገት አይጠፋም› ብሎ ያልፈዋል፡፡ ሕዝብ የነገረውን ስሕተት ከማረም ይልቅ ‹እኔ ደኅና ነኝ ችግሩ ከአፈጻጸሜ የመጣ ነው› እያለ ችላ ካለው ሕዝብ ወደ ሁለተኛው ደረጃ ይሻገራል፡፡ ጃን ሜዳ ሠፍሮ እያደመ ራስ ተፈሪን ወደ ዙፋን ያመጣው መሐል ሠፋሪ ጦር (ሠራዊቱ) ነበር፡፡ በኋላም አርሙ ቢላቸው አላርም ሲሉ በ1953 መፈንቅለ መንግሥት ያደረገው ይኼው ሠራዊት ነው፡፡
   
  ሁለተኛው የሕዝብ ማስጠንቀቂያ ‹ታረም› የሚል ነው፡፡ ሕዝብ  መሪውን ‹ታረም› ካለ ሁለት ነገሮችን አስቧል፡፡ ‹መሪው ልክ ነበር ነገር ግን  እንደማንኛውም ፍጡር ተሳስቷል› የሚለው ሐሳቡን ቀይሯል፡፡ ‹መሪው ስሕተቱን ሊያርም ይችላል› ከሚለው ወጥቷል፡፡ ይህንን ዕድል ላይመለስበት አልፎ መሪው ስሕተት የሚሠራ ሳይሆን ስሑት (የተሳሳተ) መሪ ነው፡፡ ስሕተቱ ከሥራ ሂደት ሳይሆን ከአመራሩ፣ ከአስተሳሰቡና ከአካሄዱ የመጣ ነው፡፡ ተግባሩ እንዲስተካከል መሪው መስተካከል አለበት ብሎ ሕዝቡ አምኗል ማለት ነው፡፡ ከኩርንችት በለስ፣ ከአጋምም ወይን ሊለቀም አይችልም፡፡ ውኃው እንዲስተካከል ምንጩ መስተካከል አለበት ብሎ ሕዝብ ማሰብ ጀምሯል፡፡ እንደዚያም ቢሆን ግን መሪው ራሱን ሊያረም የሚችል መሪ ነው ብሎ አምኗል፡፡
   
  በዚህ እከን ላይ የደረሰ መሪ ራሱን ፈትሾ፣ መርምሮና አንጥሮ እንደ ወይን ግንድ እየገረዘ ሸለፈቱን መጣል አለበት፡፡ ሌላውን ሰውነት ለማዳን ሲባል ሕመምተኛው የሰውነት አካል እንደሚቆረጠው ሁሉ ሀገርን ለማዳን ሲባል የሚቆረጡ አሠራሮች፣ አስተሳሰቦች፣ አካሄዶች፣ መሪዎች፣ ፖሊሲዎችና መርሖች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ‹ታረም› የተባለ መሪ እነዚህን አርሞ እንደ እባብ ሳይሆን እንደ ንሥር ታድሶ ከመጣ፤ ጥፋቱ ከአፈጻጸሜ የመጣ ነው፣ ሕዝቡ ስላልገባው ነው፣ ስላልተማረ ነው፣ ስላልሠለጠነ ነው፣ እያለ የመሥዋዕት በግ ፍለጋ ካልኳተነ፤ ‹ችግሩ እኔ  ነኝ፤ መፍትሔውም የእኔ መለወጥ ነው› ብሎ ካመነ፤ አምኖም ከሠራ፤ ሠርቶም ከተለወጠ፡፡ ሕዝቡ፡-
  ‹አሁን ወጣች ጀንበር
  ተሸሽጋ ነበር› ብሎ ይቀበለዋል፡፡
  ይህንን ሁሉ ትቶ መሪው በሕዝቡ ትዕግሥት ላይ ከቀለደ፤ ሕዝብም ለትዕግሥቱ ምላሹ ካለፈው የባሰ፣ ከተስፋው ያነሰ ሲሆንበት፤ ሕዝብ አመለካከቱን ይቀይራል፡፡ አርም፣ ታረም ማለት ዋጋ አልባ መሆኑን ይረዳል፡፡ ሊያርም ሊታረም የሚችል መሪና አመራር የለም ብሎ ያምናል፡፡ ችግሩ መሠረታዊ ነው ብሎ ይረዳል፡፡ በዚህ ጊዜ ሦስተኛውንና የመጨረሻ ማስጠንቀቂያውን ይሰጣል፡፡ ንጉሥ ኃይለ ሥላሴን ሆ ብሎ ወደ ሥልጣን ያመጣው ወታደር፣ ስሕተቶቻቸውን ማረም ሲያቅታቸው በ1953 መፈንቅለ መንግሥት ያደረገው ወታደር፤ በ1966 ደግሞ ሥልጣናቸውን አሳጣቸው፡፡ የ1953ቱ መፈንቅለ መንግሥት ‹ታረም› የሚል መልእክት እንዳለው ንጉሡ ቢረዱ ኖሮ የ66ቱን ነገር ያስቀሩት ነበር፡፡ ግን አልሆነም፡፡ ‹ታረም› የሚለውን አልረዳ ሲሉ ‹ተወገድ› የሚለው የመጨረሻው ማስጠንቀቂያ መጣ፡፡ 
   
  ደርግም እንዲህ ነበር፡፡ በ66 አብዮቱ ሲፈነዳ፣ መሬት ላራሹ ሲታወጅ የሕዝብ ድጋፍ ነበረው፡፡ ቆይቶ ስሕተት ሲያበዛ ‹አርም› የሚለው መልእክት ከያቅጣጫው መጣ፡፡ ሰልፎች፣ ወረቀቶች፣ ተቃውሞዎች መጡ፡፡ ከማረም ይልቅ ‹መረምረም› ስለመረጠ የመጀመሪያውን ዕድል አሳለፈው፡፡ ከውስጥና ከውጭ ጠብመንጃ አንሥተው ግራ ቀኝ የወጠሩት ኃይሎች ‹ታረም› ቢሉትም መታረም ትቶ ማውደምን መረጠ፡፡ የ1981 ዓም መፈንቅለ መንግሥት ‹ተወገድ› የሚለውን መለከት ነፋ፡፡ ደርግ የሚተርፍ መስሎት ለፋ፡፡ ግን ተወገድ ከተባለ በኋላ መትረፍ በተአምር ብቻ ነበርና ሊተርፍ አልቻለም፡፡
   
  ይህ ‹ተወገድ› የሚለው ሦስተኛው  ማስጠንቀቂያ የመጨረሻው የሕዝብ ጥያቄ ነው፡፡ መሪው ታምሞ አይደለም፡፡ ራሱ በሽታ ነው፡፡ ተቸግሮ አይደለም፡፡ ራሱ ችግር ነው፡፡ ደክሞ አይደለም፡፡ ራሱ ደካም ነው፡፡ ተፈትኖ አይደለም፤ ራሱ ፈተና ነው ብሎ አምኗል፡፡ ስለዚህም መፍትሔው መወገድ ብቻ ነው ብሎ ይቆርጧል፡፡ ቆርጦም ይሠራል፡፡ ሕዝብ እዚህ ደረጃ ከደረሰ በኋላ መመለስ ብዙ ጊዜ ከባድ ነው፡፡ ማረምንም መታረምንም ከሚቀበልበት እርከን አልፏልና ቀሪው ዕድል የሚሆነው በሰላም መሰናበት ነው፡፡
   
  የአንድ መሪ ብስለት በሁለት ደረጃ ይለካል፡፡ የመጀመሪያው ሲቻል በፊተኛው፣ ሳይቻል በቀጣዩ ደረጃ ላይ መንቃት፣ ነቅቶም  ተገቢውን ማድረግ፡፡ ያም ዘመን ካለፈና ጀንበር ካዘቀዘቀች ደግሞ ራሱንም ሀገሩንም ሳያጠፋ መልካም የወንድ በር ማዘጋጀት ነው፡፡
  ዘቦ እዝን ሰሚዐ ለይስማዕ፡፡  
  Read more »

 • አራቱ የጠባይ እርከኖች

                                            

   ከዳንኤል ክብረት

  የሰው ልጅ አራት የጠባይ እርከኖች አሉት ይላሉ ትውፊታውያን ሊቃውንት፡፡ በነባሩ የኢትዮጵያ ትምህርት መሠረት ጠባይና ባሕርይ ይለያያሉ፡፡ ‹ባሕርይ› ማንነት ነው፡፡ በፍጥረትህ ታገኘዋለህ፡፡ ይዘህው ትኖራለህ፡፡ አትለውጠውም፤ አታሻሽለውም፡፡ ለምሳሌ ሰውነት ባሕርይ ነው፡፡ ሰው መሆንን፣ እንስሳ ወይም ዛፍ ወይም ውኃ በመሆን አትለውጠውም፡፡ ‹ጠባይ› ደግሞ በተፈጥሮ፣ በልምድ፣ በዕውቀት፣ በውርስ፣ የሚገኝ አስተሳሰብ፣ አመለካከት፣ ልማድ፣ አኳኋን፣ አነዋወር፣ አመል ነው፡፡ በትምህርት የጠባይ ለውጥ እንጂ የባሕርይ ለውጥ አይመጣም የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ የባሕርይ ለውጥ ማለት ጨርሶ ማንነትን መለወጥ ማለት ነውና፡፡

   
  ሰው ምንም እንኳ አንድ ዓይነት ሆኖ ቢፈጠር በትምህርቱ፣ በባህሉ፣ በልምዱ፣ በልምምዱ፣ በእምነቱ፣ በፍላጎቱና በምርጫው የተነሣ በተለያዩ የጠባይ ደረጃዎች ውስጥ ሊኖር ይችላል፡፡ እነዚህ የጠባይ ደረጃዎች አውሬነት፣ እንስሳነት፣ ሰውነትና መልአክነት ናቸው፡፡ ከአንደኛው ወደ ሌላኛው ማደግና መሻሻል የሚቻለውም አንደኛውን ተረድቶ፣ አርሞና ገርቶ ለሌላኛው ተገዥ በማድረግ ነው፡፡ ዝቅተኛው የጠባይ ደረጃ አውሬነት ሲሆን ከፍተኛው ደግሞ መልአክነት ነው፡፡ የታችኛውን ሳይገሩና ሳይገዙ ቀጥሎ ያለውን ጠባይ ገንዘብ ለማድረግ የሚሞክሩ ሰዎች ለጊዜው እንደ ተዋናይ ይጫወቱ ይሆናል፡፡ ቆይቶ ግን ባላሰቡትና ባልፈለጉት ጊዜ ያልተገራውና ያልተገዛው ጠባይ ብቅ እያለ ይበጠብጣል፡፡ በተለይም በልዩ ልዩ ስሜቶች በሚናጡበት ጊዜ የደበቁት ጠባይ መገለጡና መጋለጡ አይቀርም፡፡ አንዳንድ ሰዎችም ሳያሸንፉና ሳይገዙ ሸፋፍነው የተውትን ጠባይ ይረሱታል፡፡ ‹ዝም ያለ የሌለ ይመስላል› እንዲሉ፡፡ በዐመድ እንደ ተዳፈነ የፍግ እሳት ይሆናል፡፡ እንዲህ ያለው የተዳፈነ ጠባይ በሰውነት ውስጥ ‹ሲስት› ሠርቶ እንደተቀመጠ ተሐዋሲ አመቺ ጊዜ ነው የሚጠብቀው፡፡ ‹እገሌን ሳውቀው እንዲህ አልነበረም፤ ስንጋባ ይኼ ጠባይ አልነበረውም፣ አብረን ስንሠራ እንዲህ ያለ ነገር አይቼባት አላውቅም፣ ድሮ ደኅና ሰው ነበረች› እያልን በምናውቃቸው ሰዎች ላይ ከምናዝንባቸው ምክንያቶች አንዱ ያልገሩትና ያልገዙት ጠባይ ብቅ ሲል አይተን ነው፡፡
   
  የመጀመሪያው የጠባይ ደረጃ አውሬነት ነው፡፡ አውሬነት ስግብግብነት፣ ጉልበተኛነት፣ ነውጠኛነት፣ ርኅራኄ ቢስነት፣ ለማንኛውም ችግር መፍትሔው ኃይል ነው ብሎ ማመን፣ አእምሮን የጥርስና ጉልበት ያህል አለማሠራት፣ በግዳይ መርካት፣ ከሌሎች ጋር ተግባብቶና ተስማምቶ ከመኖር ይልቅ ከልሎና አጥሮ መኖር፤ ማስደንገጥ፣ ማሸበርና ማስፈራረትን የሐሳብ ማስፈጸሚያ ማድረግ፤ በተለይ ጉልበትና ዐቅም በሌላቸው ላይ መጨከን ነው፡፡ አውሬነት ገንዘቡ የሆነ ሰው ምንም የተገራና የተገዛ ጠባይ አይኖረውም፡፡ ልምድ፣ እድሜ፣ ትምህርት፣ ተሞክሮ፣ ቅጣት፣ ሽልማት፣ ባህልና እምነት ያሻሻሉለት፣ የቀረጹለትና የለወጡለት ጠባይ አይኖረውም፡፡ ወይም ደግሞ በእነዚህ ለመሻሻልና ለመለወጥ ፈቃደኛ አይደለም፡፡ ራሱንም አላዘጋጀም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ይህንን ጠባይ በውስጣዊ አእምሮው ውስጥ እንደ ሞተር ዋናውን ቦታ ሰጥቶ ነገር ግን በትምህርት፣ በባህል፣ በእምነትና በልምድ ያገኘውን ጠባይ በላዕላይ የእእምሮው ክፍል እያስቀመጠው የሚኖር አለ፡፡ አንዱ ካንዱ ጋር ሳይገናኝ፣ ሳይሟገትና ሳይሸራረፍ፣ በምንታዌ የሚኖር፡፡ እንዲህ ያለው ሰው ዕድል፣ ሥልጣን፣ ገንዘብና አጋጣሚ ሲያገኝ ያንን እንደ ሞተርና አስኳል በአእምሮው ውስጥ ዋና ቦታ ሰጥቶ ያስቀመጠውን የአውሬነት ጠባይ ያወጣል፡፡ 
   
  ክፉ አምባገነኖች፣ ጨካኝ መሪዎችና አስቸጋሪ አለቆች የሚፈጠሩት በዚህ ምክንያት ነው፡፡ በሀብት ውስጥ፣ በዕውቀት ውስጥና በዝና ውስጥ የተደበቀ አውሬነት የሚገኘው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ የተማሩትን፣ የሠለጠኑበትን፣ ያመኑትንና ሲደሰኩሩበት የኖሩትን ትተው ከእነርሱ የማይጠበቅ የአውሬነት ሥራ ሲሠሩ የምናያቸው ‹ፊደላውያን›፣ ታዋቂ ሰዎች፣ ባለሥልጣናትና ባለ ገንዘቦች በዚህ በሽታ የተጠቁ ናቸው፡፡ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ መማራቸው፣ መሠልጠናቸውና በእምነት ውስጥ መኖራቸው አውሬነታቸውን እንዲገሩትና እንዲገዙት ከማድረግ ይልቅ ‹መልከ ጥፉውን በስም እንዲደግፉት› ያደርጋቸዋል፡፡ ለአውሬነታቸው የሃይማኖት፣ የፖለቲካ፣ የፍልስፍናና የዘር ስያሜ ይሰጡታል፡፡ መግደላቸው፣ መጨፍጨፋቸው፣ መዝረፋቸው፣ ማጥፋታቸውና ማውደማቸው ትክክል መሆኑን ለማስረዳት ሃይማኖትን፣ ፖለቲካን፣ ዘርንና ፍልስፍናን ሽፋን ያደርጓቸዋል፡፡ 
   
  ሁለተኛው የጠባይ ደረጃ እንስሳነት ነው፡፡ እንስሳነት ከሆድ ያለፈ ነገር አለማሰብ፣ መዋሰብና መዋለድን ብቻ ገንዘብ አድርጎ መኖር፤ ወደነዱት መነዳት፤ ‹ቢጭኑት አህያ ቢለጉሙት ፈረስ› መሆን፤ በተፈቀደልን መስክ ብቻ መጋጥ፣ በተቀየደልን በረት ብቻ መኖር፤ ‹ሰብተዋል ልረዳቸው፣ ደርሰዋል ልጋልባቸው› ለሚለን ሁሉ እሺ ማለት፤ ማር ሠርተን ሌሎች እየቆረጡት፣ ወተት አግተን ሌሎች እየጠጡት መኖር፤ ከምንውልበት መስክና ከምናድርበት በረትና ጋጣ አርቆ አለማሰብ ነው፡፡ ምንም እንኳን እንደ አውሬነት ጠባይ ክፋትና ተንኮል፣ ንጥቂያና ዝርፊያ፣ ደም አፍሳሽነትና ጉልበተኝነት፣ ድንበርተኛነትና አምባገነንነት ባይኖሩም ‹ሆዴ ከሞላ፣ ደረቴ ከቀላ› ከዚህ በላይ ምን እፈልጋለሁ ብሎ መኖር የእንስሳነት ዋናው መገለጫ ነው፡፡ ‹እኔ ከሰው አልደረስ፣ ሰውን አላማ፣ የሰው ገንዘብ አልነካ፣ ሰው አላስቀይም፣ ከሰው አልጣላ› እያሉ የሚመጻደቁ ሰዎች ምን ጊዜም የሚያዩት በሰው ላይ ክፉ አለማድረጋቸውን ብቻ ነው፡፡ ዛፎችም፣ ተራሮችም፣ ወንዞችም፣ ሐይቆችም ይህንን ሊናገሩ ይችላሉ፡፡ የሰው ዋና መለኪያው ምን አላደረገም? ሳይሆን ምን አደረገ? ነው፡፡ ምንም ባለማድረግማ ሙትንና ግዑዝን የሚስተካከለው አይኖርም፡፡  
   
  ብዙ ጊዜ የሌሎች አጃቢ፣ ተከታይና አድናቂ ሆነው የምናገኛቸው እነዚህን ነው፡፡ አይመዝኑም አያመዛዝኑም፣ አይገምቱም አያነጥሩም፤ የነገሯቸውን ሁሉ ያምናሉ፤ የሰጧቸውን ሁሉ ይቀበላሉ፤ ለምን፣ እንዴት፣ መቼ፣ ምን፣ የት፣ ወዴት ብለው መጠየቅ አይችሉም፣ አይወዱምም፡፡ ከሐሳብ ይልቅ በዘር፣ በዝምድና፣ በሀገር ልጅነት፣ አብሮ በመብላትና በመጠጣት፣ በመዋለድና በመጋባት ያምናሉ፡፡ ሐሳባቸውን ማሻሻል፣ ማዳበርና መለወጥ አይፈልጉም፡፡
  ሦስተኛው ጠባይ ደግሞ ሰብአዊነት ነው፡፡ ማወቅ፣ ማመዛዘን፣ መለወጥ፣ መሻሻል፣መገመት፣ መመዘን፣ ከትናንት መማር፣ ስለ ነገ መተለም፤ ከአካባቢ፣ ከዘር፣ ከጎጥ፣ ከአጥንትና ጉልጥምት ወጣ አድርጎ ማሰብ፤ ራስን የሌላውም አካል አድርጎ ማሰብ፤ ለአእምሮ ትልቅ ቦታ መስጠት፤ ስሕተትን ለማረም፣ አዲስ ነገርን ለመቅሰም፣ ለመሠልጠን፣ ለመመርመርና ለመፈልሰፍ መትጋት፤ ለፍቅር፣ ለርኅራኄ፣ ለሰላምና ለወንድማማችነት ትኩረት መስጠት፣ በሥርዓትና በሕግ መመራት፣ ከስሜት ይልቅ ለመንፈስ፣ ከፍላጎት ይልቅ ለአቋም፣ ከጥቅም ይልቅ ለመርሕ መቆም ነው ሰውነት፡፡ አእምሮ(ዕውቀት)፣ ልቡና(መድሎት)፣ እና ኅሊና(መንፈስ) ያለው ሰው ብቻ ነው፡፡ አእምሮን ለማወቅ፣ ለመረዳትና ለማሰብ፤ ልቡናውን ባወቅና በተገነዘበው ላይ ተመሥርቶ ለማገናዘብ፣ ለለማስተያየትና ለማነጻጸር፣ ለመመዘንና ለመወሰን፣ ኅሊናውን ለማምሰልሰል፣ ለማሰላሰል፣ ወደኋላ ለማሰብ፣ ወደፊት ለመተንበይ፣ ወደላይ ለመንጠቅ፣ ወደ እመቃት ለመጥለቅ ከቻለ ነው አንደ ሰው ‹ሙሉ ሰው› ሆኗል የሚባለው፡፡  
   
  ሰውነት ምንም እንኳን ከፍተኛው የሰብእና አካል ቢሆንም ጉድለቶች ግን አሉት፡፡ እንደ ዶክተር እጓለ አገላለጥ ለ‹ጽርየት› ትኩረት አይሰጥም፡፡ ‹ጽርየት› ማለት በግርድፉ ንጽሕና ነው፡፡ በዋናነት ግን የአእምሮ፣ የኅሊናና የልቡና ንጽሕናን ይመለከታል፡፡ ሰውነት በአንድ በኩል ሳይገራ ይዟቸው ከታችኞቹ ጠባያት ያመጣቸው እንከኖች፣ በሌላ በኩል ደግሞ የሐሳብ፣ የእምነት፣ የፍልስፍና፣ የዘር፣ የባህልና የሥልጣኔ ልዩነቶችን ለመፍታት በሚወስዳቸው መፍትሔዎች ምክንያት ‹ዕድፈት› ያጋጥመዋል፡፡ ‹ዕድፈት› ማለት ጥበብን፣ ዕውቀትን፣ ሥልጣንን፣ ገንዘብንና ዝናን ለግላዊ ፍላጎት ለማዋል የሚሠራ ሰብአዊ ሤራ ነው፡፡ በተለይም ይኼ ሤራ ሳይገራና ሳይገዛ ከመጣ የአውሬነትና የእንስሳነት ‹ተረፈ ጠባይ› ጋር ከተቀላቀለ አደገኛ ነው፡፡ ለአውሬነትና እንስሳነት ጠባያት የዕውቀት፣ የጥበብ፣ የሃይማኖት፣ የፖለቲካና የፍልስፍና ስያሜ እየሰጡ የሰውን ልጅ የሚያስቸግሩ ሰዎች የሚከሠቱት በዚህ ዕድፈት ምክንያት ነው፡፡ 
   
  ጽርየትን ለማግኘት ወደ አራተኛው የሰብእና ደረጃ መግባት ያስፈልጋል፡፡ ጽርየት የሚገኘው ከመልአክነት ነው፡፡ መልአክነት ዋናዎቹ መገለጫዎቹ ሁለት ናቸው ‹ለሌሎች በሚደረግ መሥዋዕትነት በመርካት› እና ‹ምስጉን ህላዌ› ናቸው፡፡ ለሌሎች በሚደረግ መሥዋዕትነት መርካት ማለት ለሀገር፣ ለወገን፣ ለዓለም ሕዝብ፣ ከዚያም አልፎ ለእንስሳትና ለዕጽዋት፣ ለወንዞችና ለሐይቆች፣ ለአእዋፍና ለዓሦች፣ ለሰማዩና ለምድሩ በሚከፈል መሥዋዕትነት መርካት ማለት ነው፡፡ ‹የራስ ደስታ የሌሎችም ደስታ ነው› ብሎ ማሰብ ሰውነት ሲሆን ‹የኔ ደስታ ከሌሎች ደስታ ይመነጫል› ብሎ ማሰብ ግን መልአክነት ነው፡፡ መልአክነት በምግብና መጠጥ፣ በልብስና ጫማ፣ በክብርና ዝና፣ በሥልጣንና ገንዘብ፣ በውበትና ቁንጅና ሳይሆን ይህቺን ዓለም መልካም የሰው ልጆች መኖሪያ ለማድረግ፣ ነጻነትንና ፍትሕን፣ እኩልነትንና ርትዕን፣ ሰላምንና መልካም አነዋወርን ለማስፈን በሚከፈል መሥዋዕትነት መርካት ነው፡፡ 
   
  ሰው በሚያገኘው ሳይሆን በሚሰጠው መደሰት፣ በሚዋልለት ሳይሆን በሚውለው፣ በሚደረግለት ሳይሆን በሚያደርገው፣ በሚከብረው ሳይሆን በሚያከብረው ነገር ይበልጥ መደሰት ሲጀምር ነው ጽርየት የሚገኘው፡፡
  ‹ምስጉን ህላዌ› ማለት ‹እያመሰገኑና እየተመሰገኑ መኖር› ነው፡፡ መላእክት እያመሰገኑና እየተመሰገኑ እንደሚኖሩት ሁሉ ሰውም ጽርየት ሲኖረው የሰዎችን መልካም ሥራ ለማየት፣ ከአድናቆት ለመጀመር፣ በስሕተታቸው ከመበሳጨት ይልቅ ከበጎ ሥራቸው ተነሥቶ ስሕተታቸውን ለማረም፣ በጉድለታቸው ከመናደድ ይልቅ ጉድለታቸውን ለመሙላት፣ ከጠማማው ግራር ታቦት ለመቅረጽ፣ ከእሾሃማው እንጨት ዕጣን ለመልቀም የሚተጋ ማለት ነው፡፡ እንዲህ ያለው ሰው የሚያጋጥመው ፈተና፣ የሚጋረጥበት ተግዳሮት፣ የሚደርስበት ችግር የለም ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን በእነዚህ ደስታውን አይነጠቅም፡፡ መሥዋዕትነቱ የሚያመጣውን በጎ ውጤት እንጂ የደረሰበትን አያስበውምና፡፡ በእርሱ ድካም የሚበረቱትን፣ በእርሱ ቁስል የሚፈወሱትን፣ በእርሱ እሥራት የሚፈቱትን፣ በእርሱ ሕማም የሚድኑትን፣ በእርሱ ሥራ የሚጠቀሙትን፣ በእርሱ ሞት የሚወለዱትን ያስባልና ደስተኛ ነው፡፡ ለዚህ ነው አመስጋኝ የሚሆነው፡፡ ተመስገኝ ህላዌም ይኖረዋል፡፡ የሚሠራው ሥራ የሚጠፋ አይደለም፡፡ ለትውልደ ትውልድ የሚኖር ነው፡፡ ምናልባት በአንድ ዘመን የተሸሸገ ቢመስል እንኳን መሬት ውስጥ እንደተቀበረ እሳተ ገሞራ አንድ ቀን ራሱን መግለጡ አይቀርም፡፡ ታሪኩን የሚጽፍለት፣ ገድሉን የሚዘክርለት ባያገኝ እንኳን እውነት ራሷ አፍ አውጥታ ምስክር ትሆነዋለች፡፡ ስለዚህ የእርሱ ኑባሬ በሞት አይገታም፡፡ ሞት ቅርጹን ይቀይረዋል እንጂ ክብሩንና ህላዌውን አይቀይረውም፡፡ እንዲያውም በቆየ ቁጥር ጣዕሙ እንደሚጨምር የገጠር ጠላ ዘመናት ባለፉ ቁጥር የሚያስታውሱትና የሚያመሰግኑት እየበዙ ይሄዳሉ፡፡ የሚፈልጉትና የሚጠቀሙበት ይጨምራሉ፡፡ ለዚህ ነው ‹ምስጉን ህላዌ› አለው ያልነው፡፡ ሲመሰገን የሚኖር ህላዌ ማለት ነው፡፡
  ጽርየትን ገንዘቡ ያደረገ ሰው ከወንጀል፣ ከጥመት፣ ከኃጢአት፣ ከጥቅመኛነት፣ ከአምባገነንነት፣ ከጥፋትና ከክፋት ጋር አይገጥምም፡፡ ይጸየፈዋል፡፡ እንዲህ ያሉትን ታግሦ፣ አቻችሎ፣ ተሸክሞ፣ እንዳላየ አልፎ፣ የራሱ ጉዳይ ብሎ፣ እኔን አይመለከተኝም ብሎ አያልፈውም፡፡ ድንግዝግዝ ሰብእና እንጂ ጽርየት እነዚህን አይታገሥምና፡፡  
   
  ዓለም የጣፈጠቺውና የምትጣፍጠው፣ በአጭሩ እድሜያችን ብዙ ነገር እንድናይ ያደረጉን፣ የሰው ልጅ ድካም ቀልሎ፣ የሰው ልጅ ሕማም ድኖ፣ የሰው ልጅ ጉድለት ሞልቶ፣ የሰው ልጅ ሥልጣኔ መጥቆ፣ የሰው ልጅ ሥርዓት ሠምሮ የምናየው በእነዚህ መልአካውያን አስተዋጽዖ የተነሣ ነው፡፡ ክፋቱ ቁጥራቸው ጥቂት ነው፡፡ ሥራቸው ግን ‹ከተባረከ ይበቃል አንዱ› እንደተባለው ነው፡፡ እነዚህ መልአካውያን በአውሬነት፣ በእንስሳነትና በሰውነት ውስጥ ያሉ ክፉ ዐመሎችን ሁሉ ገርተው፣ ቀጥተውና ገዝተው ልዕልናን ያገኙ ናቸው፡፡ በአእምሮ ሳይሆን በልዕለ አእምሮ የሚሠሩ ናቸው፡፡ ማንም እንደ ባዶ ኮምፒውተር የፈለገውን ፕሮግራም አይጭናቸውም፤ አይቀይዳቸውም፤ በሳጥን አስገብቶ አይወስናቸውም፡፡ እነርሱ በሐሳብ ልዕልና፣ በመንፈስ ንጽሕና ይራመዳሉ፡፡ ድንበሮችና አጥሮች፣ ቋንቋዎችና እምነቶች፣ ባህሎችና ልማዶች፣ ጎሳዎችና ጎጦች ሊገድቧቸው አይቻላቸውም፤ እነርሱ ‹መልዕልተ ኩሉ ሥጋውያን› ናቸው፡፡ በጥቅምና በገንዘብ፣ በክብርና በዝና፣ በሥልጣንና በርስት መደለል አይቻልም፡፡ እነዚህን ሁሉ ዐውቀው፣ ንቀው፣ ልቀው፣ መጥቀው፣ ከፍ ባለው የሰው ልጅ ክብር ‹መልአክነት› ላይ ደርሰዋል፡፡ እነዚህን ለሌሎች በመለገስ ይደሰታሉ እንጂ ለእነርሱ በማግኘት አይደሰቱም፡፡ 
   
  ዓለም በዚህ ዘመን የተቸገረቺው እነዚህን መልአካውያን እያጣች አውሬዎቹን እያበዛች፣ እንስሳቱን እያበረታታች፣ ሰብአውያኑንም ከጽርየት እየገታች በመሄዷ ነው፡፡ 
  ምንጭ:- የዳንኤል ክብረት እይታዎች
  Read more »

 • ባህላዊ ሙዚቃችን በአገርኛ እይታ ሲቃኝ

                                            

                    የሰው ልጅ ሲርበው ምግብ እንደሚያስፈልገው ሁሉ፤ በውስጡ የሚመላለሱ ሃሳቦችን ለመግለጽምና ለማስታውስ እንዲሁም መንፈሱን ለመመገብ ሙዚቃን ይጠቀማል። ሙዚቃ ዓለም አቀፋዊ ቋንቋ እንደመሆኑ መጠንም ዓለም ሁሉ በሙዚቃ ያዝንበታል፣ ይደሰትበታል፣ይግባባበታል፣ይኖርበታል ወዘተ።

  በዓለም አቀፍ ደረጃ ሙዚቃ በተለያየ ስልት እንደሚገለጽ፣ በአቶ ወሰንየለህ መብረቁ የተጻፈና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የተዘጋጀው ፅሑፍ ያትታል። እነርሱም ክላሲካል፣ጃዝ፣ፓፕና የህዝብ ሙዚቃ ሲሰኙ፤ በጥቅል አጠራራቸው ደግሞ መንፈሳዊና ዓለማዊ ይባላሉ። ይኸው ፅሑፍ ሙዚቃ ታሪክ መጻፍ ከመጀመሩ በፊት እንደተጀመረ ይገልጻል። የሰው ልጅ የገዛ ሰውነቱን እንቅስቃሴና ተፈጥሮ በማስተዋል ቀስ በቀስ ለመዘመር፣ ለመደነስና ሪትም (ቅኝት ያለው ሙዚቃን ለመፍጠር መቻሉንም ይናገራል።

  ሙዚቃ ሰዎችን በማግባባት ያስተሳስራል። የተለያዩ የጎሳ ቡድኖች አንድ እንዲሆኑ ያነሳሳል። ለምሳሌ የትግርኛ ምት በትግርኛና በአማርኛ ቃላት፤ የጉራጊኛው፣ የኦሮምኛውም ሆነ የሌሎች ቋንቋዎች ምት ከማይመስለው ቋንቋ ጋር በመቀላቀል ታጅቦ ሲቀርብ ምንም ዓይነት የቅኝትም ሆነ የስልት ልዩነት ችግር ሳያሳይ የአንዱን ቋንቋ ሌላው እንዲረዳ ያደርጋል።

  በተለይ የባህላዊ ሙዚቃ እነዚህን ተግባራት ከመከወን አንፃር ሠፊ ድርሻ እንዳላቸው ይታመናል። የሀገራችንን ባህላዊ ሙዚቃዎች በአገርኛ ባህል ሲቃኙ ቅኝታቸውን በአራት ከፍሎ ማይት ይቻላል። ትዝታ፣ አምባሰል፣ባቲና አንቺሆዬ። እነዚህን ቅኝቶችን በምሳሌ አስደግፈው አቶወሰንየለህ በፅሑፋቸው አብራርተውልናልና በጥቂቱ እንቃኛቸው።

  ትዝታ፦ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ ይህ መሰላል የሚፈጥራቸው የዜማ ስልቶች እንደ ትዝታ ያሉ የሩቅ ጊዜ ስሜትን አንፀባራቂዎች ናቸው። ኢትዮጵያውያን በውስጣቸው ሩህሩህ የሆኑ ናቸው። በሞት አምርረው ያዝናሉ። በመለያየት ይቆዝማሉ። ይህ ክስተት ተፈጥሯዊ መሆኑን በመዘንጋት ሳይሆን ተገናኝቶ መለያየትን በቀላሉ መቀበል የሚቸግራቸው በመሆኑ ነው። ትዝታም የዚህ ውስጣዊ ስሜት ነፀብራቅ ሆኖ ያገለግላል።

  አምባሰል፦ ኢትዮጵያውያን የተስፋ ሰዎች ናቸው። በባንዲራቸው ውስጥ ቢጫው ቀለም የሚገልጸውም ይኸን ተስፋቸውን ነው። ከብዙ ሀገራት ህዝቦች መሐል ኢትዮጵያውያንን የሚለያቸው በባህላቸው ውስጥ ተስፋን አካተው የሚጓዙ መሆናቸው ጭምር ነው። መከራን ለመታገስና ለማሳለፍ የሚችሉበት አቅም የሚፈጥርላቸው ይህ ብሩህ የሆነ ተስፋቸው ነው። ይህም በሙዚቃ ባህላቸው ውስጥ አንድ አድርገውም ይዘውት ይጓዛሉ። በዜማ ታግዞ መፅናናትና እራስን ማበረታታት የተለመደ ነው። ይህ ተስፋ በርቀት ያለን ሁኔታ በዓይነ ህሊና አቅርቦ የሚያሳይ ጊዜያዊውን ችግር ንቀው የሚያልፉበት መሣሪያ ነው።

  ባቲ፦ በኢትዮጵያውያን መካከል ኀዘንና ደስታ ሲፈራረቅ ሁሉንም በየመልካቸው ከሚያስተናግዱበት መንገድ መሐል አንዱ የዚህ ሙዚቃ ባህርይ የሚያስከትለው የመፅናናትና የመደፋፈር ስሜትን የመፍጠር ዘይቤ ነው። በዘፈን ጨዋታ በቀረርቶና በሽለላ ጦርነትን በድል የመወጣት መንፈስና መንገድ ያለው ባቲ ዜማ ነው። ይህ ስልት ለመነቃነቅ፣ ለመጨፈር ነፃ ስሜትን፣ ድፍረትን፣ ወኔን ለመጎናፀፍ ያስችላል። የባቲ መሠረታዊ ተልዕኮ ሞራልን፤ የአልደፈርም ባይነትን ስሜት በቀረርቶና በፍከራ አቀራረብ ስልት ማንፀባረቅ አንደኛው መንገዱ ነው።

  አንቺ ሆዬ፦ አንቺ ሆዬ ቅኝት የሚይዘው ስሜት እራስን አሳልፎ የመስጠት፤ ይበልጥ አምልኮትን የማንፀባረቅ ተሸናፊነትን ተስፋ ቆራጭነትን ለመቋቋም ፈጣሪን ከመማለድ፣ ፈጣሪን ከመማፀን ጀምሮ ያለውን ስሜት የሚገልጽና ትዝታን፣ ናፍቆትን እንዲሁም የአገር ፍቅርን ለመዝፈን የሚጠቅም ነው።

  በዚህ ዓይነት የተለያዩ ስሜቶችን ለማንፀባረቅ የሚችለው የስኬል አወቃቀር በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ ያሬዳዊ ዜማ መዋቅርን የሚከተልና የቃላቶቹ አወራረድም ፍፁም እምነታዊ አገላለጽ ያለው ነው። በዚህ መሐል ግን እነዚህን የቅኝት ዓይነቶች በመደባለቅ የሚፈጠር የዘመናዊም ሆነ የባህላዊ ሙዚቃዎች ቅንጅት መኖሩ አይካድም።

  የኢትዮጵያ ሙዚቃ በኢንዱስትሪ ደረጃ ዕድገቱ የሚነገርለት አይደለም ለማለት ያስደፍራል። ምክንያቱም ዜማና ግጥም ደራሲው በሚፈለገው ደረጃ በዕድገት መሰላል ላይ መሆናቸውን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች ለማቅረብ አይቻልምና። ዜማውን ፈትሾ፣ግጥሙንም ተንትኖ የሚዳስስ ሐያሲም በብዛት አለ ለማለት አያስደፍርም። ሙዚቃዎች በሐያሲ ሳይሆን በአድማጩ ሲገመገሙ እንኳን እዚህ ግባ የሚባሉ አልሆኑም። ዛሬ ላይ «ገንዘብ ካለህ ሌላ ቢቀር ዘፈን ታወጣለህ» እየተባለ ይነገራል። ዘፋኙ ከቤት ሳይወጣ ዜማውንም ግጥሙንም በአንድ ሌሊት ሠርቶ ያድራል። ይህ ሁሉ ለሙያው ክብርና ልዕልና አስተዋጽኦ ካላደረገ ሌላ ምክንያት መፈለጉ ከንቱ ድካም ይመስለኛል።

  ገጣሚያን የሰዎችን ስሜት የሚኮረኩሩ ማለትም በተስፋቸው፣ በሚያልሙት ነገርና በውስጣዊ ስሜታቸው ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ስንኞችን ለመጻፍ ይጥራሉ። ነገር ግን የአድማጭና ተመልካችን ቀልብ የሚስቡና ከተሰሙ በኋላም ከአዕምሮ የማይጠፉ ሙዚቃዎችን መሥራት ግን አልተቻለም። የጥንቶቹ ወይም ባህላዊ ሙዚቃዎች ሲዜሙ ዋጋና ጥቅማቸው ቁጥር ስፍር የለውም። ለአብነት ብናነሳ አንድ አዝማሪ ሲያዘምር በሙገሳው ውስጥ ተረብ ወይም ነቀፌታን በማስገባት ስህተትን ጠቁሞ የሚያልፍበትን ስንኝ ያስቀምጣል። ዜማዎቹ ቅኔያዊ እንጂ በቀላሉ የሚፈቱ አይደሉም። አሁን አሁን ግን እነዚሁ ባህላዊ ሙዚቃዎች ወይም በባህላዊ አዳራሽ የሚቀርቡና ባህላዊ ነን የሚሉት ሙዚቃዎች ከስም ውጪ የሚያስተምር ነገር አይታይባቸውም። እንደውም አንዳንዴማ ለሙገሳ ብቻ የተሠሩ ይመስላሉ። ምክንያቱም ደግሞ ለገንዘብ ማግኛ ብቻ ተብለው እየተሠሩ መሆናቸው ነው።

  በተለይ በቴሌቪዥን መስኮት የሚታዩና በባህላዊ ሙዚቃ ቤቶችም የሚዜሙ ሙዚቃዎች ባህሉንና ወጉን የማይወክሉ ገፀ ባህሪያት መሆናቸው። የሰዎችንም ስብዕና ክፉኛ እየተፈታተኑት መኖራቸው ለወደፊት ባህላዊ ሙዚቃ ዕድገት እንዳያመጣ እንደ ተግዳሮት ተጠቃሽ በመሆን ላይ ናቸው። በዚህም ኢትዮጵያዊነትን የሚያንጸባርቁ ሥራዎች ሁሉ እየጠፉ ይመስላል።

  የባህላዊ እንጉርጉሮ ሙዚቃ ሲጠቀስ፤ ለሲንቲሳይዘርና የሙዚቃ መሣሪያዎችን አጠቃቀም የሚያካትት የስቱዲዮ ሙያ መስፋፋት በምቱም ሆነ በዜማ ቅርፁ ላይ ተፅእኖ እያደረሰ ለመሆኑ፤ የሠርግ ዘፈኖችን ለአብነት ማንሳት ይቻላል።

  ሙሽሮች የሠርጋቸውን ቀን አይረሴ ከሚያደርጉበት መንገድ አንዱ የዳንስ ትዕይንት እንደሆነ ያምናሉ። በባህላዊ መንገድ ሲገለጽ ግን ሙሽራውና ሙሽሪት የቀኑ ንግስትና ንጉሦች ስለሆኑ ወዳጆቻቸው የሚያደርጉትን ትርኢት በመመልከት «የቤተ ዘመዱ ይታያል ጉዱ»፣ «ሙሽራውን ሙሽሪትን ያላችሁ እስኪ እንያችሁ»፣ «ይኼ ነው ወይ ሚዜህ አየንልህ»፣ «ይቺ ናት ወይ ሚዜሽ አየንልሽ» እና «እየበሉ እየጠጡ ዝም የጋን ወንድም» የሚሏቸውን የሠርግ ዘፈኖች ያዳምጣሉ።

  በሠርጉ የታደሙትና እንዲጨፍሩ የታዘዙትም ትዕዛዛቸውን ይፈፅማሉ። አሁን ደግሞ ነገሩ ተቀይሮ እነርሱው ዘፋኝና ደናሽ ሆነዋል። ሊያውም የእነርሱን ማንነት በማይገልጽ ሙዚቃ። በዚህ ጉዳይ ላይ በያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት የሙዚቃ መምህርና የሙዚቀኞች ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት ሰርፀ ፍሬስብሐትና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴያትር የባህል ሙዚቃ ክፍል ኃላፊ አቶ ሰለሞን ፀጋዬ እንዲሁም ሌሎች የሙዚቃ ባለሙያዎች የሚሉት አላቸው።

  የሙዚቃ ባለሙያውን ሰርፀ ፍሬስብሐትን ሃሳብ እናስቀድም «የኢትዮጵያ ሥልጣኔ የሥልጣኔ መንፈሱን በሊቃውንቱ ቅኔና በአዝማሪዎቹ ጨዋታ ውስጥ እንዲሁም በየብሔረሰቡ ውስጥ ባሉ ሥነ ቃሎች እውነተኛ መልኩን ይዞ ይገኛል። ስለዚህ ማንነትን ለማወቅ በባህላችን መኩራትም ተገቢ ነው። የምዕራቡን ባህላዊ ሙዚቃ መሣሪያ ወስዶ ለኢትዮጵያ ባህላዊ ሙዚቃ መጠቀም አንዱ የዘመናዊነት ወግ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን በምንም ዓይነት መልኩ የምዕራባዊያን ሙዚቃዊ ባህል ብቸኛ ዘይቤ አድርጎ መቀበሉ ዘመናዊ ሊያሰኝ እንደማይችል መገንዘብ ተገቢ ነው» በማለት ይገልጸዋል።

  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴያትር የባህል ሙዚቃ ክፍል ኃላፊ አቶ ሰለሞን ፀጋዬም በበኩላቸው፤ በብዛት የባህላዊ ሙዚቃዎች ግጥም የአካባቢዎ ቻቸውን የተፈጥሮ ሀብት ከማድነቅ፣ የአካባቢን ልማት ከመናገር፣ በተቃራኒ ፆታ መካከል ስላለ ፍቅርና ማህበራዊ መስተጋብርን በጥቂት የሙዚቃ ስንኝ ውበት መልዕክታቸውን ከማስተላለፋቸውም በላይ ለሕብረተሰቡ ሕልውና ወሳኞች እንደሆኑ ያስረዳሉ።

  አቶ ሰለሞን እንደሚናገሩት፤ የባህላዊ ሙዚቃ ሥራዎች የሕብረተሰቡን ማንነት መገለጫ የሆኑትን እሴቶች ከሕብረተሰቡ በማውጣት የፈጠራ ሥራዎችን በማከል ወይም እንዳሉ ቱባውን በመውሰድ ከአንዱ ወደ ሌላው ማሸጋገርና እንዲደመጡ ማድረግ ተገቢ ነው። እነዚህ ባህላዊ ሙዚቃዎች መደመጥ ከጀመሩበት አንስቶ ሥራዎቹን በመገምገም አስፈላጊ የማሻሻያ እርምጃ ወይም ገንቢና ተገቢ አስተያየት የሚሰጥበትን መንገድ መዘርጋትም ያስፈልጋል። ሆኖም ግን ይህ ተግባር ሲሠራበት አይታይም። በተለይ ቋንቋውን በማያውቁት አካላት ሙዚቃዎቹ ሲዜሙ በሕብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያሳረፉ መሆኑን ማንም ሰው የሚረዳው ጉዳይ እንደሆነም ይናገራሉ።

  በደቡብ ክልል የሙዚቃ አቀናባሪ የሆኑን አቶ ዓይነው ተስፋዬ እንደገለጹትም፤ «ባህልና እሴታቸውን የጠበቁና ሥነ ምግባር የተላበሱ ሥራዎችን ለትውልድ ማስተላለፍ የጥበበኞች ኃላፊነት ነው» ይላሉ። ለዚህም በዘርፉ ያሉ የጥበብ ባለሙያዎች ለሙዚቃው ማደግ የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ይናገራሉ። በአሁኑ ወቅት ግን አንዳንዶች ገንዘብ ለማግኘት ብቻ የሚሠሩ መኖራቸው እሙን መሆኑን በመጠቆም። ይህን አመለካከት የሚያራምዱ አካላት እራሳቸውን መፈተሽ እንደሚገባቸውም ያሳስባሉ። «ይህ ካልሆነ ግን ታሪክን፣ ባህልና ማንነት በቀላሉ በምዕራባዊያኑ እንዲዋጥ ማድረጉም አይቀርም» የሚል እምነት እንዳላቸው ይገልጻሉ።

  አቶ አየነው እንደሚናገሩት፤ስለሙዚቃዎች ሲወሳ ክሊፖችን ማነሳቱ አይቀሬ ነው። በተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙሃን የሚተላለፉና ከባህር ማዶ እንደተወረሱ የሚያሳብቁ የሙዚቃ ክሊፖች፤ ቅጥ አምባሩ በጠፋ አለባበስና በከፊል እርቃንን የሚያሳዩና በፀረ ባህል የታጀቡ መሆናቸው ለባህላዊ ሙዚቃ ትኩረት እንዳልተሰጠው የሚያሳይ ነው።

  የሙዚቃ ክሊፖቹ፣ በማህበረሰቡ በተለይ በታዳጊዎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ ግልጽ ተፅዕኖ እያሳደረ ይገኛል። የክሊፕ ተዋንያኖችም ቢሆኑ ራሳቸውን ከማስተዋወቅ፣ ዝናን ለመጎናፀፍ ከመራወጥ ይልቅ ድርጊታቸው በተመልካች ዘንድ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተፅእኖ ለአፍታም ቆም ብለው አለማሰባቸው እጅግ የሚያስቆጭ ጉዳይ ነው። እዚህ ላይ «ባህልን አቃሎ፣ ንቀትን ተላብሶ ዘመናዊ ለመሆን ምዕ ራባውያንን መምሰል አለብን?» የሚለውም መልስ የሚፈልግ ቀዳሚ ጥያቄ ነው። ማንኛውንም የውጭ ሙዚቀኛ ባህሉን ሳይለቅ ይዘፍናል። «እኛ ታዲያ የሌላን መውረስ ለምን አስፈለገን?» በማለት በቁጭት ምልስ ያላገኙለትን ጥያቄ ይጠይቃሉ።

  «ቀደም ባሉት ዓመታት ቴክኒዮሎጂ ባልተስፋፋበት ሁኔታ ዕድገት ለማምጣት አዳጋች ሆኖ ቢቆይም በርካታ ጎሳዎች ሙዚቃዎቻቸውን ለመድረክ አዘጋጅተው ለማቅረብ እንዲችሉ የማበረታቻ ኮንሰርቶች በየአካባቢው ይደረጉ ነበር። ሙዚቃን ሥዕልን በሥርዓት ማጥናት እንዲቻል ትምህርት ቤቶች ተከፍተዋል። ለምሳሌ ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት በዚህም ባህላዊ ሙዚቃ እየተስፋፋ የመጣበት ሁኔታ ይታያል።» በማለት ሃሳባቸውን ያጋሩኝ ደግሞ በኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የባህል ልማት ባለሙያ አቶ ብርሃኑ ታዬ ናቸው።

  አቶ ብርሃኑ እንደሚናገሩት ከሆነ በአሁኑ ወቅት ባሀላዊ ሙዚቃን ለማስፋፋት መስሪያ ቤታቸው የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ ነው። ጥናቶችን በሙያተኞች በማስጠናት ለባለሙያው እንዲቀርብ መደረጉንና ከክልል ለመጡ የሙዚቃ ባለሙያዎች ሥልጠና መሰጠቱን ካከናወኗቸው ተግባራት መካከል ለአብነት ይጠቅሳሉ። በቀጣይም ይህንን ሥራ በስፋት በማከናወን በዘርፉ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት በትኩረት ለመሥራት ማቀዳቸውንም ጠቁመዋል።

  ምንጭ:- አዲስ ዘመንጸሐፊ (ጽጌረዳ ጫንያለው)

   

  Read more »

 • ባቡር፣ መንገድና የሰው ጠባይ

     

  ከአዳም ረታ

  ተመርቆ የቆየው የባቡር መንገድ ስራ የጀመረ ጊዜ “ከተማችን ዘነጠች” ተባለ። “ዓለሟን አየች” ተባለ። በየልቡ “አሁን ደመቅሽ አዲሳባዬ” ተዘፈነላት። ሰው ደስታውን በተለያየ መንገድ ገለጸ። የትናንት መልካም ታሪኮችን ስለዛሬ መስዋዕት ያቀረቡ አሽቋላጮችም ነበሩ። አንዳንድ የአዲስ አበባ ኗሪዎች እጅጉን ተመጻደቁ። በነዋሪው ግብርና፣ ነገ ላቡን ጠብ አርጎ በሚከፍለው (አልያም ሞልቶ ከተረፈው ተፈጥሯዊ ሀብት በዓይነት በሚከፈል) ብድር መሰራቱን የማያውቁ ይመስል ብሽሽቅ ጀመሩ። የስልጣኔ አልፋ መሆኑን አወሩ። “የ24 ዓመቱ ልፋት አፈራ” አሉ።

  ለባቡር መንገድ ስራ ጫካ የተገባ ይመስል “የታጋዮች ደም ፍሬ እያፈራ ነው።” ተባለ። ሬድዮና ቴሌቪዥኑ ሌላ ስራውን ትቶ፥ ከሞላ ጎደል ባቡሩን ማውራት ጀመረ። ከባቡሩ በሚተርፈው ጊዜ ባለጊዜውን “ሞላ” ያቀነቅናል። ሰልፌዎች በየሰዉ ግድግዳ ተለጣጠፉ። ወሬው ባቡርና ባቡር ብቻ ሆነ። ጋዜጠኞቹ ከምን ጊዜውም በላይ መበጥረቅ ጀመሩ። አንዱ “ይሄን ታሪካዊ ትኬት አልበም ውስጥ አስቀምጬዋለሁ” ሲል ገረመኝ። ለወሬ ሲቸኩል፥ “ትልቅ ዋጋ ያለውን አረንጓዴ ትኬት ቆርጬ ረዥሙን መንገድ ነው የሄድኩት።” አለ። (ትልቅ ዋጋ ያለው ትኬት ቀዩ ነው እንጂ አረንጓዴው አይደለም።)

  ወዲህ ከፒያሳ ተነስቶ ቃሊቲ፣ ወዲያ ደግሞ ከጦር ኃይሎች ተነስቶ ሀያት የሚዘልቁ ሁለት መንገዶች ተዘረጉና ከተማችን ቄንጠኛ ሆነች ተባለ። ሰዎች ደግሞ መውረጃቸው ጋር ሲደርሱ ወደጉዳያቸው ቶሎ እንደመሄድ ወገባቸውን ይዘው እዚያው ቆመው ወሬያቸውን ሲሰልቁ ይውላሉ። የባቡሩ መንገድ ሊሰራ ሲቆፈርና በልምምድ ወቅት፣ ከብበው ይመለከቱ ከነበረው በላይ ሰዎች የባቡሩን ማለፍ ቆመው ይመለከታሉ። ያወራሉ። ምን እንደሚያወሩ ግን አይገባኝም ነበር። ፖሊሶችና ትራፊኮች የባቡር ጣቢያዎች ላይ ፈሰሱ። በቻይኖች እየተዘወረች ባቡሯ ብቅ ስትል (በየ6 ደቂቃው ነው ተብሏል) ሰዉን ያዋክቡታል። ከድንዛዜው የተነሳ ሀዲዱ ላይ ሲሰጣ፣ ተገርፎ የሚወጣም ነበር። (ሲያንሰው ነው።)

  እንዳያያዛቸው፥ የባቡሩ መንገድ ስር፣ እና ጎንና ጎን፣ አንድ ቀን እሳት አንድደው፣ ጀበና ጥደው ቡና ሳይጠጡም አይቀር። ዳስ ጥለው ጠላ ሳያንዶቆድቁም አይቀር። የእድር ስብሰባዎችም እዚያ ሳይካሄዱም አይቀር። መጀመሪያ ሰሞንማ ባቡሩን ለማየት ከቤት ተቀሳቅሰው የሚወጡ ነበሩ። እንደ ቤተ አምልኮ ሊሳለሙት ይመስል ነጠላ ጎትተው ዋናው መንገድ ላይ የሚውሉ ጎልማሶች ተበራከቱ። ጎረምሶችና ኮረዶች ደግሞ መቀጣጠሪያቸውን የባቡሩ መንገድ ያለበትን አቅጣጫ ብቻ አድርገውታል።

  በየስልኩ “ሃሎ! እሺ… አልቆይም ኧረ። ባቡሯን ይዤ ነው የምመጣው።”፣ “ውይ ባቡሯ አመለጠችኝ። በቃ ቀጣይዋን እይዛለሁ።”፣ “ባቡር አትይዥም? አቦሉ ላይ ድረሺበት…”፣ “ለትንሽ አረንጓዴዋ ትኬት አለቀችብኝ። በቀይዋ መጥቼ አቆራርጣለሁ። አልቆይም…” የሚሉ የስልክ ወሬዎች መሰማት ጀመሩ። “ችግር ያቅልል ተብሎ ችግር ሆነ እኮ። ታያለህ መንገዱን እንደዘጋጋው?” የሚሉ አሽከርካሪዎች በዙ። ።

  የባቡሩ መጫኛና ማውረጃ ቦታዎች ሁልጊዜ ትርምስ ሆነ። መንገድ መዘጋጋት ጀመረ። በተለይ ባቡሩ ዝቅ ብሎ፣ ከመኪና ጋር እየተጠባበቀ በሚያልፍበት ቦታዎች ላይ የትራፊኩ ጭንቅንቅ በዛ። ታቦት እንደሚሸኙ ሁሉ ተሻጋሪዎች ተከትረው ቆመው ይጠብቃሉ። የመርካቶ በራፎች ትርምስ በዛባቸው። ወትሮም ግር ብለው ሲወጡና ሲገቡ ቀብር የሚሄዱ የሚመስሉት የመርካቶ ሰፈር ነዋሪዎች መውጫና መግቢያ ላይ፥ አስከሬን ቆመው የሚያሳልፉ ይመስል… አልቃሽ ያዙኝ ልቀቁኝ ብላ ስትፈጠፈጥ ቆመው እስክትነሳ ይጠብቋት ይመስል…መውጫና መግቢያው ላይ መገደብ ጀመሩ። ትራፊክና ፖሊሶች ላይም ጭንቅ ሆነ። መጀመሪያ ሰሞን፥ ሰዉ ጉዳይ ሳይኖረውም ለሙከራ ይሳፈር ነበር። “እስኪ ሽርሽር እንውጣ” ይላሉ። ለሙከራ የሚሳፈሩት ሰዎች ፊት የመገረም ፈገግታ ፊታቸውን ሞልቶት ይታያል።

  ትንሽ ከርሞ ከተማዋ በዚህ ባቡር ከዘነጠች በኋላ እናቴ አንድ ሀሳብ ተከሰተላት። ካልጠፋ ነገር ባቡሩ ጣቢያ ጋር ቆሎ የማዞር ሀሳብ ተከሰተላት። መንገድ ሲሄዱ መኪና ተበላሽቶ ወርደው የሚተራመሱ ሰዎችን ሲያይ፥ “እዚህ ጋር ሻይ ቤት መክፈት ነበር” እንዳለው ስራ ፈጣሪ ጉራጌ እናቴም የስራ ሀሳብ ተከሰተላት። በቆሎ ጀምረነው፣ የሰዉን ፍላጎት እያየንና እንደ ወቅቱ ድንችና በቆሎም እንጨምራለን አለች። በፕላስቲክ የተለበጠ “ሞባይል ካርድ አለ” የሚል ወረቀት አንገቴ ላይ አንጠልጥዬ፣ ማልጄ ቆሎዬን ይዤ እንድወጣ ተፈረደብኝ።

  ባቡሩ እንቅልፌን ቀማኝ። ባቡሩ ልጅነቴ ላይ ተደራደረ። እንደፈረደብኝ ባቡር ለሚጠብቁ ሰዎች ቆሎዬን መስፈር ጀመርኩ። እንደ ስራ ሳይሆን እንደቅጣት ስለምቆጥረው በደስታ አድርጌው አላውቅም። ባቡሯ እንዳታመልጣቸው ሲዋከቡ መልስ ጥለው የሚሄዱ ሰዎች ሲያጋጥሙኝ ደስ ይለኝ ጀመር። እንደዛ ሲሆን “ስትመጣ ትከፍላለህ… ቅመሳት” እያልኩ መቀናጣትና ገበያተኛ ማማለል ይቃጣኛል።

  አንዳንዴ ደግሞ የፋጤ እድል ይገጥመኛል። ማንጎ ሸጣለት “ሽልንጌን” እያለች የጮኸችው የሀረሯ ፋጡማ ትዝ ትለኛለች። አንዳንዱ ቆሎዬን ሰፍሬለት ሳይከፍለኝ ባቡሯ ውስጥ ይገባል። እንዲህ ሆነ ስራዬ። ባቡሯ በመጣች ቅጽበት እንደ ሀይለኛ ዝናብ ሿ ይልና፣ ወዲያው ቀጥ ብሎ ያባራል። ሰፌዴን ይዤ እንደነገሩ ትከሻዬ ላይ ጣል አድርጌው እወጣና ባቡር መንገዱ አካባቢ በፀጥታ ገዢ እቃርማለሁ። ባይኖቼ እለማመጣለሁ።

  ባቡር ጠባቂው “መጣች መጣች” ይባላልና አንገት ሁሉ ሰግጎ ባይኑ አቀባበል ያደርግላታል። እሪ ይባላል፣ ይጮሃል፣ ይገፋፋል። ጨዋ የሚመስሉ ሴቶች እንኳን ቀሚሳቸውን ሰብስበው ይሯሯጣሉ። ቆሎዬን ሽጬ እቤት ከተመለስኩ በኋላ ሌላ ቆሎ ከሌለ፣ የሞባይል ካርዶቼን ይዤ ሰፌዱን አስቀምጬ እወጣለሁ። ከዚያ ለተባራሪ ፈላጊ ሞባይል ካርድ እየሸጡ ወሬ መስማት ነው።

  ባቡሩ መጀመሩ አንድ ትልቅ የወሬ ለውጥ አመጣ። ሕዝቡ ለታክሲ መጋፋቱን በባቡር መጋፋት ተካው። የሚሄድበት መንገድ አጭር የታክሲ ወይም የእግር መንገድ ቢሆን እንኳን፥ እንደምንም ብሎ ባቡሩ በሚሄድበት አቅጣጫ ሄዶ፣ በታክሲ ማቆራረጥ ጀመረ። ባቡሯን ለመጠቀም ቀደም ብሎ እየወጣ ራሱ ላይ መከራ ከመረ። ወሬው በየቦታው በየቤቱ በየቅያሱ ስለባቡርና በባቡር ስለመሄድ ሆነ። ቃሊቲና ቂሊንጦ ያሉ እስረኞችን የሚጠይቅና መንጃ ፍቃድ የሚያወጣው ሰው በዛ። ባቡሯን ቃሊቲ ድረስ ለመጠቀም ብሎ ወጥቶ ደብረ ዘይት ሄዶ የሚዝናናውም ሰው ጨመረ።

  “ፍጥነቱ ደስ ሲል። ደግሞ የሚሄድም አይመስልም… ”

  “መንገጫገጭ የለ… ታክሲው እኮ ሲንጠን እንዴት ገድሎን ነበር?”

  “አንቺ ባቡሩን ሞከርሽው? ወደ ሀያት ስትሄጂበት ደግሞ ከቃሊቲው ይለያል።” ትንታኔዎች ተደሰኮሩ።

  “ትላንት ለቅሶ ሄጄ… እንዴት ፈጥኜ መጣሁ መሰለሽ።” (ሰው ሲሞቱና ትልልቅ ጉዳዮቹ እንዳያልፉት ባቡሩ መንገድ ተከትሎ ያሉ ዘመዶቹ ጋር ዝምድናውን አጠበቀ።)

  “ደግሞ ከታክሲው ሲናጸር ዋጋው መርከሱ… ታክሲዎቹማ ሲበዘብዙን ኖሩ እኮ።”

  “ኧረ የረዳቶቹን ስድብ መጠጣቱና የጣሉትን ቂጥ ማየት መቅረቱስ”

  “’ድመት መንኩሳ ዐመሏን አትረሳ’ …አሁን ምንድን ነው መስገብገብ። ሆዱ እኮ ሰፊ ነው። ሁላችንንም ይችለናል። ኧረ ተዉ ቻይኖቹም ይታዘቡናል…”

  “ኧረ ደቂቃው እንዳይሞላብሽ ፍጠኚና ውጪ”

  “ለትንሽ ጥሎኝ ሊፈረጥጥ። ሀዲዱ ላይ መዳመጤ ነበር…ብቻ ብረቱን ይዤ ተረፍኩ።”

  “ባቡር ላይ እያስቸገረኝ ነበር። ስልኬን ወስዶ…”

  “እንዴ ባለቤቴ እኮ ባቡሯ እንዳታልፈው ስለሚጣደፍ ማምሸቱም ቆሟል። ይኸው በጊዜ፣ መጥቶ ስንላፋ ነው የምናመሸው ስልሽ…”

  ጨዋታው ባቡርና ባቡር መንገድ ሆነ።

  ባቡር ባቡር የሚሉ ዘፈኖች፣ የድሮ የዘፈን ክሮች እየተራገፉ ወጡ። አዳዲስ ግጥምና ዜማዎችም ተቀመሩ። ችኮላው አላደርስ ያላቸው የቀድሞ ዘፈኖችን ግጥሞች አድሰው ሬድዮዎቹን አጨናነቁ።

  ባለጋሪው ባለጋሪው፣
  ቶሎ ቶሎ ንዳው…

  የሚለው ዘፈን ግጥም ተቀይሮ…

  ባለባቡሩ ባለባቡሩ፣
  ሸገር ሆኗል ሀገሩ!

  ተሳፋሪ ሁሉ ባለ ጉዳይ ነው
  ታክሲና አቶቢሱን አሻግሮ ሚያየው
  የሞላ የሞላ ባለና በፊቴ
  ባሳፈረኝና እፎይ ባለ ስሜቴ፤
  እፎይ ባለ ስሜቴ፤

  ተብሎ በየኤፍ ኤሙ ተሰማ።

  በባቡር በፍቅር መንገድ ላይ በባቡር
  በባቡር በመውደድ መንገድ ላይ በባቡር
  መጓዝስ ካልቀረ ካንቺ ጋር ነበር

  የሚለው ሙዚቃ እንዳንዲስ መጠባበሻ ሆነ።

  በባቡሩ መንገድ የቆምኩት አሁን
  ስንቱን አሳልፌ ልዘልቀው ይሆን?

  የሚለው የሜሪ አርምዴ ዘፈን ከነክራሩ ከተሰቀለበት ወረደ።

  በየታክሲው ጭቅጭቁ፣ ማስፈራራቱና ዛቻው በዛ።

  “ኤጭ አትጨማለቅ እንግዲህ! ባቡር እኮ…” እያሉ የሚያስፈራሩ፣ “’እጸድቅ ብዬ ባዝላት…’ አንተ በባቡር መሄድ አቅቶኝ አይደለም።” እያሉ የሚመጻደቁ፣ “እንደውም ተወው ባቡሯ ብቅ አለች” ብለው የሚያኮርፉ ተሳፋሪዎች በረከቱ።

  “ታክሲ ጥንቡን ጣለ” ተባለ።

  ስጋቶችም አልጠፉም።

  “መብራት ቢጠፋስ?”፣ “ደግሞ ሲዘንብ ቢነዝረኝስ?”፣ “ይሄ ደንባዛ ቻይና ቢያስነጥሰውና ዐይኑ ጭራሽ ድርግም ቢልስ?” የሚሉና ሌሎች የፍርሃት ወሬዎች በሹክሹክታና በየሰዉ ልብ ውስጥ ይብላሉ ጀመረ።

  “ባቡር ጣቢያው ጋር ጠብቂኝ” “ምስጢራዊ የባቡር ጉዞዎች” “መሀልየ መሀልይ ዘባቡር” “የባቡሩ ጉዶች” “ባቡር ላይ ያየሁት ወንድ የወሰደው ልቤ” “ባቡር ተሳፍሬ” “የዘገየው ባቡር” “ከባቡር አደጋ ለመትረፍ የሚያስችሉ 8 ነጥቦች” “ባቡርን ወደ ቢዝነስ የመቀየር ጥበብ” “የባቡር ኬሚስትሪ” “ባቡሩ” “ከባቡር የወጣች ነፍስ” “ባቡር መንገዱ ዙሪያ ያሉ የወሲብ ሕይወቶች”…የሚሉ የተለያዩ ከተፋ መፅሐፍትና ፊልሞች በዙ። ሙዚቃዎችም ባይነት ባይነቱ ሆኑ። ገጣሚያንም ወገባቸውን ቋጥረው ስለባቡር ተቀኙ። ናፍቆትና ጥበቃ በባቡር ተሰማመሩ።

  “የከሸፈው የአሸባሪዎች ሴራ በባቡሩ መንገድ ላይ”፣ “እንደ ባቡራችን ፈጣኑ ኢኮኖሚያችን”፣ “ባቡር ላይ በሻዕቢያ ተላላኪ ፀረ ሰላም ኃይሎች የተቀነባበረው ፍንዳታ ምስጢር ተጋለጠ”፣ “አቶ አንዳርጋቸው እንደ ኤክስፕረስ መንገዱ የባቡሩንም ጎበኙት። ይህኛው የባቡር ጉዞዬ ከእስከዛሬው ሁሉ ለየት ያለ ነው አሉ።” እና የመሳሰሉ ዶክመንተሪዎችና የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ርዕሶች በብዛት መታየት ጀመሩ።

  እኔ ግን ኑሮ ባቡር ላይ ተጭኜ ቆሎ እሰፍራለሁ እንጂ እስከዛሬ ባቡር ተሳፍሬ አላውቅም። ባቡሩ ሆዴን እያሰብኩ ባቡር ተሳፋሪን አሳድዳለሁ። በቆሎና ስለቆሎ ያየሁት ጉድ ይበዛል። ሳድግ ግን “ባቡር መንገድ ላይ ያሳለፍኩት ልጅነቴና ትዝብቶቼ” ወይም “ባቡር መንገድና የሰው ልጅ ጠባይ” ወይም “ባቡርና ሕይወት” ወይም “ባቡር ጣቢያ ላይ የተረሳው የትንሹ ልጅ ሕይወት” የሚል መጽሐፍ ብጽፍ ደስ ይለኝ ነበር። ትምህርት ቤት አልሄድኩም እንጂ መጻፍ ብለምድና መጽሐፍ ብጽፍ ደስ ይለኝ ነበር።

  ‘ግን ሰው ከባቡር መሳፈርና ስለባቡር ማውራት ምን ጊዜ ተርፎት ያነብልኛል?’ ስል አስባለሁ።

  ማስታወሻ
  ይህንን የጻፍኩት የአዳም ረታ “ግራጫ ቃጭሎች” ላይ ገጽ፥ 127-128 ባለው “ቧንቧ፣ ልብስና የሰው ጠባይ” በሚል ንዑስ ርዕስ በተጻፈው ታሪክ መቆስቆስና ቅርጽ ነው። አንዳንድ አረፍተ ነገሮችንም በቀጥታ ከግራጫ ቃጭሎች ላይ ገልብጫለሁ።

   

   

   

   

   

  Read more »

 • ሀበሻ ለምን ይደባደባል??

   

  ቤተልሔም ኒቆዲሞስ

  በቅርቡ በስታንፈርድ ዩኒቨርስቲ የተደረገው ጥናት እንደሚያሳየው ሀበሾች በሶስት አበይት ምክኒያቶች እየተደባደቡ ይገኛሉ ፡፡
  1ኛ. የሙምባይ አየር ማረፊያ ባህር ተጠግቶ የተሰራው በጀልባ እንድንጠቀምበት ነው ብለው የባህር ዳር እና የአዋሳ ባለታንኳዎች የርስት ጥያቄ አንስተው እየተወዛገቡ ነው....
  2ኛ. እስራኤል ደርሰው የተመለሱ አሮጊቶች ይሁዲ ስረመሰረት ያለውን ዶናልድ ትራምፕን እየደገፉ ከአቻ ኔቲቭ አሮጊቶች ጋር ጠብ እየጫሩ ይገኛሉ
  ..............ከምንም በላይ ግን.........
  3ኛ. 50 ሳንቲም መልስ ስጥ አልሰጥም በሚል አበይት ርዕስ ኔቲቭ ወያላ እና ተሳፋሪ እየተናከሱ ያለበት ሁኔታ እንዳለ ተጠቁሟል ፡፡
  50 ሳንቲማችን የእድገታችን መሠረት ነው!!!
  ጉዞ ወደ ሀብት ማማ ከ50 ሳንቲም ጋር!!!
  ክድ እንግዴ!!!!

  Read more »